ታምራት ተስፋዬ
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በአሁን ወቅት በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል የሚገኘው የዱራሜ – ደምቦያ _ አንጋጫ – አመቾ እና ዋቶ – ሀላባ 65 ኪ.ሜ መንገድ፣ በጠጠር ደረጃ ያለና በግልጋሎት ብዛት ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርጎ አመታትን አስቆጥሯል። በተለይ በክረምት ወቅት ለነዋሪዎችም ሆነ ለመንገደኞች ምሬት፣ ለተሸከርካሪዎችም እጅግ ፈታኝ እንደሆነ በርካቶች ይመሰክራሉ። ይህን ያስተዋለው የኢትዮጵያ መንግስትም መንገዱ ከሚኖረው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በአስፋልት ኮንክሪት እንዲገነባ ወስኖ የመንገድ ግንባታውም በያዝነው አመት የካቲት መጀመሪያ ላይ እንደሚጀመር ተገልጿል።
በመንግስት በሚሸፈን አንድ ቢሊየን 980 ሚሊየን 658 ሺህ 256 ብር ወጪ በሚገነባ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርህ ግብር ላይም የተለያዩ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል። መንገዱ ሲጠናቀቅም የትራንስፖርት ችግር ከመቅረፉም ባለፈ በአካባቢው የሚመረተውን የሰብልና ፍራፍሬ ምርቶችን በፍጥነት ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲደርስ በማድረግ ከአካባቢው አልፎ ለሀገር የኢኮኖሚ ግንባታ ግዙፍ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።
ፕሮጀክቱ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ብሎም የጥራት ደረጃ እንዲሁም ወጪ እንዲጠናቀቅ ህገ ወጥ ግንባታና በስራ ላይ የሚያጋጥሙ የወሰን ማስከበር ጥያቄዎች በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ውሳኝ እንደሆነም አፅእኖት ሰጥተውታል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ችግሩ ምን ይሆን ሲልም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የደቡብ ሪጅን ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ጉቱ
ጥያቄ አቅርቧል። እርሳቸውም ፕሮጀክቱ ከጅምሩ ያልተገባ የካሳ ጥያቄ እንደፈተነው አረጋግጠዋል። ፕሮጀክት አራት ወራት የስራ ተቋራጩ የቅድመ ዝግጅት ማለትም፣ አስፈላጊው ማሽነሪ ጨምሮ ሌሎችም ግብአቶች የሚያቀርብበት ነው። ያለፉት ወራትም በዚህ አግባብ ነው ያለፉት። ይሁንና ጎን ለጎን ግንባታውን የማካሄድ ስራ ተጀምሯል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በአዋጅ ቢደገፍም በአገር አቀፍ ደረጃ የካሳ ግምት ለመስራት የሚያስችል ቀመር አልወጣም። ይህ በመሆኑም በክልል ወይንም በከተማ አሊያም በወረዳ አስተዳደሮች በኩል የዋጋ ግምት ይወጣል። ይህ ካሳም ይከፈላል። ይህ አሰራርም በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች በተለይ ደምቦያ እና አንጋጫ ወረዳ ላይ የተጋነነ ዋጋ እየቀረበ ነው የሚሉት አቶ ደጀኔ በተለይ በአንጋጫ ወረዳ ለቤት የሚቀርበው ዋጋ እጅግ የተጋነነ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ከቤቱ አጠቃላይ ዋጋ ጋር የሚስተካከል ከአንድ ሚሊዬን በላይ ጥያቄ እንደሚቀርብም ነው የጠቆሙት አቶ ደጀኔ። በተመሳሳይ ለሳር ግጦሽ በሄክታር በአመት ከሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር በላይ፣ ለአንድ ባህር ዛፍም ከዘጠኝ ሺህ ብር በላይ ዋጋ እየቀረበ መሆኑን ገልፀዋል። በደምቢያ ችግሩ ተመሳሳይ ነው፤ አላባ ከተማም ቢሆን የውሃ መስመር ለማንሳት በአጭር ርቀት እስከ 20 ሚሊየን ብር የተጋነነ ጥያቄ ቀርቧል።
ይህን የተጋነነ የካሳ ጥያቄ በትክክለኛ መንገድ መቅረብ እና ችግሩም መፍትሄ ማግኘት እንዳለበት አፅእኖት የሰጡት አቶ ደጀኔ፣ ፈጣን ማስተካከያ እስካልተደረገበት ድረስ የፕሮጀክቱ የመጠናቀቂያ ጊዜ ባልተገባ መልኩ እንዲራዘም ብሎም አጠቃላይ የግንባታ ወጪውም እንዲጨምር በማድረግ ከባድ ኪሳራ ሊያመጣ እንደሚችል ሳያስረዱ አላለፉም።
አቶ ደጀኔ መሰል ችግሮች ከመከሰታቸው ብሎም ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ለምን ከህብረተሰቡ ጋር አልተወያያችሁም? ቅድመ ስራዎችን አልጨረሳችሁም? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ተግባሩ መፈፀሙን አስረድተዋል።
በውጤቱም የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ተገቢው ካሳ ተከፍሎ ከ26 ኪሎ ሜትር በላይ የወሰን ማስከበር ስራ መጠናቀቁን ገልፀው፣ ይሁንና ካሳ ከተከፈላቸው በኋላ ንብረትን በፍጥነት የማንሳት ችግር በእጅጉ እንደፈተናቸው ነው ያመላከቱት።
‹‹ያልተገባ የካሳ ጥያቄ ፈተና በአንድ ፕሮጀክት ላይ ብቻ የሚስተዋል አይደለም። በደቡብ ክልል በምንሰራቸው ፕሮጀክቶች መንገድ ይወጣል ሲባል ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በርካታ ቦታዎች ላይ ማህበረሰቡ ህገ ወጥ ግንባታ ይጀምራል። ህገ ወጥ
ተክል ይተክላሉ ሲሉ ይናገራሉ። አንዳንድ ወረዳዎችም የሚያቀርቡት የምርታማነት ግምት እና ከእስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሚሰጥ መረጃም ፈፅሞ የተቀራረበ አይደለም። ይህም በፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ከባድ ፈተና እየሆነ ይገኛል።
ይህን ተከትሎ ከካሳ ጋር በሚቀርቡ ጥያቄዎች ምክንያት ንብረቶቹም ሆነ ተክሎቹ ይነሱ አይነሱም በሚል ከባድ እሠጣ ገባዎች ውስጥ እንደሚገባ ያመላከቱት ዳይሬክተሩ፣ ይህም ለፕሮጀክቶች መዘግየት ከባድ ፈተና እና የአፈፃፀም እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ሳይገልፁ አላለፉም።
ከተማ አስተዳደሮች በራሱ የወሰን ማስከበር ኮሜቴ ማቋቋም ድክመት አለባቸው ለሚለው ቅሬት በሰጡት ምላሽም፣ ኮሚቴዎቹ በአብዛኛው ስራውን ተደራቢ እና የትርፍ ሰአት አድርገው መመልከታቸው ችግሩ እልባት እንዳያገኝ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል።
የዋጋ ግምቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የራሱ ቀመር ሊወጣለት እንደሚገባ አፅእኖት የሰጡት አቶ ደጀኔ፣ ይህን የማድረግ ስራም ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ አስረድተዋል። የግምቱ ቀመሩ ወጥቶ በተስተካከለ እና ወጥ በሆነ መልኩ መቀመጥ እንዳለበት እና ይህ ካልሆነም በወረዳ፣ በከተማም ሆነ በክልሎች መካከል የግምት ልዩነት እንደሚመጣ አፅእኖት ሰጥተውታል። የመንገድ ፕሮጀክት ሁለንተናዊ ጥቅም ለአካባቢው ማህበረሰብ መሆኑን ያመላከቱት ዳይሬክተሩ፣ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች የእኔ ናቸው የሚል እሳቤ ሊኖርና በአስፈላጊው ሁሉ መተባበር የግድ እንደሚላቸው ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
የመንገዱ ግንባታ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የሚያከናውነው ሲሆን፥ የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን የትራንስፖርት ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ዘርፍ ደግሞ የማማከር ስራውን ተረክቧል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 9/2013