መላኩ ኤሮሴ
የወልቂጤ ከተማ ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 158
ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ከባህር ጠለል በላይ 1980 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው የአየር ጸባይዋ ደረቅና ሞቃታማ የሆነችው ወልቂጤ በ1999 ዓ.ም በተደረገው የህዝብና ቤት ቆጠራ መረጃ መሰረት 96ሺህ 400 ህዝብ እንዳላት ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት ከ150 ሺህ በላይ ህዝብ እንደሚኖርባት ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘ መረጃ ያሳያል።
ከተቆረቆረች ከ100 ዓመት በላይ እንዳስቆጠረች የሚነገርላት ከተማዋ ከ1983 ዓ.ም በፊት በሸዋ ክፍለ ሀገር በጨቦና ጉራጌ አውራጃ ስር የነበረች ከተማ ስትሆን፤ ከ1983 በኋላ በደቡብ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ህዝቦች ክልል የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ በመሆን ስታገለግል ቆይታለች። ከተማዋ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በከተማ አስተዳደርነት የምትታወቅ ሲሆን በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከሚገኙ የሪፎርም ከተሞች መካከል አንዷ ነች። በአሁኑ ወቅት የጉራጌ ዞን አስተዳደር መቀመጫ ከመሆኗ ባሻገር የቀቤና እና የአብሽጌ ወረዳዎች ማዕከል ሆና ታገለግላለች።
ወልቂጤ ከተማ ረጅም እድሜ ካስቆጠሩት የሀገራችን ከተሞች አንዷ ብትሆንም በተለያዩ ምክንያቶች የእድሜዋን ያህል አላደገችም። በተለያዩ ምክንያቶች ዛሬም ለከተማዋ ነዋሪ ምቹ ሁኔታ ሳይፈጠርለት፣ የመሰረተ ልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በቅጡ ሳይቀረፉ እንዲሁም የኑሮ ውድነት እና የስራ አጥነት በነዋሪው ላይ ተጭኖት እንደቆየ የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ቤተልሄም በሃይሉ እንደሚሉት፤በከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ የሚገኘው የሸቀጦች ዋጋ መናር፤ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ምክንያት እየሆነ ይገኛል። ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች እና በአካባቢው የሚመረቱ የግብርና ምርቶች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በከተማዋ ዘመናትን ያስቆጠሩ የመሰረተ ልማት ችግሮች አሉ።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሚታዩ የመንገድ ዳር መብራት የመዘርጋት እንቅስቃሴዎች ውጪ በከተማዋ ዳር መብራት አይታወቅም። ይገነባል የተባለ ሆስፒታል ግንባታ ሳይጀመር፣ የትምህርት ቤቶች ግንባታ ሳይካሄድ እንዲሁም የከተማዋን ነዋሪዎች የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶች በነዋሪዎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ውጤት ሳያመጡ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከንቲባዎች ሄደው ከንቲባዎች መጥተዋል።
የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ፤ እንዳለ ገብረመስቀል እንደሚሉት፤ ከተማዋ ከተቆረቆረች ከ100 ዓመት በላይ ያስቆጠረች ቢሆንም የእድሜዋን ያህል አላደገችም። የእድሜዋን ያክል ማደግ ቀርቶ በክልሉ በቅርቡ የተቆረቆሩ ከተሞች በልጠዋታል። ታናናሾቿ ጥለዋት ቆመሽ ጠብቂን ብለው አልፈዋታል። ከተማዋ ለበርካታ ዓመታት ከልማት ወደኋላ ቀርታለች።
የከተማዋ ከንቲባ ከሌሎች የአካባቢው ከተሞች አንጻር ሲታይ ከልማት ወደ ኋላ መቅረቷን በቁጭት ይናገራሉ። የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያነሷቸው የልማት፣ የስራ አጥነት እና የኑሮ ውድነት ጥያቄዎችም ለዘመናት የቆዩ የነዋሪዎቿ ጥያቄ ናቸው። የሚያነሷቸው ጥያቄዎችም እውነታነት ያላቸው ናቸው።
“ከተማዋ በመዋቅር ምክንያት ከታናናሾቿ አንሳለች” የሚሉት ከንቲባው፤ ከተማዋ እንዳታድግ የተደረገው በመዋቅር ነው ይላሉ። ይህም የከተማዋን እና የዞኑን ማህበረሰብ ካስቆጡት እና በሀገሪቱ በተደረገው የለውጥ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆን እና ለሀገራዊ ለውጥ የበኩሉን እንዲያበረክት ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው ይላሉ።
እንደ አቶ እንዳለ ማብራሪያ፤ የመንገድ ዳር መብራት፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች ግንባታ በፍትሃዊነት በአካባቢው ሲገነባ አልነበረም። አንዳንድ ከተሞች ቀደም ብለው የመንገድ ዳር መብራት፣ መንገድ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲያገኙ ሲደረጉ፤ ወልቂጤ ግን ለዚህ የታደለች አልነበረችም። ለ40 እና 30 ዓመታት በከተማዋ ይህ ነው የሚባል ለውጥና ልማት አልታየም። ሁሉም ነገር በነበረበት ነው የቆየው። በዚህም ምክንያት “ደኢህዴን የረሳት ከተማ” እስከመባል ደርሳለች።
የከተማዋን ሁኔታ በሁለት ዘመን ከፍለው የሚያብራሩት ከንቲባው፤ 2010 ዓ.ም ከተደረገው ለውጥ በፊትና በኋላ በማለት ያስረዳሉ። እስከ 2010 ዓ.ም ለበርካታ አስርት ዓመታት በሸፍጥ እና በመዋቅር ከተማዋ እንዳታድግ ተደረገ። ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ አመርቂ ስራዎች እየተሰሩ ነው። የከተማዋን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በርካታ ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል። አንዳንድ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የዋናው የመንገድ ዳር መብራት የመዘርጋት፣ የውስጥ ለውስጥ ኮብልስቶኖች የማንጠፍ፣ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት፣ የሆስፒታል ግንባታ እንዲሁም የውሃ ችግር ለመቅረፍ ርብርብ ተደርጓል ያሉት ከንቲባው፤ ከዚህ በተጨማሪ የከተማዋ ህዝብ ዋነኛው ጥያቄ የነበረው ሆስፒታል እየተገነባ መሆኑን አንስተዋል። ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶች የተጀመሩ ሲሆን አንዳንዶች ተጠናቀዋል። አንዳንዶቹ ሂደት ላይ ናቸው። አሁንም የሚታዩ ጉድለቶች ቢኖሩም ወደ መስመር እየገቡ ያሉ ነገሮች አሉ።
ለወጣቱ መዝናኛ ለመገንባት ተጀምሯል። ለነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እየቀረበ ነው። እና የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን ከማቅረብ አንጻር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መልካም ጅምር መታየት ተችሏል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል የሚሉት ከንቲባው፤ ከዚህ ቀደም ያልተሰሩ በርካታ ስራዎች በመኖራቸው በሶስት ዓመት የተሰሩ ስራዎች ጎልተው እንዳይታዩ ቢያደርግም ብዙ ተሰርቷል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱ የጉራጌ ማህበረሰብ አባላት እና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በሌሎች ቦታዎች ኢንቨስት ከማድረግ ጎን ለጎን ወደ ከተማዋ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማስቻል የተለያዩ ምክክሮችና ውይይቶች ተካሂደዋል። በዚህም በአሁኑ ወቅት በርካታ ኢንቨስትመንቶች እየመጡ ነው።
የሚመጡ ኢንቨስትመንቶች ያለ ቢሮክራሲ በማስተናገድ ረገድ መዋቅራዊ ችግሮች መኖራቸውን የሚያነሱት ከንቲባው፤ በከተማዋ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልግ ባለሃብት የከተማ አስተዳደሩን ሲጠይቅ አመቻችቶ ይሰጣል። ከተማ አስተዳደሩ መሬቱ እንዲፈቀድ ጥያቄ ለክልሉ የማቅረብ እንጂ መስጠት አይችልም። መሬት የማቅረብ ስልጣን ያለው የደቡብ ክልል መንግስት ነው። የክልሉ መንግስት ካላጸደቀው ወደ ስራ መግባት አይቻልም። የክልሉ መንግስት ደግሞ ከመላ ክልሉ የሚመጡ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ወራት ይፈጅበታል። አንድ የኢንቨስትመንት መሬት ጥያቄ ለማስጨረስ ከስድስት ወራት በላይ ይጠይቃል። ይህ የቢሮክራሲ መንዛዛት የከተማዋን ኢንቨስትመንት ጎድቶ ቆይቷል።
አቶ እንዳለ እንደሚሉት፤ በክልል የሚጸድቀው የኢንቨስትመንት መሬት የማጽደቅ ጉዳይ በዞን እንዲያልቅ ቢደረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ መሬት ማስረከብ የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር ። ይህ ቢሆን ቢያንስ በሁለት ወር ውስጥ መሬት ማስረከብ የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ከተሞች የኢንቨስትመንት ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ ነው ክልሉ እያጸደቀ ያለው። ይህም የሚያመላክተው መዋቅሩ የልማት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አሁንም እንቅፋት ሆኖ መቀጠሉን ነው ። በአሁኑ ወቅት ግን ይህን የተንዛዛ አካሄድ በመቀየር ከተማ አስተዳደሩ ያለ ቢሮክራሲ መሬት ለማቅረብ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
ምንም እንኳ እንቅፋቶች ቢበዙም ከለውጡ በኋላ 50 የሚሆኑ ኢንቨስተሮች በከተማዋ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገብረ ስላሴን ጨምሮ በርካቶች በከተማዋ ሆቴል ለመገንባት መሬት እየወሰዱ ነው። በአጠቃላይ 15 የሚሆኑ ባለሃብቶች ሆቴል ለመገንባት ጥያቄ አቅርበዋል። ጥያቄያቸው በከተማ አስተዳደሩ ይሁንታ ተሰጥቶት ወደ ክልል ተልኮ እንዲጸድቅ እየጠበቁ ያሉ 15 የሚሆኑ ባለ 3 እና 4 ኮኮብ ሆቴሎች አሉ። ይሄ ከተማዋ ብሩህ ተስፋ እንዳላት አመላካች ነው ።
አሁን ኢንቨስተሮች ሲመጡ ከተማ አስተዳደሩ በመልካም ሁኔታ እየተቀበላቸው ነው ያሉት ከንቲባው፤ መዋዕለ ንዋይ ሊያፈሱ መጥተው እቅዳቸውን ሳያሳኩ እንዳይሄዱ እየተደረገ ነው። የጉራጌ ተወላጆችም ሆኑ ሌሎች ኢንቨስተሮች ኢንቨስት ለማድረግ ሲመጡ የከተማ አስተዳደሩ ባለሙያዎች እና አመራሮች ሌሎች ስራዎችን በመተው ኢንቨስተሮችን በማስተናገድ ላይ ናቸው።
በፓስታና ማካሮኒ፣ በዱቄት ፋብሪካ ወደ ስራ ገብተው ከአካባቢው አልፎ ለሀገሪቱ ገበያ ጭምር እያቀረቡ ያሉ ባለሃብቶች መኖራቸውን ያነሱት ከንቲባው፤ ወደ ስራ የገቡት ለመግባት ከጠየቁት አንጻር ውስን ናቸው። አብዛኞቹ ገና የግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
መሬት ተቀብለው አጥረው ያስቀመጡም አሉ። መሬቱን በመጠቀም ከቀረጥ ነጻ የሆኑ ስራዎችን እየሰሩ ነው። ከነዚህ ጋር ውይይት እየተደረገ ነው። እነዚህ ኢንቨስተሮች ወደ ስራ ላለመግባታቸው ኮቪድ 19፣ የዶላር እጥረትን፣ የሲሚንቶ እጥረት የመሳሰሉ ችግሮችን እንደምክንያት እያቀረቡ ነው። አንዳንዶቹ ምክንያቶች ተገቢነት ያላቸው ሲሆኑ አንዳንዶች ግን ተገቢ ያልሆኑ ምክንያቶች ናቸው። በቀጣይ እነዚህን ወደ መስመር ለማስገባት መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ ብለዋል።
የከተማዋ ሌላኛው ችግር ስራ አጥነት መሆኑን ያብራሩት ከንቲባው የስራ አጥነት ችግር ጫፍ የነካ የከተማ አስተዳደሩ ሊቆጣጠረው ከሚችለው በላይ ነው ይላሉ።ለዚህ ትልቁ ችግር በአካባቢው በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሰሩ ስራዎች በጣም አነስተኛ በመሆናቸው ነው። ከዚህ ቀደም በፌዴራል መንግስቱ ለከተማዋ በከተማዋና አካባቢው ለመገንባት ቃል የተገቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ሌሎች ፕሮጀክቶች በተገባው ቃል መሰረት ወደ ስራ አለመገባቱ ስራ አጥነቱን አባብሶታል ሲሉ ይገልጻሉ።
በአካባቢው የኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት ባይቻል እንኳ በሀገር ደረጃ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተገነባባቸው ቦታዎች በፌዴራል መንግስት የተገነቡ ፓርኮች እንደመሆናቸው ከአካባቢው ወጣቶች ሄደው የሚሰሩበት ሁኔታዎች አለመፈጠራቸው ችግሩ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል።
በመገባደድ ላይ ባለው በጀት ዓመት 11 ሺህ ወጣት ወደ ስራ ለማስገባት እቅድ ቢያዝም እስከ ሚያዚያ ወደ ስራ የገበው ግን የእቅዱን 50 በመቶ እንኳ አይሆንም። በአካባቢው ካለ ቢራ ፋብሪካ እና ከወልቂጤ ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበር ስራ እድል ለመፍጠር የተደረጉ ጥረቶች አሉ። ነገር ግን አብዛኛው ስራ ጊዜያዊ ነው። የስራ አጡንም ችግር የማይቀርፍ፤ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ስራ እድል ነው የተፈጠረው።
ከንቲባው እንደሚሉት፤ ከስራ አጥነት ባሻገር በከተማዋ ያለው የኑሮ ውድነት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል። የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ከተማ አስተዳደሩ መሰራት ያለባቸው ስራዎችን አልሰራም። በተለይም አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ምርት ሰብስበው በማስቀመጥ የከተማዋን የኑሮ ውድነት ለማባባስ እንደሚሰሩ እየታወቀ እርምጃ በመውሰድ ረገድ የከተማ አስተዳደሩ ጉድለት አለበት። ምክንያቱም እርምጃዎች ሲወሰዱ ከብሄረሰብና ከሀይማኖት ጋር የማያያዝ ሁኔታ አለ። ከብሄር ጋር እንዳይያያዝ እና የሶሻል ሚዲያ ሰለባ ላለመሆን በመፍራት ተገቢው እርምጃ እየተወሰደ አይደለም።
በቅርቡ በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ምርት የሚያከማቹ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ የግድ አስፈላጊ መሆኑ ላይ ከከተማ አስተዳደሩ እና ከዞን አመራሮች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል። አሁን ስራ ተጀምሯል። ሸቀጦች እየተከማቹና እየተደበቁ መሸጥ የለባቸውም ብለን እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። እርምጃ ከመውሰድ ጎን ለጎን በከተማዋ ተፎካካሪ ነጋዴዎችን ለመፍጠር እየተሰራ ነው፡፡ ዘይት እና የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋ ላይ አላስፈላጊ ጭማሪ እንዳይደረግ እና የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ዛሬም ችግሩ ቀጥሏል ይላሉ ከንቲባው በመሆኑም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግሩን ለመቆጣጠር በስፋት ይሰራል።
ከንቲባው ከተማዋን የቱሪዝም እና ኮንፈረንስ ከተማ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። ከተማዋ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ከማዕከላዊ የኢትዮጵያ ክፍል ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚሆኑ አዳራሾች ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው። ከዚያ ጎን ለጎን በከተማዋ አቅራቢያ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን የሚጎበኙ ቱሪስቶች በከተማዋ እንዲቆዩ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 9/2013