አዲሱ ገረመው
ክፍል ሁለት
ውድ አንባብያን እንደምን ከረማችሁ? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? እኔ ዘመነ ጉንፋን አይሎብኛል። ያው ትንሽ ካፊያ ቢጤ ስላለ አቧራውን ሲያስነሳ የሚያጋጥም ነው ብዬ ተረጋግቼ እየተመለከትኩት ነው። መቼም በዚህ ዘመን ጎንፋን የሚባል ወሬ በኮሮና ስለተለወጠ ቃሉ ራሱ አዲስ ሳይሆንባችሁ አይቀርም። እንኳንስ ጉንፋን ሊታወሰን፤ ሲያነጥስ “ይማርህ” መባሉስ ቀርቶ የለ። ለማንኛውም ሰላማችሁ ይብዛላችሁ እያልኩ ሳምንት ከጉዞ ማስታወሻዬ ከጀመርኳት የፋሲለደስ ቤተ መንግስት አጭር ቅኝት ቀሪውን ክፍል እነሆ ብያለሁ።
የትም ይሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ተዘዋውሬ የማያቸው ኅልቆ ወመሳፍርት የሚዳሰሱም ሆኑ የማይዳሰሱ ቅርሶቻችንን ሳይ እኮራለሁ፤ ማንነቴን አገኘዋለሁ፤ ደስታ ይሰማኛል፤ በማያቸው ነገሮች እገረማለሁ፤ ትልቅ ታሪክ ያላት አገር ያለኝና እኔም የዚህ ታሪክ አባል መሆኔን እንደ እድል እቆጥረዋለሁ።
“የማያውቁት አገር አይናፍቅም” ቢባልም፤ እኔ ግን የማላውቃቸው የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች ሀረር ከነምንጣፏ፣ ድሬደዋ ከነአሮጌው ሰፈሯ፣ አሰበ ተፈሪ ከነብርቱካኗ፣ በሰሜኑም ቢሆን ባህር ዳር ከነ ጣናዋ፣ ጎንደር ከነ ፋሲለደሷ፣ ደቡብም፣ ምእራቡም ሁሉም…ጭራሽ እንደ ልጅነት ትዝታ ነው የሚናፍቁኝ። ይኸው ናፍቆቴን ልወጣ ከናፈቀችኝ ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ፋሲለደስ ቤተ መንግስት ውስጥ ከትሜያለሁ።
እዚህ ስፍራ ከረጅም ዓመታት በፊት የተገነቡት የጎንደር ቤተመንግስታት የኢትዮጵያን ቅድመ ልዕልና ሕይወት ሲዘሩበት በዓይናችሁ ትመለከታላችሁ። አንዱን ስመለከት ሌላኛው የሚያመልጠኝ ይመስል ሐሳቤን መሰብሰብ አቃተኝ። ሁሉም ነገር ዓይን አዋጅ ነበር። በተለይ ያለኝን ውሱን ሰአት ባሰብኩ ቁጥር ከዚያ ከወጣሁ
በኋላ ምንም የሚያስደስተኝ ነገር የሌለ አስመሰለው። እድሜዬ ልክ የቤተመንግስታቱን መካነ ሕንፃ ካየሁባት ደቂቃ በኋላ ብቻ እንዲቆጠር ፈለግኩ፤ ወደድኩትም።
ለአስጎብኚው ቲፕን ያካተተ ገንዘብ ልንከፍል ነበር። እንኳንስ የአገር ቅርስ ይቅርና እንቶ ፈንቶ የሆኑ ወሬዎችን በማህበራዊ ሚዲያ ከፍለን አይደል እንዴ የምናየው። ዳሩ ምን ያደርጋል አስጎብኚ አጣን። እያንዳንዷን ነገር አብጠርጥሮ የሚነግር ሰው ያስፈልግ ነበር። ምናልባትም ፈቃደኛ ያልሆኑት ጋዜጠኛ መሆናችንን ስላወቁና የሚያውቁትን እውነታ ቢናገሩ ሌላ ችግር ይደርስብናል ብለው ስላሰቡ ይሆናል።
ቅርሱን ከታሪክ አጣቅሶና የአሁኑን ነባራዊ እውነታ የሚነግረን ቢጠፋም ከማየት አልቦዘንኩም። ይህ ታሪካዊ ህንጻ የተገነባባት ጥበብ አስደናቂ ነው። ጥበብ የተሞላበትን ኪነ ህንፃ ሳይ በኢትዮጵያዊነቴ ኩራት ተሰማኝና ደስታዬን እያጣጣምኩ በትዝብት መመልከቴን ቀጠልኩ። ምንም እንኳን ከእርጅናው ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጠባሳዎች ቢገጥሙትም ዘመናትን ተሻግሮ ለዛሬው ትውልድ ለመድረሱ ምክንያት የሆኑትን አለማመስገን ንፉግነት ነውና ምስጋና ይገባቸዋል።
ወደ ውስጠኛው ክፍል ከመዝለቃችን በፊት ውጨኛውን ክፍል ለማየት ሞክሬ ነበር። ሊፈረካከሱ ጫፍ የደረሱ የህንጻው አካላት ይታያሉ። መቼስ በፈጣሪ ቸርነት ካልሆነ የትኛው ኃይል ደግፏቸው እንደቆዩ መመሳከሪያ የላቸውም። እዚህ ስፍራ ላይ ደርሶ ታሪክን አይቶ ከመደሰት ባሻገር ቅርሱ ተሰነጣጥቆና ተሰባብሮ ማየቱ ደግሞ ልብ ይሰብራል።
ቤተ መንግስቱን ሲያዩት ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ሊሰማዎት ይችላል። የታሪካዊነቱን ያህል እንክብካቤ መነፈጉ ያሳፍራል። እነዚያ አስጎብኚዎች ስለ ቅርሱ አንናገርም ያሉት ለካ እውነታቸውን ነው አልኩ በልቤ። ምን ይታወቃል ተናግረው ሲደክማቸው ሰሚ ቢያጡ ነው ዝምታን የመረጡት።
በጉብኝቴ ብዙ ጠብቄ ነበር። ይሁን እንጂ ያየሁት ነገር አስደንግጦኛል። እንዴት አገራዊ ቅርስን ያህል ለዚያውም ዓለም የመዘገበችውን ቅርስ ማንም በዘፈቀደ ገብቶ እንዳሻው ይጨፍርበታል? ተመልከቱ ቅርሱን ለማየት በገባንበት ቅጽበት ቁጥራቸው ከአምስት የማይዘሉ ወጣቶች ከኛ ፊት ነበሩ። እናም ባገኙት ቦታ ላይ ነው የሚቀመጡት። ቅርሱ ይጎዳል፤ ክልክል ነው የተባለ ነገር ስለሌለ ሲያሻቸው ይተሻሹበታል፤ ለፎቶአቸው ማማር ደግሞ ተኝተውበትም ቆመውበትም ይነሱበታል።
እይታዬ ሁሉ ጥልቅ ስለነበር፤ በእይታዬ ሁሉ የማባክነው የሰከንድ ቁራጭ አልነበረም። ምክንያቱም በአይኔ ያየሁት መካነ ህንጻ በልቡናዬ ከሳልኩት የተለየ ስለነበር ነው። ወደ ውስጥ ዘልቀን ስንመለከተውም የውስጠኛው የቤተ መንግስቱ ክፍሎች ግድግዳቸው ተሞነጫጭሯል። አሳፋሪ ጽሁፎች ተጽፈውባቸዋል። አንዳንዱን ግድግዳ ሲመለከቱ መጸዳጃ ቤት ውስጥ የሚጻፉ ነውሮች ሁሉ ሳይቀሩ ነው የተጻፉባቸው።
በቅርሱ ግድግዳዎች ላይ ካሉት አሳፋሪ ጽሁፎች በተጨማሪ የግድግዳው መሰነጣጠቅ አንዳንድ ቦታ ላይ ዘመም እንዲል አድርጎታል። የቆየ የሚመሰል እድሳት አልፎ አልፎ ቢታይም በንክኪ መብዛት የተነሳ ተሸርሽሯል፤ ካቦቹም ወዳድቀዋል።
በመሰረቱ ቤተመንግስቱን እኛ በጎበኘንበት ሁለት፣ ሦስት ሰዓት ጎብኝቶ መጨረስም ሆነ አገሬው በሚጠራው ፋሲል ግንብ ብሎ መግለፅ ማሳነስ ነው። የቤተመንግስታቱን መካነ ሕንፃ አብጠርጥሮ ለመጎብኘት ግማሽ ቀን በቂ አይደለም። በጣም ሰፊ፣ በጣም የሚያምር፣ የማይጠገብ ነገር ግን ጉስቁልና የተዋሃዳው ሆኗል።
መንግሥትና የሚመለከተው የቅርስ ጥበቃ አካል ቅርሱን ምን እየደረሰበት እንዳለ ማወቅና መከታተል ይጠበቅበታል። እኛ የተመለከትነው የቅርሱን ተክለ ሰውነት ብቻ ነው። በዚህ አይነት ቤተ መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን በውስጡ ያሉት ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ምን ያህል ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው የሚለው በራሱ ሌላ አጀንዳ ነው። ችግሮች ካልተፈቱ ቅርሱ አደጋ ላይ ስለሚወድቅ ሳይቃጠል በቅጠል ሊባል ይገባል።
በጉብኝታችን መጨረሻ አንዱን የግቢው ጠባቂ ቅርሱ ለምን እንዲህ ሆነ የሚል ጥያቄ በተንሻፈፈ ቋንቋ ጠየቅነው። እሱም በቀጥታ ማስረዳት ባይችልም በጨዋታ መልክ በፋሲል ግንብ ቅጥር ግቢ ውስጥ በርካታ የሰርግ ሥነ ሥርዓቶች እንደሚካሄዱና ማህበረሰቡ ስለ ቅርስ በቂ ግንዛቤ ስለሌለው ብዙዎች ፎቶ ለመነሳት ግንቦቹ ላይ እንደሚወጡ አንዳንዶች ደሞ እንደሚጨፍሩበት፣ አንዳንዶች ደግሞ ያልተገባ ነገር ሲያደርጉ የተያዙበት አጋጣሚ እንዳለ ነገሩን።
እንደ ዓለም ቅርስነቱና ታሪካዊነቱ በመንግሥትም ሆነ በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም) ትኩረት ተሰጥቶት ክትትል ሊደረግበት እንደሚገባ ዝግጅት ክፍላችን አጽንኦት ይሰጠዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 9/2013