መላኩ ኤሮሴ
ኢማም ሀያቱ ሻሚል፤ በጉራጌ ዞን በቀቤና ወረዳ የገርባጃ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ሞዴል አርሶ አደር እና የቀቤና ብሔር ባህላዊ ዳኝነት ተሳታፊ ናቸው። የልጅነት ጊዜያቸውን በአዲስ አበባ ነበር ያሳለፉት። ለትምህርት ከፍ ያለ ቦታ እንዳላቸው የሚናገሩት ኢማም ሀያቱ በአዲስ አበባ ቀን ስራ እየሰሩ ማታ ደግሞ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ነበር።
ስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ቀይ ሽብር በመከሰቱ አዲስ አበባን ለቀው ወደ ትውልድ ቀዬቸው ቀቤና ገቡ። በወቅቱ ዘናጭ እንደነበሩ የሚናገሩት ኢማም ሀያቱ፤ ‘‘ዘናጭ ሰው በኢህአፓነት ይፈረጅ ነበር’’ ይላሉ። በወቅቱ የነበረው ሁኔታ እጅግ አስፈሪ በመሆኑ በኢሕአፓነት ላለመፈረጅ የጀመሩትን ትምህርት መቀጠል አልቻሉም። ወደ ትውልድ ቀዬያቸው ከተመለሱ በኋላም ትምህርታቸውን የመቀጠል ፍላጎት ነበራቸው።
ነገር ግን እንዳሰቡት አልሆነላቸውም። ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ባሰቡበት ወቅት እናታቸው ታመው ስለነበር እሳቸውን ማስታመም እና ማገዝ የግድ ስለሆነባቸው ትምህርታቸውን ትተው ትዳር መሰረቱ። የቤተሰብ አስተዳዳሪነት ኃላፊነት ከተጨመረባቸው በኋላ በትምህርት የመቀጠል ሀሳባቸውን በመተው ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ግብርና ስራ አዞሩ። ዛሬ በአካባቢው በግብርና ዘርፍ ስኬታማ ከሚባሉ አርሶ አደሮች አንዱ ናቸው።
በተለይም በአፈር ጥበቃ እና በንብ ማነብ ለአካባቢው አርሶ አደሮች አርዓያ ናቸው። በአካባቢው እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን የአፈር መሸርሸር ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በማልማት በሰሩት ስራ ስማቸው በጉልህ ይነሳል። አቮካዶ፣ ማንጎ እና ለንቦች እንደ ምግብነት የሚያገለግሉ ዛፎችን ለአካባቢው በማላመድ የመጀመሪያ ሰው ናቸው።
ለራሳቸው ከማልማት ባሻገር የተለያዩ ዛፎች ችግኝ በማፍላት ለሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች በማቅረብ ከራሳቸው ባሻገር የአካባቢው አርሶ አደሮች የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በማምረት የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡና ገቢ እንዲያገኙ ከማስቻላቸውም ባሻገር አርሶ አደሮቹ የአፈር ጥበቃ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥረት አድርገዋል።
የተከሉት የአቮካዶ እና ማንጎ ዛፎች በአንድ በኩል መሬት እንዳይሸረሸር እየተከላከለ ሲሆን በሌላ በኩል የፍራፍሬዎችን ምርት ለቤተሰባቸው ምግብነት ከመጠቀም አልፈው ለገበያ በማቅረብ ገቢ ያገኛሉ።
ኢማም ሀያቱ፤ 30 የአቮካዶ ዛፍ አላቸው። ከነዚህ አቮካዶዎች በየጊዜው ከፍተኛ የአቮካዶ ምርት ያገኛሉ። ከፍተኛ የአቮካዶ ምርት ቢያመርቱም በመንገድ ችግር ምክንያት ወደ ከተማ ማቅረብ አልቻሉም። ከተማው ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። ቀበሌያቸውን ከከተማው ጋር የሚያገናኝ መንገድ ባለመኖሩ የአቮካዶ ምርት በተሽከርካሪ ጭነው ለገበያ ማቅረብ አልቻሉም።
በጋማ ከብት ጭነው ለመውሰድ ጥረት ቢያደርጉም የአቮካዶ ምርት በከብት ተጭኖ ሲወሰድ ስለሚበላሽ በአካባቢው በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች በርካሽ ዋጋ ለሽያጭ ለማቅረብ ይገደዳሉ። በዚህም ምክንያት የአቮካዶ ምርትን ልጆቻቸው ከመጠቀም ባሻገር በአካባቢው በመሸጥ ከሚያገኙት ከመጠነኛ ገቢ ባሻገር ለገበያ በማቅረብ ማግኘት ያለባቸውን ገቢ ማግኘት እንዳልቻሉ ያነሳሉ።
በርካታ ፍራፍሬዎችን አምርተው ወደ ገበያ የማቅረብ እቅድ ቢኖራቸውም፤ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ወደ ገበያ የሚያቀርቡበት የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ሊያለሙ አልቻሉም። መንግስት በአካባቢው የሚስተዋለው የመንገድ ችግር የሚፈታበትን መፍትሄ መዘየድ እንዳለበት ይናገራሉ።
በልጅነታቸው ከአካባቢያቸው ወጣ ብለው አዲስ አበባን እና ሌሎች አካባቢዎችን ማየታቸው የፍራፍሬን ጥቅም እንዲያውቁና በአግባቡ እንዲረዱ ምክንያት ሆኗቸዋል። በተጨማሪም የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር በቅርበት መስራታቸው ሌሎች አካባቢዎችን ማየታቸው ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ ምክንያት ሆኗል።
የተለያዩ ዛፎችን ከማላመድና ከማባዛት ባሻገር፤ የንብ እርባታ ስራ ላይ በትኩረት ይሰራሉ።በተለይም የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል የተከሏቸው ዛፎች ለንብ እርባታ ስራቸው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ከስምንት በላይ የንብ ቀፎዎች ያላቸው ኢማም ሀያቱ ከአንድ ቀፎ በአንድ ጊዜ ከ20 እስከ 25 ኪሎ ማር ያመርታሉ።ማርን ለገበያ በማቅረብም ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ላይ ይገኛሉ።
ንብ የማነብ ስራ የቀፎዎችን አቀማመጥ ከማስተካከል እና ጉንዳን መሰል ተባዮች እንዳያጠቁት ከመከላከል ባሻገር ግብዓት እና የሰው ሀይል የማይጠይቅ መሆኑን የሚያብራሩት ኢማም ሃያቱ በዚህም ምክንያት ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከሌላው የግብርና ስራ ጎን ለጎን ንብ ማነብ እንደጀመሩ ነው የሚገልጹት።
የሰብሎች ተባይ ለማጥፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች በንብ ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑን የሚያነሱት ኢማም ሃያቱ፤ በዚህም ምክንያት በተለይም ሰብል ላይ ኬሚካሎች በሚረጩበት ወቅት ከፍተኛ የማር ምርት ማሽቆልቆል እያስከተለ መሆኑን ያብራራሉ። የአየር ሁኔታ መቀያየር፣ እጽዋት የሚያብበት ወቅት እና የዝናብ መብዛትና ማነስም ሁኔታም የማር ምርት እንዲጨምርና እንዲቀንስ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በአዝርዕት ላይ የሚረጩ ኬሚካሎች በንቦቹ ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩን ለመከላከል አዲስ ዘዴ ዘይደዋል። በንቦች እጅግ ተወዳጅ የሆነውን ካላንድራ የተሰኘ ዛፍ በመትከል ንቦቹ ከአካባቢው ርቀው ኬሚካል ወደሚረጭባቸው ቦታዎች እንዳይሄዱ እና ቀፎ አካባቢ እንዲቆዩ እያደረጉ ነው። ሆኖም ዛፎቹ ረጅም ጊዜ የማይቆዩ እና በየአምስት ዓመቱ መተካት ያለበት ነው። በመሆኑም ዛፎቹን በቀጣይ ዓመታት ለመተካት ዝግጅት እያደረጉ ነው።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ንብ ለማነብ ጥቅም ላይ የሚውሉ አብዛኞቹ እቃዎች እጥረት ዋጋ መጨመር እየተስተዋለ መሆኑን የሚያብራሩት ኢማም ሃያቱ፤ በተለይም ማር መጭመቂያ እና ሰም ማተሚያ እቃዎች በጣም ውድ መሆናቸውን ያነሳሉ። ይህ ደግሞ ለተራ ንብ አናቢ ከባድ ነው። የሀገሪቱ የማር ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ከተፈለገ የነዚህ እቃዎች ዋጋ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ መንግስት ትኩረት ማድረግ አለበት።
ኢማም ሃያቱ በአፈር ጥበቃ እና በንብ እርባታ ባሳዩት በጎ ስራ ከወረዳ እስከ ፌዴራል የተለያዩ ሽልማቶችን ተሸልመዋል። ሰርተፊኬት አግኝተዋል፤ የንብ ቀፎ በሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ካገኙዋቸው ሽልማቶች መካከል ከቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እጅ የተቀበሉት ሽልማት ከሌሎቹ ሁሉ ከፍ ያለ መሆኑን ያነሳሉ።
ሰባት ሄክታር ገደማ መሬት ባለቤት የሆኑት ኢማም ሀያቱ የተለያዩ ሰብሎችን ያመርታሉ። ከሚያመርቷቸው ሰብሎች መካከል ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ እና ሽምብራ ተጠቃሽ ናቸው። መሬትን አፈራርቆ መጠቀም ምርታማነት ለመጨመር ከፍተኛ ሚና እንዳለው በራሳቸው ተሞክሮ እንደደረሱበት ይናገራሉ። አምና ስንዴ የዘሩበት መሬት ላይ በቆሎ ለመዝራት በአሁኑ ወቅት ግማሽ ሄክታር ገደማ መሬት አርሰው አዘጋጅተው ዝናብን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ለበቆሎ የሚሆን ማዳበሪያ በእጃቸው ይዘዋል። ምርጥ ዘር ለመውሰድም በቀበሌ ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
ከሚያመርቷቸው ሰብሎች ዋነኛው ጤፍ ሲሆን ካላቸው ማሳ አብዛኛውን በጤፍ ነው የሚሸፍኑት። አምና ስንዴ እና በቆሎ የዘሩበት መሬት ላይ ዘንድሮ ጤፍ የመዝራት እቅድ ይዘዋል። በሚያዝያ ወር ዝናብ እንደሚጥል ተስፋ እንዳላቸው የሚናገሩት አርሶ አደሩ ዝናቡ እንደጣለ ለጤፍና ስንዴ የሚውል ማሳ እርሻ ለመጀመር መዘጋጀታቸውን ያነሳሉ።
የጤፍ ምርታማነት ከዓመት ዓመት ይለያያል፤ አንዳንድ ጊዜ በተመሳሳይ መሬት ላይ አንድ አይነት ሰብል በተደጋጋሚ ሲዘራ፣ ግብዓት በአግባቡ ስራ ላይ ሳይውል ሲቀር ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎች ምርታማነት ይቀንሳል። ግብዓቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለና አፈራርቀው ሲዘሩ በሄክታር እስከ 15 ኩንታል ጤፍ ያገኛሉ።
የማዳበሪያ ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ፣ የጸረ ተባይ እና የጸረ አረም ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መሄድ ከባድ ተግዳሮት እየሆነ መሆኑን የሚያብራሩት ኢማም ሃያቱ በተለይም ጤፍን ማምረት ከባድ እየሆነ መምጣቱን ያነሳሉ። ጤፍ ለማምረት የሚወጣ ወጪ ከሚገኘው ገቢ ጋር የማይጣጣም እየሆነ ነው ይላሉ።
ኢማም ሃያቱ እንደሚሉት፤ የግብርና ስራ በቴክኖሎጂ ካልታገዘ አስቸጋሪ ነው። በቀቤና አካባቢ የቴክኖሎጂ አቅርቦት አነስተኛ መሆን የግብርና ስራን አስቸጋሪ እያደረገው ነው። በተለይም የከርሰ ምድር ውሃን አውጥቶ ለመጠቀም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ባለመቅረባቸው በአመት አንድ ጊዜ ብቻ እያመረቱ ነው።የከርሰ ምድር ውሃን አውጥቶ ለመጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂ ቢቀርብ በዓመት ከሁለት እና ከዚያ ጊዜ በላይ በማምረት ራሳቸውን እና ሀገራቸውን መጥቀም ይችሉ እንደነበር ያነሳሉ።
የ10 ልጆች አባት የሆኑት ኢማም ሃያቱ እሳቸው በሁኔታዎች አለመመቻቸት ምክንያት በትምህርት መግፋት አለመቻላቸው ሁሌም ይቆጫቸዋል። ልጆቻቸው ኋላ ቀር የግብርና ስራን እንዲወርሱ አይፈልጉም። በትምህርት የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ይፈልጋሉ። በመሆኑም ልጆቻቸውን በማስተማር ላይ ይገኛሉ። አንድ ልጃቸው የመጀመሪያ ዲግሪውን ተመርቆ እና የመንግስታዊ ስራ ተቀጥሮ እየሰራ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ታናናሾቹ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው። የተወሰኑት ትምህርት አቋርጠው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ውጭ ወጥተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 7/2013