‹‹ከአትክልት ዘር የማላመርተው የለም። በዓመት ሦስቴ የማመርተውን ሽንኩርት ጨምሮ ሁሉንም አመርታለሁ›› ያሉን አርሶ አደር ትዕግስት ሆሬሳ የመቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ሕብረት ሥራ ዩኒየን አባል ናቸው።ሆኖም በዩኒየኑ በአባልነት ከመታቀፋቸው በፊት በነበሩት ረጅም ዓመታት በፊት በምርታቸው ተጠቃሚ እንዳልነበሩም ነግረውናል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ያኔ ምርታቸውን የሚቀበላቸው ማህበር ባለመኖሩ ነበር። በመሆኑም ያመረቱት ምርት በቤት ውስጥ ከሚጠቀሙት ውጪ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የሚባክንበትና የሚበላሽበት ሁኔታ እንደነበር ያስታውሳሉ ። በዚህ ምክንያት ተስፋ የቆረጡበት ጊዜ ብዙ እንደነበረ ይናገራሉ ። ‹‹አምርቼ ተጠቃሚ ባለመሆኔ ካላመረተው የማልለይበት ሁኔታ ነበር ›› ሲሉም ይገልፁታል። ስለሆነም ወርሀዊ ወጪያቸውን መሸፈን ይቸገሩ ነበር ።
አሁን ግን በዩኒየኑ በአባልነት ከታቀፉ ጊዜ ጀምሮ በማህበራት አማካኝነት ምርታቸውን የሚያስረክቡበት ሰፊ ዕድል በማግኘታቸው የልፋታቸው ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ተጠቃሚነታቸው ባቀረቡት የአትክልት መጠን በተሳትፎና በዕጣ ላይ የተመሰረተ ነው። በተጨማሪም በዩኒየኑ አማካኝነት ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የተለያዩ ስልጠናዎችና የባለሙያ ድጋፎችን በተከታታይ ማግኘት መቻላቸውንም አስረድተዋል።
ሌላው የዩኒየኑ አባል አርሶ አደር እቼ ደላሼ የሀጤለማ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የተሰማሩት በአትክልት ምርት ላይ ነው። እንደሳቸው የሚኖሩበት ዞን ስምጥ ሸለቆ ውስጥ እንደመሆኑ የአየር ፀባዩም ሆነ አፈሩ አትክልት በስፋት ለማምረት ምቹ ነው።አትክልት በስፋት ማምረት ማስቻሉ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ በኩልም እንደ አንድ አማራጭ የሚወሰድ ነው። በመስኩ የተሰማሩትም ከቤተሰባቸው ጀምሮ እንደ ሀገር የሚሰጠውን ይሄንኑ ጥቅም ታሳቢ አድርገው ነበር ። ሆኖም በገበያና በአትክልት ዘር አቅርቦት ዕጦት ሲቸገሩ ኖረዋል። ታሳቢ አድርገው የተነሱበትን ስኬትም በቅርቡና በቀላሉ መሸጥ ሳይችሉ ቆይተዋል።ይሄ ችግራቸው የተቀረፈው የዩኒየኑ አባል ከሆኑ በኋላ ነው። በአንድ ዕጣ ከ2 ሺህ 500 ብር ጀምሮ ተሳትፎ ማድረግ መጀመራቸውንም አልሸሸጉም ። በተለይ የፈለጉትን አይነት ዘር በፈለጉት ጊዜ ከዩኒየኑ ማግኘት በመቻላቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ ።
አርሶ አደር ጅማ አምዴ በፍራፍሬ ምርት ቢሰማሩም በአብዛኛው ግን ፓፖያ ነው የሚያመርቱት። በተለይ ለፓፓያ አካባቢው ተስማሚ እንደሆነ ይናገራሉ። ፍራፍሬ በተለይም ፓፓያ በባህሪው ቶሎ ይበላሻል። በመሆኑም የሚመረትበትም ሆነ ለገበያ የሚቀርብበት መንገድ ጥራቱ የተጠበቀ ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ መሆን እንዳለበት ምክራቸውን ይለግሳሉ። አሁን በዚህ መንገድ ለሀገር ውስጥ ገበያ በዩኒየኑ አማካኝነት እያቀረቡ ከሚገኙት ምርቶች መካከል ፓፓያና ሀባብ ፍራፍሬዎች ይገኙበታል።
አርሶ አደር ሼህ ሁሴን የአዳሚ ቱሉ ነዋሪ ናቸው። በ1999 ዓ.ም ዩኒየኑን በአባልነት መቀላቀላችውን ያወሳሉ። የሚኖሩበት አካባቢ ቆላና ደጋ የአየር ንብረት ያለው ነው ። በበጋም ሆነ በበልግና በክረምት ምርት ለማምረት ያመቻል። በዚህ ላይ የዘዋይ ሀይቅ የሚገኘው በአቅራቢያቸው ነው። ምስራቅ ሸዋ ዞን የብዙ ወራጅና የከርሰ ምድር ውሀ ባለቤት ነው። ዓመቱን ሙሉ ሳያርፉ አትክልትና ፍራፍሬ በስፋት ለማልማት አስችሏቸዋል። ጎመን ፣ሽንኩርትና ቲማቲም ዓመቱን ሙሉ በማሳቸው ከሚያለሟቸው የአትክልት ምርቶች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም የበቆሎ ምርጥ ዘርም ያመርታሉ። ያመረቱትን ምርት ለዩኒየኑ በማቅረብና በዕጣና በተሳትፎ እስከ 400 ሺህ ብር የሚጠጋውን ከፍተኛ ጠቀሜታ በማግኘት ቀዳሚ ናቸው። እኝህን አርሶ አደር ከሌላው አርሶ አደር የሚለያቸው የዩኒየኑን ጥቅም በተገቢው መንገድ ተረድተው አንድ ልጃቸውንና ባለቤታቸውን የዩኒየኑ አባል ማድረጋቸው ነው። በተጨማሪም በሥራቸው 125 አርሶ አደሮች አቅፈው ይዘዋል።
አርሶ አደሮቹ እንደ እርሳቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ዩኒየኑ በየዓመቱ የሚያስረክባቸውን ከአንድ ሺህ ኩንታል በላይ የአትክልት ዘር በራሳቸው መጋዘን በማከማቸት ያከፋፍላሉ። እርሳቸው ለአካባቢው አርሶ አደሮች አርአያ ሲሆኑ ማሳቸው ደግሞ በሰርቶ ማሳያነት ያገልግላል። በዚህ ሁሉ በዩኒየኑ አማካኝነት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የገበያ ትስስር ችግራቸውን ከመፍታት ባሻገር ሀብት መፍጠር ችለዋል። በጥሬው ያኖሩት ገንዘብ ሳይጨምር በቋሚ ንብረትነት ወፍጮ ቤት፣ በተለያዩ አካባቢ ያሉ ሁለት መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ለምርታቸው ማጓጓዣ አይሱዙ መኪና ማፍራት ችለዋል። በራሳቸው የፈጠሩት የሥራ ዕድልም አለ። አሁን ላይ በመካከለኛ ባለሀብቶች ረድፍ ለመሰለፍና በጥረታቸው በተደጋጋሚ የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማቶችን ከመንግስት አካላት ለመቋደስም በቅተዋል።
አቶ አሸናፊ ሮባ የዩኒየኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት ዩኒየኑ በአካባቢው የሚገኙ ተፈጥሯዊ ምቹ ሁኔታዎችን ሁሉ በመጠቀም በምርቱ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን በማሰባሰብ ከተመሰረተ ሁለት አሥርት ዓመታትን አስቆጥሯል። አመሰራረቱ በአካባቢው በፍራፍሬና አትክልት ምርት ላይ የተሰማሩ የነዚህኑ አርሶ አደሮችን የገበያ ችግር መፍታትን መሰረት አድርጎ የተነሳ ነበር። ከዚሁ ጎን ለጎን የአርሶ አደሩንና የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ሰንቆ ነበር። የፍራፍሬና አትክልት ምርትን በጥራት ማምረትና ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ ማቆየትንም ታሳቢ ማድረጉ ለምስረታው መነሻ የነበረ መሆኑን ይጠቅሳሉ ። እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ የተመሰረተው በ500 ሺህ ብር ካፒታል ነው። ያኔ ሌላው ቀርቶ በስብሰባ ወቅት አባላቱ የሚቀመጡበት ደረጃውን የጠበቀ ወንበር እንኳን አልነበረውም። የነበሩት መሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማህበራት አባላትም ቢሆኑ 12 ነበሩ። አሁን ላይ የነዚህ ማህበራት ቁጥር ወደ 152 አድጓል። በግለሰብ ደረጃ በተናጠል ያሉት አባላት ቁጥር ደግሞ ዘጠኝ ሺህ ደርሷል። ዩኒየኑ በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥና በውጪ በፈጠረው የገበያ ትስስር ዕድል አርሶ አደሩ የነበረበትን የገበያ ችግር ሙሉ በሙሉ ፈቷል።
እያንዳንዱ አርሶ አደር 2ሺህ 500 ብር የአንድ ዕጣ ጀምሮ በሚያቀርበው ምርት መጠን ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ ነው። እንደ መሰረታዊ ማህበር በገንዘብ የሚገኘው ጥቅም ትንሹ 10ሺህ ትልቁ ደግሞ ከ330 ሺህ እስከ 400 ሺህ ይደርሳል። ከዘር ጀምሮም ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችን ለአርሶ አደሩ እያቀረበ ይገኛል። አባላቱ ምርቱን ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ አልፎ ለዓለም ገበያ ወደ ማቅረብ ከፍ እንዲሉ የሚያስችል ትልቅ አቅም ፈጥሯል። በአሁኑ ወቅትም ካፒታሉ 74 ሚሊዮን ብር ደርሷል። አባላቱ በተናጠል ማፍራት የቻሉት ሀብትም ለተጠቃሚነታቸው ለመሥራቱ መገለጫ ይሆናል። በዚህ ላይ የተለያዩ ሙያዊ እገዛዎችን ያደርጋል ። በባለሙያዎች አማካኝነት ለአርሶ አደሩ በዘር መረጣ፣ በፀረ-ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ዙሪያ ምክር በመስጠት ድጋፍ ያደርጋል። ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል በመፍጠርም በኩል አስተዋጾው የጎላ ነው።
ዩኒየኑ ለ97 ቋሚ እና በተከላ፣ በኩትኳቱና በምርት ስብሰባ ወቅት ለሚቀጠሩ ጊዜያዊ ሰራተኛነት ከ200 በላይ ሰራተኞች የስራ እድል ፈጥሯል። በዚህም የሴቶቹ ቁጥር ከፍተኛ ነው ።
በአጠቃላይ በድህረ ምርት ሂደት ፣ በእንክብካቤና አያያዝ እንዲሁም በምርት እሸጋ የሥራ ሂደቶች ከ90 በመቶ በላይ ለሆኑ ሴቶች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል።ዩኒየኑ በፈጠረው የምርትና ገበያ ድጋፍ ተጠቃሚ በመሆን ምንም አቅም ያልነበራቸው ከ15 በላይ አርሶ አደሮች አቅማቸውን ማጎልበትና ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በየራሳቸው የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። እራሳቸውን በማብቃት የትራክተርና የተለያዩ ንብረቶች ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። የራሳቸውን የገበያ ማዕከል አዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች የከፈቱ መኖራቸውንም ገልጸዋል ።
‹‹የአትክልትና ፍራፍሬ ምርታችንን እሴት በመጨመር ጭምር በስፋት የምናቀርበው ለአዲስ አበባ ከተማ ነው›› ይላሉ አቶ አሸናፊ ። ምርታቸው ሳይበላሽ ለገበያ የሚያቀርቡትም ባላቸው የማቆያና የማጓጓዣ ማቀዝቀዣ መጋዘኖችና መኪኖች መሆኑን ይናገራሉ። ምርቶቹን ለገበያ የሚያቀርቡት ጥራቱን ባሟላ መልኩ ሲሆን ይሄም በአሁኑ ወቅት የኣለም አቀፍ የምርጥ ጥራት ደረጃን አሟልቶ እንዲገኝ አስችሎታል። በዚህም ዓለም አቀፍ ለሆኑ የሀገር ውስጥና የውጪ ተቋማት የምርት አቅራቢ ለመሆን መብቃቱን ይጠቅሳሉ ።
ዩኒየኑ ምርቱን ከሚያቀርብላቸው ተቋማት መካከል የኢትዮዽያ አየር መንገድ እንደሚገኝበት የገለፁልን ደግሞ የዩኒየኑ የገበያ ክፍል ኃላፊ አቶ ብሩ መልካ ናቸው።‹‹ዩኒየኑ አትክልትና ፍራፍሬ የሚያቀርበው እንደ ደንበኛው ፍላጎት ነው››የሚሉት ኃላፊው አየር መንገድ ጋር በገባው ውል አማካኝነት 10 ዓይነት የአትክልትና ፍራፍሬዎችን እንደሚያቀርቡ ይናገራሉ። ከሚያቀርባቸው ምርቶች መካከል ሽንኩርት፣ቲማቲም ፎሶሊያ፣ጥቅል ጎመን፣ዱባ፣የሀበሻ ጎመን ፣ቃርያ እንዲሁም ከፍራፍሬ ሀባብና ፓፓያ ይገኙበታል።ዩኒየኑ በአዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ የችርቻሮ መደብሮች፣ለሸማች ማህበራትና በከተማዋ ለሚገኙ የተለያዩ ዩኒየኖች በፈጠረው የገበያ ትስስር በመታገዝ የሚያቀርብ መሆኑንም ነግረውናል።በተጨማሪም ለመቂና ለአዳማ ያቀርባል።
የዩኒየኑ የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ያደሳ እንደሚሉት ፤ አርሶ አደሩ የተሻለ የትርፍ ክፍፍል ተጠቃሚ መሆን ችሏል። በአሁኑ ወቅት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተደራሽ ለመሆን እየተጋ ይገኛል።በአዲስ አበባ ብቻ አምስት የመሸጫ መደብሮች አሉት።በአዳማና በመቂም እንዲሁ መደብሮች ያሉት ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎንም ቡታጅራ አካባቢ በሚገኝ አንድ ድርጅት አማካኝነት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶቹን ወደ ውጪ በመላክ ለውጪ ገበያ እያቀረበ ይገኛል።ለአብነትም በቅርቡ 10 ኩንታል ፎሶሊያ መላኩን ይጠቀሳሉ።እንዲሁም ትልቁን ድቡልቡል ቃርያ (ቼሌ ራዴ) እና ትንሽዋን ሾጣጣ ቅርጽ ያላት ሚጥሚጣ (አይቨርድ ችሊ) ወደ ውጭ የመላክ ውል አጠናቅቆ በዝግጅት ላይ መሆኑን ይጠቅሳሉ። በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን በጠበቀ መልኩ የምርት አቅርቦት በማድረግ ለመሳተፍ 400 አርሶ አደሮች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል።
ዩኒየኑ በዚህ ዓመት በትጋት ሲሰራ የቆየው 152 አባል ማህበራቱን ወደ 177 ማሳደግ ላይ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ።ዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግና ግሎባል ሰርተፊኬት ለማግኘት 48 አቅም ያላቸው አርሶ አደሮች በማደራጀት እየሰራ ይገኛል።ምርቶቹን በስፋት ወደ አዲስ አበባ የሚያቀርበው የመቂ ባቱ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ኀብረት ሥራ ዩኒየን በምርት ላይ እሴት በመጨመርና ምርት እንዳይበላሽ በቀዝቃዛ ማቆያ መጋዘንና ማቀዝቀዣ ባላቸው ማጓጓዣ መኪኖች በመጠቀም ምርቱን ከብክነትና ከብልሽት ይታደጋል። ይህም በዓለምም ሆነ በሀገር ውስጥ ገበያ ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያደርገዋል ። መልካም ንባብ!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27/2013