ከኢትዮጵያ ሕዝብ 85 በመቶ የሚሆነው በገጠር የሚኖር እና በእርሻ ስራ የሚተዳደር ነው። የግብርና ዘርፉ ለምግብ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን በወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይታወቃል። በኢንቨስትመንቱ መስፋፋት የጎላ ድርሻ ሲኖረው በሥራ ዕድል ፈጠራም የማይናቅ ሚና ይጫወታል።
በመሆኑም በክረምት ወራት መላውን አርሶ አደር ጨምሮ የዘርፉ ማህበረሰብ በሙሉ የግብርና ሥራውን የተሳለጠ ለማድረግ ርብርብ ይደረጋል። በተለይም የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በመኽርም ሆነ በበልግ እንዲሁም በመስኖ የግብርና ልማት ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቶት በስፋት ይሰራል። በመሆኑም ከፍተኛ መጠን ያለውን የሰብል ምርት ያቀርባል፡፡ በዚህም የዜጎችን የመኖር ህልውና እያስጠበቀ ይገኛል።
በ2013/14 የመኽር ምርት ዘመን በ4 ነጥብ 59 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ላይ 131 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት አቅዶ ወደ ሥራ የገባበት ሁኔታ ነበር። ይሁንና አሸባሪው የህወሓት ቡድን ይሄን እንደ ሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለውን ዋነኛ የግብርና ሥራ ወቅት ጠብቆና መንግስት ለግብርናው ሥራ ከፍተኛ አበርክቶ ያደርጋል በሚል ያደረገውን የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት ለጥፋት ሥራው በማዋል ክልሉን በጦርነት ሲያምስ ከርሟል። በዚህም አርሶ አደሮችን ጨምሮ ሌሎችም ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። አንዳንዶቹ የእርሻ ስራቸውን አቋረጠው ለህልውና ዘመቻው ተሰልፈዋል። በዚህም የእርሻ ስራቸው ተስተጓጉላል።
ዋግ ኽምራ፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደርና ሰሜን ወሎ በእብሪት ከወረራቸውና የግብርና ሥራው ከተስተጓጎለባቸው አካባቢዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ከክልሉ ግብርና ቢሮ እንዳገኘነው መረጃ በነዚህ አራት ዞኖች የሚገኙ 42 ወረዳዎች የግብርና ሥራው ላይ የክፋት ቡድኑ የከፋ ውድመት ፈጽሟል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ የታረሱ የእርሻ ማሳዎች በዘር ሳይሸፈኑ ጾም እንዲያድሩ፣ ቀድመው የተዘሩ ሰብሎች በጦርነት፣ በአረም፣ በተባይና በእንስሳት እንዲወድሙ ማድረጉን ያወሳሉ። ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ሌሎች ለሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከነበሩበት የዩኒየኖች መጋዘን ዘርፏል፤ የተረፈውን አቃጥሎ ከጥቅም ውጪ አድርጓል። ለጥፋት በተነሳው ቡድን ምክንያት ሰብሉ የከፋ ጉዳት ስለደረሰበት በማሳ ላይ ተበትኖ የነበረው ማዳበሪያም ለብክነት ተጋልጧል።
የግብርና መምሪያዎች፣ የወረዳ እና የቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤቶች እንዲሁም የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማት፣ ተሽከርካሪዎች የዘረፋው ሰለባ ሆነዋል። የእንስሳት ሕክምና መስጫ ክሊኒኮች፣ ቁሳቁሶችና መድሃኒቶችም እንዲሁ ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል። በአጠቃላይ ለግብርና ጠቃሚ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ተጎድተዋል።
ለአብነትም ለመስኖ ልማት የተዘጋጁ የመስኖ አውታር ግንባታዎች ላይ የደረሰውን ለማሳያነት ይጠቅሳሉ። ቡድኑ ለመኽር ምርት ይደርሳል ተብሎ የለማ የቀይ ሽንኩርት ከዛው ከማሳው ሳይነሳ እንዲበላሽ አድርጓል። ችግኝ ጣቢያዎችን ካምፕ ከማድረግ አልፎ የፈሉ ችግኞች ላይ ጉዳት አድርሷል። በአጠቃላይ በእነዚህ አራት ዞኖች የሚገኝ ሕብረተሰብ ለዓመታት ደክሞ ያከናወናቸው የአፈርና ውሃ ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። ቡድኑ በእንስሳቱ ልማት ዘርፍም ከእርሻ ማሳና ከምርት ግብዓቱ ባልተናነሰ ሁኔታ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ተስፋሁን ያወሳሉ።
በርካታ የእርሻ በሬዎችና እንስሳት በቡድኑ ታርደው መብላታቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል። ከዚህም አልፎ አሸባሪው ቡድን በአስገራሚና በአሳዛኝ ሁኔታ የቤት እንስሳቱን እንደ ሰው በጥይት ተኩስ መግደሉን ይናገራሉ ።
በመሆኑም ቢሮው ይሄን ውድመት ለማካካስና፤ በ2013/14 ምርት ዘመን በ4 ነጥብ 59 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ 131 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት የተነሳበትን ዕቅድ ለስኬት ለማብቃት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የማካካሻ ዕቅድ አቅዶ በትጋት ሲሰራ ቆይቷል። 4 ሚሊዮን 580 ሺህ 434 ሄክታሩ መሬት በማረስ አሁንም እየሰራ ይገኛል። 224 ሺህ ሄክታር በ 760 ትራክተሮች በመታገዝ መታረስ የቻለ ሲሆን ከታረሰው ማሣ ውስጥ 4 ሚሊዮን 500 ሺህ ወይም 95 በመቶው በበቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ ሰሊጥ ዘር መሸፈን ችሏል። ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ተስፋሁን እንደነገሩን ማካካሻ ሥራው በአጠቃላይ ጦርነት በተካሄደባቸው በአራቱ ዞኖችም ሆነ በሌሎችና ትርፍ አምራች በሆኑ አካባቢዎች ምርትና ምርታማነትን በብዙ እጥፍ ለመጨመር ያለመና በሦስት ስትራቴጂዎች የተቃኘ ነው። ያልተከናወኑ ሥራዎችን በቀሪዎቹ ጊዜያት ማከናወን፣ በመስኖና በበልግ የሚሰሩ የእርሻ ሥራዎችን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በውጤታማነትና በፍጥነት መተግበር የስትራቴጂ ቅኝቱ የሚያጠነጥንበት አብይት ጉዳይ ነው።
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ ቡድኑ ባደረሰው ውድመት ምክንያት ለረሀብ የተዳረጉ አርሶ አደሮችንና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መታደግ በሚያስችሉና በፍጥነት በሚደርሱ ሰብሎች ማሳዎችን መሸፈን ቀዳሚው ሥራ ነው።
በቀሪዎቹ ጊዜያት በቡድኑ የእብሪት ወረራ ምክንያት ሥራ ያቆሙ የግብርና ተቋማትና አርሶ አደሮች ወደ ሥራ ፊታቸውን እንዲመልሱ በማድረግ በዘር ያልተሸፈኑ የታረሱ ማሳዎችን ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎች እንዲዘራባቸው በማስቻል በዘር መሸፈን ሥራ ይሰራል። እስከ አሁንም በፍጥነት በሚደርሱና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ፍራፍሬና አትክልት ላይ ትኩረት አድርጎ እየተካሄደ ባለው በአረንጓዴ አሻራ ተግባር በመታጀብ ሲሰራ ቆይቷል። ሁሉንም የመስኖ ውሃ አማራጮች አሟጦ በመጠቀም ከሚዘሩትና ከተዘሩት ምርቶች መካከልም ሥራ ሥር፣ ቅጠላ ቅጠል፣ የጓሮ አትክልትና ሌሎች በፍጥነት የሚደርሱ ሰብሎችን በቅንጅት ማልማት ተችሏል።
ለቀጣይ ምርት ዘመን ከሚያስፈልገው የተለያየ ምርጥ ዘር ብዜት ጀምሮም ለምግብ ዘይት ግብዓት የሚውለውንና ለፋብሪካ በጥሬ ዕቃ ግብዓትን የሚያገለግለውን አኩሪ አተር በስፋት ማምረትን ሰንቋል።
የክልሉ መንግስት በክልሉ ብዛት ያላቸው የዱቄት፣ ፓስታ፣ ዘይትና የተለያዩ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እየገቡ መሆናቸውን ተከትሎ በተለይም በገበያ ላይ እንደ ሀገር እያጋጠመ ያለውን የዘይት እጥረት ለመፍታት፤ የአኩሪ አተር ምርትን ለፋብሪካዎች በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ ይቻል ዘንድ 143 ሺ ሄክታር መሬት አቅርቧል።
በ2013/14 ምርት ዘመንም ከሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ አኩሪ አተር ለማምረት አቅዶ ሲሰራ ቆይቷል። ከቀረበው መሬት 109 ሺ ሄክታር የሚሆነው ታርሷል። ከታረሰው ውስጥም ከ85 ሺ ሄክታር በላይ ኩታ ገጠም ማሳ በአኩሪ አተር ዘር እንዲሸፈን ተደርጓል። በአርሶ አደሩ፣ በባለሀብቱና በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንክብካቤ እየተደረገለት ይገኛል። እስከ አሁን ባለው ጊዜ 75 በመቶውን መሬት ለአኩሪ አተር ምርት ማዋል ተችሏል። የቀረውን መሬት በዘር የመሸፈን ስራ ተጠናክሮ እየተካሄደ ይገኛል። በክልሉ በአዊ አስተዳደር ዞን፣ በማዕከላዊ ጎንደር እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም አራት ዞኖች አኩሪ አተር በስፋት ይመረታል። አኩሪ አተር አምራች ከሆኑ ዞኖች በዋንኛነት የአዊ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር ይጠቀሳል። ምርቱ በዞኑ በጓንጓ፣ በአየሁ ጓጉሳ፣ በዚገም ወረዳዎች ይለማል። የምርት ሂደቱ ከተለመደው አሰራር ወጣ ያለና በህያው ማዳበሪያ አቅርቦትና በፓኬጅ ስልጠና የታገዘ ነው። በኩታ ገጠም እርሻም ተቃኝቶ በአራት የክልሉ ዞኖች እየተከናወነ ነው።
ለቀጣይ ዓመታት የእርሻ ሥራ ዘር የሚውል የ2013/14 ምርት ዘመን የዘር ብዜት ሥራን አስመልክተው ኃላፊው እንደተናገሩት፤ ምርጥ ዘር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መሰረት ከሆኑ ግብዓቶች ዋነኛው ነው። ክልሉ በምርጥ ዘር አቅርቦት በኩል ላለው ስራ ትኩረት በመስጠቱ በምርት ዘመኑ በምርጥ ዘር እጥረት ምክንያት የተስተጓጎለ የእርሻ ሥራ ወቅት አለመኖሩ ማሳያ ነው። ክልሉ የክልሉን አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ለማሟላት በዙሪያው ያሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ እስከ መሥራት ደርሷል። ይህን መሰረት አድርጎ በ2013/14 ምርት ዘመንም በ21 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት ለማከናወን አቅዶ ሲሰራ ቆይቷል። ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስም 10 ሺ 600 ሄክታር ማሳ በበቆሎ፣ በጤፍ፣ በማሽላና ለቀጣይ ዓመታት እርሻ ማሳ ግብዓት በሚውሉ በተለያዩ ምርጥ ዘሮች ተሸፍኗል።
ይህም ከ408 ሺ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር በማምረት ክልሉ በዘር አቅርቦት ራሱን እንዲችል ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። ‹‹በክልላችን በጣና ሀይቅ ዙሪያ ብቻ እንኳን ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለሩዝ ተስማሚ መሬት አለ›› ያሉት አቶ ተስፋሁን የዛሬ 10 ዓመት አጠቃላይ በኢትዮጵያ ከሚመረተው ሩዝ 70 በመቶው በክልሉ ይመረት እንደነበርም የፎገራ ወረዳ ብሄራዊ የሩዝ ምርምር ስልጠና ማዕከልን መረጃ ዋቢ አድርገው ጠቅሰዋል።
መታዘብ እንደቻልነውም ሩዝ በአሁኑ ወቅት በተለይም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ ሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆችና እህል ገበያዎች ኪሎው ከ55 እስከ 60 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ሆኖም ይህንኑ የፎገራ ሩዝ በስፋት ለማምረት መታቀዱንና ሥራው ሲሰራ መቆየቱንም ኃላፊው አብራርተዋል። በዘንድሮ ምርት ዘመንም ከ22 ሺ ሄክታር በላይ ማሳ በሩዝ ዘር መሸፈኑንና አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት መጠበቁን ገልጸዋል። ከሩዝ ምርት ገቢ 50 በመቶው ለአረም አራሚዎች ጉልበት ክፍያ እንደሚውል ከመረጃዎች የተገነዘብነው የሩዝ ሰብል የአረም ሥራ መከናወኑንም ከኃላፊው ተረድተናል። እንደሳቸው የሰብል እንክብካቤና የአረም ሥራው በስትራቴጂው መሰረት በሌሎች ሰብሎች ላይም በተለይም ቡድኑ በእብሪት የከፈተውን የህልውና ጦርነት ዘመቻውን ለመመከት የተቀላቀሉ አርሶ አደሮችን ማሳ በማካተት በስፋት የተከናወነበት ሁኔታ አለ።
አቶ ተስፋሁን ሥራው ከተከናወነባቸው ዞኖች መካከልም ከደቡብ ወሎ ዞን ዙሪያ ወረዳ የሀገርን ክብርና ህልውና ለማስጠበቅ ጦርነቱን የተቀላቀሉ አርሶ አደሮች ሰብል እንክብካቤ የተደረገለትና የታረመ መሆኑን ለማሳያነት አንስተዋል። ቢሮው ለህልውና ዘመቻው 45 ኩንታል የበሶ ዱቄትና ስንቅ ጀምሮ አርሶ አደሩ ከእርሻ ሥራው ጎን ለጎን፤ ካልተቻለም ለህልውና ዘመቻው ቅድሚያ እንዲሰጥ በማስተባበር የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በተለይ የህልውና ዘመቻውን 18 ሺ 120 አርሶ አደር ሚሊሽያዎች የተቀላቀሉበት ሁኔታ አለ። ወደ ጦርነቱ ከገቡ አርሶ አደሮች ማሳ መካከልም 13 ሺ ሄክታር መሬት የታረሰ ሲሆን 12 ሺ 522 ሄክታር ማሳም በዘር ተሸፍኗል።
በቀጣይም ቀሪው ማሳ በተለያየ ጥራጥሬ፣ በዳጉሳ በማሾና በሌሎች ምርቶች ዘር የሚሸፈንበት ተግባርም ተመቻችቷል። በተለይ ቡድኑ በከፈተው ጦርነት የተጎዳውንና የታጣውን ምርት የማካካሱ ስራ በጦርነት በተጎዱና ጦርነት በተካሄደባቸው ቦታዎች ብቻ የተወሰነ አይደለም። እንደ አቶ ተስፋሁን ጦርነት ባልተካሄደባቸውና ውድመት ባልደረሰባቸውም አካባቢዎች የሚካሄድ ነው። በተለይ ደግሞ ትርፍ አምራች በሆኑ አካባቢዎች በስፋት ይካሄዳል። ትርፍ አምራች ከሆኑት አካባቢዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው ዘልማ ቀበሌ አንዱ ነው። ቀበሌው በቆሎ በስፋት ይመረትበታል። አርሶ አደር ተስፋ መኮንን እንዳወጉን ተደጋግሞ በታረሰ በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱና በአግባቡ ስለቀረበላቸው በቆሎ ዘርተዋል። የዘሩት በኩታ ገጠም ማሳ ነው።
በዚህ መልክ መዝራታቸው የአርማና ኩትኳቶ ሥራውንም ሆነ ማንኛውንም የሰብል እንክብካቤ በጋራ ለማከናወን አግዟቸዋል። የተሻለና በቡድኑ የወደመውን ምርትና በግብርናው ዘርፍ የደረሰውን ኪሳራ ማካካስ የሚያስችል የተሻለ ምርት እንደሚስገኝላቸው ዕምነት አላቸው። የዘልማ ቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ስሜነህ አሞኘም ከትርፍ አምራቹ ዘልማ ቀበሌ በምርት ዘመኑ ከለማው የበቆሎ ሰብል ጉዳቱን የሚያካክስ የተሻለ ምርት እንደሚገኝ አረጋግጠዋል። እኛም በዚህ መልኩ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር በቡድኑ የደረሰውን ጉዳት የማካካሱ ተግባር በአማራ ክልል ተጠናክሮ ይቀጥል፤ ተሞክሮውም በሁሉም ክልሎች ይስፋ በማለት አበቃን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2013