የግብርናው ዘርፍ እንደ ሀገር በንጥረ ነገር የበለፀጉ ምርቶችን የማቅረብ ግዴታ ተጥሎበታል። እነዚህ ምርቶች ከሰብል ጀምሮ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ እንደ ወተት፣ አይብና ሥጋ ያሉ የእንስሳት ተዋፅኦን የያዙ ናቸው። በፕሮቲን፣ ሚኒራልስ፣ ቫይታሚን እንዲሁም በካርቦሃይድሬት መበልፀግም እንዳለባቸው የግብርናው ዘርፍና የመስኩ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
የግብርናው ዘርፍ ባለሙያዎችም ሆኑ የመስኩ ተመራማሪዎች እንደሚሉት በንጥረ ነገር አለመበልፀጋቸው በሰውነታችን ላይ የተለያየ የጤና ችግር እንዲከሰት ያደርጋል። አንዱ የመቀንጨር ወይም የመቀጨጭ በሽታ ነው። ደህንነታቸው አለመጠበቁም የጤና ችግር የሚያመጣ ሲሆን በድህረ ምርትና በዝግጅት ወቅት የሚከሰት ብክነትም ነው።
በንጥረ ነገር ካለመበልፀጋቸው ጋር ተያይዞ ከሚያስከትሉት የጤና ችግሮች መካከል መቀንጨር ወይም መቀጨጭ የተባለው በሽታ በተለይ እጅግ አስከፊ እና ለህጻናት አእምሮና እድገትን የሚገታ ነው። ከአምስት ዓመት በፊት በአፍሪካ አህጉር ደረጃ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ እነዚህን ንጥረ ነገሮች የያዙ ምግቦች ባለመመገብ የሚመጣው መቀንጨር ከአፍሪካ ሀገራት የተሻለች አይደለችም።
ለዚህም ምክንያቱ ከዚህ ቀደም እንደ ሀገር የሥነ ምግብ ጥራትና ይዘት ላይ ትኩረት ተደርጎ አለመሰራቱ ሲሆን፤ ጋቦን፣ ናሚቢያ፣ ጋና ቤኒን ኬንያ በተሻለ ደረጃ ላይ እንዳሉ ጥናቱ ቢያመለክትም ውጤታቸው በእጅጉ የተጠጋጋ በመሆኑ እምብዛም ልዩነት ነበራቸው ማለት አይቻልም። ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ያለች የአፍሪካ ሀገር ብሩንዲ ብቻ እንደሆነችም ይጠቅሳል። የኢትዮጵያ የመቀንጨር ወይም የመቀጨጭ በሽታ ተጋላጭነት 40 በመቶ ነበር። አሁን ወደ 37 በመቶ መውረድ ችሏል። እንደ ክልል ያለውም መሻሻል እያሳየ ነው። አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ እንዲሁም አዲስ አበባ የመቀንጨር ወይም የመቀጨጭ በሽታ ተጠቂ የነበሩ ናቸው።
ለአብነትም ጥናቱ በተካሄደበት ወቅት አዲስ አበባ ላይ የነበረው 14 በመቶ የቀነጨሩ (የቀጨጩ) ህፃናት ቁጥር አሁን ወደ ስድስት በመቶ ወርዷል። የአዲስ አበባም ሆነ እንደ አጠቃላይ በሀገር ያለው የመቀንጨር በሽታ (የስነ ምግብ ችግር) መሻሻል ያሳየው ግብርና ሚኒስቴር፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከጤናውና ሌሎች ዘርፎች ጋር በመቀናጀት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና የሥነ ምግብ ዳይሬክተር ዶክተር ካሳዬ ቶሎሳ ይናገራሉ።
እንደሳቸው ገለፃ ዳይሬክቶሬቱ ከማሳ እስከ ገበታ የዘለቀ የስነ ምግብ ደህንነትንና ጥራትን ታሳቢ አድርጎ እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም ነው ‹‹የምግብ ሳይንስና ምርምር›› ተብሎ ተቋቁሟል። በሥሩም ሦስት ብሄራዊ የምርምር መርሐ ግብሮች አሉ። ቀዳሚው የምግብ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂ የተሰኘው መርሐ ግብር ነው። ሁለተኛው የምግብ ጥራትና ሥነ ምግብ ሲሆን ሦስተኛው የምግብ ደህንነት መርሐ ግብር ነው። በተለይ በምግብ ደህንነት በኩል በሀገራችን እጅግ የከፋ ችግር አለ። ምርቶች ለጤና ጎጂ ለሆነው አፍላ ቶክሲን (ሻጋታ) የተጋለጡበት ሁኔታ ሰፊ ነው። ውጤቱ በያዝነው መስከረም ወር ይፋ የሚደረግ ቢሆንም እንደ ኢንስቲትዩቱ በበርበሬ፣ በሽሮ፣ በለውዝ በቅቤ፣ በቡና በቆሎ፣ በበሶ፣ በወተት ምርቶች ላይ የአፍላ ቶክሲን ችግር መኖርና አለመኖሩን ለማረጋገጥ ምርምር ተካሂዷል።
በማንኛውም ምርቶች ውስጥ የሚገኝ አፍላ ቶክሲን የጉበት ካንሰርና የተለያዩ የጤና ችግሮችን በማምጣት ሰውነታችንን ለበሽታ የሚያጋልጥ ነገር የሚቀላቀልበትና ለህብረተሰቡ የሚሰራጭበት ሁኔታ መኖሩም ተቃኝቷል። እንጀራ፣ ወተት፣ ቡናና ሌሎች ምርቶች ላይ በሚጨመሩ ባእድ ነገሮች ዙሪያም ምርምርና ጥናት እያደረገ ይገኛል። ከነዚህ ነፃ የሆኑና ደህንነታቸው የተጠበቀ እና በንጥረ ነገር የበለፀጉ ተጨማሪ ምርቶች (ምግቦች) ለሰው ልጆች በተለይም የነገ ሀገር ተረካቢ ለሆኑ ህፃናት በእጅጉ ያስፈልጋሉ።
ህፃናትም ሆኑ አዋቂዎች ለሰውነታቸው ካርቦሃይድሬትን ጨምሮ እንደ ሀገር በዋናነት ሦስት ንጥረ ነገሮች ይጎድላሉ። የሚጎድሉን ሦስቱ ንጥረ ነገሮች ፕሮቲን፣ ሚኒራልስና ቫይታሚን መሆናቸው በጥናት ተረጋግጧል። ዳይሬክቶሬቱ በእነዚህ በሦስቱ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ የህፃናትና የአዋቂ ምግቦች ላይ እየሰራ ነው ።
እንደ ዳይሬክቶሬቱ እምነት አንደኛ ምግቡ መኖር አለበት። ሁለተኛ የሚበላው ምግብ እነዚህን አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች መያዝ ይገባዋል። ሆኖም እኛ ጋር እንደ ሀገር ያለው ትልቁ ችግርም ንጥረ ነገሮችን ያሟላ ምርት አንድም አለመመረቱ፣ ቢመረትም ለገበያ አለመቅረቡና አለመመገባችን እንዲሁም እነዚህን ምግቦች የመጠቀም ግንዛቤ በህብረተሰቡ ዘንድ አናሳ በመሆኑ ጭምር ነው።
ዳይሬክቶሬቱ ከኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች እንዲሁም ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከጤናው ዘርፍና ከሌሎች ዘርፎች ጋር በመቀናጀት በሰፊው እንዲመረቱና ምርታቸው እንዲጨምር በማድረግ ይሰራል። ‹‹በተለይ የፍራፍሬና አትክልት ምርት በባህርያቸው ቶሎ የመበላሸትና የመባከን ችግር አለባቸው›› የሚሉት ዶክተር ካሳዬ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩበትን ቴክኖሎጂ በማሳደጉ ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሰራ ሥራ መኖሩን ገልፀውልናል።
አርሶ አደሩና ማህበረሰቡ ስለ ሥነ ምግብ ዕውቀት እንዲኖረው ስልጠና መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ሥራው ስልጠናውን በመስጠት ላይ ትኩረት ያደርጋል። ከሥራው ከፍተኛው ተግባር የሚከናወንበት የምርት ምንጭ ወይም መገኛ የሆነው የግብርና ሚኒስቴር ነው። መቀንጨርና መቀጨጭ የሚያመጣው ዚንክና አይረን ንጥረ ነገሮች ናቸው። በቦሎቄና በባቄላ ንጥረ ነገር እንዲኖር ይደረጋል። ‹‹እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሚመረተው በቆሎ ካርቦ ሃይድሬት የያዘ ነበር›› የሚሉት ተመራማሪዋ ዶክተር ካሳዬ ጉልበትና ሰውነት በመገንባት አቅም የሚፈጥር ፕሮቲን ንጥረ ነገር የያዘ በቆሎ እንዲመረት የተደረገበት የምርት ሂደት መኖሩንም ይጠቅሳሉ።
‹‹መደበኛው ስኳር ድንች አብዛኛውን ካርቦሃይድሬት ነው የሚይዘው›› በተመሳሳይ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሥነ ምግብ ችግሩን ለመቅረፍ ከማሳ ጀምሮ በቫይታሚን ኤ የበለፀገ ስኳር ድንች እንዲመረት እያደረገ ያለበት ሁኔታ መኖሩንም ይናገራሉ።
እንደ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትም የነዚህኑ በግብርና ሚኒስቴር አማካኝነት የሚመረቱ የሰብልና የእንስሳት ምርቶች ደህንነት የሚያረጋግጥ የሰብልና የእንስሳት ምርት ክፍል መኖሩንም ይጠቁማሉ። ተመራማሪዋ ዶክተር ካሳዬ አያይዘውም ክፍሉ አዳዲስ የምርት ዝርያዎች ሲወጡ በግብርና ሚኒስቴር አማካኝነት በስፋት በማሳ ከመመረታቸው በፊት የጥራትና የንጥረ ነገር ይዘታቸው ምን እንደሚመስል ያያል። በስፋት ከመመረታቸው፣ ገበያ ከመውጣታቸውና ለህብረተሰቡ ከመሰራጨታቸው በፊት ይህን ማየትና የያዙትን ንጥረ ነገር አስቀድሞ ማወቅ የግድ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ለጤና ጎጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ሊኖራቸው ይችላል ብለዋል። በመሆኑም ክፍሉ ሰርክ አዳዲስ የሚወጡትን የምርት ዝርያዎች የንጥረ ነገር ትንታኔ ይሰራል። ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያደርጉትም አስቀድሞ የንጥረ ነገር ይዘታቸው ከታወቀ በኋላ ነው።
ከዚሁ ከምርት ደህንነት ጋር ከተያያዘ ሥራ ሳይወጣ በምግብና ምርት ደህንነት በኩል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችም መኖራቸውን ይጠቅሳሉ ። ከገበያ ላይ ናሙና በመውሰድ ለጤና ጎጂ ለሆነው አፍላቶክሲን ተጋላጭ የሆኑ የተወሰኑ እንደ ወተት፣ በርበሬ፣ የለውዝ ቅቤ፣ ቡና የመሳሰሉ ምግቦች ላይ የተጀመረው ተጠቃሽ ናቸው። ከምርትም የበቆሎ ናሙና ተወስዶ ደህንነቱ እንዲታይ ጥናትና ምርምር እየተደረገበት ይገኝበታል። ውጤቱ በዚህ በመስከረም ወር ውስጥ ይፋ የሚሆን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ጥናቱ ያተኮረው የአፍላቶክሲኑ ችግር በምን ምክንያት እንደመጣና ችግሩን መቅረፍ የሚቻለው በምን መንገድ እንደሆነ መፍትሄውንም የሚያመላክት ይሆናል። የምግብ ደህንነት መርሐ ግብር የተቀረፀውም የሀገሪቱ የምግብ ደህንነት ጉዳይ ምን ይመስላል የሚለውን በሳይንሳዊ ምርምር ላይ የተመሰረተ መረጃ ለማቅረብ ነው።
‹‹በምርትና ምግቦቻችን ላይ የሚፈለጉ ማዕድኖች እንዳሉ ሁሉ የማንፈልጋቸውና በሰውነታችን ላይ እንደ ካንሰር ያሉ አደገኛ በሽታዎችን የሚያመጡም ማዕድናት አሉ›› ይላሉ ተመራማሪው ዶክተር ካሳዬ ። የንጥረ ነገሮቹ በምርት ውስጥ ከሚፈለገው በላይ መገኘትም በራሱ ለጤና ጠንቅ ነው። ምርምርና ጥናት የተደረገውም ከአዲስ አበባና ከስምጥ ሸለቆዎች አካባቢ በተወሰደ ናሙና ነው። ችግሩ ከፋብሪካዎች ከሚወጣ ፍሳሽ ጋር የሚያያዝበት አጋጣሚ መኖሩን ያመላከተ ነው። ለአብነት እንደጠቀሱት ከፋብሪካ የሚወጣ ፍሳሽ ቆሻሻ ምርት ከሚመረትበት ማሳ አቅራቢያ ካለ ወንዝ ጋር ከተገናኘ ውሃው በቀላሉ ሊበከል ይችላል። የተበከለ ውሃውን በመስኖ አማካኝነት አርሶ አደሩ በስፋት ለአትክልትና ፍራፍሬ ወይም ለሰብል ልማት በሚጠቀምበት ጊዜ ብክለቱ ወደ ምርቱ የመሄድ ባህርይ አለው።
ምርቱ ተዘጋጅቶ ለምግብነት ሲውል በጤናችን ላይ ጉዳት ያስከትላል። ኢንስቲትዩቱ በእነዚህ ዙሪያ እያደረጋቸው ያሉ ጥናትና ምርምሮች ችግሮቹን በመፍታት የጉዳቱን መጠን ይቀንሳል። ከዚህም ባሻገር ለመንግስት ፍሳሾቹ እንዴት እንደሚወገዱ አቅጣጫ በመስጠት፤ በሌላ በኩል ንጥረ ነገሮቹ ከሚፈለገው በላይ በመሆናቸው በጤና ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን በመጠቆም ግብዓት ይሆናሉ። እንደ መቀንጨር ያሉትን የሥነ ምግብ ችግሮችን በመቅረፍም ዓይነተኛ መፍትሄ ይሆናሉ።
በአሁኑ ወቅት የመቀጨጭ በሽታ እንደ ሀገር ያለበት ደረጃ 37 በመቶ ሲሆን በተለይ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህፃናትን በማጥቃት ላይ ይገኛል። የመቀንጨር የበሽታው መንስኤ ህፃናቱ የሚበሉት ምግብ ፕሮቲን፣ ሚኒራልስና ቫይታሚን ያለመያዙ ሲሆን ተጠቂዎቹ ቁመታቸው ከዕድሜያቸው ጋር የማይመጣጠን አጭር መሆኑ የበሽታው ምልክት ነው። በአካል ብቻ ሳይሆን በአእምሮም የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ጎልቶ ይታይባቸዋል። በትምህርት ገበታቸው ላይ የመረዳት ችግር ይገጥማቸዋል። አንድ ክፍል ላይ ብዙ ጊዜ ይደጋግማሉ። በመቀንጨር ሳቢያ እስከ መሞት ሊደርሱ ይችላሉ። በሽታው ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍበት ጊዜም ቀላል አይደለም።
በተለይም ሴቷ የምትወልደው ልጅ እንደ አባቱ ወይም እንደ እሷ ሁሉ የመቀንጨር በሽታ ተላልፎበት ሊወለድ ይችላል። በየጊዜው መታመም፤ ሲታመሙ ለሆስፒታል ወጪ ያስወጣሉ። ካደጉ በኋላም ሰርተው የሚበሉበት አቅማቸው አናሳ ስለሚሆን ከራሳቸው አልፎ ለቤተሰብ፣ ብሎም ለማህበረሰብ እንዲሁም እንደ ሀገር በመንግስት ኢኮኖሚ ላይ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ስለሚቀንስ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርሳሉ። መንግስት የመቀንጨር በሽታን ለመከላከል በሚያደርገው ጥረትም ከፍተኛ ወጪ እንዲያወጣ ይገደዳል።
በመሆኑም ዳይሬክቶሬቱ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር የሚመረቱት ምርቶች ፕሮቲን፣ ሚኒራልስና ቫይታሚን እንዲኖራቸው በማድረግ እየሰራ ይገኛል። ለአብነትም ዳይሬክቶሬቱ በ2011 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ እንደተቋቋመ ኤሲኦ በተሰኘ ፕሮጀክት በመታገዝ በተለያዩ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉና ደህንነታቸው የተጠበቁ ምርቶችንና ምግቦችን በማጎልበት በመቀንጨር ለተጠቁ ወረዳዎች ተደራሽ አድርጓል። በቪዲዮ የተደገፉ ስልጠናዎችን ሰጥቷል። ዳይሬክቶሬቱ በንጥረ ነገሮች የበለፀጉና ደህንነታቸው የተጠበቁ ምርቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ በድህረ ምርት ወቅት የሚባክነውን ምርትና ንጥረ ነገር በመቀነስና የምግብ አሰራር ቴክኖሎጂዎችን የማሻሻል ሥራም ይሰራል።
ሥራው እንደ ማንጎ ፓፓያ ያሉ ፍራፍሬዎችን እንዲሁም ከአትክልት እንደ ጎመን ካሮት ያሉትን አርሶ አደሩ ለረጅም ጊዜ ሳይበላሹ በማቆየት እንዲጠቀምባቸው ማድረግንም ያካትታል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2014