አርሶ አደሩ ዘንድሮም እንደ አምናውና ታች አምናው ቢያንስ በዓመት ሁለቴ አምርቷል። በተለይ ትርፍ አምራች የሆኑ አካባቢዎች መስኖና በልግን ጨምሮ ሦስት ጊዜም አምርተዋል። ይሁን እንጂ በሁሉም አይነት የግብርና ምርቶች በተለይ ደግሞ ጤፍ፣ ምስር እና ስንዴ ላይ የተጋነነ የዋጋ ንረት ይታያል።
ይሄ ሁኔታ ሸማቹን ሕብረተሰብ ብቻ ሳይሆን ራሱን የምርቱን ባለቤት ጭምር አሳስቦታል፤ አስገርሞታል። የማመርተው ምርት ታድያ የቱ ጋር ነው ያለው የሚል ጥያቄ እንዲያነሳ አድርጎታል። በእርግጥ አሁን ወቅቱ ጎተራ ያለው የሚያልቅበት፤ ማሳ ላይ ያለውም ገና ያልደረሰበት ጊዜ ነው። ቢሆንም አሁን እንደሚታየው የግብርና ምርቶች ዋጋ እንዲህ እንዲያሸቅብ ምክንያት ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ የሕብረት ሥራ ግብይት ዳይሬክቶሬት እንዳጠናው ጥናት፤ በአርሶ አደሩ ጎተራ ከፍተኛ የምርት ክምችት አለ።
የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ በአዳማ ከተማ የግብርና ግብይት ትስስር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። የመድረኩ ዋና ዓላማ አምራችና ሸማች ሕብረት ሥራ ማህበራት እና ሌሎች የግብርና ምርት ገዢዎች የግብርና ምርት የግብይት ትስስር እንዲፈፅሙ ማድረግ ነው። በዚህም በሀገራችን እየታየ ያለውን የግብርና ምርቶች የዋጋ ንረት መከላከል ነው። መድረኩን ያዘጋጀው ሀገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ነው። በእርግጥ ትንሽም ሆነ ትልቅ ጦርነት የማይበላው የማያጠፋው ነገር የለም። የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣሙና የዋጋ ንረቱ ከዚህ አንፃር መምጣት አለመምጣቱን ለማጥራት ፍተሻም አካሂጿል። ሆኖም አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎችና ደላሎች ከዚሁ ጋር አያይዘው ንረትና እጥረት ያለ ሊያስመስሉ ቢሞክሩም የተደረገው የዳሰሳ ጥናቱ ከዚህ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ አጣርቷል። ሆኖም አዝማሚያው አስጊ በመሆኑ ሕብረት ሥራ ማህበራት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው በሚል አምራች ሕብረት ሥራን ከሸማች ሕብረት ሥራ ማህበር ጋር የሚያስተሳስር መድረክ ለማዘጋጀት በቅቷል።
በመድረኩ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ‹‹እጥረቱ በተወሰኑ የምርት ዓይነቶች ላይ የለም ባይባልም በሰዎች አእምሮ የተፈጠረው አርቲፊሻል የሆነ እጥረት ነው››ብለዋል። ከፍላጎት ጋር ያልተጣጣመ የአቅርቦት እጥረት ያለው በርበሬ ላይ ቢሆንም በሁሉም ምርቶች ላይ እጥረት እንዳለ አድርጎ ሕብረተሰቡን እንዳይረጋጋ ያደረገው ደላላውና ሕገወጥ ነጋዴው ነው። ሀገሪቱ ካለችበትና ከገባችበት ጦርነት ጋር እንዲያዝ የማድረግ እንድምታም አለው። በመሆኑም ሕብረተሰቡ ይሄን ተከትሎ ምርት የለም የሚል የጥርጣሬ ስጋትና ሽብር ውስጥ ገብቷል። ይሄ ስግብግብ ነጋዴና ደላላ እንደፈለገ በሚቆርጥለት ዋጋ የግብርና ምርቶችን የሚገዛበት ሂደት ልክ ሀገር ውስጥ ምርት እንዳልተመረተ የሚያደርግ አስፈሪ ተግባር ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ነጋዴውም ሆነ ህብረተሰቡ መጠቀም የምችለው ሀገር ስትረጋጋና ሰላም ሲኖራት ነው የሚል ዕምነት ሊኖረው ይገባል። ነገር ግን አሁን እጥረት አለ ብሎ ራሱን ስላሳመነ በፍፁም በውድ ዋጋ አልገዛም አይልም። ገንዘብ ያለው የሚበቃውን ያህል ብቻ ሳይሆን ከእዛ በላይ እየሸመተ ያከማቻል። ለጊዜው የሚያገኙትን ትርፍ ብቻ የሚያዩ ክፍሎችም በሀገር ውስጥ ምርት እያለ እንደሌለ የሚያደርጉበት ዘዴ ብዙ ነው። አንዱ ምርቱን አብዝተው ወደ ገበያ ባለማውጣትና በመደበቅ ሰውሰራሽ እጥረት መፍጠር ነው። ሁለተኛው የምርቱን ዋጋ ማጋነን ነው። ነጋዴው ትርፍ ለማግኘት የሚነግድ ቢሆንም ገንዘብ ያለው የግብርና ምርቶችን አብዝቶ እንዲሸምትና የተወሰኑ ወገኖች የግብርና ምርቱን እየገዙ እንዲያከማቹ ማድረጉን አንስተዋል።
አምራች ሕብረት ሥራን ከሸማች ሕብረት ሥራ ማህበር ጋር በማስተሳሰር ጤናማ የግብርና ምርቶች ግብይት እንዲካሄድ ለማድረግ ቢሞከርም ጤናማ ግብይት መፍጠር ያልተቻለበት ችግር መለየቱን የግብርና ሚኒስትሩ ይናገራሉ። አንዱ የብድር አቅርቦት ችግር በመሆኑ ይሄም ከባንኮች ጋር እንዲተሳሰሩ በማድረግ ችግሩ እንዲፈታ ተደርጓል። ሆኖም እነዚህ አካላት ምርቱን በፍጥነት ለገበያ የማያቀርቡና ሕብረተሰቡ የምርት እጥረት አለ በሚል ከገባበት ስጋት ወጥቶ እንዲረጋጋ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይሄ ካልሆነ ግን ባዛርና ኤግዚብሽን በማዘጋጀት ሰፋ ያለ ምርት እንዲቀርብ እንደሚደረግ ነው የገለጹት።
ለዚህ ስኬታማነት የሚያመርተው ምርት የት ቦታ እንዳለ ለማሳየት ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ይሰራል። ህገወጥ ነጋዴውና ደላላው ከፍ ያደረጉትን የግብርና ምርቶች ዋጋ ዝቅ እንዲያደርጉ በማድረግ ትልቅ አስተዋጾ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል።
የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር በአሁኑ ጊዜ ሀገራችንን እያጋጣማትና በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እያሳደረ የሚገኘው የግብርና ምርቶች የተጋነነ የዋጋ ንረትና የምርት አቅርቦት እጥረት በቂ ምክንያት የሌለው መሆኑን ይገልጻሉ። ይሄ ሁኔታ ሀገራችን አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ሀገር ለማፍረስ ለከፈተብን ጦርነት ሀገር የማዳን ህልውና ዘመቻ እያደረገችበት ባለችበት ወሳኝ ወቅት መከሰቱ ይበልጥ አሳሳቢ እንደሚያደርገውም አልሸሸጉ። በመሆኑም በሀገር ላይ ለተቃጣው ጦርነት የመከላከያ ሠራዊታችን ደጀን በመሆን ለሀገራችን ህልውና ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር አጥጋቢ ምክንያት በሌለው ምግብ ነክ የግብርና ምርቶች ላይ ኢኮኖያዊ አሻጥር በመፈፀም በሕዝቡ ላይ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት በጋራ መመከትና ሕዝቡን መታደግ ይገባል። የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋትና ወደ ነበረበት ለመመለስ መስራት ይገባል ብለዋል። ለዚህም የሕብረት ሥራ ማህበራት የአንበሳውን ሚና የሚጫወቱ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የህብረት ስራ ማህበራት በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የግብርና ምርቶች ዋጋ ንረትና አቅርቦት ችግር ሲከሰት ያለምንም ተጨማሪ የግብይት ሰንሰለት ቀጥተኛ የአምራችና ሸማች የገበያ ትስስር በመፍጠር ዋጋ በማረጋጋትና የአቅርቦት ችግር በማቃለል ለመመከት ያደረጉትን አስተዋጾ አንስተዋል። ዘንድሮ ወቅት ጠብቆ የተፈጠረውን ያልተገባ የግብርና ምርቶች ዋጋና ሰው ሰራሽ እጥረትን ለመከላከልም የድርሻቸውን አስተዋጾ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል። ሆኖም ሸማቹ ሕብረተሰብም ሆነ መንግስት የሚጠብቀውን ያህል አለመሆኑና ገና ብዙ አስተዋጾ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል። በመሆኑም ማህበራቱ የጀመሩትን ቀጥተኛ የአምራችና ሸማች የገበያ ትስስር በዘላቂነት አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
እንደሳቸው ለስኬታማነቱም የሁለቱንም አካላት የተቀናጀና የተናበበ ጥረት ይጠይቃል። በተለይ ሕብረት ሥራ ማህበራት በግብርና ምርቶች ግብይት ሊኖራቸው የሚገባውን የጎላ ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጄንሲ የህብረት ሥራ ግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋለም እንየው፤ የግብርና ምርቶች የዋጋ ንረትና የአቅርቦት እጥረት ሰው ሰራሽ መሆኑን አቅርቦትና ፍላጎቱን በማነፃፀር በማስረጃ አስደግፈው ነው ያብራሩት።
‹‹ሕብረት ሥራ ማህበራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘርፈ ብዙ ተግባራቶች ላይ ተሰማርተዋል›› ያሉት ዳይሬክተሯ ከተሰማሩባቸው ዘርፎች አንዱ ከሀገር ውስጥ በቂ ምርት በማሰባሰብ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ፤ ያሰባሰቡትን ምርት እሴት በመጨመር ለሀገር ውስጥ ገበያዎች ማቅረብ እንደሆነም ጠቅሰዋል። የቀጣይ ወራት የሕብረት ሥራ ማህበራት የግብርና ምርቶች አቅርቦትና ፍላጎት ሁኔታ ከበርበሬ በስተቀር እጥረት መኖሩን አያሳይም። በአሁኑ ወቅት ለገበያ ትስስር ዝግጁ የተደረገ ምርትም ቢሆን እጥረት አለመኖሩን ነው የሚያመለክተው። ለምሳሌ ያህልም በማህበራቱ በኩል ለትስስር ዝግጁ የተደረገው ከበርበሬ በስተቀር እጥረት አለመኖሩን የሚያሳይ ነው።
ጤፍ በኦሮሚያ ክልል በስምንት አቅራቢዎች በመጋዘን 28 ሺህ 500 ኩንታል፣ በአማራ ክልል በስድስት አቅራቢዎች መጋዘን የሚገኘው 47 ሺህ 100 ኩንታል ሲሆን ደቡብ ላይ 2 ሺህ ኩንታል አለ። በአጠቃላይ በሦስቱ ክልሎች መጋዘን ያለውና በማህበራቱ አማካኝነት ለቀጣይ ወራት ለማቅረብ ለገበያ ትስስር የተዘጋጀው የጤፍ ብዛት 77 ሺህ 600 ኩንታል መሆኑን በዳይሬክተሯ የቀረበው ጽሑፉ ያመለክታል።
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ያለው ስንዴም እጥረቱና የዋጋ ንረቱ ምክንያት አልባና መሬት ካለው ዕውነታ በላይ የተጋነነ መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑን ነው የጠቀሱት። በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሦስት አቅራቢዎች መጋዘን 13ሺህ ኩንታል ስንዴ ሲኖር በአማራ ክልል በሁለት አቅራቢዎች 6 ሺህ ኩንታል ይገኛል። በእነዚሁ ሁለት ክልሎች በሚገኙ የሕብረት ሥራ ማህበራት መጋዘን ያለው የበቆሎ መጠን እና በማህበራት አማካኝነት ለገበያ ትስስር ዝግጁ የተደረገው 86 ኩንታል በርበሬን ጨምሮ 128 ሺህ 186 ኩንታል የግብርና ምርት ውጤት መሆኑን ዳይሬክተሯ በጽሑፋቸው አመላክተዋል።
በዚሁ የግብርና ውጤቶች ምርት ዓይነት በማህበራቱ አማካኝነት የተመላከተው የአቅርቦትና ፍላጎት ሁኔታም ሲቃኝ የዋጋ ንረቱና የምርት እጥረቱ መሰረት አልባ መሆኑን ይጠቁማል። ለአብነት በጤፍ፣ በስንዴ፣ በቆሎና በርበሬ ምርት በኩል ያለውን የአቅርቦትና ፍላጎት ምጣኔ አስመልክቶ ጽሑፉ እንደዳሰሰው በርበሬ ምርት ላይ ያለው የፍላጎት ምጣኔ 1 ሺህ 400 ኩንታል ቢሆንም አቅርቦቱ 86 ኩንታል ብቻ በመሆኑ መጣጣም አለመቻሉና ዕጥረት ማሳየቱ ዕውነት ነው። የጤፍ ፍላጎት 43ሺህ 910 ኩንታል ሲሆን አቅርቦቱ 77ሺህ 600 ኩንታል በመሆኑ በፍፁም የጤፍ ምርት እጥረት መኖሩን አያሳይም። በስንዴ በኩል ፍላጎቱ 13 ሺህ 360 ነው። ሆኖም አቅርቦቱ ከፍላጎቱ በላይ 19 ሺህ በመሆኑ እጥረት አለመኖሩን ያመለክታል። የበቆሎ ምርት ፍላጎቱ 11 ሺህ 600 ኩንታል ነው። አቅርቦቱ ደግሞ የፍላጎቱን ሦስት እጥፍ የሚሸፍን 31 ሺህ 500 ኩንታል በመሆኑ ምን አልባት እጥረት ቢከሰት እንኳን ችግሩን መቅረፍ የሚያስችል 19 ሺህ 900 ኩንታል በቆሎ የመኖሩን ልዩነት ያመላክታል። በርበሬን ጨምሮ በድምሩ በአራቱ የግብርና ምርቶች ያለው ፍላጎት ሲቃኝ 70 ሺህ 270 ሲሆን አቅርቦቱ 128 ሺህ 186 መሆኑ በጽሑፉ ተመላክቷል።
አቅርቦቱ ከፍላጎቱ በእጅጉ ያየለ በመሆኑም በማናቸውም ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ሁኔታዎች በሀገሪቱ ድንገተኛ የምርት እጥረት ቢከሰት ችግሩን በፍጥነት መቅረፍ የሚያስችል 57 ሺህ 916 ኩንታል ትርፍ ምርት በመጋዘን መኖሩ በጽሑፉ ተመላክቷል። በጽሑፉ መሰረት የዋጋ ንረቱና የምርት እጥረቱ ምክንያት አልባ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል።
በመድረኩ በአማራ ክልል የወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ አረጋ መኮንን እንደተናገሩት ሕገወጥ ግብይትና የደላላ ገበያ ውስጥ መግባት በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ሂደት ያዛባል። በዚህ ምክንያት ዘንድሮ ዩኒየኑ 100 ሺህ ኩንታል ምርት ለመግዛት ቢያቅድም መሰብሰብ የቻለው 42ሺህ ኩንታል ብቻ ነው። ከሰበሰበው ደግሞ 90 በመቶው ጤፍ ምርት ነው። በትስስር 29ሺህ ኩንታል ገብስ ሲሸጥ በአሁኑ ወቅት በመጋዘኑ ያለውና ያልተሸጠው 14ሺህ 226 ኩንታል ነው። ሆኖም ምርት በበቂ ሁኔታ ስላለ ደላላና ህገወጥ ነጋዴ ከገበያ የሚወጣበት ሁኔታ በመንግስት ከተመቻቸ ዩኒየኑ አሁንም ምርቱን ሰብስቦ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ሕብረተሰብ ለማድረስ ዝግጁ ነው።
ከኦሮሚያ ክልል ሎሚ አዳማ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን የመጡት አቶ ታደለ አብዲ እንደገለፁት፤ ዘንድሮ 95 ሺህ ኩንታል ለመሰብሰብ ቢያቅዱም 61 ሺህ ኩንታል ምርት ብቻ የገዙበት ምክንያት ከሕገወጥ ግብይትና ደላላ ተፅዕኖ የራቀ አይደለም። በመሆኑም የግብይት ስርዓቱ የቁጥጥርና ክትትል መስመር ይዞ በቀሪው ጊዜ ያለውን ምርት ለሸማቹ በማቅረብ ገበያውን እናረጋጋለን የሚል ዕምነት አላቸው። በአጠቃላይ ከመድረኩ እንደተረዳነውና ዳይሬክተሯም በጽሑፋቸው እንዳመላከቱት አሁን የሚታየው የግብርና ዋጋ መናር ምክንያት የለውም። አንደኛ በሀገር ደረጃ ምርታማነት ጨምሯል እንጂ አልቀነሰም። ሁለተኛ ከሕብረት ሥራ ማህበራት የተሰበሰበው መረጃ እንደሚያሳየው እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ሕብረት ሥራ ማህበራት እጅ ላይ አለ። ሦስተኛ በማህበራቱ ያልተሰበሰበ በአርሶ አደሩ እጅም እንዲሁም ምርት ያለበት ሁኔታ አለ። አራተኛ ፍላጎትና አቅርቦቱ ሲነፃፀር እንዴውም አቅርቦቱ ሰፊ ፍላጎቱ አነስተኛ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20/2013