አንተነህ ቸሬ
የኢትዮጵያ ሙዚቃ በቅርቡ ሁለት አንጋፋ ባለውለታዎቹን አጥቷል። እነዚህ አንጋፋዎች ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ያበረከቱት አስተዋፅዖ በዋጋ የማይተመንና በቃላት የማይገለፅ ታላቅ ውለታ ነው። አንዱ ግጥምና ዜማ በመስራት፣ የሙዚቃ መሳሪያ በመጫወት፣ በውዝዋዜና በዘፈን፤ ሌላኛው ደግሞ ድምፃውያንን እያበረታቱ ስራዎቻቸውን አሳትሞ ለሕዝብ በማቅረብ። ሁለቱም የሙዚቃ ሰዎች ድምፃውያንን በማፍራት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመን የማይሽረውና ጊዜ የማያደበዝዘው ደማቅ ውለታ ውለዋል። እነዚህ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ደማቅ ክዋክብት የሙዚቃ አሳታሚው ዓሊ አብደላ ኬይፋ (ዓሊ ታንጎ) እና ድምጻዊ፣ ተወዛዋዥ፣ የግጥምና የዜማ ደራሲ እና የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች አየለ ማሞ ናቸው።
፩). ዓሊ ታንጎ
ሙሉ ስማቸው ዓሊ አብደላ ኬይፋ ነው። ኢትዮጵያውያን የሚያውቋቸው ‹‹ዓሊ ታንጎ›› በሚባለው ስማቸው ነው። ዛሬ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀሱ ኢትዮጵያውያን ዘፋኞች መካከል የብዙዎቹን ስራዎች ያሳተመው ንብረትነቱ የእርሳቸው የሆነው ‹‹ታንጎ ሙዚቃ ቤት›› ነው። ጀማሪ ድምፃውያንን እያበረታቱ ለታላቅ ደረጃ አድርሰዋቸዋል። ኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ወዳጆችም ከድምፃውያኑ ስራዎች ጎን ለጎን የስራዎቹ አሳታሚ የሆኑትን ዓሊ ታንጎንና ሙዚቃ ቤታቸውን ያውቁታል፤ ያስታውሱታል።
አሊ የተወለደው በ1934 ዓ.ም ጅማ ከተማ ውስጥ ነው። አባቱ የመናዊ ሲሆኑ እናቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊት ናቸው። ወደ አዲስ አበባ የመጣው በልጅነቱ ነው። በአዲስ አበባም የመን ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ገበቶ አረብኛ ተምሯል። ከዚያም ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን ተከታትሏል። እግር ኳስ ይወድ ስለነበር ለሰፈር ቡድኖች እንዲሁም ለቅዱስ ጊዮርጊሥ ክለብ ተጫውቷል።
የወላጆቹ ትዳር በመለያየት ከተደመደመ በኋላ አባቱ ወደ የመን ሲመለሱ ዓሊ ከእናቱና እናቱ አዲስ ካገቡት ባል ጋር ኢትዮጵያ ቀረ። ከትምህርቱ ጎን ለጎን በቡና፣ በጫማ እንዲሁም በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ንግድ ተሰማርቶ የነበረው ዓሊ ‹‹ከመሞቴ በፊት የልጅ ልጅ ማየት እፈልጋለሁ›› የሚለውን የእናቱን ቃል ለማክበር ትዳር የመሰረተው በ18 ዓመቱ ነበር።
ዓሊ ሙዚቃ ወደማሳተም ስራ የገባው በጌታቸው ካሣ የሙዚቃ ስራዎች በመደመሙ እንደነበር በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ ጠቅሷል። በእርግጥ በወቅቱ ጌታቸው ካሣ ከሌላ አሳታሚ ጋር ስምምነት ፈፅሞ ስለነበር ዓሊ የወደደውን የጌታቸውን ሙዚቃ ማሳተም ባይችልም በሙዚቃ ዝግጅት ሕይወቱ የመጀመሪያ የሆኑውን ‹‹በላያ በላያ›› የተሰኘውን የዓለማየሁ ቦረቦርን ሙዚቃ ማሳተምና ማከፋፈል ችሏል። ከዚያ በኋላ ዓሊ ሙዚቃ ማሳተሙን ቀጥሎበት በ‹‹ታንጎ ሙዚቃ ቤት›› አማካኝነት የጌታቸው ካሣን፣ የስዩም ገብረየስን፤ የሙሉቀን መለሰንና የሌሎችን በርካታ ዘፋኞችን ሥራዎች በሸክላ አሳተመ። ዓሊ ለበርካታ ድምፃውያን የመጀመሪያ አልበማቸውን በማሳተም ተወዳጅና ታዋቂ እንዲሆኑ መሠረት ሆኗቸዋል። ከነዚህ ድምፃውያን መካከል ተወዳጇ አስቴር አወቀ አንዷ ናት።
ዓሊ የጥላሁን ገሠሠን ‹‹የአለፈው አልፏል›› ሌሎች አምስት ዘፈኖች በአጠቃለይ ስድስት ዘፈኖችን የያዙ ሦስት ሸክላዎችን አሳትሞ አከፋፍሏል። ዓሊ የብዙነሽ በቀለን፣ የኂሩት በቀለን፣ የዓለማየሁ እሸቴን፣ የኃይሉ ዲሳሳን፣ የገመቹ ኢታናን፣ የአሊ ቢራን፣ የአስቴር ከበደን፣ የሐመልማል አባተን እና የሌሎች በርካታ ዘፋኞችን ሸክላና ካሴት በማሳተም በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅና ታዋቂ እንዲሆኑ በማድረግ የላቀ ድርሻ አለው።
አንጋፋውን ድምፃዊ ዓሊ ቢራን ለታላቅነት ያበቃውም ዓሊ ታንጎ ነው። ታንጐ ሙዚቃ ቤት በር ላይ አንዲት አሮጌ የእጅ ቦርሣ ይዞ ለበርካታ ጊዜያት ያህል ደጅ የሚጠና አንድ ዘፋኝ ነበር። ይህ ዘፋኝ በድሬዳዋ ከተማ ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ አፍረንቀሎ በሚባል የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ያደገው ዓሊ ቢራ ነበር።
ዓሊ አብደላ ኬይፋ ዓሊ ቢራን በአንድ ወቅት እንዲህ አለው። ‹‹በአሁኑ ጊዜ ኦሮምኛ እንደ አማርኛ ሙዚቃ ገበያ ላይ አይሸጥም፤ ስለዚህ ኪሣራ ውስጥ እንዳታስገባኝ።›› ዓሊ ቢራ ግን ተስፋ አልቆረጠም፤ ዓሊ ኬይፋ ጠዋት ወደ ሙዚቃ ቤቱ ሲገባ ዓሊ ቢራ በር ላይ ቆሞ ይጠብቀዋል። ዓሊ ኬይፋ ግን በመጨረሻ የዓሊ ቢራን ጥያቄ ተቀብሎ ‹‹አማሌሌሌ››፣ ‹‹እሹሩሩሩ›› እና ‹‹እያዲኒ›› የሚሉ ዘፍኖች የተካተቱበትን አሥር ዘፈኖች የያዘ ማስተር ካሴት ራሱ ጣጣውን ጨርሶ ለሕትመት ብቻ ለዓሊ አስረክበው። በኬይፋ ሪከርድስ የታተመው የዓሊ ቢራ የመጀመሪያ ካሴት በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘቱ በጅማ፣ በጐጃም፣ በጐንደር፣ በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍለ ሀገራት ተከፋፍሎ ዓሊ ቢራ ተወዳጅነትና ታዋቂነትን ሊያገኝ ችሏል።
ኅብስት ጥሩነህንም ለታዋቂነት ያበቃት ዓሊ ነው። ድምጻዊ ኅብስት ጥሩነህ ከዓሊ ጋር የሰራችው የመጀመሪያዋን አልበም ብቻ ቢሆንም ቀጣይ ስራዋን እንድትሰራም እገዛ አድርጎላታል። ሁለተኛ አልበሟን ለመስራት በዝግጅት ላይ ሳለች ነበር ዓሊ ከሀገር ለመውጣት በሂደት ላይ የነበረው። በመሆኑም ዓሊ፣ ኅብስት ሁለተኛ አልበሟን እንድታወጣ ከኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ባለቤት ጋር አገናኛት። እርሷም ሁለተኛ አልበሟን ሰርታ ለህዝብ አቀረበች።
‹‹ … በእውነቱ ከሆነ ጋሽ ዓሊ ለእኔና ለቤተሰቦቼ ከጠበቅኩት በላይ ነው በርካታ ነገር ያደረገው፤ ልክ እንደ አባት በመሆን ትልቅ አክብሮትና ድጋፍ ነው ያደረገልኝ። አሁን እኔ እዚህ ደረጃ እንድደርስ የዓሊ ድርሻ ከፍተኛ ነው። ልክ እንደ አባቴ ነው። የመጀመሪያ አልበሜን በምሰራበት ጊዜ እንደአባት እየተቆጣጠረና እየመከረ ስኬታማ እንድሆን የረዳኝ መሰረቴ ነው፤ ከእርሱ ጋር የስጋ ዝምድና ያለኝ ያህል ነው የሚሰማኝ›› የምትለውና የዓሊ ታንጎን ውለታ የማትረሳው ድምጻዊት ኅብስት ጥሩነህ፣ ‹‹ዓሊ ታንጎ የሙዚቃ ማሳተም ስራ ላይ ብቻ አያተኩርም፤ በሙዚቃ ውበት፣ በሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾችና በድምጻውያን መካከል ስለሚኖረው ውህደትና መግባባት የእራሱ የሆነ እውቀትና ክህሎት ነበረው … ›› ብላለች።
ከወጣትነት ጊዜያቸው ጀምሮ ለበርካታ የኢትዮጵያ ድምፃውያን መሠረት በመሆኑ በርካቶችን በሙያቸው ተወዳጅና ታዋቂ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት ዓሊ አብደላ ኬይፋ በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ከሙዚቃ አዘጋጅነትና አሳታሚነት ሥራቸው እንዲሸሹ የሚያደርግ አጋጣሚ ተፈጠረ። ዓሊ በዚህ ጉዳይ ላይ ‹‹ሆድ ይፍጅው … የቤተሰብ ጉዳይ ነው›› ከማለት ውጪ ዝርዝር ጉዳዩን ለመግለፅ ምንም ዓይነት ፍላጐት አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁት አካላት እንደሚያስረዱት፣ ዓሊ በወቅቱ ወደ ትውልድ ቦታው ጅማ በመሄድ ከወላጆቻቸው የተረከቡትን የቡና እርሻ በማስተዳደር ከፍተኛ የቡና ንግድ ሥራ ያከናውኑ ነበር። ሆኖም ግን የንግድ አሻጥርና የደህንነት ችግር ዓሊ ከሚወዷት ሀገራቸውና ከሚወዱት ሙያቸው ሳይወዱ በግድ እንዲለዩ አድርገዋቸዋል ተብሏል። ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ ከ23 ዓመታት በኋላ፣ በ2010 ዓ.ም፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ነበር።
‹‹እኔ ሀገሬ ኢትዮጵያን በጣም ነው የምወዳት፤ አውሮጳ፣ አሜሪካና ሌሎች ዓለማትን ዐይቻለሁ፤ የአሜሪካ ዜግነት አግኝቻለሁ። እንደ ኢትዮጵያ የምደስትበት ሀገር የለም። ሆኖም ግን ከልጅነት እስከ ጉልምስና ባለው ዕድሜ ያፈራሁትን ሐብትና ንብረት ተቀምቻለሁ፤ ድርጅቴ ተወስዷል፤ እኔ አሁን ባዶ እጄን ነው ያለሁት፤ …. መቼም ብዙ ተስፋ አልቆርጥም›› ያሉት አንጋፋው የሙዚቃ ሰው ዓሊ፣ በጥር ወር 2012 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ሙዚቃና ሙዚቀኞች እድገትና መሻሻል ያበረከቱትን አስተዋፅዖ የሚዘክር የእውቅናና የሽልማት መርሃ- ግብር በአዲስ አበባ፣ ሸራተን ሆቴል ተዘጋጅቶላቸው ነበር።
መንፈሰ ጠንካራና ዘናጭ የነበሩት አሊ አብደላ ኬይፋ ትዳር መስርተው 13 ልጆችን ወልደዋል፤ ከ35 በላይ የልጅ ልጆችንም ዐይተዋል። ለበርካታ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች መነሻ የሆነው የታንጎ ሙዚቃ ቤት መስራችና ባለቤት፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃና ሙዚቀኞች ባለውለታ የሆኑት ዓሊ አብደላ ኬይፋ (አሊ ታንጎ) ባደረባቸው ሕመም በሀገረ አሜሪካ በህክምና ሲረዱ ቆይተው መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ስርዓተ ቀብራቸውም በሲያትል፣ አሜሪካ ተፈፅሟል።
፪). አየለ ማሞ
ማንዶሊን የተሰኘች እንደ ሊድ ጊታር ያለች፣ ከሊድ ጊታር የምታንስ፣ እንደክራር ዓይነት ድምፅ የምታወጣ፣ ባለአራት ገመድ የክር መሣሪያ ላይ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ሲጠበቡባት ኖረዋል። ከክብር ዘበኛ ሙዚቀኞቹ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ እና ሻምበል ግርማ ሓድጉ በአደራ የተረከቧት ይች መሳጭ ድምፅ የምታወጣ መሳሪያ ከእርሳቸው ሌላ የሚያሽሞነሙናት ሰው ዐላየችም። በመሳሪያዋ ላይ ያሳዩት የአጨዋወት ችሎታና ጥበብ ‹‹የማንዶሊን ንጉሥ›› የተሰኘ ስም አሰጥታቸዋለች። የተዋጣላቸው የግጥምና የዜማ ደራሲም ነበሩ። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠሩ ድምፃውያን መካከል ከእርሳቸው ግጥምና ዜማ ያልተቋደሰ የለም። ከዘፋኝነታቸውና ከግጥምና ዜማ ደራሲነታቸው በተጨማሪ ተወዛዋዥነታቸው ሌላው አስደናቂው ችሎታቸው ነው … አርቲስት አየለ ማሞ!
አየለ ማሞ የተወለደው በ1934 ዓ.ም በቀድሞው ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ በሰላሌ አውራጃ፣ ልዩ ስሙ ‹‹ሳላይሽ ጊዮርጊሥ›› በተባለ ስፍራ ነው። በልጅነቱ የሃይማኖት ትምህርቱን ተከታትሎ ዲቁና ተቀብሎ ያደገበትን ደብር በዲቁና አገልግሏል። ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላም በደብረ አሚን ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በዲቁና አገልግሏል። በ1948 ዓ.ም የተክለሃይማኖት በዓል በተከበረበት ወቅት በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዲያቆን አየለ በክብረ በዓሉ ላይ ባሰማው ጥዑም ቅዳሴ በመደሰታቸው 20 ብር እና መጽሐፍ ቅዱስ ሸልመውታል።
በተፈጥሮ የታደለው ጥዑም ድምጽ እና የንጉሰ ነገሥቱ ሽልማት ታዋቂ ያደረገው አየለ፣ በ1949 ዓ.ም የክብር ዘበኛን የሙዚቃ ክፍልን ተቀላቀለ። አየለም ‹‹የኔ ውብ ዓይናማ ነይማ ነይማ›› የተሰኘውን የመጀመሪያ ስራውን አቅርቦ ተስፋ ያለው ሙዚቀኛ መሆኑን አስመሰከረ። ከዚያም በወቅቱ ከነበሩ አንጋፋ ድምፃውያንና ተወዛዋዦች ጋር መሆን የሙዚቃ ውስጥ ሕይወቱን አጠንክሮ ቀጠለ። ከአማርኛ በተጨማሪ በሌሎች ቋንቋዎችም ያቀረባቸው ስራዎቹ ተወዳጅነትንና ተደናቂነትን አስገኙለት። ከአንጋፋ ባለሙያዎች ያገኘው ስልጠና የተዋጣለት ዘፋኝና ዳንሰኛ እንዲሁም የዘፈንና የውዝዋዜ አሰልጣኝ እንዲሆን አስቻለው።
በግጥምና በዜማ ድርሰቶቻቸው የሚታወቁትና ‹‹የክብር ዘበኛ የሙዚቃ ክፍል የጀርባ አጥንት›› እየተባሉ የሚታወቁት ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ስለማንዶሊን አጨዋወት ከአንድ ጣሊያናዊ ይማሩ ነበር፤ አየለም ከእርሳቸው ጋር ሆኖ ማንዶሊንን መጫወት ለመደ። አየለ ማንዶሊንን የተማረው ከክብር ዘበኛ ሙዚቀኞቹ ከሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ እና ከሻምበል ግርማ ሓድጉ ነው።
በ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራን የመሩት ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ የክብር ዘበኛ ጦር ዋና አዛዥ ስለነበሩ ‹‹የጦሩ የሙዚቃ ክፍል የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ደግፏል›› ተብሎ የክፍሉ ሙዚቀኞች ለእስራትና ለእንግልት ተዳረጉ። በወቅቱ ብዙም ታዋቂ ያልነበረው ወጣቱ አየለ ማንዶሊኑን በመያዝ ድምፃውያንን የማጀብና ከታላላቅ ድምፃውያን ጋር እንደልቡ እየተገናኘ የመስራትና ተሰጥኦውን የማሳደግ እድል አገኘ። አየለ የበለጠ እውቅናን ያተረፈው በማንዶሊኑ በተጫወተው ‹‹ወይ ካሊፕሶ›› በተባለው ዘፈን ነበር።
አየለ የተዋጣላት የግጥምና የዜማ ደራሲ ነበር። ስመ ጥር ከሚባሉ ድምጻውያን መካከል ከአየለ ግጥምና ዜማ ያልወሰዱትን መጥቀስ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ጥላሁን ገሰሰ፣ ማኅሙድ አህመድ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ውብሻው ስለሺ፣ መንበረ በየነ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ሐመልማል አባተ፣ ብፅአት ስዩም፣ ወሮታው ውበት፣ አስቴር ከበደ፣ እያዩ ማንያዘዋል፣ ሻምበል በላይነህ፣ ደረጄ ደገፋው፣ ጌታቸው ጋዲሳ፣ ጌታቸው ካሣ፣ ተፈራ ካሣ፣ ፀሐይ እንዳለ፣ ምንያህል ጥላሁን ገሰሰ፣ ትዕግስት ይልማ፣ ከበቡሽ ነጋሽ (ሚሚ)፣ ገነነ ኃይሌ፣ ወርቅነህ ክፍሌ፣ አቦነሽ አድነው፣ ፀጋዬ ስሜ፣ ሀብታሙ ገብረ ፃዲቅ (ፈረንጁ)፣ ሕብስት ጥሩነህ፣ ዓለማየሁ ግዛው፣ ሔለን በርሄ … እነዚህ ሁሉ አየለ የገጠማቸውን የዘፈን ግጥሞችና የሰራቸውን ዜማዎች ተጫውተዋል።
አየለ ማሞ ድምፃዊ ብቻ አልነበረም፤ ተወዛዋዥም ጭምር ነበር። ሲወዛወዝ የተመለከቱት ‹‹ተወዛዋዥነቱ እጅግ ያስገርማል›› ይላሉ፤ ዘፋኝነቱን ሲመለከቱ ደግሞ ዘፋኝነቱ ይበልጥ ያስደንቃቸዋል። በዘፋኝነቱ የሚያውቁት ደግሞ ዘፋኝነቱን ያስበልጡና ተወዛዋዥነቱን ሲመለከቱ የበለጠ ይገረማሉ። አየለ ማሞ ማለት ሰውን ሁሉ በብቃታቸው የሚያስደንቁ ባለሙያ ናቸው። በአጠቃላይ ከ200 በላይ የሙዚቃ ስራዎችን እንደሰሩ ታሪካቸው ያስረዳል። በርካታ ሙያተኞችንም አፍርተዋል።
ለጥላሁን ገሠሠ ከሰጡት ስራዎች መካከል ‹‹ሁሉም በሐገር ነው››፣ ‹‹የጣት ቀለበቴን ውሰጅ››፣ ‹‹ጠይም ናት ጠይም መልከ ቀና››፣ ‹‹በጥርሷ ሸኝታኝ አለችኝ ደህና እደር››፣ ‹‹ናፍቆቷ ነው ያስጨነቀኝ››፣ ‹‹ይገርማል ቁመናና ዛላ››፣ ‹‹ለውዲቷ ለእናት ኢትዮጵያ››፣ ‹‹ዘማች ነኝ›› የሚሉት ይጠቀሳሉ። ብዙነሽ በቀለ ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ ያቀነቀነችውን ‹‹አሸብርቆ ደምቆ እንደፀሐይ›› የሚለውን ዘፈን ያገኘችው ከአየለ ነው። ‹‹አምሮበታል ሙሽራው›› እና ‹‹ከንቱ ስጋ›› ሙዚቃወቿም የአየለ ናቸው።
የማህሙድ አህመድ ‹‹ያባብላል አይኗ ያባብላል›› እና ‹‹ንገሯት መላ ትስጠኝ›› ዘመን ተሻጋሪ ዘፈኖች እንዲሁም የኅብስት ጥሩነህ ‹‹እንቡጥ ነኝ›› እና ‹‹እናቴን አደራ›› የአየለ ማሞ ስራዎች ናቸው። ‹‹እስከዛሬ ከሰራሀቸው በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዘፈኖች ሁሉ አስበልጠህ የምትወዳቸውን ዘፈን ምረጥ ብትባል የትኛውን ትመርጣለህ?›› ተብለው ተጠይቀው ‹‹ሁሉም በሀገር ነው›› የሚለው ስራቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
አርቲስት አየለ ከማንዶሊን በተጨማሪ ሊድ ጊታርና ቤዝ ጊታር ይጫወታሉ፤ ድራምም ይሞካክሩ ነበር። በበርካታ የዓለም አገራት ተዘዋውረው ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፤ ሽልማቶችንም አግኝተዋል። የክብር ዘበኛን ጨምሮ በክስታኔ እና በአኮስቲክ ባንዶች ከ50 ዓመታት በላይ አገልግለዋል።
አንጋፋው የግጥምና የዜማ ደራሲ፣ ድምፃዊ፣ ተወዛዋዥና የሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋች አየለ ማሞ ለድምፃዊት ብዙነሽ በቀለ በሰሩት ግጥምና ዜማ፡-
‹‹አሸብርቆ ደምቆ እንደ ፀሐይ፣
ተውቦና አጊጦ የምናይ።
የዛሬው አበባው ገላችን፣
ነገ አፈር ቀለብ ነው ስጋችን።
ምንም ብንጓጓለት፣
ብንስገበገብለት።
ይፈርሳል በጊዜያቱ፣
ስጋ ነውና ከንቱ›› ብለው እንደፃፉትና እንዳዜሙት ሞት አይቀርምና፣ በታላላቅ ድምጻውያን ስራዎች ውስጥ አሻራቸውን አኑረው፣ በድምጻዊነት፣ በተወዛዋዥነትና በሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋችነት ሙዚቃን አገልግለው፣ መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል። ስርዓተ ቀብራቸውም በአዲስ አበባ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል።