ምህረት ሞገስ
አዲስ አበባ በሰዎች ርምጃና ሩጫ መጨነቅ የምትጀመረው ገና ከተማዋ ላይ ብርሃን ሆኖ ዓይን ለዓይን መተያየት በማይቻልበት ሰዓት መንጋቱ ከመታወጁ በፊት ነው፡፡ ከማለዳው 11 ሰዓት ከ30 ጀምሮ መንገዱ ለዓይን ያዝ ቢያደርግም እዚህና እዚያ ትራንስፖርት ለማግኘት የሚራወጡ ሰዎችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ እየነጋ ሲሄድ መንገድ ላይ የሚታየው ሰው ቁጥር እየጨመረ
ይሄዳል፡፡ ከቀጫጭን አስፓልቶች ውስጥ በገፍ በግራና በቀኝ የሚወጣው እግረኛ ወዴት እየተመመ ነው ያሰኛል፡፡
በእግረኞቹ መሃል ደግሞ ባለመኪናው እያሽከረከረ ተጠባብቆ መሃሉን ይዞ ይጓዛል፡፡ ይጓዛል ብቻ
ነው፡፡ ጉዞ የቱ ጋር እንደሚያበቃ አይታወቅም፡፡ ከጀሞ የተነሳው ተጓዥ መቆሚያው ሜዝሲኮ ይሁን ለገሃር፤ ፒያሳ ይሁን መርካቶ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ብቻ በገፍ መንገዱን ይዞ መፍሰስ ነው፡፡ የጀሞው ተጓዥ የመከኒሳውን አስከትሎ የሜክሲኮውን ጨምሮ እየተገፋፋ ይጓዛል፡፡
የጎሮ፣ የገርጂውን አስከትሎ መገናኛ ይደርሳል፡፡ የሃያቱ፣ የሰሚቱ፣ የየካ አባዶ፣ የኮተቤው ሁሉም ወዴት እንደሚሄድ አይታወቅም ብቻ መጓዝ ነው፡፡ በእግሩ ከሚሄደው ባሻገር እየተጋፋ ታክሲና አውቶቡስ እየጠበቀ የሚሳፈርውም የትየለሌ ነው፡፡
ፀሐይዋ መውጣት ስትጀምር እና ሱቆች ሲከፈቱ በፒያሳ መስመር በዮሐንስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ያሉ ሱቆች፤ በሰሚት እና በሃያት መስመር ሚካኤል አካባቢ በእያንዳንዳቸው ሱቆች አቅራቢያ ከአራት እስከ ስድስት የሚጠጉ ጎረምሶች ቆመው አንዳንዶቹ ደግሞ ተቀምጠው ይታያሉ፡፡ በተለየ መርካቶ ከሱቅ ውጪ የሚቆሙ ወጣቶችን መቁጠር እጅግ አዳጋች ነው፡፡ እንዲያውም ‹‹ይሄ ሁሉ ሰው አልጋ አግኝቶ ተኝቶ፤ የሚበላ አግኝቶ በልቶ አድሮ ይሆን?›› ያስብላል፡፡
በእግር ከሚሄደው ጎን ለጎን እየተከተሉ ‹‹ምን ትገዛለህ? ምን እናጋዛህ?›› እያሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ‹‹የወለል ምንጣፍ ነው? መጋረጃ? የሶፋ ጨርቅ? ፍራሽ ነው?›› እያሉ እየጠየቁ ገና ወደ ገበያው ሳይገባ መንገድ የሚከለክሉ እና የሚያዋክቡት የትዬለሌ ናቸው፡ ፡ አንዳንዶቹ ወጣቶች እንጀራ ፍለጋ የወጡ ቢሆንም ከእነሱ ጋር ተመሳስለው የሚዘርፉ ወይም የሚያስዘርፉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች በስጋት ወጣቶቹን ቢሸሹም አይፈረድባቸውም፡፡ እገዛለሁ ብሎ ወጥቶ ተሸጦ መምጣት አለና፡፡ አካባቢው ሕዝብ የሚርመሰመስበት በመሆኑ ከአንዱ ሌባ ማምለጥ ቢቻል ከሌላው ለማምለጥ አዳጋች ነው፡፡
ሱቆች ስለበዙ መግዢያ ቦታዎች በሙሉ በሰዎች ብዛት ተጨናንቀዋል ለማለት ቢያዳግትም የአገልግሎት መስጫ ተቋማት አካባቢ ግን የሰዎች ቁጥር ከአገልግሎት ሰጪውና ፈላጊው አቅም በላይ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች አካባቢ ያለው የሰዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምን የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር ጨመረ? ወይም ለምን ይህን ያህል ሕዝብ በከተማው ይርመሰመሳል? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ወይንም ጥናት ማድረግ ይገባል፡፡ ነገር ግን እኔን ግራ ያጋባኝና በዚህ መልኩ ለመፃፍ ያስገደደኝ ቀኑን ሙሉ ሰዎች ጎዳና ላይ መታየታቸው ነው፡፡
በከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ከሚታወቁ ከተሞች መካከል ከ21 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ይዛ እንደምትውል የሚነገርላት የቻይናዋ ከተማ ቤጂንግ ቀን 5 ሰዓት ጎዳናዎቿ ቢታዩ በሰው ዓይን ውስጥ የሚገቡት ሰዎች ቁጥር ምናልባት ሁለት ቢበዛ አምስት ብቻ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ግን በአንድ ጎዳና ላይ ምናልባት በሦስት መቶ ሜትር ርቀት ውስጥ ጎዳና ላይ የሚታየው ሰው ቁጥር በመቶዎች የሚቆጠር መሆኑን በማንኛውም ሰዓት በመገናኛ፣ በአራት ኪሎ በፒያሳ ወይም በመርካቶ አካባቢ በማየት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ዋነኛው ጥያቄ እዚህ ጋር ይጀምራል? ለምን ሰዎች ጎዳና ላይበዙ? ለዚህ መንግሥት ማለትም የሚመለከታቸው ተቋማት በጥናት የተደገፈ ምላሽ መስጠት አለባቸው፡፡
ሥራ የለም? የሰዎች ቁጥር በዝቷል? አብዛኛው ሰው ሥራውን የሚያከናውነው ጎዳና ላይ ነው? ወይስ የሥራ ባህላችን ደካማ ሆኖ ሰዎች ሥራቸውን ጥለው እየወጡ በየጎዳናው ሲንከራተቱ ይውላሉ? ወይስ ሌላ ምክንያት አለ? መጨረሻ ላይ የሚመጣው ውጤትስ ምን ይሆናል? እውነት በየጎዳናው የሚርመሰመሰው ሰው በዚሁ በአዲስ አበባ ተወልዶና አድጎ ነው? ወይስ ከሌሎች አካባቢዎች መጥቶ? ከተወለደና ከመጣ ጥቅምና ጉዳቱ ምንድን ነው? ይህ ጉዳይ ለከተማዋም ሆነ ለአገር ስጋት ነው ተስፋ? የሚለው በሙሉ በደንብ ተመርምሮ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ እኔ በበኩሌ የሚርመሰመሰው የሰው ቁጥር አስጨንቆኛል፡፡ መንስኤው የሰው ቁጥር ብቻ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ቤጂንግ ከአዲስ አበባ ከሦስት እጥፍ በላይ የሰዎች ቁጥር ቢኖሩም የሚታዩት ጠዋትና ማታ ከሥራ ወደ ማደሪያቸው ሲንቀሳቀሱ ብቻ ነው፡፡ የአዲስ አበባው የቀን ሙሉ ትርምስ መላ የሚያስፈልገው ይመስላልና የሚመለከተው አካል መላ ይበል ብለናል ሰላም፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም