የኑሮ ውድነት ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ነው። በተለይም በያዝነው ዓመት የምግብ ሰብል፣ ሸቀጣ ሸቀጦች፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል። ይህም ኅብረተሰቡን እያማረረና ሥራ አጥ ዜጎችም እንዲበራከቱ ምክንያት እየሆነ ነው። በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ ነጭ ጤፍ 53 ብር፣ ቀይ ጤፍ 42 ብር፣ ብርቱካን አንድ ኪሎ 120 ብር፤ ካሮት 45 ብር፣ ምስር ክክ 90 ብር፣ አንድ ሊትር ዘይት 120 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል። በሀገር ውስጥ የተመረቱ ምርቶች በዚህ ደረጃ ዋጋቸው ሽቅብ መውጣቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው፣ የመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ20 ነጥብ 6 ከመቶ ከፍ ብሎ ታይቷል። በእህሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በያዝነው ወርም የቀጠለ ሲሆን ይህም ለምግብ ዋጋ ግሽበት መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክቷል።
እንዲሁም የመጋቢት ወር የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ22 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ገልጿል። ይሄ የሚያሳየው በእያንዳንዱ የምግብ ምርቶች ላይ ያለው ዋጋ እየጨመረ መምጣቱን ነው። ይሄም በኅብረተሰቡ ኑሮ ላይ የራሱን ተፅዕኖ እያሳደረና ሕዝብን ለምሬትና ስቃይ እየዳረገው ይገኛል። ሆኖም ግን መንግሥት ችግሩን በዝምታ እያየው አይደለም። ይልቁንም የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት የበጀት ድጎማ ከማድረግ አንስቶ አስፈላጊ የሆኑ የክትትልና የቁጥጥር እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል።
በመንግሥት ከተወሰዱ እርምጃዎችም ውስጥ የዋጋ ተመንን የማስቀመጥና አላግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ሸቀጦችን በሚያከማቹ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ተገቢውን እርምጃ የመውሰድ ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት 500 ሚሊዮን ብር በመመደብ የግብርና ምርቶች በበቂ ሁኔታ ወደ መዲናዋ እንዲገቡና ለነዋሪው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ፤ ከዚህ ቀደም የነበረውን የተንዛዛ የግብይት ሰንሰለት በማስቀረት የህብረት ሥራ ማህበራት ከዩኒየኖች በቀጥታ እንዲረከቡ እንዲሁም ወደ ከተማው የገቡት ምርቶች በትክክል ነዋሪው ጋር እንዲደርሱ የማድረግ የክትትል እና የቁጥጥር ሥራ እንደሚሰራ አስታውቆ ነበር። በዚህ መልክ በተወሰነ ደረጃ እንቅስቃሴ ቢደረግም አጥጋቢ የሆነ ምላሽ ግን ሲሰጥ አልታየም። የክትትልና የቁጥጥር ሥራውም ውጤት አምጥቷል ለማለት አያስደፍርም።
ለምሳሌ ያህል መንግሥት የሲሚንቶን ዋጋ ለማረጋጋት በሰራው ሥራ ለሦስት ቀናት ያህል የሲሚንቶ ዋጋ ከነበረበት የተጋነነ ዋጋ በግማሽ ወርዶ ተጠቃሚውን እፎይ አሰኝቶ ነበር። ሆኖም ግን ይሄ ውጤት ከሁለትና ሦስት ቀናት የዘለለ አልነበረም። ተመልሶም የሲሚንቶ ዋጋ ተሰቀለ፤ ከገበያ ላይም ጠፋ። የዘይት ዋጋም በተመሳሳይ ከ360 ብር በላይ እንዳይሸጥ መመሪያ ወርዶ ነበር። ሆኖም በዚህ ዋጋ የሸጠ ነጋዴ ማየት አልተቻለም። ይልቁንም ምርቱ ከመደብር ፊት እንዲጠፋ ሆነ፤ ትንሽ ከተረሳሳ በኋላ ግን አሁን በአደባባይ አምስት ሊትር ዘይት እስከ 570 ብር እየተቸበቸበ ይገኛል።
ይሄ የሚያሳየው የሚደረገው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ጠንካራ አለመሆኑን ነው። የሚወሰደው እርምጃም ነገ እንዳይደገም በሚያደርግ መልኩ አይደለም። የክትትልና የቁጥጥር እርምጃው ለውጥ የሚያመጣና አስተማሪ ባለመሆኑ አሁን መንግሥትና አንዳንድ ሕገወጥ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ድብብቆሽ እየተጫወቱ ይገኛሉ። ጠዋት መንግሠት የዋጋ ተመን እና መመሪያ ያወጣል። ነጋዴ ደግሞ ከሰዓት በኋላ የራሱን ተመን አውጥቶ በተጋነነ ዋጋ ይቸበችባል። ይሄ የሚያሳየው የንግዱ ማህበረሰብ ከንግድ ሥርዓት ውጪ መሆኑን ነው።
ስለዚህ መንግሥት በሕገወጥ መንገድ ለመክበር ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት በሚፈጥሩ ነጋዴዎችና ደላሎች እንዲሁም ተባባሪዎቻቸው ላይ አስተማሪ ቅጣት ሊጥል ይገባል። የወጣው መመሪያም በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም መንግሠት ነዋሪውን በኢኮኖሚ የመጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ በሕገወጥ መንገድ ለመክበር በተጋነነ ዋጋ በመሸጥ ሕዝብን በሚያማርሩ አካላት ላይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ ሊወስድ ይገባል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም