የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ማስቆም አይቻልም!

ኢትዮጵያ በአኩሪ ታሪኮች የታጀበች ሀገር ናት፡፡ በየዘመናቱ የመጡ ሀገር ወራሪዎችን አሳፍራ ከመመለሷም ባሻገር ለተጨቆኑ ሕዝቦች ጭምር የነጻነት ተምሳሌት ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ ከዚሁ ባሻገር ደግሞ የትኛውንም ሀገር በኃይል ወራ የማታውቅና መልካም ጉርብትናን የምታስቀድም ሀገር ነች፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራትም አልፋ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሲቸገሩ ፈጥና የምትደርስና ከችግሮቻቸው እንዲወጡ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ከተቸገሩት ጎን የምትቆም መከታ ናት፡፡ ለአብነትም ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ጭቆና ስር በነበረችበት ጊዜ የነጻነት ታጋዩን ኔልሰን ማንዴላን ሀገሯ ድረስ ጠርታ በመከለልና በማሰልጠን ደቡብ አፍሪካ ነጻነቷን እንድትጎናጸፍ የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች፡፡ በቅኝ አገዛዝ ስር የነበረችውም ዙምባቤም ነጻነቷን እስክታውጅ ድረስ የኢትዮጵያ ድጋፍ ተለይቷት አያውቅም፡፡

ወደ ጎረቤት ሀገራትም ስንመጣ ይኸው ሚናዋ ጎልቶ ይታያል፡፡ ግጭት ባልቆመባቸው በሱዳን የአብዩ ግዛትና በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይልን በመላክ ኢትዮጵያ ለአባል ሀገራቱ ጥላና ከለላ መሆን ችላለች፡፡ በቀውስ ውስጥ የምትገኘውን ሱዳንን ወደ ሰላም ለመመለስም በብቸኝነት የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡

ኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይሏን በመላክ መንግሥት አልባ ሆና የቆችውን ሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት እንድትመሰርት እና አንጻራዊ መረጋጋት እንዲኖራት የሕይወት ውድ መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ቀጣናዊ ግዴታዋን ተወጥታለች፡፡

ሆኖም ይኸው ውለታዋ በአንዳንድ ሀገራት ዘንድ በአግባቡ ከግንዛቤ የገባ አይመስልም፡፡ ወይንም ደግሞ ሆን ተብሎ የተነዘነጋ ይመስላል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሕዝብና መንግሥት የከፈለችውን ውለታ ቸል በማለት ድንበር አቋርጠው ከመጡ የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ኢትዮጵያ ላይ ሴራ እስከማሴር ተደርሷል፡፡

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች ያለች ሀገር ነች፡፡ የሕዝብ ቁጥሯም በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ የያዘ እና በቀጣይም እያደገ የሚሄድ ነው፡፡ ስለዚህም የዚህን ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት መጠነ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ያስፈልጋታል፡፡ ይህንን ለማሳካት ደግሞ በዋነኛነት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እና የባህር በር ጥያቄዎቿ ሊመለሱላት ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በኃይል እጥረት የሚሰቃይ ሕዝብ ነው፡፡ 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ምንም አይነት የኤሌክትሪክ አገልግሎት አያገኝም፡፡ አብዛኞቹ ፋብሪካዎች በኃይል እጥረት ምክንያት በተገቢው መጠን ለማምረት የሚቸገሩ ናቸው፡፡

ስለዚህም ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅማ የኃይል ፍላጎቷን ማሟላት ለነገ የማትለው ጥያቄ ነው፡፡ ይህን መሰረት በማድረግም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በመገንባት ዛሬ ላይ ወደ ማጠናቀቁ ደርሳለች፡፡ እስካሁንም ባለው ሁኔታ አራት ተርባይኖች ወደ ኃይል ማምረት የገቡ ሲሆን፤ ቀሪ ሥራዎችም እስከ 2017 መጨረሻ ድረስ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

ታላቁ የዓባይ ግድብ ኃይል ባመነጨበት ቅጽበትም ከሀገር ውስጥ ፍላጎት አልፎ ለጎረቤት ኬንያ እና ሱዳን ጭምር የኃይል አማራጭ መሆን ችሏል፡፡ በጎረቤት ሀገራትም ዘንድ የትብብር እና የወዳጅነት ማህተም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ሆኖም ይህ ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ በርካታ ፈተናዎችን አልፏል፡፡ በተለይም በውሃው ላይ የቅኝ ግዛት ውሎችን ጭምር በማንሳት የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱ አንዳንድ ሀገራት ግንባታውን ለማስተጓጎል ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ በሀገር ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ ቅጥረኞችን ከማሰማራት አንስቶ በጸጥታው ምክር ቤት ጭምር በርካታ ጫናዎች ተደርገዋል፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የያዙት ፍትሐዊ የመልማት ጥያቄ በመሆኑ ልማቱን ለማስተጓጎል የቻለ አንዳችም ኃይል የለም፡፡

በተመሳሳይም ኢትዮጵያ ኢፍትሐዊ በሆነ መልኩ የባህር በር ያጣች ሀገር ናት፡፡ በዚህም ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ተዳርጋ ቆይታለች፡፡

ስለዚህም እያደገ የሚሄደውን የሕዝብ ቁጥሯን ለመመገብ እና የኢኮኖሚ ጥያቄዋን ለመመለስ የአማራጭ ወደቦች ባለቤት መሆን አለባት፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ሰላማዊ አማራጮችን እየተጠቀመች ነው፡፡

አሁንም የኢትዮጵያ ጥያቄ መልስ እንዳያገኝ የሚመኙ እና በዓባይ ግድብ የተሸነፉ ሀገራት ጉዳዩን የተለየ መልክ በመስጠት በሰላም አስከባሪ ስም ምሥራቅ አፍሪካ ድረስ በመምጣት ቀጣናውን የግጭት ማዕከል ለማድረግ እየጣሩ ነው፡፡

ሆኖም እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ያነሱት ጥያቄ ፍትሐዊ ነውና ጥያቄውን በአግባቡ ከመመለስ ውጪ አማራጭ የለም፡፡ ኢትዮጵያውያን ያነሱት ትክክለኛ የመልማት እና የማደግ ጥያቄ በመሆኑ እነዚህን ጥያቄዎች በጭራሽ ማስቆም አይቻልም!

አዲስ ዘመን መስከረም 8/2017 ዓ.ም

Recommended For You