ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
የፈለጋችሁትን በሉኝ ከዚህ ትውልድ አይደለሁም። ራሴን በገዛ ፍቃዴ ከስሜታዊው ትውልድ አግልያለው። እኔ በምክንያት የተፈጠርኩ፣ በምክንያት የምኖር ሰው ነኝ። ለሀገሬ ምርጡን የማስብ፣ ለድሀው ወገኔ የምጨነቅ ባለ ራዕይ ወጣት ነኝ። እኔ የኢትዮጵያን ስም በመልካም ከሚያስተጋቡት ምርጦች ውስጥ ነኝ። በዘርና በብሔር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ከሚባሉት ውስጥ አይደለሁም። የሚያግባቡንና አንድ የሚያደርጉን ብዙ ነገሮች እያሉ፤ በለያዩን ጥቂት ነገሮች የምሸነፍና ድንጋይ ከሚያነሱት ውስጥ አይደለሁም…እንደ እኔ ትውልዱን የጠላ፣ በማሰብ የሚኖር፣ ኢትዮጵያን ያለ ታማኝ ዜጋ ካለ ይከተለኝ…ይሄን ያለ አብሮኝ ይቁም።
በእኔና በእናንተ መካከል የቆመ የማንነት ድንበር፣ ብሔርተኝነትን የሚሽር የህልውና አጥር፣ የአንድነት ምሰሶ ኢትዮጵያዊነት ነው። በዚህ ስም ካልተግባባን በሌላ በምንም አንግባባም። ኢትዮጵያ መግባቢያ ቋንቋችን ናት..ሀሁ ፊደላችን። በእያንዳንዳችን ነፍስ ላይ የተሳለች የደም ጠብታችን። በእያንዳንዳችን ከንፈር ላይ፣ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ደምቃ የተጻፈች ሀቃችን እንዲህም እላታለው። ዛሬ ላይ በብሔር ስም ብዙ ነገር እየሆነን ያለንው ኢትዮጵያዊነትን ስላልተረዳነውና ስላልተቀበልንው ነው። ከትላንት እስከዛሬ በአንድነት ያቆሙን በርካታ እሴቶች አሉን። ዛሬ ላይ እነዛን መልካም እሴቶች ከማጠንከርና ለትውልድ ከማስተላለፍ ይልቅ በማጥፋት በምትኩ ትውልድ የሚመርዙ እኩይ ነገሮችን በማባዛት ላይ ተጠምደናል።
ሐበሻነት በእያንዳንዳችን ደም ውስጥ ያለ የአንድነት ሐውልት ነው። ለልጆቻችን የምናስተላልፈው የጋራ ሀገር የጋራ እውነት ይኑረን። ኢትዮጵያዊነት ምንድነው ስንባል የምንመልሰው የጋራ እውነት ሊኖረን ይገባል። እኔ ግን እላለው ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ሌላ ብሔር፣ ሌላ ማንነት የለኝም። የኔ ብሔር..የማንነቴ ጥላ..ዋርካዬ ኢትዮጵያ ናት። አገራችን ኢትዮጵያ ለሁላችን የምትበቃ ማህፀነ ለምለም ሀገር ናት። እኛ ለእሷ እንመቻት እንጂ እሷ ለእኛ የሚሆን ብዙ ነገር አላት። እኛ በፍቅር፣ በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንቁም እንጂ ማጀቷ ሙሉ ነው። ሌማቷ ጎሎ አያውቅም። አይደለም ለእኛ ለሌሎች የሚሆን ብዙ ነገር ያለን ህዝቦች ነን። አንዳችን ለአንዳችን እናስፈልጋለን። ራሱን ወልዶ ያሳደገ ማንም የለም።
ሁላችንም ጀግናና ብርቱ የሆንው ከሌሎች ጋር ቆመን ነው። አሁን ያለንበት ቦታ ለመድረሳችን የብዙ ኢትዮጵያዊ ልፋት አለበት። ብቻውን ተራምዶ፣ ብቻውን ሮጦ ያሸነፈ የለም። ያደግነው.. ለቁም ነገር የበቃነው፤ ወልደን የሳምነው፣ ዘርተን የቃምነው በሌሎች ተመርቀን፣ በሌሎች ተወድሰን ነው። ሁላችንም ለሁላችን እናስፈልጋለን። እዚህ የደረስነው በእቁብና፣ በእድር በማህበር እየተረዳዳን ነው ። ቡና እየተጣጣን፣ በእኔ ጉዳይ ጎረቤት ያገባኛል እያለ፣ በጎረቤቴ ጉዳይ እኔ ያገባኛል እንዲህ ሆነን ነው የኖርንው። ኢትዮጵያዊነት መተሳሰብ.. አብሮ መቆም ነው። እኔ አማራ ብቻ፣ ኦሮሞ ብቻ ወይም ትግሬ ብቻ አይደለሁም፣ እኔ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ደግፎ ያቆመኝ የብሔረሰብ ልጅ..የብሔረሰብ ቅይጥ ነኝ። እኔ እዚህ ቦታ ሰው ሆኜ እንድቆም አማራው፣ ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ወላይታው፣ ጋሞው፣ ጉራጌው፣ አርጉባው ሁሉም ብሔር አስተዋጽኦ አድርጓል። እንዴት ራሴን በክብር ካቆመኝ ከዚህ ህዝብ መገንጠል እችላለሁ? እንዴትስ ውለታውን ረስቼ ኦሮሞ ነኝ፣ አማራ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ እላለሁ? እንዴት በኩራት ካቆመኝ ብሔር ብሔረሰብ ተለይቼ ሲዳማ ነኝ፣ ጉራጌ ነኝ እላለሁ? እኔ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ ነኝ። የእኔ የምለው ብሔር የለኝም። የኔ ካልኩም የኔ የምላት ኢትዮጵያዬን ብቻ ነው።
የእኔ ብሔር እሷ ናት..እኔ እሷን ነኝ፣ እሷም እኔን ናት። መልካም ያደረገልኝን ህዝብ በእሷ ውስጥ ነው የማየው። ለዚህ ክብር ያበቃኝን ብሔረሰብ በእሷ ውስጥ ነው የማገኘው። ውለታውንም አገሬን በመውደድ፣ ህዝቦቿን በማፍቀር እመልሰዋለው። ኢትዮጵያ የእኔም የእናተም የሁላችንም ብሔር ናት። በእሷ እንጠራ። ዓለም የሚያውቀን እኮ በኦሮሞነት፣ በአማራነት ወይም ደግሞ በትግሬነታችን አይደለም በኢትዮጵያዊነታችን ነው። እኔ እኮ የቤተሰቤ፣ የአካባቢዬ፣ የማህበረሰቤ፣ የመምህራኖቼና የጓደኞቼ ድምር ውጤት ነኝ። እኔ እዚህ የደረስኩት የተለያዩ ኢትዮጵያዊያን ስመውኝ፣ አስተምረውኝና መክረውኝ ነው። አማራ መምህራን አልነበሩንም? ኦሮሞና ትግሬ መምህሮች አላስተማሩንም? ጉራጌ ጎረቤት አልነበረንም? ሲዳማና ወላይታ ሀዲያና ከንባታ ጓደኛ አልነበረንም? የመልካምነት ጥጉ ጋሞነት አላሳደገንም? ብቻችንን የኖርንው ህይወት የለንም።
እዚህ የደረስነው ከትላንት እስከ ዛሬ ተያይዘን ተደጋግፈን ነው። ለእኔ ሰው መሆን የእናንተ ዋጋ ከፍተኛ ነበር። ለእናተ ሰው መሆን የእኔ አስተዋጽኦ ነበረበት። እኛ እኮ እኔ ብለን ራሳችንን ብቻ እንዳንጠራ ሆነን የኖርን ህዝቦች ነን። እኛ እኮ በዓለም ታሪክ በሌለ አንድነትና ቤተሰባዊነት ተቃቅፈን የምንኖር ህዝቦች ነን። እኛ እኮ ውል የሌለን ቋጠሮዎች ነበርን…አሁንም ድሮነት ይመለስ እላለው። በዚች ሀገር ላይ የአባቶቻችን የአብሮነት ሥርዓት እንዲመጣ እፈልጋለው። የዓድዋ ድል የማነው? የኦሮሞ ብቻ ነው? የአማራና ትግሬ ብቻ ነው? የሁላችንም ድል አይደል? ሕብረታችን አንድነታችን ያስገኘው ነው። በኦጋዴን፣ በማይጨው ማን ሞተ? አማራ ብቻ ነው የሞተው? ትግሬና ኦሮሞ ብቻ ነው? በአንባላጌ፣ በካራማራ ደሙን ያፈሰሰው፣ አጥንቱን የከሰከሰው ማነው? የኢትዮጵያ ህዝብ አይደል? አማራው ኦሮሞው ትግሬው፣ ሀድያው፣ ከንባታው አይደል? ታዲያ ከዚህ በላይ እኛ ምንድነን? የሞትንላት የተጎሳቆልንላት ሀገር አንድ አይደለች? ካተረፍንም ካከሰርንም አብረን ነው።
ለብቻ የሚኖረን ሠርግና መርዶ የለንም። የጋራ እንጂ የተናጠል ታሪክ የለንም። እኔ የራሴ ሰው አይደለሁም። በእርግጠኝነት እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም..እኔ ከእናንተ ውጭ የራሴ የምለው ምንም ነገር የለኝም። ደስታዬም ሀዘኔም ከእናተ ጋር ነው። አንድ ሆኜ ህዝብ ነኝ። አንድ ሆኜ ብሔር ብሔረሰብ ነኝ። አንድ ሆኜ ሙስሊምም ክርስቲያንም ነኝ። አንድ ሆኜ አማራ ነኝ፣ አንድ ሆኜ ኦሮሞ ነኝ። አንድ ሆኜ ትግሬ ነኝ። አንድ ሆኜ አፋር ቤንሻጉል ነኝ። በመካከላችሁ ተዘርቼ የበቀልኩ፣ በቅዬም የፀደኩ አንድ ሆኜ ሚሊዮን የሆንኩ ነኝ። ካለ እናተ ካለወንድሞቼ መኖር የማልችል ብኩን ነኝ።
ከቋንቋችሁ፣ ከባህላችሁ፣ ከመልካችሁ የተቀላቀልኩ ያለ እናንተ ያለ ኢትዮጵያ ብቻዬን መቆም የማልችል እኔ እናንተን ነኝ። ከበረታሁ ከእናተ ጋር ነው። ከቆምኩ፣ ከወደኩም አብሬአችሁ ነው። የቆምኩት በጉልበታችሁ ነውና። እኔ እኔን የሆንኩት በእናተ ድጋፍ ነው። የምተነፍሰው እኮ የእናተን አየር ነው። እስኪ ከእናንተ በቀር የእኔ የምለው ምን አለኝ? እናተ የሌላችሁበት ኢትዮጵያ ምን ልትጠቅመኝ? ቅይጥ ቋንቋችሁ፣ ቅይጥ መልካችሁ ይናፍቀኛል። የዋህነታችሁ ያኖረኛል። ባህል ወጋችሁ ክብሬ ነው። መኖራችሁ መኖሬ ነው። ስለዚህ እባካችሁ ማነህ? ከየት ነህ? ምንድነህ አትበሉኝ። ገፄን ገፃችሁ ላይ እያያችሁ፣ መልኬን መልካችሁ ላይ ተነቅሳችሁ፣ ስሜን ከስማችሁ ቀይጣችሁ፣ ደሜን ከደማችሁ ደባልቃችሁ እኔ እናተን እናተም እኔን ሆናችሁ ማነህ አትበሉኝ። እኔ እናተን ነኝ።
እኔ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብን ነኝ። በኦሮሚያ ኤሬቻን፣ በአማራ አሸንድዬ ሶለንን፣ በትግራይ አሸንዳን፣ በጉራጌ መስቀልን ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር በአንድነት በፍቅር አክብሬአለው። በሲዳማ ፍቼ ጫንባላላን፣ በወላይታ ጊፋታን፣ በጋሞ ዮ መስቀላን፣ በሐመር ኢቫንጋዲን በሚደነቅ ኢትዮጵያዊ አብሮነት አክብሬአለው። ጨፍሬአለው። አመስግኛለው። በጌዲኦ ዳራሮን፣ በአላባ ሴራን፣ በሀዲያ..በአፋር..በሐረሪ በኢትዮጵያዊ ወግና ባህል ተደስቼ አውቃለው። መኖራችሁ ያስፈልገኛል…ያለእናተ..ያለ ኢትዮጵያ ወገኖቼ እኔ ምንም ነኝ። እንተቃቀፍ..እንደማመጥ። ልክ እንደ ጋሞዎች አባቶቹን የሚሰማ፣ ለታላላቆቹ የሚያጎነብስ ትውልድ ያስፈልገናል። በይቅርታ የሚያምን፣ የአባቶቹን ሥርዓት ያልተወ፣ ክፉ ነገርን ጎሚ ነው ብሎ የሚፀየፍ ትውልድ እንሻለን።
ጋሞነት የሰብዓዊነት ጥግ፣ የሰው መሆን ልክ ሆኖ አይተናል። በእርጥብ ሣር ትውልድ የሚመሩ አባቶች የሚኖሩባት የገነት ህዝቦች አብራክ ብያቼዋለው። ጥያቄያችን መልካም ሀገርና ህዝብ ከሆነ በግብረገብነት እንዳደጉ፣ የአባቶቻቸውን ወግና ሥርዓት እንዳልተው እንደ ጋሞ ልጆች ሁሉም ቤተሰብ በፍቅርና በይቅርታ የሚያምኑ ተረከዝ ያዥ ልጆችን ወልዶ ማሳደግ ይኖርበታል። እውነት ያለው በደጋግ ልቦች ውስጥ ነው። ፍቅርም ከንፁህ ነፍስ ውጭ ቦታ የላትም። ለአባቶቻችን ቦታ ይኑረን። ኢትዮጵያ ውስጥ በኩራትና በልዕልና የሚያኖሩን የተለያዩ መልካም እሴቶች አሉን። በኢትዮጵያ ጥላ ሥር የምንኖር ሁላችንንም የሚያግባባን፣ አንድ አድርጎ የሚያቆመን ብሔር ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ነው። ብሔር በአንድ አገር ውስጥ የነበረ፣ ያለና፣ የሚኖር፣ ዘለዓለማዊ ጥያቄ ነው ግን ከአገር አይበልጥም። ሰው ከመሆን አይልቅም። ከሁሉም የምንበልጠው እኛ ነን.. ኢትዮጵያ የሚለው ስም።
ጣሊያን የመጣው አማራን ወይም ኦሮሞን ለመግጠም አይደለም። ድንበር ጥሰው የመጡት ግብጽና ሱማሌ፤ ከትግሬና ከሌላው ብሔር ጋር ብቻ ለመዋጋት አይደለም ኢትዮጵያን ብለው ነው። ታላቅ በሆነው ስማችን አንድ ልንሆን ይገባል። ከሱማሌ በቀር ሁሉም የዓለም አገራት የተለያየ ብሔር፣ የተለያየ ሃይማኖት፣ የተለያየ ቋንቋና ባህል ያላቸው ናቸው። ግን በብሔራቸው ወይም ደግሞ በልዩነታቸው እንደ እኛ ያን ያክል ውዝግብ ውስጥ ገብተው አያውቁም። ብሔራቸው፣ ሃይማኖታቸው፣ ቋንቋና ባህላቸው ከአገራቸው በልጦባቸው አያውቅም። አገር ፈርሳ የምንገነባው ብሔርና ሃይማኖት የለንም።
ህንድ ሰባት መቶ የተለያዩ ቋንቋዎች ያሏት አገር ናት። ህንዳዊያን በሰባት መቶ የተለያዩ ቋንቋዎች እየተነጋገሩ በህንድ ቀልድ አያውቁም። በሰባት መቶ የተለያዩ ቋንቋዎች እየተግባቡ በልዩነት ውስጥ ተቻችለው የሚኖሩ ስልጡን ህዝቦች ናቸው። ህንዳዊያን በምንም ነገር ላይ ቅድሚያ ለህንድ የሚል መፈክር አላቸው። በዚህም አብሮነታቸው ዓለም ላይ ትልቁን ኢኮኖሚ ለመገንባት ችለዋል። ወደ አንድነት እንመለስ። አንድ ብሔር ብቻ የሆነ ህዝብ የለም። የአንድ በሔር ውጤቶችም አይደለንም። በእያንዳንዳችን ሰውነት ላይ የእያንዳንዱ ብሔር መልካም አሻራ አለ። የኖርነው..እየኖርን ያለነው በሌሎች ብሔር ታላቅ አስተዋጽኦ ነው። ያለን ይመስለናል እንጂ ብቻችንን የኖርነው ቅንጣት ህይወት የለንም። ዛሬም ነገም በሌሎች ጥላ ሥር ነን። ብቻችንን ተአምር የለንም። ብቻችንን አገርና ህዝብ መሆን አንችልም። ብቻችንን መብለጥ..ማሸነፍ አንችልም።
ብዙ መሆናችን ሃይል ነው። የተለያየን መሆናችን ውበት ነው። አንድ መሆን ከሃይልና ከውበት ባለፈ አስፈሪነትም ነው። ግርማ ሞገስ ነው። አንበሳነት ነው..ኩራት ነው። ታዲያ ወንድማማችነት አይሻልም ትላላችሁ? አስፈሪና ባለግርማ ሞገስ፣ አንበሳና ኩሩ የምንሆነው ኦሮሞ ወይም አማራ ወይም ትግሬ ወይም ሌላ ስንሆን ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ስንሆን ብቻ ነው። ልዩነታችንን ለውበት እንጂ ለመለያየት አንጠቀመው። ብዙሃነታችንን ለልማት እንጂ ለሁከት አናድርገው። ስለዚህም እንዲህ አልኩ..ከዚህ ትውልድ አይደለሁም። እኔ ኢትዮጵያዊነት እንጂ ብሔር አይገዛኝም። ወንድማማችነት እንጂ ጥልና ክርክር አይረታኝም። በእናተ ፍቅር ጨርቄን ጥዬ ያበድኩ የአካላችሁ ክፋይ ነኝ። በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ርሃብና ሰቆቃ፣ ድህነትና ኋላ ቀርነት እንዲጠፉ በብርቱ የምታገል ከመልካሞቹ አንዱ ነኝ። ኢትዮጵያን ያለ..ኢትዮጵያን ብቻ አላማው ያደረገ ይከተለኝ። አበቃሁ..ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 5/2013