ወንድወሰን መኮንን
ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው። አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው ናዝሬት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ቀጥለውም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርክቴክቸርና ኧርባን ዲዛይን በድሮው ሕንፃ ኮሌጅ አምስት ዓመት ተምረው ዲግሪያቸውን ወስደዋል። ሁለተኛ ዲግሪያችውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ አርክቴክቸር፣ ሕንፃ ግንባታ እና ከተማ ልማት ተቋም በሀውሲንግ ኤንድ ሰስቴይነበል ዴቨሎፕመንት የትምህርት ዘርፍ ሰርተዋል። በአሁኑ ወቅትም በዚሁ ተቋም በመምህርነት እየሰሩ ይገኛሉ። የዛሬዋ እንግዳችን አርክቴክት አብነት ገዛኸኝ።
አርክቴክት አብነት ከዚህ በተጨማሪ በሕንፃዎች ላይ የአየር ወለድ በሽታዎችን በዲዛይን የመከላከል ሥነዘዴ (ኤርቦርን ኢንፌክሽን ኮንትሮል ፎር ቢዩልዲንግ ሴቲንግስ) በማጥናት ከሀርቫድ ስኩል ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ ፖስት ግራዱዌት ሰርተፍኬት ዲፕሎማ ወስደዋል። በሄልዝ ኬር ፋሲሊቲ ዲዛይን የሙያ መስክ ብዙ ሥራዎችን ሰርተዋል። ይህ የሙያ ዘርፍ በሀገራችን ብዙ የተለመደ መስክ አይደለም። እኛም የዚህን የተለየ ሙያ ምንነት፣ በዚሁ ሙያ ምን ሥራዎች እንደሰሩና በሀገራችን ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገንላቸዋል፤ ይከታተሉት።
አዲስ ዘመን፡–ትምህርትዎን ከጨረሱ በኋላ ለሥራ የት ተመደቡ?
አርክቴክት አብነት፡– በእኛ ጊዜ ምደባ የለም። ሥራ ፈልገን ነው የምንቀጠረው። ከዛሬ 19 ዓመት በፊት የግል ዘርፍ ላይ ቲኬ ኮንሰልቲንግ አርክቴክትስ ኤንድ ኢንጂነርስ የሚል ረዥም ዓመት የሥራ ልምድ ያለው ድርጅት ነው የተቀጠርኩት።
አዲስ ዘመን፡– የትና ምን ምን ሕንፃዎችን ሰሩ?
አርክቴክት አብነት፡– በዚሁ ድርጅት በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ብሎም በደቡብ ሱዳን የተለያዩ መኖሪያ ቤቶችን፣ ፋብሪካዎችን፣ የቢሮ ሕንፃዎች ዲዛይንና ሱፐር ቪዥን እንዲሁም የአንድ የልብ ህሙማን ህክምና ማዕክል ዲዛይን ሞዲፊኬሽን እና ሱፐርቪዥን ከሥራ ባልደረባዎቼ ጋር በመቀናጀት ሰርቻለሁ። ይህ ድርጅት በዕድሜም ሆነ በዕውቀት ያደኩበት ስለሆነ በተለይ መስራቹን ኢንጅነር ታደሰ ካሳሁንን ማመስገን እሻለሁ።
በወቅቱ ዩኤስኤይድ ክራውን ኤጀንትስ ዩኤስ ኤ በሚባል ድርጅት በኩል ባለሙያዎችን እየቀጠረ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያሰማራበት በነበረው ሄልዝ ሴንተር ሪኖቬሽን ኤንድ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ላይ ተቀጥሬ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፌደራል አርክቴክት በሚል መደብ ሁለት ዓመት ሰራሁ። በእኛ 2000 ዓ.ም አካባቢ የጤና ጣቢያዎች ማስፋፊያ ፕሮጀክት በጣም በሰፊው ይሰራ የነበረበት ወቅት ሲሆን ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ዩኒት የሚባል ልዩ ቢሮ አቋቁሞ በሱ ስር ነበር የምንሰራው። በሀገር ደረጃ ብዙ የጤና ጣቢያዎች ሲሰሩ በብዛት ያተኮርነው ፕሮጀክት ማኔጅመንት ላይ በተለይም ሱፐር ቪዥኑን የግንባታ ግብአት ቁጥጥሩን በየክልሉ የተሰማሩትን የፕሮጀክቱን ባለሙያዎች ማስተባበር ሙያዊ ድጋፍ መስጠት እንዲሁም ብዙ ባለድርሻ አካላትን ማስተባበርም የሥራው አካል ነበር።
አዲስ ዘመን፡– ባለድርሻ አካላቱ እነማን ነበሩ?
አርክቴክት አብነት፡– ከወረዳ ጤና ቢሮ ጀምሮ የዞን የክልል ጤና ቢሮዎች ኮንትራክተሮች የክልል ከተማ ልማት መሐንዲሶችን እንዲሁም የአካባቢ ነዋሪዎችን ያካትታል።
አዲስ ዘመን፡– ጤና ጥበቃ እያላችሁ የት የት ክልሎች ላይ ሰሩ?
ሜዲካል አርክቴክት አብነት፡– አሶሳና ትግራይ ነው የሰራሁት::
አዲስ ዘመን፡– ምን ያህል የጤና ጣቢያዎች ሰራችሁ?
አርክቴክት አብነት፡– በሁለቱ ክልሎች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጤና ጣቢያዎች ተሰርተዋል።
አዲስ ዘመን፡– ምን ያህል ጊዜ ወሰደባችሁ?
አርክቴክት አብነት፡– በአማካይ ብዙዎቹ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ወስደዋል። ረዘም ያለ ጊዜ የወሰዱም አሉ።
አዲስ ዘመን፡– ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኋላ የት ሰሩ?
አርክቴክት አብነት:- ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኋላ የሰራሁት ኬሞኒክስ ኢንተርናሽናል ኢንኮርፖሬትድ የሚባል መሰረቱን አሜሪካ ያደረገ ድርጅት ውስጥ በዲዛይን ኤንድ ኢንጅነሪንግ ዳይሬክተርነት ነው። ድርጅቱ ሄልዝ ሲስተም ኤክስፓንሽን ፕሮጀክት የተሰኘ የሦስት ዓመት የዩኤስኤይድ ፕሮጀክት አሸንፎ ከጤና ጥበቃ ጋር በቅርብ ነበር የምንሰራው። ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በተለያዩ ዳይሬክተሮችና ባለሙያዎች ፕሮጀክቱ ላይ ተሰርተዋል። በተለይም ደግሞ የውሃና የኤሌክትሪክ ችግር ያለባቸው ጤና ጣቢያዎች ተመርጠው በንፋስ ኃይል እንዲሁም በፒቪ ሶላር የሚሰራ ተለዋጭ ኃይል በፓይለት ፕሮጀክት መልክ ተሰርቷል። የውሃ ጉድጓድና ሬን ዋተር ሃርቨስቲንግም/የዝናብ ውሃን የማቀብ ሥራ/ ተሰርቷል።
አዲስ ዘመን፡- አርክቴክቸር ሙያ ዘርፈ ብዙ ነው። እርስዎ የሚሰሩት በሆስፒታሎች ዙሪያ በሚያተኩረው በሄልዝ ኬር ፋሲሊቲ ዲዛይን ነው። በዘርፉ በሀገራችን ምን ያህል ባለሙያዎች አላችሁ? በዚህ ዘርፍ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ማስተማር ተጀምሯል ?
አርክቴክት አብነት፡- በዚህ ዘርፍ የሚሰሩ ባለሙያዎች አሉ። ብዙዎቹ ከጤና ጥበቃ የመነጩ ናቸው። እስከማውቀው ድረስ ትምህርቱ የተጀመረ አይመስለኝም። ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ስላሉ እኔ የምናገረው ስለ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ነው። የሄልዝ ኬር ፋሲሊቲ ዲዛይን ትምህርት መሰጠት አልተጀመረም።
አዲስ ዘመን፡– ሄልዝ ኬር ፋሲሊቲ ዲዛይን ምንድነው?
አርክቴክት አብነት፡– አርክቴክቸር የተለያየ ዘርፎች አሉት። የሄልዝ ኬር ፋሲሊቲ ዲዛይን አንዱ ሲሆን የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ሕንፃ እንዴት መሰራትና በውስጡ ምን መካተት እንዳለበት የሚጠናበትና የሚተገበርበት ዘርፍ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ከሄልዝ ኬር ፋሲሊቲ ዲዛይን አንጻር አንድ ለጤና ተቋም የሚሆን ሕንፃ ዲዛይን ስታደርጉ ምን ምን ማሟላት አለበት?
አርክቴክት አብነት፡– የጤና አገልግሎት ተደራሽነት፣ ፍትሀዊነትና ጥራት በመሠረተ ልማት ስርጭት ላይ የተመረኮዘ ነው። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሀገራችን በተለያዩ የጤና አጠባበቅ ደረጃዎች ላይ እድገት ቢኖርም፣ ሆስፒታሎችና የጤና ጣቢያዎች ቢሰሩም ከሕዝባችን ቁጥር አንጻር ይህ በቂ አይደለም። ከጤና ጣቢያዎችና ሄልዝ ፖስት (የጤና ኬላዎች) ጀምሮ እስከ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ድረስ የጤና ተቋም ንድፍ መሠረታዊ ሂደቶች በየደረጃው ይኖሩታል። መሟላት ያለባቸው ነገሮችም አሉ።
አዲስ ዘመን፡– ምንድነው መሟላት ያለበት?
አርክቴክት አብነት፡– መጀመሪያ እንደ ማንኛውም ፕሮጀክት አንድ የጤና ተቋም ንድፍና ግንባታው የተሳካ እንዲሆን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማለትም የተቋሙ ባለቤት፣ ተጠቃሚው ማህበረሰብ፣ ተቆጣጣሪው ተቋም፣ ከንድፍና ከግንባታ ባለሙያዎች ጋር በከፍተኛ ቅንጅትና መግባባት መስራት ይኖርባቸዋል። ይሄ በጣም ቁልፉ ነገር ነው። በመቀጠል ደግሞ የአንድ የጤና ተቋም የንድፍ ሥራ ከቦታ መረጣ (ሳይት ሴሌክሽን) ጀምሮ ወይም የቦታውን አቀማመጥ ከመወሰን ጀምሮ ብዙ መካተት የሚኖርባቸው ነገሮች አሉ።
አዲስ ዘመን፡– ምንድናቸው የሚካተቱት?
አርክቴክት አብነት፡– በመጀመሪያ ደረጃ ፊዚቢሊቲ ስተዲ/የአዋጭነት ጥናት/ በጣም አስፈላጊ ነው። ቦታው ለምን ያህል ሰው ተደራሽነት አለው የሚለው ይታያል። ቦታ መረጣውን በተመለከተ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተዘጋጀው ዝቅተኛ መስፈርት/ሚኒመም ስታንደርድ/ ላይ ተመርኩዞ አንድ የንድፍ ባለሙያ ሌሎችም ማከል ያለበት ነገሮች አሉ። የጤና ተቋሙ ከድምጽ ብክለት ከጭስ ከአቧራና አስከፊ ጠረን ካለው ቦታ ርቆ መቋቋም ይኖርበታል። የመሬቱ አቀማመጥ ተዳፋቱ ለመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ምቹ መሆን አለበት። ከባቡር መንገድ ከትላልቅ አውራ ጎዳናዎች ከአየር መንገድም ተገቢውን ርቀት ጠብቆ መቀመጥ ይኖርበታል። የድምጽ ብክለት ስንል ትናንሽም ትላልቅም ድርጅቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ከወፍጮ ቤት፣ ከከባድ ኢንዱስትሪዎች፣ ከነዳጅ ማደያና ከቆሻሻ ማጠራቀሚያ ስፍራዎች መራቅ ይኖርበታል። ምድረ ግቢው ከመዳረሻ መንገዱ ጀምሮ በግልጽ መታየት አለበት። መሬቱ ሲመረጥ ይሄንንም ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል። ትልቅ የጤና ተቋም ሰርተህ አለመታየቱና በቀላሉ ሊገኝ አለመቻሉ ችግር ነው። መዳረሻ መንገዱ ከትራፊክ ጭንቅንቅ ነፃ መሆን አለበት። ለምሳሌ በአደጋ ጊዜ ወደ ጤና ጣቢያው ወይንም ወደ ሆስፒታሉ ተጎጂዎችን ለማመላለስ ነፃና ግልጽ መሆን አለበት። ግቢው ራሱ ለድንገተኛ አደጋ (ኢመርጀንሲ) ታካሚዎች፣ ለተመላላሽ ታካሚዎች (ኦፒዲ) እና ለሰርቪስ ቢያንስ ሦስት መግቢያ ለየብቻው ሊኖረው ይገባል። ቦታው የተመቸ ከሆነ ሌላ ተጨማሪ መግቢያዎች ማካተት ተመራጭ ነው። ዋና መግቢያ (ኦፊሽያል ኤንትራንስ)፣ ሰርቪስ መግቢያውም ተከፋፍሎ እንዲሁም የአስከሬን ማስወጫ ያስፈልገዋል። ካልሆነ ግን ሰርቪስ መግቢያው ደርቦ መስራት ይችላል። ሌላው ደግሞ የምድረ ግቢው ስፋት ከሚኒመም ስታንዳርዱ ማነስ የለበትም። ምድረ ግቢውና ሕንፃው ግልጽ የሆነ አቅጣጫ አመላካች ሊኖረው ይገባል። የሆስፒታል ደንበኛ ብዙ ጊዜ ሕመሙን እያዳመጠ የሚቸገር ሰው ነውና የት መሄድ እንዳለበት ግራ መጋባት የለበትም (ዌይ ፋይንዲንግ) ቀላል መሆን አለበት። ግቢው ውስጥ ለተጠቃሚው ግልፅና ምቹ ጠቋሚ ምልክቶች ሊኖሩ ይገባል። ማየት እና መስማት ለተሳናቸው ልዩ አጋዥ ምልክቶችም መደረግ ይኖርባቸዋል። በአደጋ ጊዜ ደግሞ ነፃ የሆነ የማምለጫ መንገድ ዝግጁ ሆኖ መቀመጥ ይኖርበታል። ሌላው የጤና ተቋሙ የሚሰራበት ቦታ መሠረተ ልማቶች ያስፈልጉታል። ንጹህ የመጠጥ ውሃ፤ መብራትና ሌላም ተለዋጭ የኃይል ምንጮች መኖራቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡–ተለዋጭ ኃይሎች ምንድ ናቸው?
አርክቴክት አብነት፡– በኤሌክትሪክና በውሃ ላይ ነው ተለዋጭ ኃይሎች መኖር አለባቸው። ውሃው ከማዘጋጃ ቤቱ መስመር ጋር የተገናኘ ከሆነ ጥሩ ነው። ካልሆነ ግን የከርሰ ምድር ውሃ እንዳለው ማጣራት ሌላም ምንጭ ካለ ማሰብ ይገባል። ተለዋጭ ኃይል ስልህ ከኤሌክትሪክ ጋር በተያያዘ ጀነሬተር ብዙም ባይመከር ታሳቢ ይደረጋል። ከመብራት ኃይል ብቻ ከምንጠብቅ ቦታው ለሶላር ኃይል የሚያመች ነወይ? በንፋስ ኃይልስ መጠቀም ይቻላል ወይ የሚለውን ታሳቢ ማድረግ አለብን። ሌላው ደግሞ ከጤና ተቋሙ የሚወጣ ቆሻሻ አካባቢውን እንዳይበክል ከቦታው አቀማመጥ ጀምሮ ለወደፊቱ መታሰብ አለበት። የቆሻሻ ማስወገጃ (ዌስት ማኔጅመንት) ሲስተም አብሮ መዘርጋቱን ማሰብ ያስፈልጋል። ጤና ተቋሙ ሲሰራ ዌስት ማኔጅመንት ከቦታው መረጣ ከንድፉና ከግንባታው ጀምሮ በጥራት ሊታሰብበት ይገባል። ፓርኪንግ፣ አረንጓዴ ስፍራዎች እንዲሁም በስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደረጃ ደግሞ ሄሊኮፕተር ማስቀመጫም ያስፈልጋል። ፓርኪንግ ስንል ግዴታ መኪና ማቆሚያ ብቻ አይሆንም። ገጠር የሚሰራ የጤና ተቋም ይህ ሁሉ ይኖረዋል ማለት አይደለም። እዚያ ደግሞ በደረጃው በወሳንሳ፣ በፈረስ፣ በጋሪ የሚመጣ ታካሚ አለ። ለፈረሶቹ ለጋሪዎቹ ማቆሚያ ቦታ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– አንድ የጤና ተቋም ዲዛይን ምን ዓይነት መስፈርቶች ማሟላት አለበት?
አርክቴክት አብነት፡– አንድ የጤና ተቋም ንድፍ አምስት ዋና ዋና መስፈርቶች አሉት። በአንደኛ ደረጃ ንድፉ ሲሰራ የሥራ ቅልጥፍናን (ኢፊሸንሲ) የሚያሟላና ወጪ ቆጣቢ መሆን አለበት። ሁለተኛ በቀላሉ ማስፋፋትና ማስተካከል የሚቻል (ፍሌክሲቢሊቲና ኤክስፓንደቢለቲ) ሊኖረው ይገባል። በሦስተኛ ደረጃ የፈውስ ድባብ ያለው መሆን አለበት። በአራተኛ ደረጃ ንጽህናን ለመጠበቅ ምቹ ሁኔታ ያለው በአምስተኛ ደረጃ ደግሞ በቀላሉ ተደራሽነት ያለው ቢሆን ተመራጭ ነው። የመጀመሪያውን መስፈርት ከሁለት አቅጣጫ እናየዋለን። አንደኛው የታካሚ መጠበቂያ ቦታዎች ስፋታቸው በቂ መሆኑን የአየር ዝውውሩ የተሟላ ሆኖ ተፈላጊ የመዝናኛና የንጽህና መጠበቂያ ስፍራዎች ጋር ማሟላታቸውን እናያለን። የታካሚውንና የአጃቢ ቤተሰቦችን ምቾት በጠበቀ መልኩ ማለት ነው። ይህ ከተሟላ ኮሪደሮች አይጨናነቁም የሥራውም ፍሰት ይቀላጠፋል። የሥራ ቅልጥፍናን ለማሟላት ኮሪደሮች፣ ሊፍቶች (ኤሊቬተሮቹ) እና ደረጃዎች (ሆሪዘንታልና ቨርቲካል ሰርኩሌሽን) ሊያስተናገዱ የሚችሉትን የሰው ብዛት ባገናዝበ መልኩ ቢነደፉ መልካም ነው። አላግባብ የረዘሙ ኮሪደሮች ካሉ አጭር ማድረግ የሕክምና ባለሙያዎችን እንቅስቃሴ አድካሚ እንዳይሆን ያደርጋል። የሕክምና ቁሳቁሶች የሕክምና ባለሙያዎችንና የታካሚውን እንቅስቃሴ በዲዛይን ማቀናጀት ግዴታ ነው። ሌላው ወጪ ቆጣቢ ስንል ከግንባታው ሂደት ጀምሮ እስከ ግንባታ ግብአቶች ድረስ መታሰብ አለበት። የሰውን ኃይል የማቴሪያል ሀብትና ሌላውንም በአግባቡ መጠቀም የወጣው ንድፍ አስተዋጽኦ ነው። ምክንያቱም የምንጠቀመው ማቴሪያል የምንጠቀምባቸው ነገሮች በሙሉ ወደፊት ሕንፃው ላይ ተጽእኖ ስለሚኖራቸው ነው።
ሁለተኛው መስፈርት ፍሌክሲቢሊቲና ኤክስፓንደቢሊቲ የሚለው በቀላሉ መሰራትና መቀያየር የሚችል ለማለት ነው። የሕክምና ሙያ ቴክኖሎጂው በፍጥነት እየተቀያየረና ሁሌም የሚያድግ ስለሆነ ሕንፃውም ይህንን ለውጥ ለማስተናገድ ብቁ መሆን ይጠበቅበታል። አንድ ሕንፃ ከሃምሳ እስከ መቶ ዓመት ዕድሜ አለው ተብሎ ነው የሚታሰበው። ስለዚህ የሚሰራው ሕንፃ የአሁኑን ቴክኖሎጂና የሕዝብ ፍላጎት ከማሟላት በተጨማሪ የወደፊቱን የሕዝብ ፍላጎትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ማካተት ይኖርበታል። ድንገተኛ አደጋዎች ለምሳሌ ከፍተኛ ቁጥር (ማስ ካዥዋሊቲ) ሲመጣ የጤና ተቋሙ ማስተናገድ መቻል አለበት። ቅርብ ጊዜ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመጣ ሰዓት በዓለም ደረጃ የሆስፒታሎች አቅም እንዴት እንደተፈተነ አይተናል። ይሄን ዓይነት ክስተቶችን አስቀድሞ ታሳቢ በማድረግ ንድፉ መሰራት ይኖርበታል ማለት ነው። ሦስተኛው መስፈርት ላይ ንጽሕናን የመጠበቅ ሁኔታን በተለያየ መልኩ ማየት እንችላለን። አንደኛው ሰርኩሌሽን መለየት ይኖርባቸዋል። የንጹህ ሕክምናና የቆሻሻ ሕክምና ግብአቶች ምንም ሳይገናኙ በተለያየ መንገድ መተላለፍ አለባቸው። በተጨማሪ ደግሞ የፊኒሺንግ ማቴሪያሎች የምንላቸው ወለሉ፣ ጣሪያው፣ ሁሉም ነገር በቀላሉ መጽዳት የሚችሉ የተመሰከረላቸው ግብአቶችን መምረጥ ይኖርብናል። በቀላሉ ካልጸዳ ታካሚዎች ኢንፌክሽን ዴቨሎፕ አድርገው አለአግባብ ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችላል። ተደራሽነት (አክሰሰብል) የሚለው መስፈርት ደግሞ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ከግቢው ጀምሮ በቂ ስፋትና ጥራት ያላቸው መንገዶች መኖር አለባቸው። በተጨማሪ በሮቹ፣ ኮሪደሮቹ፣ ኤሊቬተሮቹ፣ መታጠቢያ ቤቶቹ ለአካል ጉዳተኛ ተደራሽ መሆን አለባቸው። እነዚህ መስፈርቶች የሚሳኩት አርክቴክቱ፤ ሳኒተሪ ኢንጂነሩ፣ ስትራክቸራል ኢንጂነሩ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ኢንጂነሩ እንዲሁም ሌሎች ባለሙያዎች ተናበው ሲሰሩ ነው። የሕንፃው ንድፍና ግንባታም ተሟልቶ ከተሰራ በኋላ ደግሞ ሕንፃውን በቅርብ የሚንከባከብ ባለሙያ (ፋሲሊቲ ማናጀር) ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ በተጨማሪ የጤና ተቋም ሕንፃ ዲዛይን ሲሰራ መታሰብ ያለባቸው ነገሮች አሉ?
አርክቴክት አብነት፡– አዎ፤ የጤና ተቋም ሕንፃ ዲዛይን ሲሰራ የተጠቃሚውን በተለይ የታካሚውን ደህንነትና ዋስትና ሊያረጋግጥ የሚችል ፕሮግራምና የቦታውን አደረጃጀት ማሰብ ይጠይቃል። በእኔ አስተያየት ጥሩ የጤና ተቋም ሕንፃ ተጠቃሚው በተለይ ታካሚው ወደ ሕክምና ስፍራ መምጣቱ ሳይከብደው እንዲሁም ሕመሙንና ጭንቀቱን ሳያስተውል የሚስተናገድበት ሁኔታ የሚያመቻች መሆን አለበት።
የጤና ተቋም ሕንፃ ሲነደፍ ከሁለት አንግሎች ማየት ይኖርብናል። አንደኛው ከታካሚው አቅጣጫ በመሆን የሕክምና ሂደቱ ተመችቶት ቆይታውም መልካም ሆኖ ድኖ እንዲወጣ ምን ያስፈልገዋል የሚለውን የዲዛይን ባለሙያው ማሰብ አለበት። ሁለተኛው የጤና አገልግሎት ከሚሰጡት በተለያየ ደረጃ ካሉት የሕክምና ባለሙያዎችና ረዳቶቻቸው አቅጣጫ በመሆን እንዴት ሥራቸውን ማቀላጠፍ ማቅለልና ምቹ ማድረግ እንደምንችል በማሰብ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የጤና ተቋም ሕንፃ ሲሰራ የአካባቢውን ሕዝብ ባሕል ያገነዘበ መሆን አለበት። በእኛ ሀገር ለምሳሌ በአደጋ ክስተት ጊዜ የተጎዳው አንድ ሰው ቢሆንም አጅቦት የሚመጣው ዘምድና ወዳጅ ቁጥር ከፍ ያለ ነው። ይህ ሂደት ወላድ ወደ ሆስፒታል በምትመጣበትም ጊዜ በሰፊው ይስተዋላል። የአስታማሚና የጠያቂ ቤተሰብም ቁጥር ከፍተኛ ነው። ስለዚህ የሚሰራው ሕንፃም ሆነ ቅጥር ጊቢው ይህንን የኅብረተሰብ አካል ያለምንም እንግልትና ቅሬታ ማስተናገድ ይኖርበታል። ሌላው ከባህል ጋር በተያያዘ የታካሚውን ፕራይቬሲ የተለየ ትኩረት በመስጠት የምርመራ ክፍሎችና ሌሎችም አገልግሎቶች መነደፍ ይኖርባቸዋል። የአስከሬን መውጫ በርም ከሌላው አገልግሎት ገለል ብሎ የኀዘንተኛውን መብት እንደጠበቀ ግን የሌላውን ተጠቃሚ ደግሞ ሥነልቦናም በማይረብሽ መልኩ መቀመጥ ይኖርበታል። ከባህል ጋር በተያያዘ ብዙ ማለት ቢቻልም የዲዛይን ባለሙያው ጥናት አድርጎ ለአካባቢው የሚመጥን ሥራ ይሰራል ብለን እንቋጨው።
ሄልዝ ኬር ፋሲሊቲ ዲዛይን የጤና ተቋም ሕንፃ አገልግሎት በተሳካ መልኩ እንዲከናወን ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ይህንን ስል ሕንፃውና ንድፉ ብቻ በቂ ናቸው ማለት አይደለም። ከፊዚካልና ስፓሻል ጥራቱ በተጨማሪ የህክምናውን ሂደት የማስተዳደሩ ሥርዓትና የእያንዳንዱ ተጠቃሚ አያያዝም (አድሚኒስትራቲቭ እና ፐርሰናል) ጉልህ ሚና ይጫወታሉ። የእኛ ትኩረት ፊዚካልና ስፓሻል ላይ ስለሆነ እስካሁን ያወራነው በዚያ ዙሪያ ላይ ነው።
ለማጠቃለል ያህል ታካሚዎች እንዲሁም ሌላ ተጠቃሚዎች በጤና ተቋሙ ውስጥ አስደሳችና ጤናማ ቆይታ እንዲኖራቸው የቦታው ይዘት ጥራት (ስፓሻል ኳሊቲ) መሟላት ይኖርበታል። የሕንፃው ውበት፣ የእያንዳንዱ ክፍል ቁመት፣ ስፋትና ልኬት (ስኬል)፣ በቂ የአየር ዝውውር መኖሩ፣ በቂ የተፈጥሮ ፀሐይ ብርሃን መግባቱ፣ የግድግዳዎቹ ቀለማት ብሩህና አስደሳች መሆናቸው ወዘተ የተቋሙን ጥራት ከፍ ያደርጋሉ። ሕንፃው፣ ጊቢው እንዲሁም በአጠቃላይ አካባቢው ፈዋሽ ድባብ (ሂሊንግ ኢንቫሮመንት) እንዲኖረው ተደርጎ መነደፍ ይኖርበታል። ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ተፈጥሮን ማካተት ለዚህ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። እፅዋትና የውሃ አካላትን ማካተት ተመራጭ ነው። የአደገኛ ተህዋሲያን መራቢያ እንዳይሆኑ ግን በጥንቃቄ ኢንፌክሽን ፐሪቬንሽን ፕሮቶኮሉን ተከትሎ መሰራት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡– የእኛ ሆስፒታሎች መሠረታዊ ችግር ምንድነው?
አርክቴክት አብነት፡– በእኛ ሀገር በብዙዎቹ ነባር ሆስፒታሎችም ሆነ ክሊኒኮች ላይ ያለው ችግር የተጠቃሚው ቁጥር ከአቅማቸው በላይ መሆኑ ነው። ከአዳዲስ ግንባታና ዲዛይን ሥራ ጋር ተያይዞ የሚነሳው በእኔ አስተያየት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት አለመሟላት እንዲሁም ተናቦ አለመስራት ሌላው ችግር ነው።
አዲስ ዘመን፡– ሆስፒታሎችን በብዛት የሚሰራው መንግሥት ብቻ ነው ወይንስ የግል ባለሀብቶችም ተሳትፎ የጎላ ነው ?
አርክቴክት አብነት፡– የግል ባለሀብቶች፣ የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የእርዳታ ድርጅቶችም ሥራው ላይ ይሳተፉሉ።
አዲስ ዘመን፡– አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከማስተማሩ ጎን ለጎን ከዚሁ ከሆስፒታሎችና ከክሊኒኮች ጋር በተያያዘ በአሁን ሰዓት ምን እየሰሩ ነው ያሉት ?
አርክቴክት አብነት፡– አሁን ሁለት ሆስፒታሎች ሥራ ላይ እየተሳተፍኩ ነው። ሁለቱም አዲስ አበባ ውስጥ ናቸው። አንደኛው የእናቶችና የሕፃናት ሆስፒታል ነው። ሁለተኛው ደግሞ አጠቃላይ ሆስፒታል ነው።
አዲስ ዘመን፡– ከመምህርነቱም ባሻገር ከሆስፒታልና ክሊኒክ አንጻር በሄልዝ ኬር ፋሲሊቲ ዲዛይን ብዙ ዓመታት ሰርተዋል። በሀገራችን የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ምን መሰራት አለበት ብለው ያስባሉ ?
አርክቴክት አብነት፡– የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እድገት ቢያሳይም ብዙ ሥራም መሰራት ይኖርበታል። ይሄን ለማድረግ የሁላችንም አስተዋጽኦ ያስፈልጋል። እኔ በግሌ ብዙ መስራት ይጠበቅብኛል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን።
አርክቴክት አብነት ገዛኸኝ፡– እኔም እጅግ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 5/2013