ኃይሉ ሣህለድንግል
ሰላምና ደህንነት ለሰው ልጅ መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው። የዜጎችም የሀገርም ህልውና የሚቆመው ሰላምና ደህንነት ሲጠበቅ ብቻ ነው። ይህ እንዲሆን ሁላችንም እንፈልጋልን። ትክክል ነን። በተለይ እኛ በሰላምና ደህንነት እጦት ብዙ እንደማጣታችን ጥያቄው ተገቢና ወቅታዊም ነው። ሰላምና ደህነንት ካልተጠበቀ ሠርተን አንውልም፤ ያለንን መብላትም ሆነ መጠጣት አንችልም። በገነባነው ቤታችንና ባቀናነው ቀዬችን መኖርም አንችልም።
እዚህም እዚያም በሚቀሰቀስ ግጭት እና በሚሰነዘር ጥቃት ሳቢያ ንፁኋን ወገኖቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲጨፈጨፉ፤ የቅርብ ዘመዶቻቸው የተጎዱባቸው ወገኖች የሰላምን ፋይዳ አሳምረው ያውቁታል። በተመሳሳይ ስለሞቱትና ስለቆሰሉት በቂ መረጃው ያላቸው መላ ኢትዮጵያውያንም ዋጋውን በሚገባ ይገነዘቡታል። እናም ሰዎች መንግሥት የሕግ የበላይነት እንዲጠበቅ እንዲሠራ አጥብቀው ነጋ ጠባ መጠየቃቸው ትክክል ነው። የሕግ የበላይነት የሚጠበቀው እንዴትና በማን ነው? የሚለው ግን መታወቅ ይኖርበታል። መንግሥት ማለት ህዝብ ነው። ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። የሕግ የበላይነት እንዲጠበቅ መንግሥት እንዲሠራ ሲጠየቅ ይሄው ጥያቄ ለህዝብም ጭምር መሆኑ መታወቅ አለበት።
በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ሰላምና ደህንነትን እንዲያስጠብቅ የሚፈለገው በመንግሥት ብቻ ነው። ችግሩ ያለው እዚህ ላይ ነው። ህዝብም ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ማድረግ ይኖርበታል። ለመንግሥት የቤት ሥራ ሰጥቶ ቆሞ ወይም ተቀምጦ መጠበቅ የለበትም። ለመንግሥት መረጃ በመስጠት፣ በየአካባቢው ተደራጅቶ ሰላሙን በማስጠበቅ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። መንግሥትን በጠየቅን ቁጥር የእኛን ድርሻም ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ህዝቡ ሚናው በግልጽ በታወቀ ጊዜ መረጃ በመስጠት፤ ፀረ ሰላም ሃይሎችን በማጋለጥ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል።
መንግሥት ከዚህም በላይ ከህዝብ ሊፈልግ ይችላል። የፋይናንስ የቁሳቁስ ድጋፎች የሚያስፈልጉበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። እነዚህን ሁሉ ለማድረግ በተግባር የሚታይ ዝግጁነትና ፈቃደኝነቱ ከሌለ ግን መንግሥትን ‹‹የሕግ የበላይትን አስከብር›› ብሎ መጠየቅ በቅሎ ግዙ ግዙ አንድ አሞሌ ላይገዙ ይሆናል ነገሩ።
ከወራት በፊት በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ አንዳንድ ድርጅቶች፣ ክልሎች የመንግሥትን እርምጃ እንደሚደግፉ በመግለጫና በመሳሰለው ሁሉ ማረጋገጫ ከመስጠታቸው በተጨማሪ ለሰብአዊ አገልግሎት የሚውል የፋይናንስና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ። የራስን ድርሻ መወጣት ማለት ይሄ ነው። በክልሉ ለሕግ ማስከበሩ፣ ለሰብአዊ ድጋፉ፣ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባቱ ሥራ ምን ያህል ሀብት እንደሚያስፈልግ መገመት አይከብደም። ህዝቡ መንግሥት የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር ያቀርብ ከነበረው ጥያቄ አንፃር ሲታይ ግን ድጋፉ ገና ይቀራል ባይ ነኝ። መንግሥት የሕግ የበላይነት እንዲከበር ስንጠይቅ፣ ከእኛ የሚጠበቀውንም እያሟላን ነውን ብለን ራሳችንን እንጠይቅ።
በአዲስ አበባ ዝርፊያ በርክቷል፤ ለዚያውም የተደራጀ ዘረፋ። የሰዎች ንብረት ብቻ ሳይሆን ህይወትም ጭምር በዘራፊዎች እየተቀማ ነው። ፖሊስ ይህን ችግር ይፍታልን የሚሉ ጥያቄዎች ይሰነዘራሉ። ተገቢ ጥያቄዎች ናቸው። ፖሊስ መረጃ ሲጠይቅ ግን መተባበሩ የለም፤ ወንጀል ሲፈፀም ነገ በእኔ ማለቱ ቀርቶ እያዩ ማለፍ ተለምዷል። ይህም ከእኛ በእጅጉ የጎደለ እንዳለ ያመለክታል። ድርሻችንን እየተወጣን አይደለም። ለምን የሚለው መመለስ አለበት።
መንግሥት ሕግ የሚያስከብረው፣ መሰረተ ልማት የሚገነባው ወዘተ… ሀብት እንደ ቅጠል እየሸመጠጠ ወይም በአስማት እያገኘ አይደለም። ከህዝብ የሚሰበሰበውን ገቢ እያብቃቃ ፣ ወደፊት ሠርተን እንከፍላለን በሚል ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማትና ከሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት እየተበደረና ዕርዳታ ጭምር እየተቀበለ ነው።
በአገራችን የሚሰበሰበው ግብር ከዓመት ዓመት እየጨመረ መጥቷል። ይህ ትልቅ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደተናሩት፤ አገሪቱ በ2010 በጀት ዓመት 176 ነጥብ9 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስባለች። በ2011 በጀት ዓመት ደግሞ 196 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል። በ2012 ደግሞ 228 ነጥብ ቢሊዮን 9 ብር ገቢ ተሰብስቧል፤ በተያዘው 2013 በጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 191 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል።
‹‹ይህ የሚታይ ዕድገት ነው፤ ግን በቂ አይደለም።›› ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበው፣ የኢትዮጵያ ገቢ ማስገባት ከሚገባው አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑንም ገልፀዋል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም እየተሰበሰበ ያለው ገቢ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ጋር ሲነፃፀር ብዙ የሚባል አለመሆኑን በመጥቀስ ይህንኑ ሲያጠናክሩ ነው የሚደመጠው።
ገቢው ለምን የሚጠበቀውን ያህል ሊሆን አልቻለም? አገራችን ግብር በመክፈል በኩል ለረጅም ዓመታት ተጠቃሽ የሆኑት የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው። የተቀረው የሕብረተሰብ ክፍል ግን ግብር በአግባቡ አይከፍልም፤ እረ ጨርሶ የማይከፍልም ሞልቷል። አንዳንዱ ገቢውን አያሳውቅም፣ የሚያሳውቀውም ትክክለኛውን ገቢ አያሳውቅም። በዚህ ላይ ያለ ንግድ ፈቃድ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት በአየር በአየር ነጋዴዎች ይንቀሳቀሳል። እነዚህ ሃላፊነታቸውን ያልተወጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መንግሥት ልማት እንዲያፋጥንላቸው አጥብቀው ይጠይቃሉ። ለመሆኑ መስጠትን መለገስን የማያውቅ አምጡ ማለትን ማን አስተማረው ነው የሚባለው፤ አባባሉን በአግባቡ አላልኩት ሊሆን ይችላል፤ ሀሳቡን ብቻ ተረዱልኝ።
እንደሚታወቀው አገራችን በአሁኑ ወቅት ሥር በሰደደ የኑሮ ውድነት ውስጥ ትገኛለች። በዚህ ላይ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ሕግ ማስከበር ተከትሎ እየቀረበ ያለው ሰብአዊ ድጋፍ፣ በጁንታው የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መጠገን፣ ወዘተ ብዙ ሀብት የሚፈልጉ ናቸው። የኑሮ ውድነቱ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በሚል ለመሰረታዊ ፍጆታዎች አቅርቦት ሀብት መመደብ ያስፈልጋል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የነዳጅ፣ የስንዴና የመሳሰሉት ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። ለአገራችን ይህን ሁሉ መሸከም ከባድ ነው።
በእዚህ መተዛዘን መተሳሰብ በሚያስፈልግበት ወቅት የኑሮ ውድነቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዋጋ አለአግባብ በአናት በአናቱ በመጨመር ለመክበር የሚሯሯጡ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። እነዚህ ሀብት የሚገኘው ሀገር ስትለማ ወይ ስትደማ ነው በሚል ፈሊጥ የሚመሩ ስግብግቦች አገር እየደማች ባለችበት በዚህ ወቅት በመጋዘን ባከማቹት ሸቀጥ ላይ ጭምር ዋጋ እየጨመሩ ህዝብ ያስለቅሳሉ፡ ፡
ይህን ሁሉ ችግር ለማለፍ ሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት ያስፈልጋታል። አንዱ በእጃችን ያለው ሀብት ማግኛው መንገድ ግብር መሰብሰብ ነው። ግብር በአግባቡ የሚከፍሉ ይህንኑ ማጠናከር፣ በአግባቡ የማይከፍሉት በአግባቡ መክፍል እንዲሁም ጨርሶ የማይከፍሉትም በእዚህ ወሳኝ ወቅት ወደ ግብር መረቡ ውስጥ በመግባት ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው። ሁሉም ይህን ሃላፊነታቸውን መወጣት ሲችሉ ነው መንግሥት ሊያደርግላቸው የሚፈልጉትን መጠየቅ ያለባቸው ሃላፊነትን ሳይወጡ መንግሥትን መጠየቅ አይገባም።
መንግሥት በርካታ ግዙፍ ሥራዎች ላይ ተጠምዷል። በዚህ ወቅት እንደ ግለሰብም ይሁን እንደ ማህበረሰብ የሚጠበቅብንን ብቻ ሳይሆን ከሚጠበቅብንም በላይ በመፈፀም መንግሥት እያካሄደ ያለው የለውጥ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን በሁሉም መስኩ መደገፍ ይጠበቅብናል እንጂ ከመንግሥት ብዙ መፈለግ የለብንም። መንግሥትን ስንጠይቅ እኛንም እየጠየቅን መሆኑን እናስተውል። የሰላምም ሆነ የኢኮኖሚ የትኛውም ጥያቄ ከተወሰነ ቡድን ወይም ከተወሰኑ ግለሰቦች ጋር ብቻ የተጣበቀ አይደለም። የሁሉም ሃላፊነትን የመወጣት ተግባር ካልታከለበት መንግሥት ሰላም አላሰፈነም፤ መንግሥት ኢኮኖሚውን አላሳደገም፤ መንግሥት የኑሮ ውድነትን ይቆጣጠርልን ማለት ብቻ መፍትሔ አያመጣም። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 5/2013