ሰሞኑን ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው ኪንሻሳ ያደረጉት ድርድር ያለስኬት ተበትኗል። ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው ግብጽና ሱዳን የአባይን ውሃ ፍትሐዊ አጠቃቀም አለመቀበላቸውና ውሃውን እኛ ብቻ እንጠቀም የሚል ግትር አቋም በመያዛቸው እንደሆነ ነው። ይህም ግላዊ አስተሳሰብ በአባይ ውሃ ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ የሚደረገውን ድርድር አዳጋች እያደረገው እንደሚገኝ ጥርጥር የለውም። የአሁኑን ድርድር ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ በርካታ ድርድሮች ቢደረጉም በፍትሐዊ ተጠቃሚነት የማያምኑት ግብጽና ሱዳን ከስምምነት ለመድረስ ተቸግረዋል።
ግብፅና ሱዳን ይህንኑ “ፍትሐዊ ተጠቃሚነት”ን በመጥላትና በመሸሽ ድርድሩ ውሳኔ ላይ እንዳይደርስና ኢትዮጵያ 86 በመቶ በሆነው ሃብቷ ላይ ልማት እንዳታለማ እንቅፋት በመፍጠር ላይ መጠመዳቸው ከሰሞኑ በኪንሻሳ የተካሄደው ድርድር መቋረጥ አንዱ አመላካች ማሳያ ይሆናል። ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ዳግም እድል አልነፈገቻቸውም፡፡ ሁለቱ ሃገራት ከመጪው ክረምት የውሃ ሙሌት አስቀድመው መረጃ ለመለዋወጥ ባለሙያዎቻቸውን እንዲልኩ ጠይቃለች፡፡
ግብፅ የኢ-ፍትሐዊነት አቀንቃኝ፤ የፍትሐዊነት ተቀናቃኝ በመሆን ያዙኝ ልቀቁኝ ስትል ይህ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያዋ አይደለም። ገና ከአፄ ዘርአያእቆብ (1426-1460) ጀምሮ ከቀይ ባህርና አባይ ወንዝ አካባቢ ኢትዮጵያን ለመንቀልና ራሷንና አጃቢዎቿን ብቻ የአባይ ተጠቃሚ ለማድረግ ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም። የዚህ ሁሉ መነሻው ደግሞ ልክ እንደዛሬው ሁሉ አባይ ወንዝና አጠቃቀሙን አስመልክቶ የተወሰነው የቅኝ ገዥዎች ፍርደ-ገምድል ውሳኔ ነው።
እነዛ ፍርደ-ገምድልነት ውሳኔዎች ኢትዮጵያን ከጨዋታ ውጪ ያደረጉ ነበሩ። እነዚህ የቅኝ ግዛት ውሎች እጅግ አድሏዊ፣ ፍትሐዊነት፣ ምክንያታዊነትና እኩል ተጠቃሚነትን ፍፁም ያላገናዘቡ ሲሆን፤ ውሀውን በመቶኛ ሲያከፋፍሉ ለትነት ሁሉ 10 በመቶ ሰጥተው ለኢትዮጵያ ግን ዜሮን ያስታቀፉ ውሎች እንደነበሩ ታሪክ መዝግቦ ይዞታል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ያንን ሁሉ ከምንም ባለመቁጠር፣ የደረሰባትን ግፍና በደል በመሰረዝ የነበረውን ፍርደ-ገምድልነት ወደ ፍትሐዊ የውሀ ተጠቃሚነት ፊቱን በማዞር ሁሉንም ባካተተ መልኩ ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ እየሰራች ትገኛለች። አሁንም ሆነ ወደፊት የኢትዮጵያ አቋም ይኸው ሲሆን፤ ከዚህ ሌላ ማንንም በመጉዳት ማንንም መጥቀም የምትፈልግ አገር አይደለችም። ይህ ደግሞ የውጪ ግንኙነት ስራዋን አንድ ብላ ከጀመረችበት ዘመን ጀምሮ የነበራት የዲፕሎማቲክ እሴት ሲሆን ወደ ፊትም በዚሁ እንደምትቀጥል አያያዟ ብቻ ሳይሆን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ሰማኒያ ስድስት በመቶ ድርሻውን ከኢትዮጵያ የሚይዘው አባይ ወንዝ አንድ ሶስተኛ የአገሪቱን ቆዳ ስፋት፣ ስድስት ክልሎችን፣ በእነዚህ ቦታዎችም 50 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርና ህይወታቸውም በእሱው ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ባጠቃላይ የ90 ሚሊዮን ሕዝብን ህይወት በቀጥታ የሚነካ መሆኑ በተደጋጋሚ ጥናቶች የተረጋገጠ መሆኑ ከታወቀ ሰንብቷል። ግብፅም ይህንን አሳምራ ታውቃለች። ይሁን እንጂ የ”ፍትሐዊ ተጠቃሚነት” ጉዳይ ሲነሳ እንደምንግዜውም ሁሉ ዛሬም ፊቷን ከማዞር የታቀበችበት አንዳችም ጊዜ የለም።
በግብፅ በኩል “አገራዊ ጥቅም” የሚባለው መሰረታዊ ጉዳይ ሲነሳ ይሰማል። ግብፅ ብሔራዊ ጥቅሜ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብቴ ተነካ ትበል እንጂ ከአባይ ወንዝና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ አንድም የተነካባት ብሄራዊ ጥቅም እንደሌለ እራሷ ግብፅን ጨምሮ ሁሉም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያውቀዋል።
የህዳሴ ግድባችን የተፋሰሱ አገራትን በፍትሐዊነት መርህ የሚያስተሳስር መቀነት፤ በኢትዮጵያ ላይ ለዘመናት ተጥሎ የነበረውን የኢ-ፍትሐዊነት ቀንበር የሚሰብር እና ሌሎች የተፋሰሱ አገራትንም ነፃ ከማውጣት ባሻገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በአህጉራችንና በኢትዮጵያ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ብሔራዊ ምልክት እንደሆነ የሚነገርለት ፕሮጀክት ነው። በአሁኑ ሰዓትም ግንባታው 80 በመቶ የደረሰው ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ከፅንሱ ጀምሮ እስከ ወዲያኛው ድረስ ፍትሐዊ የውሀ ሀብት ክፍፍልን ታሳቢና መሰረት ያደረገ እንደሆነ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። አሁንም ግብፅና ሱዳን በፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም ላይ ስምምነት ለመድረስ ጊዜው ያልረፈደባቸው እንደሆነ አምነው የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ሊሳተፉ ይገባል። ነገር ግን “ፍትሐዊ ተጠቃሚነት” ምንግዜም የማይናወጥ የኢትዮጵያ አቋም በመሆኑ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይሆንም።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 5/2013