በተወዳጁ እግር ኳስ የዝውውር ገበያ ሰሞን ክለቦች ውጤታማ ያደርጉናል ብለው የሚያስቧቸውን ተጫዋቾች የግላቸው ለማድረግ ይውተረተራሉ። የእግር ኳስ ደላሎች ( ወኪሎች) ሥራ ይበዛባቸዋል። ከአንዱ ክለብ ወደሌላው ለሚዘዋወሩ ወይም በነበሩበት መቆየት ለሚፈልጉት ተጫዋቾቻቸው የተለያዩ ድርድሮችን ያካሂዳሉ፡፡በትውልድ ጣልያናዊ በዜግነት ሆላንዳዊ የሆነው ካርማይን ሚኖ ራዮላ በዝውውር ገበያው መከፈት ሥራ ከሚበዛባቸው ወኪሎች ዋነኛው ነው።
ለተለያዩ ክለቦች ወኪል በመሆን ጥቅማቸውን የሚያስጠብቀውና ከእያንዳንዳቸው ዝውውርም ጠቀም ያለ ኮሚሽን የሚቀበለው ይህ ሰው የተወለደው እ.ኤ.አ ህዳር ወር፣ 1967 በጣልያን ደቡባዊ ክፍል ናሲዮና ኢንፍሮሬ ሳሌርኖ ከተማ ነው፡፡
ውልደቱ ጣሊያን ቢሆንም ያደገው ሆላንድ ነው፡፡ ከቤተሰቦቹ ጋር ጣሊያንን የለቀቀውም ገና የአንድ ዓመት ልጅ እያለ ሲሆን ከልጅነት እስከ አዋቂነት ያለው የህይወት ጉዞውን ያሳለፈው በሆላንዷ ሃርለም ከተማ ነው፡፡
የራዮላ አባት ነጋዴና የጣልያንን ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች የሚያቀርብ ታዋቂ ሬስቶራንት ባለቤት ሲሆን ከትምህርት ቤት መልስ ሬስቶራንት ውስጥ በአስተናጋጅነት እየሰራ ፤ አልፎ አልፎ በሚያገኘው የዕረፍት ጊዜም እግር ኳስ ይጫወት ነበር፡፡
አፈ ጮሌ እንደሆነ የሚነገርለት ራዮላ፤ ከልጅነቱ አንስቶ ለእግር ኳስ ልዩ ፍቅር ነበረው፡፡ ፍቅርም ብቻ ሳይሆን በሚኖርበት ከተማ ለሚገኘው ሃርለም እግር ኳስ ክለብም ለመጫወት በቅቷል።
እ.ኤ.አ 1987 እግር ኳስ ተጫዋችነቱን በመተው ወደ አመራርነት ወንበር የመጣው ሰው፤ በክለብ ውስጥ በተጫዋችነት፣ በቦርድ አባልነትና በተለያዩ የአስተዳደር ሥራዎች መስራቱም ከእግር ኳስ ጋር በደንብ እንዲተዋወቅ አስችሎታል።
ክለቡን ከለቀቀ በኋላም፤ በአንድ የእግር ኳስ ኤጀንት ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ በመስራት ተዋቂ ተጫዋቾችን ወደተለያዩ ክለቦች እንዲዘዋወሩ ማድረግ ችሏል።ከእነዚህ ውስጥም ስመጥር የሆላንድ ተጫዋቾች ብዙውን ቁጥር ወስደዋል።አብዛኞቹን ያዘዋወራቸው ወደ ጣልያን ክለቦች ሲሆን ከመካከላቸውም አርሰናልን ከመቀላቀሉ በፊት ለጣልያኑ ኢንተርሚላን የተጫወተው የብርቱካናማዎቹ ኮከብ ዴኒስ ቤርካምፕ ይገኝበታል፡፡
የኒውካስልም ሆነ የአርሰናል ደጋፊዎች ከማይረሱት ከዚህ ድንቅ ተጫዋች ባሻገር አሌክስ፤ ብርያን ሮይ፣ ማርሲያኖ ቪንክ፣ ዊም ጆንክና ሚሼል ክሪክ የተባሉ ኮከብ ተጫዋቾች እ.ኤ.አ ከ1992 እስከ 94 ድረስ በራዮላ ደላላነት ከሆላንድ ወጥተው በጣልያን ለሚገኙ የተለያዩ ክለቦች ፈርመዋል።
በዝውውር ገበያው የወኪልነት ተሳትፎ የሰመረለት ራዮላ በሃያ ዓመት ዕድሜው ተቀጥሮ ከሚሰራበት ድርጅት በመውጣት የራሱን ኤጀንሲ የከፈተ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘዋወረው ተጫዋች ደግሞ በ1990ዎቹ መጨረሻ ገናና የነበረውን የቼክ ብሔራዊ ቡድን የመሃል ሜዳ ሞተር የነበረውን ፓቬል ኔድቬድ ነው።
ቼክ ሪፐብሊክ እ.ኤ.አ በ1996 በተደረገው የአውሮፓ ዋንጫ መድረክ በአስገራሚ ብቃት ለፍፃሜ ብትደርስም 2 ለ1 በሆነ ውጤት በጀርመን ተሸንፋ በወርቃማ ግብ ጦስ ዋንጫውን ብትነጠቅም በመድረኩ ተሳትፎዋ ከሁሉ በላይ ኮከብ ልጇን አሳይታበታለች።
በአገሪቱ የአውሮፓ ፍልሚያ እስከ ፍጻሜው መድረስ ድንቅ ሚና ሲጫወት የነበረው ፓቬል ኔድቬድም፤ ከመድረኩ ፍልሚያ መቋጨት በኋላ፤ የበርካታ ክለቦችን ዓይን ያማለለ ተጫዋች እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ ከክለቡ ስፓርታፕራግ ኮብልሎ ለጣልያኑ ላዚዮ እንዲፈርም ማድረግም ችሏል።
ራዮላ በተለይ በሆላንዱ የኮከቦች መፍለቂያ ክለብ በሆነው በአያክስ አምስተርዳም በድንቅ እግር ኳሳዊ ችሎታ የተካኑ ወጣት ኮከቦችን አድኖ ወኪላቸው በመሆን በታላቅነት ዙፋን ላይ አስቀምጧቸዋል። ወክሎ ለዓለም ካስተዋወቃቸውና ተመልካችን ከመቀመጫው ከፍ ዝቅ በማድረግ ምትሃታዊ ችሎታ ከተካኑ ተጫዋቾች መካከልም ስዊድናዊው ዝላታን ኢብራሂሞቪች ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው።
ዝላታን ከአያክስ አምስተርዳም ወደ ጁቬንቱስ ያዘዋወረው ራዮላ ሲሆን፤ በወቅቱ ስኬታማ የተባለው የዚህ ስምምነት የዝውውር ዋጋም 16 ሚሊዮን ዩሮ ነበር፡፡ በጁቬንቱስ ምርጥ ብቃቱን ያሳየው ዝላታን ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ኢንተርሚላንን ከዚያም ወደ ስፔን በማምራት እ.ኤ.አ በ2009 የካታላኑን ባርሴሎና ሲቀላቀል፤ኤሲሚላንና ፓሪስ ሴንት ዠርሜን ማንቸስተር ዩናይትድ ሲዘዋወር የወኪሉ ድንቅ የአደራዳሪነትና የማሳመን ብቃት ሚና ገዝፎ ታይቷል።
ሚኖ ራዮላ ከዝላታን ኢብራሂሞቪች በተጨማሪ ኤሲ ሚላንን በተቀላቀሉ 5 ተጫዋቾች ዝውውር ውስጥ እጁ አለበት፡፡ብራዚላዊውን የቀድሞ የሪያል ማድሪድ፤የማንቸስተር ሲቲ፤ኮከብ ሮቢንሆ፣እንዲሁም ሆላንዳዊውንም ማርክ ቫንቦሜል የመሳሰሉ ኮከቦች የሮስነሪዎቹን የተቀላቀሉት በራዮላ አደራዳሪነት ነው፡ ፡
አፉን የፈታው በደች ቋንቋ ቢሆንም ከዚያ በተጨማሪ ሰባት አይነት ቋንቋን ይናገራል።ጣሊያን፤ እንግሊዝ፤ ጀርመን ስፔን ፈረንሳይ ፖርቹጋል እንዲሁም የደች ቋንቋን ያቀላጥፋል።ይህም በቀላሉ ለመግባባት ረድቶታል።
ከዓለማችን ኮከቦች የዝውውር ሂደት ጀርባ ስሙ የሚነሳው ራዮላ፤ በወኪልነት ብቃቱ የሚያደንቁትን ያህል የሚጠሉትም በርካታ ናቸው።በተለይ በቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከሚጠሉ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ ምናልባትም በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ የግል ታሪካቸውን በሰነዱበት መጽሐፍ ወኪሉን በእጅጉ ወቅሰውታል። ምክንያቱ ደግሞ ፖል ፖግባ ነው።የፖግባ ወኪል የሆነው ራዮላ ወጣቱን ፈረንሳያዊ እ.ኤ.አ በ2012 ከኦልትራፎርድ አስኮብልሎ ከጁቬንቱስ የቀላቀለው እሱ ነው፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት ፖል ፖግባ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሲመለስ የዓለም ክብረ ወሰን ለመሆን በተቃረበ የዝውውር ሂሳብ ለተጫዋቹ 105 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ በማስደረግ፤ ከዚህም ክፍያ ላይ 25 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ኪሱ ማስገባቱም ይነገርለታል።
ራዮላ በአሁኑ ወቅት ብቻ በተለያዩ የአውሮፓ ሊግ ውስጥ የሚጫወቱ ከ20 በላይ ተጫዋቾችን በወኪልነት ያገለግላል። ከመካከላቸውም የቀያይ ሳይጣኖቹ ኮከቦች ፖል ፖግባና ሮሜሎ ሉካኩ፣ የፒኤስጂው ብሌስ ሚቲውዲና የሊቨርፑሉ ድንቅ ግብ ጠባቂ ጅያንሉጂ ዶናሩማ የአርሰናሉ ሀነሪክ ሚኪቴሪያን፤ማሪዮ ፓላቶሊ ይገኙበታል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011
በታምራት ተስፋዬ