ታምራት ተስፋዬ
የስነ-ህንጻ ተመራማሪዎች ማርስ ላይ የመጀመሪያ ጊዜ ለህይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በሙሉ የተሟሉለትን ከተማ ግንባታ ዕቅድ ይፋ አድርገዋል። እቅዱን ይፋ ያደረገውም የስነ-ህንጻ ምርምር ድርጅቱ አቢቦ መሆኑም ታውቃል፡
በቀያ ፕላኔት ላይ ይገነባሉ ከተባሉ አምስት ከተሞች መካከል ኑዋ ዋና መዲና እንደምትሆን ተገልጿል። ኑዋ የሚል መጠሪያ ስያሜ ያገኘውም በቻይና ከሚነገሩ ተረቶች በአንዱ አምስት ድንጋዮችን በማቅለጥ ጠንካራ ምሰሶ ያለው ቤት ከሰራው ጣኦት ስም እንደሆነ ተነግሯል።
የከባቢ ጫና እና ጨረርን ለመከላከልም የግንባታው ስራ ከተለመደው ለየት እንደሚል ታውቋል። ከተማውም 250ሺ ሰዎችን ማኖር ያስችላል። ከምድር በተመሳሳይ የመኖሪያ መንደሩ አስፈላጊ የሚባሉ እንደ ቢሮ፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት፣ የገበያ ስፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችና የአረንጋዴ ስፍራ፣ ዩኒቨርሲቲ፣ የባቡር ጣቢያ የተሟሉለት ነው።
በከተማው የሚገነቡት ቤቶች ከ25 እስከ 35 ስኩየር ሜትር ስፋት ይኖራቸዋል። በመኖሪያ መንደሮቹም ሆነ ከከተማ ወደ ከተማ ለመንቀሳቀስ ፈጣን አሳንሰሮች፣ ቀላል ባቡሮችና አውቶብሶች ትራንስፖርት እንደሚዘረጉ ታውቃል።
ተራራማ አካባቢዎችም ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለምግብ ማምረቻ እንዲሁም ለሃይል አቅርቦት ጣቢያ ግንባታ የተለዩ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ እነዚህ ቦታዎችም ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የቁጥጥር ስራው የሚከናወነው በሮቦቶች ይሆናል››ተብሏል። በሸለቆማ ቦታዎች የግብርና ስራ እንዲሁም በእንስሳት አሳማ፣ ዶሮ እና አሳ እርባታ ምቹ ይደረጋል። ይሑንና እንስሳቱ ማርባት እንጂ መብላት አይቻልም ተብላል።
ሰዎች እንዴት ሊሄዱ ይችላሉ የሚለውም በግልፅ መስፈርት እና ግዴታ ወጥቶለታል። አንድ ሰው ወደማርስ ለጉብኝት ለመሔድ ይችላል። ይሁንና ከፍተኛ ብር ሊኖረው የግድ ይላል። ሶስት መቶ ሺህ ዶላር መክፈል ግድ ይለዋል። ጉዞውም ከአንድ እስከ ሶስት ወር ሊዘልቅ እንደሚች ታውቋል። በዚያ የሚኖሩ ሰዎችም ከ60 እስከ ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን የስራ ሰዓታቸውን የሚያሳልፉት በከተማዋ በሚሰጥ ስራ እንደሆነ ተነግሯል።
በማርስ ለመኖር በዋናነት ራስን ከአደገኛ ጨረር ለመጠበቅ የሚያስችል መከላከያ የሚያስፈልግ መሆኑን ያስታወሰው ከዚህ በተጨማሪም ሁሉንም ምግብ ከምድር መውሰድ ስለማይቻል ማርስ ላይ የምግብ ሰብሎችን ለማምረት የሚያስችል ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበትም እምነቱን ገልጧል።
እነዚህን ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ለመቅረፍም ተቋሙ ከማርስ ሶሳይቲ እና ሶኔት ኔትወርክ ከተባለ የምሁራን ስብስብ ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን አሳውቋል። ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ የተመራማሪዎቹ ስብስቡ ቴምፔ ሜንሳ የተባለ የማርስ አካባቢን ለይተዋል ተብላል። የስነ-ህንጻ ምርምር ድርጅቱ አቢቦ መስራች አልፍሬዶ ሙኖዝ፣ በእቅዱ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮችን ሁሉ መፍትሄዎችም ከሳይንቲስቶች ጋር በቅርበት እየሰራን ነው ሲሉ ለዮሮ ኒውስ. ተናግረዋል።
የማርስ ላይ ከተማ ግንባታ እኤአ በ2054 እውን ይሆናል የሚል ግምት ተሰምቷል። ለዚህ ግምት ማረጋገጫ የሚሰጥ አካል ባይመጣም፣ ፕሮጀክቱ ግን እኤአ እስከ 2100 እንደማይቆይ በርካቶች ጥርጥር የለንም ሲሉ ተደምጠዋል።
በርካታ አገራት እና ስመጥር ግለሰቦችበ ብሎም ባለፀጎች ካርል ሳገን፣ ሮበርት ዙብሪን እንዲሁም የስፔስ ኤክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤለን ማስ በቀያ ፕላኔት ላይ የሰው ልጅን ስለማስፈር እና ከተማ መገንባት ቋምጠዋል። ምኞታቸው እውን እንዲሆንም በየፊናቸው መትጋትን አላቋረጡም። መረጃውን ለማጠናቀር ዴይሊ ሜል እና ያሆ ኢንተርቴመንት ኒውስን ተጠቅመናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2013