የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት መርሐግብር በሳምንቱ የእረፍት ቀናትም በተለያዩ ከተሞች ተካሂዷል። ሳምንቱ የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከወላይታ ድቻ አገናኝቷል። ሶዶ ላይ የተካሄደውን ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች አሸንፈዋል። ድቻዎች ጨዋታውን ሁለት ለባዶ ያሸነፉ ሲሆን፣ የባለሜዳዎቹን የማሸነፊያ ግቦችም ቸርነት ጉግሳና ፀጋዬ አበራ አስቆጥረዋል።
ከዚህ ጨዋታ ቀድሞ ለዘጠኝ ተከታታይ ጨዋታዎች ያለድል የተጓዙት ድቻዎች ፈረሰኞቹ ላይ ያስመዘገቡትን ውጤት ተከትሎ ደረጃቸውን ማሻሻል ችለዋል። ተሸናፊው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ መሪነቱን ለማስጠበቅ የሚያስችለው ውጤት ከመነጠቅ ባለፈ መሪነቱን ለሲዳማ ቡና አሳልፈው ለመስጠት ተገደዋል። በውጤቱም ፈረሰኞቹ የመጀመሪያውን ዙር የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር 26 ነጥብ ይዘው እንዲቋጩ ግድ ብሏቸዋል። ዛሬ ጨዋታውን የሚያደርገው መቀሌ ድሬዳዋን ማሸነፍ ከቻለም ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሶስተኛ ደረጃ የሚወርድበት ሁኔታ ይፈጠራል።
በሌላ የሳምንቱ መርሀ ግብር በሊጉ የደረጃ ግርጌ የሚገኘው ደደቢት ከሃዋሳ ከተማ ጋር ተጫውቷል። በትግራይ ስታዲየም በተካሄደው በዚህ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ሽንፈት ተጠናቋል። በሜዳቸው የሚያሳዩትን አቋምና አቅም ከሜዳቸው ውጪ ለማድረግ ሲቸገሩ የሚስተዋሉት ሃዋሳዎች ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ መቀሌ ተጉዘው አንድ ለባዶ በማሸነፍ ሦስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል። ደስታ ዮሐንስ የግቧ ባለቤት ሆኗል። በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር መርሃ ግብር ሁሉንም ጨዋታዎች የተጫወቱት ሃዋሳዎች ነጥባቸውን 24 በማድረግ አንደኛውን ዙር አጠናቀዋል።
ደደቢቶች በአንፃሩ የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ እጅጉን ክብዷቸዋል። በተለይ በሜዳቸው ከሚያደርጓቸው ጨዋታዎች እንኳን ነጥብ ማግኘት አለመቻላቸው እስካሁን ያሸነፉት ጨዋታ ብዛትም አንድ ብቻ መሆኑ የክለቡን የሊግ ቆይታ አጠራጣሪ እንዲሆን አድርጎታል።
ሌላኛው ጨዋታ ባህርዳር ከተማን ከአዳማ ከተማ አገናኝቷል። በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የተካሄደው ይህ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ፍፃሜውን አግኝቷል። አዳማ በዘንድሮ የሊግ ውድድር ደካማ ሆኖ የታየበትን የግብ ማግባት ድክመት በዚህ ጨዋታም ማሻሻል አልሆን ብሎት ታይታል። አዳማ ከተማም ሙሉ አስራ አምስት ጨዋታዎችን በማድረግ 21 ነጥቦችን ማግኘት ችሏል።
ሊጉ ትላንትም ቀጥሎ ውሏል፡፡ ፋሲል ከነማ ከስሁል ሽረ ተገናኝተዋል። በፋሲለደስ ስታዲየም፤ የተካሄደው ይህን ጨዋታ ባለሜዳው ፋሲል ከነማ ሶስት ለዜሮ አሽንፏል።ለአፄዎቹ ሱራፌል ዳኛቸው ሁለት ግቦች ሲያስቆጥር ኢዙ አዙካ ተጨማሪዋን ግብ ከመረብ አዋህዷል።
ያለፉትን ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ከመጋራት ባለፈ አሸናፊ መሆን ያልቻሉት አፄዎቹ፤ ከዚህ ጨዋታ ቀድሞ በሜዳቸው አዳማ ከተማን አስተናግደው በርካታ የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታውን ያለምንም ግብ መጨረሳቸው ይታወሳል።
በዘንድሮው የሊጉ መርሃ ግብር 14 ጨዋታዎች ያደረጉትና እስካሁን በሜዳቸው ሽንፈት ያልደረሰባቸው አጼዎቹ ዘንድሮ ጎንደር ላይ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ሦስቱን በድል ሲያጠናቅቁ በቀሪዎቹ ሦስቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
ከመቐለ ጋር በነበረው ተስተካካይ ጨዋታ ሽንፈትማስተናገዳቸውም ወደ መሪነቱ አናት እንዳይጠጉ ሁነኛ ዋጋ ያስከፈላቸው አፄዎቹ፤ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀራቸው ሲሆን፣ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ የሚችሉ ከሆነም ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ ይችላሉ።
ከባህርዳር ሽንፈት መልስ አፄዎቹን የገጠሙትና በተለይም በሊጉ ሰንጠረዥ በወራጅ ቀጣና ውስጥ የተቀመጡት ስሁል ሽረዎች የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳትፏቸው የሊጉ ደረጃ አጋማሽ ላይ መቀመጥ ግድ ብሏቸዋል።
በሌላ ጨዋታ ደቡብ ፖሊስ ከጅማ አባጅፋር በሃዋሳ ስታዲየም ተገናኝተዋል። ደቡብ ፖሊሶች ጨዋታውን ስድስት ለአንድ አሸንፏል። ባሳልፈነው ሳምንት አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን በማሰናበት በቀድሞ ተጫዋች አላዛር መለሰ እየተመሩ ወደ አሸናፊነት የመጡት ደቡብ ፖሊሶች አሁን ደግሞ በዋና አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እየተመሩ አሸናፊነትን ማስቀጠል ችለዋል።
በጨዋታው ለደቡብ ፖሊስ የተሻ ግዛውና፤ ሄኖክ አየለ እና ዘላለም ኢሳያስ እያንዳንዳቸው ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥሩ የጅማ አባጅፋርን ግብ አስቻለው ግርማ ማስቆጠሩን የሶከር ኢትዮጵያ መረጃ አመላክቷል።
ሜዳው ላይ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ አስገራሚ በነበረ 3 ለ3 ውጤት ጨዋታውን የፈፀመው የዓምናው የሊጉ ሻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር ያስመዘገበው ውጤትለጅማ አባጅፋሮች በታሪኩ መሪር ሽንፈት ያስተናገደበት ጨዋታ ሆኖ ተመዝገቧል።
አባ ጅፋር እስካሁን ከሜዳው ውጪ ስድስት ጨዋታዎችን ሲያደርግ በሁለቱ ሽንፈት በሁለቱ ደግሞ የአቻ ውጤቶች ሲገጥሙት በመጀመሪያው እና በመጨረሻው ጨዋታዎቹ ግን በድል መመለስ ችለዋል። በዘንድሮው የሊግ ውድድር ትንሽ ጨዋታ ያደረገው ጅማ አባጅፋር አራት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ይሆናል።
ጅማ አባጅፋር ምንም እንኳን በዘንድሮው የሊጉ ተሳትፎው ደካማ አቋም እያሳየ ቢገኝም፤ባሳልፈነው ዓመት ሊጉን በተቀላቀለ የመጀመሪያ ዓመት ድንቅ አቋም በማሳየት በመጀመሪያ ተሳትፎው የመጀመሪያ የሊግ ድሉን መቋደሱ አይዘነጋም።
በሌላ ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ከሲዳማ ቡና ተጫውተዋል። በትግራይ ስታዲየም፤ በተካሄደው ይህ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል። በተስተካካይ መርሐ ግብር ድቻን በመርታት አራተኛ ተከታታይ ድል ያሳኩት ሲዳማዎች ከጨዋታው አንድ ነጥብ ማግኘታቸውን ተከትሎ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጠዋል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀራቸው ሊጉን በ27 ነጥብ መምራት ችለዋል።
በ14ኛው ሳምንት መርሃ ግብር ስሑል ሽረን በሜዳው በመርታት ታሪክ የፃፉት ወልዋሎዎች ከሲዳማ ቡና ጋር ያደረጉት ጨዋታ የዘንድሮው የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ዙር የመጨ ረሻቸው ሆኗል።
ሊጉ ዛሬም ሲቀጥል አዲስ አበባ ላይ መከላከያ ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ። በ14ተኛው ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ በተቀመጡት ደቡብ ፖሊሶች 2 ለ 1 የተሸነፉት ቡናማዎቹ፤ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አስራ አምስት ግቦችን ካስተናገደው መከላከያ ጋር የሚፋለሙ ይሆናል።ይህ ጨዋታ በተለይ ለቡናማዎቹ በሊጉ ሻምፒዮን የመሆን ጉዞ ላይ ጉልህ ሚና ይጫወታል።
በሊጉ የተፍረከረከ የተከላካይ ክፍል የገነባው መከላከያ በውጤት ማጣት ሲሸበር የፊት መስመር ተሰላፊው ምን ይሉህ ወንድሙ በአንፃሩ የፊት መስመሩ ላይ ድንቅ ብቃት እያሳየ ይገኛል። የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ምን ይሉህ ወንድሙ11ግቦችን በማስቆጠር ሲመራ፤ የመቀሌው አማኑኤል ገብረ ሚካኤል እንዲሁም የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ9 ግቦች ይከተሉታል።
የደረጃ ሰንጠረዡን ሲዳማ ቡና በ27 ነጥብ ቀዳሚ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስና መቀሌ 70 እንደርታ በእኩል 26 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011
በታምራት ተስፋዬ