ግርማ መንግሥቴ
መቼም ዘመን ሲነሳ ፍልስፍናው፤ ፍልስፍና ሲነሳ ዘመኑ ከነቦታና ጊዜው መነሳቱ የግድ ነው። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ደግሞ የፖለቲካ ስርአት የሚሉት የአስተዳደር ዘይቤ አለ። በዚህ ውስጥም የአስተዳደር ዘመን፤ አሁንም በዚህ ውስጥ የአስተዳደሩ ርእዮት፤ በተጓዳኝም፣ ምንልባትም በቀዳሚነት ደግሞ የመሪ ሚና አለ። ቀጥሎም የተመሪው ወይም የህዝብ ሚና አለ። የእነዚህ ሁሉ ጥምርና ድምር የሚያስገኘው ውጤት ነው እንግዲህ ለአገርና ህዝብ ውድቀትም ሆነ እድገት ወሳኙን ድርሻ የሚጫወተው።
በዚሁ በተንደረደርንበት ሀሳብ መመልከቻነት የኋለኛዎቹን ዘመናት በተለያዩ ዘውጎቻቸው ከፋፍለን ብናያቸው የምናገኘው ድምር ውጤቶች የየስርአቶቹን አጠቃላይ መገለጫ ነው። (ለምሳሌ “በእያሱ ዳቦ ነው ትራሱ”፣በዘውዲቱ ተደፋ ሌማቱ “በተፈሪ ጠፋ ፍርፋሪ” ወዘተ አይነቶችን፤ “በመለስ – – -” የሚለውን ለማሟላት “አሰብ የማን ናት?”ን ያነቧል።)
(እ.ኤ.አ. በ161 ዙፋን ላይ የወጣውና እስከ 169 ድረስ ሲያስተዳድር የነበረው የሮማ ንጉሠ ነገሥት ማርከስ ኦሬሊየስ በሚያራምደው ፍልስፍና ለሥነ- ምግባር ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ የነበረ ሲሆን፤ ጥንታዊ ሕጎች እና ፈጠራዎች ብዙም እውቅና አላገኙም ብሎ የሚያምን፤ በአገሪቱ ነባር የፍልስፍና አዝማሚያዎችን (አካዳሚክ፣ ሥነ-ተዋልዶ፣ ስቶክ እና ኤፒኩሪያን) በመለየት ለእያንዳንዳቸው አራት አራት የፍልስፍና መምሪያዎችን ያቋቋመና ፍልስፍናን መሰረቱና መርሁ ያደረገ መሪ እንደነበር የተመሰከረለት መሆኑ እየተነጋገርንበት ያለውን ሀሳብ ያራምድልናል ብለን እናስባለን።)
በአንድ የፖለቲካ/የአስተዳደር ስርአት ውስጥ ስርአቱ የሚመራበት ርእዮትና ስርአቱን በበላይነት የሚመራው ቁንጮ (መሪው) በማንኛውም የአገሪቱ ሁኔታ ቀዳሚ ተወቃሽ ወይም/እና ተሞጋሽ ናቸው። በዚሁ ሙገሳም ይሁን ወቀሳ ውስጥ ደግሞ ሁሉም አለ፤ የሚከተለው “የፍልስፍና አቅጣጫ” ጭምር። ወደ ርእሰ ጉዳያችን ስንመጣም ያው ሲሆን፤ የመሪው (የተቃናም ይሁን የተንሸዋረረ) የመሪነት አተያይ ለሁለንተናዊው የአገር ውስጥ እንቅስቃሴም ይሁን አጠቃላይ እድገት የሚጫወተው ገንቢም ይሁን አፍራሽ ሚና ተኪ የለውም። ማውደም ከፈለገ (እሱ እራሱ (አብሮም ሆነ ለብቻው) እስኪወድም ድረስ ያወድማል፤ በተቃራኒውም ከፈለገ እንደዛው።
በእስከ ዛሬው የአገራችን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ወዘተ ህይወት ጉዞ ውስጥ ያልተፈራረቀ ሀዘንና ደስታ፤ ዘፈንና ለቅሶ፤ መስቀልና ሰላጢን፤ ድልና ሽንፈት፤ ትርፍና ኪሳራ፤ ሞትና ሽረት ወዘተ የለም ማለት ይቻላል፤ ደም ፈሷል፣ አጥንት ተከስክሷል፣ ሀብት ንብረት ወድሟል። ምንም እንኳን አንዳንድ ሰዎች እዚህ የተደረሰው እንደ ቀልድ ቢመስላቸውና ዛሬ ድንገት ብድግ እያሉ “አገር ይፍረስ/አይፍረስ” እያሉ ቢፎክሩም (የወፍ ጎጆ እንኳን በዚህ ደረጃ አይፎከርበትም)፤ እውነቱ ግን ይህና ከዚህም በላይ ነው። (ከፍልስፍናችን መፍረስ ጋር ተያይዞ ዝርዝሩ ብዙ ስለሆነ እንዝለለው።)
“ለውጥ” የሚለው ቃል እንደ ትርጉሙ ነው፤ መለወጥን ይዞ ይመጣልና ለውጥ አለ ማለት ነው። ችግሩ ግን “ምን አይነት ለውጥ?” የሚለው ሲሆን ይህ እራሱን በቻለ ጥናት የሚመለስ ይሆንና ዋናው ግን “ለውጥ” መኖሩ ላይ መስማማቱ ተገቢ ይሆናል።
ለውጡ (መጋቢት 24/ 2010 ዓ.ም) ከውስጥ በመሆኑ በኢህአዴግ አባላት ተይዞ የነበረው ስልጣን በሌሎች የኢህአዴግ አባላት ተወሰደ። በመሀል መኮራረፍ መጣ። ጁንታ ተፈጠረ። ወደ ጦርነትም እስከ መግባት ተኬዶ ታሪክ የማይሽረው ስህተት ተፈፀመ። ይሁን እንጂ ጎን ለጎን ለውጦች እየተካሄዱና በተግባርም እየታዩ መሄድ ጀመሩ። አንዱም እየተነጋገርንበት ያለው ፍልስፍና ነክ የሆነው ጉዳይ ሲሆን፤ ይህ በፊት ያልነበረ፤ እንዲኖር ሀሳብ ሲቀርብ እንኳን የሚያስጠይቅ ጉዳይ ዛሬ በአደባባይ እየታየ በመምጣት ላይ ይገኛል። “አዲስ ወግ”ን፤ ከቴሌቪዥንም “የልቦና ውቅር”ን እና የመሳሳሉትን በቀዳሚ ምሳሌነት መውሰድ ይቻላል።
እነዚህ ሁለቱንና ሌሎችንም እዚህ በምሳሌነት ስናመጣ ፍልስፍና እና ፍልስፍና ነክ ውይይቶች በሀገራችን እንደገና እየተጀመሩ፤ “አገር በቀል እውቀት” በማለት ብዙዎቻችን ስንጮህላቸው የነበሩት ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች እንደገና በህዳሴ መልክ ወደ ነበሩበት እየተመለሱ፤ ከተነቀሉበት እየተተከሉ መሆናቸውን ያመላክታሉ ብለን በማሰብ ሲሆን ይህንንም እንደሚከተለው በተለያዩ ማስተንተኛዎች አማካኝነት እንመለከታለን።
ምልከታችን በሁለት ግዙፍ እና ተፃራሪ ጎራዎች ማለትም የማቴሪያሊስት /ቁስ አካላዊያን/ እና የአይዲያሊስት / ሀሳባዊን / “ፍልስፍና” ላይ ይመሰረታል፡፡ በርካታ የፍልስፍና ዘውግ አራማጆች የየራሳቸውን ብያኔና “ተጨባጭ” ማብራሪያ ሲያቀርቡ ኖረዋል፡፡(ወደፊትም እንዲሁ) ቢሆንም በመካከላቸው አንዳንዴ እጅግ የከረረ (“የማይታረቅ” የሚሉት) ልዩነት ይፈጠራል፡፡ (ለምሳሌ በ”ሶሻሊዝም” እና በ”ካፒታሊዝም”፤ በ”አውዳሚነት” እና “ሰብአዊነት” ወዘተ መካከል እንዳለው አይነት) ያም ሆኖ በአንድ መሰረታዊ የፍልስፍና ብያኔ ላይ ግን ይስማማሉ። እሱም “አለምን፣ ተፈጥሮን፣ ማህበረሰብን፣ አካባቢን ወዘተ በሚገባ ለማወቅ፣ ለመመርመር፣ ለመረዳትና ለመገንዘብ፤ የተለያዩ የስሜት ህዋሳታችንን በመጠቀም ለመለየት፣ ማብራራት ለመተንተን፤ ችግሮችን ለይቶ ለማወቅና መፍትሄውን ለማፍለቅ” የሚለው ሲሆን ከሳይንስ በተለይም ከተፈጥሮ ሳይንስ ጋር በተደጋገፈ መልኩ ያን ክፍተት ለመሙላት እና የመሳሰሉትንም ያካተተ ነው። ሌላው “የፍልስፍና እውቀት” ሲሆን፤ እሱም እራሱን የቻለ ብያኔ ተሰጥቶት እናገኛለን።
እንደ “የማርክሳዊ-ሌኒናዊ ፍልስፍና መሰረተ- ሀሳቦች” መጽሐፍ “የፍልስፍና እውቀት” ማለት “በትርፍ ሰዓት በብቸኝነት የሚመረት አዝመራ አይደለም። የሳይንስ እና የማህበራዊ እድገት ውጤት የሚንፀባረቅበት፤ የተለያዩ መደቦች አመለካከት እና ርእዮተ-ዓለማዊ አቋም የሚገለፅበት፤ በዚህም ሆነ በዚያኛው ሀገር ውስጥ የትኛውም ወቅት የሚገኝ ማህበራዊ ቅራኔ እና ግጭት የሚከሰትበት የማህበራዊ ንቃተ-ህሊና ቅርጽ ነው።” (ገጽ 23) በዚሁ ምክንያትም ካርል ማርክስ ጽንሰ-ሀሳቡን “የመንፈስ ግሩም-ድንቅ ማስረጃ ነው፤ የባህል ህያው ልብ ነው።” በማለት እንዳብራራውም በዚሁ “ዲያሌክቲካዊ ቁስ-አካልነት”ን በሚያብራራው የፍልስፍና መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል። (የ”ንቃተ-ህሊና” (Consciousness) ጉዳይ አንባቢያን ከተገቢ ምንጭ በመመርመር ተገቢውን ግንዛቤ ያገኛሉ ተብሎ ይታሰባል።)
“የፍልስፍና እውቀት ፋይዳ”ን በተመለከተም በበርካቶች ብዙ የተባለ ሲሆን በሁሉም ዘንድ ግን የአንድን ግለሰብ “የመረዳት፣ የማስረዳት፣ የመጠየቅ፣ የመተንተንና የመሳሰሉትን ችሎታዎች የሚያዳብር ሲሆን፤ የግለሰቡንም ሆነ ማህበረሰብን የምክንያታዊነት፣ ተጠየቃዊነት፣ ሰብአዊነት ወዘተ ስሜትን፣ እውቀትን የማስረፅ፤ የሰዎች አመለካከትን፣ አስተሳሰብን – – – የመቅረፅ አቅም ያለው መሆኑ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በተለይም “ሰዎች ስለሚኖሩባት አለም ስለእድገቷም ህግጋት፣ አለምን ተመራምሮ እንደምን መገንዘብ እንደሚቻል በስርአት የተቀናበሩ አመለካከቶችን” እንደሚያበረክት ወዘተ ያለ ልዩነት ስምምነት አለ። ይህ እንዳለ ሆኖ፤ እስከዚያው ግን (ከ”ንቃተ-ህሊና” ጋር በተያያዘ የሚከተለውን በጋራ መግባቢያነት መያዝ ይቻላል።
“ንቃተ-ህሊና” ማለት “የሚገነዘብ”፣ “ስሜትን የሚረዳ”፣ “እኔነትን በውል የሚለይ”፣ “አቅሙን፣ የእውቀት ደረጃውን፣ የራሱን ልዩ ተሰጥኦ ለይቶ ማወቅ”፣ “አካባቢውን፣ ተፈጥሮን መረዳት”፣ ወይም ደግሞ “ሙሉ አዕምሮን የሚቆጣጠር ሰው”፤ መብትና ግዴታውን የተገነዘበ፤ ጭቆናን የማይቀበል፤ ለማህበረሰብ እሴቶች የሚገዛ ወዘተ የሚሉ ብዙ ትርጓሜዎች አሉት። ስለሆነም ንቃተ-ህሊና ብዙ የአዕምሮ ተግባራትን በዋናነት የሚያስተናግድ ዐቢይ ክፍል ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም Christof Koch (ጁን 1፣ 201)ን “What Is Consciousness?” በሚል ርእስ ያቀረቡትን ጥናታዊ ጽሑፍ መመልከት ይቻላል።
እዚህ ላይ የሰውን ልጅ “አስተሳሰብ” የሚመለከተውን የ”ንቃተ-ህሊና” ጉዳይ ብንወስድ “የሰው ሰውነቱ ማሰቡን ማወቁ ላይ” መሆኑን የፍልስፍና እምብርቱ ያደረገውን ፈረንሳዊው ሳይንቲስት፣ የሂሳብ ሊቅና ፈላስፋ ሬኔ ዴካርት ተለይቶ የሚታወቅበትን መሪ ሀሳብ የምናስታውስ ሲሆን፤ እሱም “I think therefore I am” (‘Cogito ergo sum’) ነው። ዴካርቴ ከበርካታ አቻዎቹ ቀስት ይወርወርበት እንጂ ለእኛ፣ ቢያንስ በዚህ ጽሑፍ ደረጃ ሊያከራክር በማይችል መልኩ ተገቢ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ “አለሁ፤ አስባለሁ።” ፍልስፍና እያለን የማናስብ ከሆነ፤ አስበን ምክንያታዊ፣ ሀልዮታዊ፣ ስነምግባራዊ ወዘተ መሆን የማንችል ከሆነ፤ መኖራችን እምኑ ላይ ነው?” የሚል ጥያቄን ካላጫረ እውነትም ዴካርት ተሳስቷል፤ ፍልስፍናውም ችግር አለበት ማለት ይቻል ይሆናል።
“ፍልስፍናዊ ወግ”ን ወይም ፍልስፍናን መሰረት ያደረገ (የሚያደርግም ጭምር) ውይይትም ይሁን ክርክር (በየትኛውም ደረጃና የአኗኗር ዘይቤ ላይ ይገኝ) ለሰው ልጅ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ለማስረገጥ ሲባል ከላይ የተሰነዘረውን አስተያየት ማስፈር በማስፈለጉ ተደርጓል። የዚህም አቢይ አላማ ቀጥሎ የሚመጣውን ሀሳብ መሰረት ለማስያዝ የግድ አስፈላጊ ስለሆነና ከአንባቢ ጋር በቀላሉ መግባባት ይቻል ዘንድ ፋይዳ ስላለው ነው።
ፍልስፍናን መሰረት ያደረጉ የትምህርት አቀራረቦች፣ ውይይቶች፣ ክርክሮች፣ የፍርድና ፍትህ ሂደቶች ወዘተ ለአለማችን በተለይም ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ የጥንታዊ ስልጣኔ መነሻዎች አዲስ ጉዳይ አይደለም፤ ወይም አልነበረም። የኢትዮጵያን እንኳን ብንወስድ የእውቀት ዘርፉ ከጥንት ከመሰረቱ የነበረ ሲሆን ለዚህ ማረጋገጫችንም በአፍሪካ የመጀመሪያው ፈላስፋና በአለም የዘመናዊ ፍልስፍና (ሞደርን ፊሎሶፊ) ፋና ወጊ መሆኑ የተመሰከረለት ዘርአ ያእቆብ እና ደቀ-መዝሙር ወልደ ህይወት ናቸው። (በስራዎቻቸው (“ሀተታዎች (Treatise)” እና በእነሱ ህይወት ላይ የተደረጉ ጥናቶችን ይመለከቷል፤ ለምሳሌ የብሩህ ዓለምነህ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና”፤ “ቁጥር አንድ” እና “ቁጥር ሁለትን”።)
ወደ “ዘመናዊቷ” ኢትዮጵያ ስንመጣም ይህ “ፍልስፍናዊ ወግ” ብዙም እርቆን አይታይም። በንጉስ ኃይለ ሥላሴም ነበር፤ በደርግም ነበር፤ በኢህአዴግም ነበር።
በንጉሱ ጊዜ በግልፅ የሚታወቅና ለታሪክ ምስክርነት የበቃ “ፍልስፍናዊ ወግ”ን የመሰለ ተግባር ቢኖር እራሳቸውን ንጉሱን የገለበጠው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሲሆን፤ እሱም ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል በፍልስፍና በታሹ ውይይቶች፣ የሥነጽሑፍ ስራዎች (በተለይ ግጥሞች)፣ ክርክሮች፣ የጋዜጣና መጽሄት ጽሑፎች ወዘተ ነበሩ። ወደ ደርግም ስንመጣ ያው ቀጥሎ (በተለይ በመጽሄትና ጋዜጦች) በርካታ ፍልስፍናዊ (“ፖለቲካል ፊሎሶፊ”ን የታገጉ) ክርክሮች ነበሩ፤ በኋላ ሁሉም ተካረሩና በቀይና ነጭ ቀለማት ተፈራርጀው ወደ መተላለቁ ሲያመሩ ሁሉም ቀረ፤ ሞተና ተቀበረም።
ወደ ኢህአዴግ ስንመጣም ተመሳሳይ ሂደትን ነው የምናገኘው። ኢህአዴግ ገባ፤ ሁሉም ነገር 100 በ100 ነፃ ተደረገ፤ መደራጀት፣ መፃፍ፣ ማንበብ፣ ሀሳብን – – – ሁሉ ያለገደብ ሆነ። ታፍኖ የኖረው ሁሉ እድሉን በማግኘቱ ያው እዚህ ዘርዝረን የማንዘልቃቸው የፕሬስ ውጤቶችና ሰላማዊ ሰልፎች ሁሉ ሰዓት በሰዓት፣ እለት በእለት ይካሄዱ ነበር። ከተገኘው ነፃነት የተፈጠሩት እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ማህበራት፣ በርካታ ደራሲያንና ጋዜጠኞችን ያፈሩ አማተር የጋዜጠኝነት፣ አማተር የሥነ ጽሑፍ (ኪነጥበብ) – ፍካት የደራሲያን ክበብ፣ ውበት አማተር ጋዜጠኝነት ክበብ፤ ማህበረ ኪን የኪነጥበብ ማህበር ወዘተን ማስታወስና በእነዚህ ክበባት ውስጥ ታቅፈው ከነበሩት መካከል ምን ያህሎቹ በአሁኑ ሰዓት ስመ-ጥር ጋዜጠኛና ጸሀፊ ለመሆን እንደበቁ ማስታወሱ በቂ ማስረጃ ነው። ታዲያ ምን ያደርጋል መከኑ። (እያወራን ያለነው የውይይት ክበባት፣ “አዲስ ወግ”፣ “የልቦና ውቅር”ን የመሳሰሉ የአዳራሽና የቴሌቪዥን ፍልስፍናዊ ወጎች ማለትም ውይይቶች፣ ክርክሮች፣ ዲስኩሮች ወዘተ የነቃ ማህበረሰብ፤ የተረዳ፣ ምክንያታዊና ተንታኝ ትውልድ፣ የገባውና የሚያገናዝብ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያላቸው ፋይዳ ከምንገምተውና ከሰጠናቸው ያልተገባ ዝቅተኛ ግምት በላይ ስለመሆኑ ነው።)
በኢህአዴግ እየተነጋገርንባቸው ካሉት “ፍልስፍናዊ ወግ”ን የውይይትና ክርክር አይነት መድረኮች በምሁራኑ ደረጃም መታየት ጀምረው የነበሩ ሲሆን፤ በመምህራን ማህበር፣ ሰራተኛ ማህበር ወዘተ አካባቢም ይሄው ተግባር መከናወን ጀምሮ ነበር። በግለሰቦች ደረጃም “ፍልስፍናዊ ወግ”ን በተግባር የማዋሉ ጉዳይ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን ፕሮፌሰር መስፍንና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ በማወያየታቸው ምክንያት ብቻ ሶቅራጥስ በዘመኑ የደረሰበትን አይነት የቅጣት ደረጃ ባይደርስም ከቆሙበት መድረክ ወደ ቃሊቲ ይወርዱ ዘንደ ተገደው ሌሎች እንዲህ አይነቱን ነገር እንዳያስቡት ለማድረግ በማስተማሪያነት አገልግለዋል። በቃ፤ የኢህአዴግ መንግስት ከመልካም ጅምሩ ወረደና፣ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ጭራሹን አጥብቦ ወደ ለየለት አምባገነንነት ተቀየረና ሁሉንም “ፍልስፍናዊ ወግ” ተብዬ አይነት እንቅስቃሴዎችን ቀጥ አደረጋቸው። የቀጠለ ነገር ቢኖር ገዥው (አውራው) ፓርቲ ያመነበትን ብቻ በተወካዮቹ አማካኝነት ወደ ታች ማውረድና በወረደው ላይ መወያየት ብቻ ሆነና አረፈው።
ከመጋቢት 24/ 2010 ዓ.ም ለውጥ መከሰት በኋላ (ያሉት አስከፊ ችግሮች እንዳሉ ሆነው) በርካታ ለውጦች ብቅ ብቅ አሉ። የሌሎቹን ትተን ከጉዳያችን ጋር የሚሄዱትን ስንመለከት ብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ ያሳስር የነበረ ተግባር ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ገብቶ “በአዲስ መልክ” እንዲሉ ነባሩ የአገራችን ፍልስፍናዊ ወግ “አዲስ ወግ” ሆኖ መጥቷል። (እዚህ ላይ ከላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ደረጃ ሲጀመር እታች ድረስ ይወርዳል ተብሎ ይጠበቃልና ሊታሰብበት ይገባል፡፡)
በቅርቡ (ኢዜአ እንዳስነበበው) “የሩሲያ-አፍሪካ ባህልን መልሶ መገንባት” በሚል ርእስ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ተካሂዶ ነበር። ጉባኤውንና አላማውንም በመደገፍ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግስትን አስተዳደር የተመለከቱ የፍልስፍና አስተምህሮዎችን በመከተል በሀላፊነት” መንቀሳቀስ እንዳለባቸው የተናገሩ ሲሆን ከዚህ አኳያ “ሩሲያ የፈላስፎች አገር” መሆኗንም አመልክተዋል።
“እኔም ይህንን እሳቤ የሚያራምደውን የብልፅግና ፓርቲ በሊቀመንበርነት በመምራት ላይ እገኛለሁ” በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠቀስነውና በጽሕፈት ቤታቸው በሚካሄደው “አዲስ ወግ” ላይ በመገኘት ጠንካራ ተሳትፎ የሚያደርጉ ሲሆን “የዚህ አይነቱ ውይይት ለአገራችን አስፈላጊ” መሆኑንም ደጋግመው ይናገራሉ።
ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ቃል ከልብ መሆኑን አምነን ከተቀበልን፤ የሚመሩት ፓርቲ/ አስተዳደር ይህንኑ ፍልስፍና አምኖ የተቀበለና ወደ ተግባር የሚለውጥ ከሆነ፤ አባላቱ (ሁሉም) ልክ እንደ እሳቸው በ”ፍልስፍናዊ ወግ” የሚያምኑና ለተግባራዊነቱ የሚተጉ ከሆነ (ልክ መግቢያችን ላይ እንደጠቀስነው እሮማው ንጉስ ማርከስ ኦሬሊየስ እና አስተዳደራቸው) አገራችን ከገባችበት አረንቋ መውጫ መንገዶች አንዱ ይሄው “ፍልስፍናዊ ወግ” አይነት የውይይት፣ ክርክርና ሙግት ፕሮግራም ስለመሆኑ መጠራጠር አይቻልም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2013