53 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ወደ ጎተራ ገብቷል
አዲስ አበባ፡- በ2016/17 ዓ.ም በመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነ 20 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እስካሁን ድረስ በሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የደረሰው ሰብል መሰብሰቡን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ከተሰበሰበው ሰብል 53 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ወደ ጎተራ መግባቱን ተጠቁሟል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ኢሳያስ ለማ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በ2016/17 ዓ.ም በመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነ 20 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ድረስ ወደ ሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የደረሰው ሰብል ተሰብስቧል፡፡ ከተሰበሰበው ሰብልም እስከ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 53 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ወደ ጎተራ ገብቷል፡፡ የተሰበሰበው ሰብል ሙሉ ለሙሉ ሲወቃ የምርት መጠኑ እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡
በ2016/17 ዓ.ም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሠራ ጠንካራ ሥራ 20 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመኸር የእርሻ ሰብል የመሸፈን ሥራ መሠራቱን አውስተው፤ በመኸር ወቅት ከተሸፈነ 20 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 12 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ያለው ሰብል
ለመሰብሰብ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ ከተሰበሰበው ሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥም ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮኑን ሄክታር ላይ የደረሰው ሰብል በሰው ኃይል፤ 360 ሺህ ሄክታሩን በኮምባይነር የመሰብሰብ ሥራ መከናወኑን አብራርተዋል፡፡
ከ2016/17 ዓ.ም የመኸር ሰብል ለመሰብሰብ ከደረሰው 12 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋው ሄክታር መሬት አለመሰብሰቡን ጠቁመው፤ ይህን የደረሰ ሰብል ለመሰብሰብም የሚያስፈልገውን የሰው ኃይልና ኮምባይነር በመጠቀም የመሰብሰብ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ከምርት አሰባሰቡ ጀምሮ ጎተራ እስኪገባ ድረስ የምርት ብክነት እንዳይደርስ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸው፤ በምርት አቀማመጥ ላይ የምርት ጥራት ጉድለትና ብክነት እንዳይደርስ ዘመናዊ ጎተራዎችንና ምርቱን ከነቀዝ የሚከላከሉ ኬሚካሎችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀምባቸው እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከ2016/17 ዓ.ም የመኸር ምርት ዘመን 615 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቀም አቶ ኢሳያስ ጠቁመው፤ የተጠበቀውን ምርት ለማግኘትም የደረሱ ሰብሎችን በወቅታቸው የመሰብሰብና የመውቃት ሥራ እየተሠራ ነው፤ እየተሠራ ያለውም ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ኅዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም