“የጉልበት እና የነውጥ አማራጮች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር አይፈቱም” – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ

አዲስ አበባ፦ በምንም አይነት መንገድ የጉልበትና የነውጥ አማራጮች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር የማይፈቱ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) አስታወቁ። ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በሀሳብ ልዕልና መሆኑን አመለከቱ።

ቢቂላ (ዶ/ር) የብልፅግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመትን አስመልክተው በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሆነ አጠቃላይ ችግር በጉልበት የሚፈታ አይደለም፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ የጉልበትና የነውጥ አማራጮች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር አይፈቱም ብለዋል።

በመሣሪያ አፈሙዝ ወይም ደግሞ ጫካ በመግባት የሚገኝ ውጤት የለም፡፡ በጎዳና ላይ ነውጥም የሚገኝ ድል እንደሌለ ያመለከቱት ቢቂላ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በሐሳብ ልዕልና ብቻ እንደሆነ አስታውቀዋል። የሀገራችን የፖለቲካ ድባብ ከጉልበትና ከመጠፋፋት፤ ከጦርነትና ከደም መፋሰስ መንገድ ወጥቶ ወደ ሐሳብ ልዕልና መሸጋገር እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የትኛውም የፖለቲካ ጥያቄ ሆነ ያልተፈቱ ችግሮች አሉኝ የሚል ማንኛውም አካል መንግሥት የከፈተውን የሠላም አማራጭ ተጠቅሞ ወደ ውይይት በመምጣት፣ ሐሳብ ካለው በሐሳብ ልዕልና በማመን፣ ሠላማዊ የፖለቲካ መድረክ ላይ ሐሳቡን በማንሸራሸር የፖለቲካ ችግሮች እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የዜጎቻችንን ችግር የምንፈታው እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ተባብረንና በጋራ ሠርተን ሀገራችንን ከድህነትና ከጉስቁልና በማውጣት ነው ያሉት ቢቂላ (ዶ/ር)፤ ለዚህም እዚህም እዚያም የሚታዩ የአክራሪነት እና የጽንፈኝነት ኃይሎች እንቅስቃሴ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል ፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን  ኅዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You