ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
ብርሃን ከጨለማ ቀጥሎ የሚመጣ የተስፋ ምልክት ነው።የብዙ ራዕዮች፣ የብዙ ህልሞች መፍለቂያም ነው።ብርሃን የነፍሶች ደስታ፣ የስጋ ሀሴት ፌስታም ነው።ከማታነት መውጫ፣ ከፍርሀት ከድንጋጤ ማገገሚያ የሰው ልጅ ሁሉ የአርነት ትንሳኤም ነው። ብርሃን የስልጣኔ የብልጽግና ማሳያ ነው።እኔም በነገዋ ኢትዮጵያ ማህጸን ውስጥ የሚታየኝ ይሄ ነው።እስኪ ወደፊት በደንብ ተመልከቱ.. በኢትዮጵያ ምድር ብርሃን አይታያችሁም? ሊነጋ ያሉ፣ ከጨለማ ለመላቀቅ የሚታትሩ ብሩህ ነገዎች አይታዩዋችሁም? ተስፋ ያቆጠቆጡ፣ እውነት የሰነቁ የጎህ ጀንበሮች በሰማዩ ግርጌ አይታዩዋችሁም? ጨለምተኛ ካልሆናችሁ ማየት ትችላላችሁ።የኢትዮጵያ ከፍታ.. እድገት ብልጽግናዋን የማትወዱ ካልሆናችሁ በስተቀር ማየት ትችላላችሁ። ብታምኑም ባታምኑም ጊዜው የኢትዮጵያ ነው.. ወደሚደነቅ ብርሃን እየተጓዝን ነው።ችግሮቻችንን ጥለን ድህነት ኋላ ቀርነታችንን ገለን ወደ ታላቅ ብልጽግና እየተሸጋገርን ነው።
እንደምታውቁት ብዙዎቻችን ብርሃን ናፋቂዎች ነን። ለመሄድ.. ወደ ከፍታ ለመውጣት.. ህልማችንን ለማሳካት ከትላንት የተሻለ ቀን የምንጠብቅ ብዙ ነን። ብሩህ ነገ የምንናፍቅ፣ ጸአዳ ማለዳ የምንጠብቅ እልፎች ነን.. በብርሃን ናፍቆት የምንሰቃይ ሞልተናል። የብርሃን ዋጋው ብዙ ነው… በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ የአስተሳሰብ ጨለማ የአመለካከት ውሱንነት አለ። በእያንዳንዳችን ዛሬ ውስጥ ያልተኖረ ትላንት ያላለቀ አምና አለ።በኢትዮጵያ ምድር ብዙዎቻችን የጨለማው ጊዜ ትላንት የሚቆጨን ነው። ኢትዮጵያ መቼ ይሆን የሚነጋላት…ኧረ አይነጋም ወይ እያልን ዘፍነናል አዚመናል።ስለ ችግሮቿ፣ ስለ ድህነቷና ኋላቀርነቷ ጽፈናል.. አውርተናል። ብሩህ ነገ ናፍቀን ስለ ብሩህ ነገዎች ተቀኝተናል.. ባልነጉ.. መሽተው በቀሩ በርካታ ትላንትናዎች ብኩን ሆነን ኖረን እናውቃለን.. አሁን ግን የብርሃን ጊዜ ነው። ወደ ትንሳኤ፣ ወደ ከፍታ የምናደርገው የሽግግር ጊዜ ላይ ነን። ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በብዙ ተስፋና በብዙ ራዕይ የተሞላን ህዝቦች ነን።ለውጥ እንደ ውሀ የጠማን ጊዜ ላይ ነን።በትላንት የጨለማ ጊዜአችን የምንቆጭ እንዲህም ነን። የሚሰሩ እጆች የተበራከቱበት፣ የሚያስቡ ጭንቅላቶች የበዙበት ጊዜ ላይ ነን። በብዙ ተስፋና በብዙ ራዕይ ወደፊት በመራመድ ላይ ነን። ከፊታችን የማይመሽ ቀን አለ… ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ የበራ ብሩህ ቀን እየጠበቀን ነው።በዚህ የብርሃን ጊዜአችን ላይ ከመለያየት ይልቅ የአንድነት መንገድን ወደፊት መሄድ ይጠበቅብናል።
ጨለማችንን በብርሃን በማሸነፍ አዲስና ብሩህ ሀገር ለመፍጠር መትጋት የትውልዱ ግዴታ እንዲሆን እሻለሁ። እንደ ትላንት ያለ የህዝቦች ድምጽ የማይሰማበት ጭንጋፍ ጊዜ እንዳይመጣ መበርታት ይኖርብናል። በኢትዮጵያ ምድር እንዲነጉ የምንፈልጋቸው በርካታ ጨለማዎች አሉ።እንዲጠሩ የምንፈልጋቸው ጉሞች አሉ።በእያንዳንዳችን ትላንት ውስጥ ያልነጋና ያልመሸ ቅይጥ አለማት አለ።ወዴት እንደምንራመድ መንገድ የጠፋን ሞልተናል።በሀገሪቱ ፖለቲካ መፈናፈኛ አጥተን ብርሃን ስንጠብቅ ጨለማ ውስጥ የቆምን ብዙዎች ነን።ለመልካም ነገር ስንተጋ አሸባሪዎች ተብለናል።ለህዝባችን የሚጠቅም ነገር ይዘን ስንመጣ ውሸታምና አጭበርባሪ ተብለን እናውቃለን። ማንም የማይሰማቸው እዛም እዚም በርካታ ሀገር ገንቢ የታፈኑ ድምጾች አሉ። ሀገር የሚገነቡ፣ ለህዝብ ተስፋ የሆነ የትውልድ ድምጾች ካለ አድማጭ የትም ከርቸሌ ቀርተዋል።ትላንት መናገር እየፈለግን እንዳንናገር ተፈርዶብን ከነ እውነታችን ቆመን ነበር።ትላንት መንግስትና ህዝብ ሆድና ጀርባ የሆኑበት ጊዜ ነበር።ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች እያሉን የተማረ የጠፋበት፣ ብዙ ወጣቶች ቆመው ተስፋ የታጣበት ነበር…ዛሬ አዲስ ቀን ነው።ለሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ…ወደ ብርሃን ጉዞ ላይ ናችሁ። ግን አንድነታችን ግድ ነው… አንድ እንጨት ብቻውን እንደማይነድ ሁሉ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ መፈጠር የሁላችንም ርብርብ አስፈላጊ ነው።
ከጨለማ ለመውጣት…የህልማችንን ፍሬ ለመብላት አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ትክክለኛ ጊዜ ላይ ነን። ከጨለማ የጸዱ.. ለጽልመት እጅ የማይሰጡ እልፍ አእላፍ ዓመታት ስለ እኛ እየዘመሩ ይሰማኛል… ኢትዮጵያ… ኢትዮጵያ የሚሉ የከፍታ መዝሙሮች በአራቱም የአለማችን ማዕዘናት ሲያስተጋቡ ይሰማኛል።መጪው ጊዜ የእኛ ነው.. ድሮነታችንን የምንመልስበት እንደ አባቶቻችን በአንድነትና በአብሮነት የምንቆምበት ጊዜ ነው።በስልጣኔ ዓለምን ያስደነቅንበት የጥንቱ ጊዜ ዳግም በአዲሱ ትውልድ ላይ እያንሰራራ ነው።በዘር በቋንቋ በብሄር የምንባላው ቀርቶ ፍጹም በሆነ የወንድማማችነት ስሜት እጅ ለእጅ የምንያየዝበት.. የጥላቻ ሰንኮፋችንን ጥለን በአዲስ አስተሳሰብ አዲስ ሆነን የምንፈጠርበት ጊዜ ከፊታችን እየመጣ ነው። በህዝቦች ተሳትፎ፣ በብሄር ብሄረሰብ እኩልነት የደመቀች ሀገር እየመጣች ነው።ብዙ ነገራችን እየተቀየረ ነው።አንድነታችን እየተመለሰ ነው። የህልማችን መንገድ ላይ ነን።መሆን የምንፈልገውን ልንሆን ጉዞ ላይ ነን።ከደመና መሀል እንደምትወጣ የማለዳ ጀንበር የምንናፍቃትም ኢትዮጵያ ተብትቦ የያዛትን ችግርና መከራ አሸንፋ ልትወጣ በመታተር ላይ ትገኛለች።
መጪው ጊዜ የእኛ እንደሆነ የሚያመላክቱ በርካታ ሀገራዊና ህዝባዊ ለውጦች እየታዩ ነው።ሁለት የመረጃ ሳታላይቶችን ወደ ህዋ አምጥቀናል፣ ከፊታችን የብዙዎቻችንን ተስፋ ይዞ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አለ።በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው አመርቂ ውጤት በማምጣት ላይ ነን። የሀገሪቱን የስራ አጥ ቁጥር የሚቀንሱ ትልልቅና ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች በመገንባት ላይ ናቸው። ከሰሞኑ ብዙዎቻችንን ያነጋገረ ደመናን የማዝነብ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የዝናብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ዝናብ አዝንበናል።በአይነቱ ለየት ያለ ይህ ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቂት ሀገሮች የሚጠቀሙበት ሲሆን በአፍሪካም ሀገራችን ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ከጥቂት ሀገራት አንዷ ሆናለች። ጊዜው የኢትዮጵያ ነው ያልኩት በምክንያት ነው።ይህ ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ ለሀገራችን ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል ብዬ አምናለሁ።የዝናብ እጥረት ባለባቸውና ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ያለውን የግብርና ምርት ከማሳደጉም በላይ በተለያየ ጊዜ የሚከሰተውን ለሀገራችንን የኑሮ ውድነት በከፍተኛ ደረጃ ያሻሽለዋል ብዬ አምናለሁ። ይሄ ብቻ አይደለም ድህነትን በመቀነስ ምርታማነትን በመጨመር በገጠርም በከተማም ላለው ማህበረሰብ ዋስትና መሆን የሚችል ዘመናዊ ዘዴ ነው።ወደፊት በቴክኖሎጂው እየተጠቀምን ስንሄድ በዛው ልክ የተሻለ እድሎች እየተፈጠሩ ስለመሄዳቸው ጥርጥር የለኝም።
ጊዜው የለውጥ ነው.. ጊዜው የታላላቅ ሀሳቦች ነው። በዚህ ስልጡን ዘመን ላይ ትንንሽ ሀሳቦች ዋጋ ሀሳቦች ሁሌም ትንሽ ናቸው ህዝብና ሀገር ከመጉዳት ባለፈ የሚጠቅሙት ነገር የለም። ትንንሽ ሀሳቦችን ለመስማትም ሆነ ለመናገር ጊዜ አይኑራችሁ። ትንንሽ ሀሳቦች ጎጂ ናቸው።ወደ ብርሃን እየሄዳችሁ ለራሳችሁም ሆነ ለሌሎች የሚበጅ ታላቅ ነገር አስቡ እንጂ እርባና ቢስ በሆኑ ትናንሽ ጉዳዮች አትወሰዱ።ብርሃን የትልቅ ሀሳብ ውጤት ነው።በአስተሳሰባችሁ ስትልቁ ራሳችሁን በብርሃን ውስጥ ታገኙታላችሁ።ሀገራችን ኢትዮጵያ ለበርካታ ጊዜ ከትንሽ ጭንቅላት በሚወጡ ትንንሽ ሀሳቦች ስትታመስ ኖራለች።ትንንሽ ሀሳቦች በውስጣቸው ትልቅ ነገር የለም።ነውጥና ድንቁርናን ከመፍጠር ባለፈ የሚፈይዱት አንዳች ማህበራዊ እሴት የለም።ለራሳችሁም ሆነ ለጊዜው የሚመጥን ተራማጅ አስተሳሰብን አፍልቁ።ወደ ብርሃን እየሄዳችሁ ወደኋላ የሚመልስ አሉታዊ እሳቤን አታስቡ። ከእንግዲህ ለሚጠቅመን ነገር ነው መልፋት ያለብን ከመንግስት ጎን በመቆም የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል እንጂ ማደናቀፍ ጠቃሚ ነገር አይደለም። እንደነገርኳችህ መጪው ጊዜ ለእኛ ብሩህ ነው.. ይበልጥ ብሩህ እንዲሆን ግን ከትችት መውጣት አለብን:: ለአንድ አላማ መሰለፍ ይኖርብናል። ለሀገር የሚበጅ የተሻለ ነገር በመፍጠር የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንጂ በመከራ የተገኘን የለውጥ ብርሃን ማጨለም ተገቢ አይሆንም፡፡
በአብሮነት ከቆምን ድህነትን ታሪክ የማድረግ ብርቱ ኃይል አለን። ልክ እንደ እናት ሁሉ አዲስቷን ኢትዮጵያ ናፍቀው ከሚጠብቁት ውስጥ ነኝ።እርግጠኛ ነኝ ብርሃን ናፍቋችኋል.. አዲስ ሀገር.. አዲስ አስተሳሰብ ሽታችኋል። አዲስ ትውልድ አዲስ መንፈስ አስፈልጓችኋል፡፡…ወደ ከፍታ እየወጣን ነው.. ወደ ህልማችን እየሄድን ነው። ሀገር ልባም መሪ ይፈልጋል… ልባም መሪ ልባም ህዝብ ይፈጥራል።ወደ ከፍታ ወደ ብልጽግና ለምናደርገው ጉዞ ሁላችንም አስፈላጊዎች ነን። ከእኔና ከአንተ በላይ ለዚች ሀገር አስፈላጊ የለም። አንዱ እያለማ ሌላው እያጠወለገ የምትበለጽግ ሀገር የለችም።ወደፊት ለምትፈጠረው ኢትዮጵያ አብሮነታችን ዋጋ አለው።በመልካም መንገድ ላይ ነን… በሎጥ መንገድ ላይ ቆመናል… ወደ ከንዐን እየሄድን ነው ወደፊት እንጂ ወደኋላ ማለት የለብንም።ለዘመናት ከኖርነው ድህነት መውጣት አለብን።
ለዘመናት ከኖርነው ኋላ ቀርነት መላቀቅ አለብን…ከፊታችን ብዙ ብሩህ ተስፋዎች አሉ ከዛ መድረስ አለብን።የአዲስቷ ኢትዮጵያ ብርሃናማ ነገዎች በእያንዳንዳችን እጅ ውስጥ ናቸው።ከእያንዳንዳችን አስተሳሰብ ውስጥ፣ ከእያንዳንዳችን እውቀት ውስጥ የሚዋጣ ህዝባዊ ተሳትፎ ነው።ብርሃን ዝም ብሎ አይገኝም።ብርሃን የልፋት ውጤት ነው እያንዳንዳችን የምናዋጣው.. በስራ በትጋት የምናገኘው የልፋት ፍሬ ነው።የኢትዮጵያ የነገ ብርሃን ያልኳችሁ ይሄንን ነው።የኢትዮጶያ የነገ ብርሃን ከእያንዳንዳችን ላይ የተወሰደ፣ የእያንዳንዳችን የራዕይና የላብ ውጤት ነው።ብርሃናችሁ ደምቆ እንዲያበራ ጠብቁት… ብርሃናችን የሚፈካውም የሚጨልመውም በእኛ ነው።ትላንትናችን የጨለመብን አለን.. ሁላችሁም ለሀገራችሁ የሚበጅ ለህዝባችሁ የሚጠቅም ብርሃናማ ድምጽ ይኑራችሁ።
እውቀታችሁን.. ሀሳባችሁን ለለውጥ ተጠቀሙበት።የነገዋ ብርሃናማ ኢትዮጵያ በሁላችን ድምጽ፣ በሁላችን መልካም እውቀት የምትፈጠር እንጂ በመንግስትና በጥቂቶች የምትፈጠር አይደለችም።ወደ ምስራቅ ተመልከቱ… ወደ ብርሃን እዩ።በሀገራችን ጉዳይ ምን ያገባኛል ማለት በራስ ህልውና ላይ መቀለድ ነው።…ድምጻችሁን እያሰማችሁ እጆቻችሁን ለልማት እያበረታችሁ ወደ ብርሃናችሁ አቅኑ። እስከዛሬ እንዳንናገር ሆነን በጨለማ ኖረናል.. ብንናገርም አድማጭ አልነበረንም ብንደመጥም ፋይዳ አልነበረንም አሁን ግን በርካታ የታፈኑ ድምጾች የሚሰሙበት ከዛም ከዚም በርካታ አስተሳሰቦች የተፈጠሩበት ጊዜ ላይ ነን።ለራሳችሁም ሆነ ለሀገራችሁ የምትሰሩበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ናችሁ።ከዚህም በላይ ሀገር ገንቢ የሆኑ ድምጾች መሰማት አለባቸው። ብርሃናችንን የሚያፈኩ ድንቅ ሀሳቦች እየመጡ ነው።ሀገራችን ኢትዮጵያ እያደረገችው ላለው የለውጥና የከፍታ ጉዞ ኃይል በመሆን ከጎን ቁሙ ያኔ የነገዋ ብርሃናማ ኢትዮጵያ ካልተፈጠረች ምናለ በሉኝ።
ጨለማ ውስጥ ተቀምጦ ብርሃን መናፈቅ ሞኝነት ነው።ሳይሰሩ ለውጥና ብልጽግናን መናፈቅ እብደት ነው።ብርሃን ከጨለማ መውጣትን ይፈልጋል።ስልጣኔ ጥሩ ማሰብን ይሻል።ብልጽግና የሚሰሩ እጆች የሚያስቡ ጭንቅላቶችን ይፈልጋል።ከፊታችን የእኛን ከጨለማ መውጣት የሚጠብቁ በርካታ ልማቶች አሉ።ከፊታችን ደመና እንዳዘነብን ሁሉ ለነገዋ ኢትዮጵያ ጉልበት የሚሆኑ ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አሉ። ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚወስዱ፣ ከድህነት ወደ ብልጽግና፣ ከኋላቀርነት ወደ ዘመነ ሉአላዊነት የሚወስዱን ሀገር አሻጋሪ አስተሳሰቦች እየወጡ ነው።በዚህ ድንቅ አስተሳሰብ የቆመች ሀገር ታስፈልገናለች። በዚህ ድንቅ አስተሳሰብ የቆመ ማህበረሰብ ያስፈለገናል።ብርሃን ያልኳችሁ ይሄን ነው።ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2013