አስቴር ኤልያስ
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ ይጥራ እንጂ መንግስት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተገንጥሎ የወጣ ነው በሚል ኦነግ ሸኔ ሲል ሲጠራው ይደመጣል።ይኸው ኃይል ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ ባደረሰው ጥቃት ንጹሃን ዜጎችን መግደሉን የክልሉ መንግስት በመግለጫው አሳውቋል።ይህ ጽንፈኛ ኃይል ይህን ድርጊት ሲፈጸም በተደጋጋሚ የመሆኑን ያህል የክልሉ መንግስትም እንዲሁ ተደጋጋሚ መግለጫ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል።ይሁንና የቱንም ያህል መግለጫም እርምጃ ይወሰድ እንጂ በእስካሁኑ ሂደት የንጹኃን ህይወት ከመጥፋት ያበቃበት ሁኔታ እምብዛም ካለመታየቱም በተጨማሪ ጉዳዩም ሲረግብ አይስተዋልም።ይህም የንጹሃን ዜጎች ጥቃት ጉዳይ የህዝብ አንድነትና የአመራር ቁርጠኝነት የማይኖር ከሆነ በአንድ በምዕራብ ወለጋ ዞን ብቻ ተወስኖ ስለማይቀር ጎረቤት የሆነው የምስራቅ ወለጋ ዞን ምን ሁኔታ ላይ እንዳለና የዞኑ ነዋሪዎችስ ለሰላም ያላቸው ቁርጠኝነት የት ድረስ ነው የሚለውንና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ ዘመን ከዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ጋር ያረገውን ቃለ ምልልስ አጠናቅሮ ተከታዩን አሰናድቷልና መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- በምስራቅ ወለጋ ዞን ከሰላምና ጸጥታ ጋር በተያያዘ ያለው ሁኔታ እንደምን ይገለጻል? ከአጎራባቹ ምዕራብ ወለጋ ዞንስ ጋርስ ያለው የሰላም ሁኔታ እንዴት ነው?
አቶ አለማየሁ፡- የምስራቅ ወለጋ ዞን የተከፋፈለው 18 ወረዳ እና በአንድ ከተማ አስተዳደር ሲሆን፣ በአብዛኛው ማህበረሰብ ውስጥ ጥሩ የሚባል የሰላም ሁኔታ ነው ያለው ማለት ይቻላል።በብዙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች እንዲሁም ነቀምቴ ከተማችንን ጨምሮ የሰላም እና የጸጥታ ሁኔታው መልካም የሚባል ነው።
በእርግጥ በምዕራብ ወለጋ ዞን በጣም ውስን በሆኑ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ለውጡን ተጻርረው የቆሙ ተላላኪ ኃይሎች ሁሉም እንደሚያውቀው በቅርቡ ገብተው የህዝቡን ሰላም ማደፍረሳቸው ይታወሳል።እነዚህ በአማጺ መልክ ገብተው የንጹሃንን ህይወት የቀጠፉ ግፈኞች ናቸው፡፡
እነዚህ አማጻያን ኃይሎች በተለይ ደግሞ ኦነግ ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ደምቢ ዶሎ አካባቢ ሲገባ ህዝቡ አማጺ ኃይሉ ግፍ በተሞላበት አካሄድ ሰዎችን ሲያሰቃይ የነበረ ሲሆን፣ በዞኑ ያሉ ብዙ ወረዳዎች በሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ለውጡን እና የለውጡን አመራር ደግፈው ፍላጎቱን የገለጸበት ሁኔታ ነው ያለው።በአሁኑ ወቅት ደግሞ የተወሰኑ ቀበሌዎች በተለይ ደግሞ ቆላማ የሆኑ አካባቢዎች መጥፎ የሚባል ሁኔታ ተፈጥሯል።በተለይ ከአማራ ክልል ጋር በሚያጎራብቱ ማህበረሰቦች እንዲሁም በመተከል ደግሞ ከካማሺ ጋር ባሉ ቦታዎች የተለያዩ ችግሮች ሲከሰቱ ቆይተዋል፡፡
እነዚህ አማጺያን ኃይሎች አንዱ ዘንድ ብቻ ጥፋት ፈጽመው እዚያው የሚቆዩ ሳይሆን፤ አንዱ አካባቢ ጥፋት ፈጽመው ሲያበቁ ያንን ስፍራ ደግሞ ብዙም ሳይቆዩበት ትተው ወደሌላ ቦታ ያቀናሉ።ጥፋት ፈጸሙ የተባለበት ቦታ ፍተሻ ሲደረግም ያንን በመተው ወደ ጫካ ሄደው መሽገው የሚቀመጡ አይነት ናቸው።አሁን የጸጥታ ኃይሉም ተጠናክሮ በአንድነት ደግሞ የጋራ እቅድ ይዞ ሸማቂዎችን በመቆጣጠር ላይ ነው ያለው።በመሆኑም አሁን ላይ ያለው ሁኔታ የሚመስለው ይህን ነው፡፡
በእርግጥ የሰላም መታጣት የልማት ስራውን የሚጎዳው ቢሆንም፤ አሁን ላይ ሁሉም ወረዳዎች ላይ የልማት እንቅስቃሴያችን ወደ 95 በመቶ ያህል የሚሆኑ ቀበሌዎች መደበኛ ልማት እና የመልካም አስተዳደር በመሰራት ላይ ነው ያለው።ምርጫ አስፈጻሚዎችም በተያዘላቸው እቅድ መሰረት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው።ለምርጫው ሂደት የሚያስፈልገውን ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛሉ።ይህን የሰላም ሁኔታ አልፈው ጸጥታውን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይላት ቢኖሩ ደግሞ በቁጥጥር ስር ይውላሉ ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው።
አዲስ ዘመን፡- የኦሮሚያ ክልል መንግስትም ሆነ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በየራሳቸው በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ በንጹሃን ሰዎች ላይ የደረሰውን የግፍ ጭፍጨፋ አስመልክተው የሰጡት መግለጫ አለ፤ እናንተ ይህን አይነት የግፍ ጭፍጨፋ በምስራቅ ወለጋ ይከሰት ይሆናል የሚል ስጋት የላችሁም? ካላችሁስ በምን አይነት ሁኔታ ነው ለመከላከል የተዘጋጃችሁት?
አቶ አለማየሁ፡- በእኛ ዞን በተለይ ደግሞ ስድስት ሰባት ወረዳ ብሄርን መለየት በሚያስቸግር ሁኔታ ህዝቡ ተሰባጥሮ ነው እየኖረ ያለው።በአንድ ቀበሌ ውስጥ ብቻ የተለያየ አይነት ብሄር ይኖራል።ለምሳሌ አማራውም፣ ኦሮሞውም ጉሙዙም እንዲሁም ሌላውም ብሄር የሚኖረው በጋራ ነው።በአምስት ስድስት ወረዳ ውስጥ ያለው ሁኔታ ይህንን የሚያሳይ ነው።
በአሁኑ ወቅት ጽንፈኛው ሽፍታ ቡድን ብሄርን ማዕከል ያደረገ ጥፋት አቅዶ ምንም እንኳ በምዕራብ ወለጋ ውስጥ የደረሰውን ያህል የከፋ አይሁን እንጂ በእኛ በምስራቅ ወለጋ በተወሰኑ ቀበሌዎች ሙከራ አድርጎ ህይወት እንዲጠፋ እና ደም እንዲፈስ አድርጓል፡፡
በእኛ በኩል የወሰድነው አቋም የትም አካባቢ ያለው ህዝብ በቃ ህዝብ ነው የሚል ነው።በእኛም ከነቀምቴ ከተማ ጀምሮ በሁሉም ወረዳ ማለት ይቻላል አማራም ኦሮሞም እንደጎንደር፣ ጎጃምም ሆነ እንደ አዲስ አበባ ሁሉ ባለን ቀበሌዎች ሁሉ አብረን ነው በጋራ እየኖርን ያለነው።አማጺውና ጽንፈኛው ኃይል የየትኛውም ብሄር ጠላት የሆነው የኦነግ ሸኔ ኃይል የተቀመጠው ቆላማ በሆኑ አከባቢዎች መሽጎ ነው።መንግስት የጸጥታ ኃይል ቢልክ እንኳ ቶሎ መድረስ በማይችልበት ስፍራ ነው ያለው።ይህ ኃይል ኦሮሞ ላይ ጥቃት አድርሶ ኦሮሞን አማራ እንዳጠቃው ለማስመሰል እየጣረ ብሄር ተኮር ጥቃት ነው በማለት ጉዳዩን ያሳያል።
ነገር ግን አብዛኛው ህዝብ አማራውም ሆነ ኦሮሞውም አንድነቱን አጠናክሮ ከሚሊሻው ጋርም ሆነ ካለው የክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር ተቀናጅቶ ጽንፈኛውን ኃይል በመከላከል ላይ ነው ያለው።በዚህም ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው በምዕራብ ወለጋ ዞን ሰሞኑን እንደተሰማው ያለምንም ጥፋት ዜጎች በግፍ እየሞቱ እና እየተጎዱ ሲሆን፣ እነዚህም ደግሞ ንጹሃን የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፤ መንግስት እየወሰደ ያለው ለዚህ የሚመጥን አጸፋዊ እርምጃ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ አለማየሁ፡- መንግስት በአሁኑ ሰዓት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በጣም የተሻለ ነው ማለት ይቻላል።ህዝቡም ጽንፈኛውን የኦነግ ሸኔ ኃይል ፍላጎቱ ምን እንደሆነ በደንብ ተረድቶታል።ይኸው ጽንፈኛ ኃይል ህዝቡን ለሁለት እና ሶስት ዓመት ያህል ሲዘርፈው ነው የነበረው።የህዝቡን ልጆች ወደ ጦር ከመክተቱም በላይ ሲያስገድል ነው የሰነበተው።በመሆኑም የዚህን ኃይል ዓላማ በአግባቡ ተገንዝቦ የማያዋጣው መሆኑንም ተረድቶ በአሁኑ ሰዓት ህዝቡ ራሱ እየተዋጋው ነው ያለው።
መንግስትም በችግሩ መጠን ትኩረት ሰጥቶታል የሚል እምነት አለኝ።ለዚህም ደግሞ የክልል እና የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎችን አቀናጅቶ በተናበበ ሁኔታ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልም ከአራቱ የወለጋ ዞኖችም ጋርም ተቀናጅቶ የመጨረሻውን የማጽዳት ስራ እየሰራ ነው።
የሸማቂ ኃይል ባህሪ ይታወቃል።ሸማቂው ኃይል ምሽግ ይዞ ለራሱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠነቀቀ ራሱን ላለማስነካት የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ነው የሚዋጋው።አንድ ቦታ አለመቀመጥ ደግሞ ዋናው ባህሪው ነው።እንደሚታወቀው ለአንድ ሰዓት ያህል የቆየበት ቦታ ዝም ብሎ አይቀመጥም።ለምሳሌ አንደኛው ዞን ላይ ያጠፋውን ጥፋት በመከተል በመንግስት እርምጃ ሲወሰድበት ሌላ ዞን ብሎም ሌላም ክልል ይከሰታል።
በዚህም ምክንያት አራቱም የወለጋ ዞኖችም ሆኑ ካሚሺና መተከልም ማለትም በሶስቱም ክልል በኦሮሚያ፣ አማራ እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ውስጥ በተቀናጀ ሁኔታ እየተሰራ ነው ያለው።ይህን መንግስት እያካሄደ ያለውን ኦፕሬሽን በየቦታው ያለው ሕዝብ ደግሞ ከደገፈው እና ከተባበረ ችግሩን በቁጥጥር ስር ማድረግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎም እንዳሉት ሸማቂው ኃይል አንድ ቦታ ተወስኖ አይቀመጥም ብለዋል፤ ከዚህ የተነሳ ምስራቅ ወለጋ ዞን የሚጣል የሚል ስጋት የላችሁም?
አቶ አለማየሁ፡- ይኖረናል እንጂ! ይህ ሸማቂ ኃይል እንዳልኩሽ በተለይ የመሰረተ ልማት በሌለበትና በጣም ሰፋፊ የሆኑ ቆላማ ቦታዎች ላይ ነው የሚንቀሳቀሰው፤ አሁንም ቢሆን በተወሰነ ቆላማ በሆኑ እና ወደበረሃነት በሚያደሉ ቦታዎች እየተንቀሳቀሰ ነው።ስለዚህ ሸማቂው ኃይል ገና ወደፊት ይመጣል ሳይሆን አሁንም አለ ለማለት እችላለሁ፤ ይህም በግልጽ የሚታወቅ ነው።ለዚህም ደግሞ እርምጃ እየተወሰደበት ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስት በየጊዜው ጉዳዩን በተመለከተ በተለይ ንጹሃን ዜጎች በግፍ በተገደሉ ማግስት መግለጫ ያወጣል፤ ይሁንና የሚያወጣው መግለጫ ምንም ውጤት እያመጣ አይደለም በመባል ይነገራል።እርስዎ ደግሞ በቅርበት ላይም ስላሉ ይህን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ አለማየሁ፡- ይህ እኮ አይቀርም፤ ንጹሃን ዜጎች በደል ሲደርስባቸው ማንኛውም ለህዝብ እታገላለሁ የሚል መንግስት ድርጊቱን አውግዞ እና ኮንኖ መግለጫ መስጠቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ የወሰደው ኃላፊነትም ጭምር ነው። ምክንያቱም የሚያስተዳድረው ህዝብን እና አገርን ነውና ሐሳቡን ደግሞ ለሚያስተዳድረው ህዝብ መግለጽ አለበት።መግለጫ መስጠት ብቻ ሳይሆን ደግሞ የመንግስት አመራር እና የመንግስት የጸጥታ ኃይል ዋጋ ከፍሎ እና ህይወቱን ሰውቶ እንዲሁም ደሙን እያፈሰሰ እና አጥንቱን እየከሰከሰ ብሎም እየተሰዋ ይህን ጽንፈኛ ኃይል እየተቆጣጠረው ነው ያለው።
አሁን ይህ ሁኔታ ሲስተዋል ጽንፈኛው ኃይል የአንድ ወር ወይም የአንድ ሳምንት ዝግጅት አድርጎ አይደለም ችግር እያደረሰ ያለው።ችግሩን ለማስወገድ ደግሞ በመንግስት በኩል በርካታ ሙከራ የተደረገ ሲሆን፣ ለሁለት ዓመት ያህል ትዕግስት ተደርጎ፣ እንዲሁም ወደ እርቅ እንዲመጡም ተደርጎ ይህ ሁሉ እድል ተሰጥቷቸው ነው፤ በተለያየ ደረጃ ሲሸመገልም የነበረ ጉዳይ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ይሁንና ይህ የጽንፈኛው ኃይል የተያያዘው ነገር ቢኖር ጉዳት ባደረሰ ጊዜ የመንግስት የጸጥታ ኃይል ሲመታው በሌላ አቅጣጫ ሄዶ ንጹሃን ዜጎችን ይመታል።ሸማቂው ኃይል ያለው እንደዚህ አይነት ባህሪ ነው።ስለዚህም መንግስት ችላ አላለም።ለውጡ እንደጀመረ አካባቢ ጽንፈኛው ኃይል ከኤርትራ እንደገባ የለውጥ አመራሩ ላይ ነው በአደባባይ ቦምብ የጣለው።ስለዚህም በዚህ ያህል ደረጃ ጽንፈኛ መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡
ሚዲያዎች በግፍ በደል በማድረስ ያለው ይህንን ኃይል ባህሪውን፣ አካሄዱን ብሎም ስልቱን በመግለጽ ህዝቡ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንዲተባበር ግንዛቤ በመስጠት መቀስቀስ ይጠበቅባቸዋል፤ መንግስት የሚወስደውን እርምጃ ጭምር ህዝቡ እንዲደግፍ ቢሰራ ጥሩ ነው የሚል አመለካከት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ጥቃት ፈጻሚውን ጽንፈኛ ኃይል ባስታገሰ ወይም በመታ ቁጥር እነሱ ደግሞ ንጹሃንን ዜጎች በግፍ እየገደሉ ነው፤ ይህን ተከትሎ አንዳንዶች ለጽንፈኛው ቡድን በዛ አካባቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል እንደ ምሽግ ምቹ ሁኔታን ስለፈጠረለት ነው የግፍ ተግባሩን የሚያካሂደው እያሉ ነው ያሉትና ይህን እንዴት ያዩታል?
አቶ አለማየሁ፡- ይህ በአሁኑ ሰዓት ሳይሆን ቀደም ሲል ከውጭ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ በተደረገ ጊዜ የለውጡ ዓላማ እና ይዘት እንዲሁም የወደፊት አቅጣጫው ነጥሮ ባልወጣበት ህዝቡ የተለያየ ብዥታ ውስጥ ገብቶ እንደነበር የሚታወስ ነው ።
በአሁኑ ሰዓት ግን ኦነግ ሸኔ የአማራ ጠላት ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ህዝብ ጠላት ነው።ኦነግ ሸኔ አፋን ኦሮሞ የሚናገር ጁንታም ነው።ህዝቡ ቤቱ ተቀምጦ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ስብሰባዎችም ሆነ ባገኘው አጋጣሚ ለዚህ ጽንፈኛ ቡድን ጥላቻውን በተለያየ የመገናኛ ብዙኃን ጭምር በመግለጽ እያወገዘው ነው ያለው።እንዲያውም በዚህ ጉዳይ ከሁለት ወር ገደማ በፊት ህዝቡ ያለማንም ቀስቃሽና ውትወታ ከየቀበሌው ወጥቶ እንደ ኦሮሚያ ክልል የተደረገው ሰልፍ ብቻ ሳይሆን በተለይ ምስራቅ ወለጋ ላይ ከሁሉም ቀበሌ በመውጣት ሲያወግዘው ነበር የሰነበተው፡፡
ህዝቡ ምሽግ ይሆነዋል ሳይሆን ሸማቂው ኃይል የሰለጠነ የሽምቅ ኃይሉ ወታደር አለ፤ መንግስት እስኪደርስለት ፍራት ይኖረዋል እንጂ በአሁኑ ሰዓት በማንኛውም መመዘኛ የኦሮሞ ህዝብ ሆነ ሌላውም ብሄር ኦነግ ሸኔን ይደግፋል የሚል ምንም መሰረት የለም፤ እኛ ይህን እናውቃለን፤ አማራውን ብትወስጂ እየሞተበት ያለው ልጁ ነው።ሴት ልጅ እየተደፈረች ያለችው አባቷ እና እናቷ አጠገብ ነው።ይኸው ጽንፈኛ ኃይል ባለቤቷን አስሮ አጠገቡ ሚስቱን ነው እየደፈረ ያለው።ወገኖቻችንን በቁም እያረደ ነው ያለው።እንደዚህ በዚህ መልኩ በግፍና በጭካኔ ጉዳት እያደረሰ ያለው ኃይል ሰው ሳይሆን አውሬ ነው እያለ ነው ህዝቡ እያወገዘ ያለው።ስለዚህም በዚህ ደረጃ መሆኑ ግንዛቤ ቢወሰድ መልካም ነው የሚል አተያይ አለኝ።ምክንያቱም መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ይህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ምርጫ ሊካሄድ የቀረው በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፤ ይህ ጽንፈኛ ኃይል ደግሞ ሰሞኑን ለውጡን ለማደናቀፍ እና የሰዎችን አመለካከት ከለውጡ ወደሌላ የከፋ መንገድ ለመቀልበስ ሲል ንጹሃንን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉ ተረጋግጧል፤ ምርጫው በሰላም እንዲካሄድ የምስራቅ ወለጋን እና ጎረቤት ዞንን ከዚህ የሰላም ማጣት ስጋት የጸዳ ለማድረግ ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ አለማየሁ፡- ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ዋናው እና ወሳኙ ኃይል ህዝቡ ነው።የባለፈው ጊዜ የአምስቱ ዙር አይነት ምርጫ አካሄድ እንዳይደገም በንቃት መስራት የግድ የሚል ነው።ህዝቡ የፈለገውን መምረጥ እንዲችል ማድረግም እንዲሁ ወሳኝ ጉዳይ ነው።ከማሸነፍና ከመሸነፍ በላይ ዴሞክራሲ በአገራችን እንዲሰፍን እና ፍሬውም እንዲታይ በተለይ የዴሞክራሲን መሰረት አስቀምጠን ነው ማለፍ የምንፈልገው።በዚህ ደረጃ በምርጫውም ሂደት ይሁን የምርጫውም ውጤት ሆነ ከምርጫውም በኋላ የሕዝብ ድምጽ እንዳይነካ፣ አስቀድሞም ህዝቡ ይበጀኛል ያለውን በካርዱ እንዲመርጥ መንግስት ለአመራሩ፣ ለአባላቱ ብሎም ለደጋፊዎቹ በአጠቃላይ ለምርጫ አስፈጻሚው ብቻ ሳይሆን ለጸጥታ ኃይሉም ጠበቅ ያለና ለየት ያለ ስልጠና እየሰጠ ነው ያለው።
ምርጫ የሚካሄደው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ነው።ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ጽንፈኛውን ኃይል መቆጣጠር አለብን ብለን ከወትሮው በበለጠ ጠንክረን እየሰራን ነው የምንገኘው።በዚህ ደረጃ ግንዛቤ ቢያዝበት መልካም ነው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አንዱ ሌላው ዘንድ የመኖር መብቱ የተጠበቀ ስለመሆኑና ይህንንም እውነት እንዲሁም እውነተኛ የሆነ ፌዴራሊዝምን በአግባቡ ተገንዝቦ የዞኑ ማህበረሰብ ተግባራዊ እንዲያደርገው በየትኛው ልክ ነው እየተገለጸለት ያለው?
አቶ አለማየሁ፡- ለህዝባችን እያልነው ያለ ነገር ቢኖር ጽንፈኝነት ምንም አያዋጣም ነው፤ ህዝባችን አንድነቱን ብሎም ወንድማማችነቱን አጠናክሮ ሰላሙን ማስጠበቅ ነው ያለበት።ከሰላም ጎን ለጎን ደግሞ የሚበጀውን ይህን ለውጥ ማስቀጠል ነው ያለበትም።የጽንፈኝነቱን አካሄድ እና የፖለቲካ ክፍፍሉን ወደጎን በመተው በአብሮነት ነው መኖር የሚጠበቅበት።ህዝቡ ቀደም ሲልም ይህ የለውጡ መንግስት ከመምጣቱ በፊት በነበረው መንግስትም በሆነ ከዛም ቀደም ብሎ ባለው መንግስት ሲኖር የነበረው በጋራ እና በአንድነት ነው።ይህንን አንድነቱን ነው ዛሬም ቢሆን ማጠናከር ያለበት።አንደኛው መንግስት ሄዶ ሌላው ሲመጣ ህዝብ ሁሌም ቢሆን አብሮ የሚኖር ነው፤ ይህ ደግሞ የማይቀር እውነታ ነው።ስለዚህም ይኸውም ህዝብ ሰላሙን ለማስጠበቅ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ቅንጅትን ፈጥሮ መስራት አለበት።ጊዜያችንም የሚፈልገው ይህንኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኦነግ ሸኔ አፋን ኦሮሞ የሚናገር ጁንታ ነው ብለው ጠቀስ አድርገዋል፤ ይህንኑ አካል ህዝቡ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ይምረጥና ውጤቱን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መስማት እንዲችል ጽንፈኛውን ኃይል እንዴት ነው መከላከልና መመከት ያለበት ብለው ይመክራሉ?
አቶ አለማየሁ፡- ህዝቡ ማድረግ ያለበት አንደኛ ከምንም በላይ ሰላሙን ማስጠበቅ አለበት።ይህን ማድረግ የሚጠበቅበት ደግሞ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር በመሆን ነው።ሌላው ደግሞ የፖለቲካ ኃይል ነኝ ብሎ የሚመጣን የተደራጀ ኃይል ሐሳብ ብቻ ይዞ እንዲመጣ ህዝቡ ማስገደድ አለበት።ከሐሳብ ውጪ የሚደረግ እንቅስቃሴ ለድርጅቱም አይበጅም፤ ለህዝባችንም አይበጅም፤ እንዲሁም ለአገራችንም የሚበጅ አይደለም።በአሁኑ ሰዓት ህዝቡ በዚህ ደረጃ ነው የተገነዘበው።ይህን ግንዛቤውን ደግሞ ማጎልበት እና ይበልጥ ማጠናከር አለበት፡፡
ደግሞም ከፖለቲካ ድርጅት በላይ አገር የሚባለው ትልቁ ጉዳይ ከፍ ያለ ስፍራ የሚሰጠው ነገር ነው።ህዝቡ የፈለገውን ለመምረጥ የሚችለው እና መርጦም ውጤቱን መጠበቅ የሚችለው አገር ስትኖርና ሰላሟም ሲጠበቅ መሆኑን ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል።ምርጫም ቢሆን ከህዝብ እና ከአገር በታች እንደሆነ ህዝቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ መረዳት ይኖርበታል።
ስለዚህም የብልጽግና ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደህዝቡ ሲቀርቡ ሐሳብ ብቻ ይዘው እንዲቀርቡ የግድ ይላል።ምንም አይነት አስገዳጅ ሁኔታ ባይኖር ተመራጭ ነው።ህዝቡን በብሄር ብሎም በእምነትና በሰፈር የማጋጨትን አጀንዳ አድርጎ ተቀባይነት ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ወዲያ ሊጥሉ ይገባል።እነርሱም ቢሆኑ ከምርጫ አስፈጻሚው እና ከጸጥታ ኃይሉ ጋር አብረው በመስራት ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ብሎም የህዝብ ሉዓላዊነት የተረጋገጠበት ምርጫ እንዲሆን ተሳትፏቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ጎረቤት በሆነው ምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ በጽንፈኛው ኃይል በግፍ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦችና ወገኖች የሚሉት ነገር ካለ?
አቶ አለማየሁ፡- በጽንፈኛው ኃይል ህይወታቸውን ብሎም ሀብት ንብረታቸውን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማኝ ጥልቅ ያለ ሀዘን ነው።ለቤተሰቦቻቸውና ለዘመዶቻቸው እግዚአብሔር መጽናናቱን ይስጥ ለማለት እወዳለሁ።
ምዕራብ ወለጋ ዞንም የወለጋ አካል ነው፤ ለመስተዳደር መዋቅር ተብሎ ነው የተከፋለው፤ ከህብረተሰቡ ጋርም አብረን ነው የምንሰራው።እኛም የበኩላችንን ድጋፍ በማድረግ ላይ ነን።እንዲህ የከፋ የግፍ አይነት ተመልሶ እንዳይከሰት የየበኩላችን ለመወጣት ዝግጁዎች ነን፤ ጽንፈኞቹ ምኞታቸው አንዱን ብሄር ከሌላው ብሄር ጋር በማላተም አገር ወደጥፋት እንድትሄድ ማድረግ ነው።በተለይ ደግሞ የአማራ እና የኦሮሞን ህዝብ ማባላት ይፈልጋሉና ይህ የአማራም ሆነ የኦሮሞ ህዝብ ይበልጥ ወንድማችነቱንና አንድነቱን አጠናክሮ ጽንፈኛውን ኃይል ማሳፈር ይኖርበታል፤ የጽንፈኛው ፍላጎት አገር ብትንትኗ እንዲወጣ ነውና በዚህ ላይ ግንዛቤ መውሰዱ አዋጭ ነው።የብሄር ጥቃት እንዲቀጣጠል የሚያደርገውን የትኛውንም ኃይል ህዝቡ ቦታ እንዳይሰጠው እና ከቀዬው ሊያባርረው ተገቢ ነው የሚል መልዕክት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በምስራቅ ወለጋም ይሁን በሌሎቹ የወለጋ ዞኖች ውስጥ ያለው አካል ነገ ምን እሆናለሁ በሚል እያንዳንዷ ሌሊት የምታሰጋው ናትና ለእነዚህ ወገኖች ምን ይሏቸዋል?
አቶ አለማየሁ፡- ህዝቡ አሁን ያለውን ሁኔታ ተረድቶታል። ከሩቅ ላለ ሰው በወለጋ የትኛውም ቦታ መንቀሳቀስ እጅግ አስፈሪና የማይታሰብ ተደርጎ ይሳላል እንጂ በአብዛኛው የወለጋ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች እንደሌላው የኦሮሚያ ክፍል ተነጻጻሪ የሆነ የሰላም ሁኔታ ነው የሚታይበት። በቀሩት ቦታዎች ላይ ህዝቡ ከጸጥታው ኃይል ጋር ሆኖ ግፈኛውን ኃይል ለመደምሰስ ጥረት እያደረገና እየተሳተፈ ነው ያለው።የለውጡን ኃይልና የጸጥታውን ኃይል ደግፎ ጽንፈኛው ኃይል አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ትብብር ማድረግ አለበት።ከዚህ ውጭ ያለው የልማት፣ የመልካም አስተዳደር ስራ እንደ ሌላውም ዞን ሁሉ ተጠናክሮ በዞናችን እየተካሄደ ነው ያለው።በመሆኑም ህዝቡን የሚያሰጋው ቦታ የለም። በዚህ ደረጃ ቢወሰድ መልካም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናሁ፡፡
አቶ አለማየሁ፡- እኔም ደግሞ በሚዲያችሁ በኩል ለአካባቢያችን ሰላምና ደህንነት አጽንኦት ሰጥታችሁና ተከታትላችሁ በዚህ ደረጃ ህዝቡም ለሰላም በይበልጥ ተሳታፊ እንዲሆን ስላደረጋችሁት ጥረት ከልብ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2013