የመኖሪያ ቤት ሽያጭ በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባና በክልል ከተሞች የማይቀመስ እየሆነ መጥቷል፡፡ ቦታ መሸጥ ክልክል ቢሆንም በተለያዩ መንገዶች ቦታ ሲሰጥ ይስተዋላል፡፡
ገንዘብ የሌለው በኪራይ ይኖራል፤አልያም መጨረሻ የሌለውን የኮንዶሚኒየም ቤት እጣ እስኪደርሰው ይጠባበቃል፡፡ ያለው ማማሩ እንዲሉ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ቱጃሮች ደግሞ ከቦታ ቦታ እያማራጡ ረብጣ ገንዘባቸውን በማፍሰስ ቦታዎችን በሊዝም በሌላውም ሲገዙ ይስተዋላል፡፡
በውጪው አለምም በተለይ ተራራማ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የሚገነቡ መኖሪያ ቤቶች የተለየ እይታን ስለሚያጎናፅፉ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ይፈስባቸዋል፡፡ በርካታ በሪል እስቴት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶችም መዋእለ ነዋያቸውን ያፈሱባቸዋል፡፡ ሆኖም አለታማ ተራራዎችና ጉብታዎች ለመኖሪያ ቤት ግንባታነት ሲውሉ ማየት ግን እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡
ከሰሞኑ ኦዲቲ ሴንትራል የተሰኘው ድህረ ገፅ ከወደ እንግሊዝ ባወጣው መረጃ አንድ የተናጠጠ ቱጃር ተራራዎችን ካልገዛሁ ሲል ተደምጧል፡፡ ይህም ምን አልባት አለታማ ተራራዎችን ለመሸጥ ጥረት ሲያደርጉ ለነበሩና በቀጣይም ለመሸጥ ሃሳብ ላላቸው ግለሰቦችም ሆኑ የመንግሥት አካላት መልካም ዜና ሳይሆን እንዳልቀረ ተገልጿል፡፡
በተለይም ሃሽ ሃሽ የተሰኘው የኦን ላይን ቅንጡ ገበያ ድህረ ገፅ አስገራሚው እንግሊዚያዊው ሚሊኒየር ተራራዎችን የመግዛት ያልተለመደ የገበያ ጥያቄ ይዞ ብቅ ማለት በርካቶችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ ቱጃሩ እምብዛም ጥቅም ለሌለው አለታማ ተራራ በርካታ ገንዘብ በማውጣት ለመግዛት የፈለገበት ምክንያት በተራራው ላይ ውሻውን ጨምሮ የቤተሰቦቹን ሃውልት ሊያስቀርፅበት መሆኑ ደግሞ የበለጠ አስግርሟል፡፡
ግለሰቡ ለተራራ ግዢ እስከ 12 ሚሊ©ን ፓውንድ ወይም 15 ነጥብ 5 ሚሊ©ን የአሜሪካ ዶላር ለማውጣት ዝግጁ መሆኑን ዘገባው ያስታወቀ ሲሆን በተራራው ላይ ለሚቀርፀው የቤተሰቦቹ ሃውልት ተጨማሪ በጀት እንደያዘም ታውቋል፡፡
ሀሽ ሀሽ የተሰኘው የኦን ላይን ግብይት ድህረ ገፅ ዝርዝር የተራራ ሽያጭ መረጃ ይዞ የወጣ ባይሆንም ያልታወቀው ይኽው እንግሊዛዊ ሚሊየነር የድህረ ገፁ ታማኝ ደንበኛ በመሆኑ አመቺ ተራራ ሊያገኝ ይችላል በሚል ጥያቄውን ተቀብሎ ለገበያ ይፋ አድርጓል፡፡
እስካሁን በኦን ላይን ግብይት ከመጡ የገበያ ጥያቄዎች ውስጥ ይሄኛው የተለየ መሆኑን የድህረ ገፁ ባለቤት የጠቆሙ ሲሆን፤ ምን አልባት ሚሊ©ነሩ ተጨማሪ እርዳታዎችን ከሚመለከታቸው አካላት የሚያገኘ ከሆነ ሃሳቡ እውን ሊሆንለት እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011
በአስናቀ ፀጋዬ