የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው አቶ ኃይሉ ዘበርጋ ከሸማቾች ማህበራት ዘይት ይገዛሉ፡፡ ዋጋው ከሌላ ቦታ የ22 ብር ቅናሽ እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ያገኘናቸው በአራዳ ክፍለ ከተማ እፎይታ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ሸቀጦችን ሲሸምቱ ነው፡፡ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር አባል ባይሆኑም በአካባቢው ነዋሪነት የተለያዩ ምርቶችን በመግዛት እንደሚጠቀሙ ነው የሚያስረዱት።
እንደ አቶ ኃይሉ ሁሉ ወይዘሮ ማህሌት ታዬም አገልግሎቱን አስመልክቶ በነዋሪነታቸው መግዛት የሚፈልጉትን ምርት እንደሚገዙ ይናገራሉ፡፡ ምርቶቹ አንዳንዴ በሁለት ሳምንት፣ አልፎ አልፎ ደግሞ እስከ አራት ወራት የሚቆዩበት ጊዜ እንዳለ ተናግረዋል።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የመሳለሚያ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ሥር በሚተዳደረው አማኑኤል ሆስፒታል አቅራቢያ ባለው ሱፐር ማርኬት ያገኘናቸው ወይዘሮ ፍቅሬ ፍስሓ ዕቃ ለመውሰድ ካርድ እንደሚጠየቁ ጠቅሰው፤ እርሳቸው ደግሞ እንደሌላው ነው የሚናገሩት፡፡ ወይዘሮዋ፣ ‹‹በየ15 ቀን ምርት ይመጣል፤ አንዳንዴ ይቆያል። ድሃ አይታይም፡፡ ሁኔታው ቅር ያሰኛል፡፡ ቢሆንም ከሞላ ጎደል እየተገለገልኩ ነው፤ ዘይት አምስት ሊትሩ 126 ብር ሲሆን፣ ስኳር ደግሞ አምስት ኪሎ 116ብር ይሸጣሉ። የኪሎ ጉድለትም ይታያል፡፡ እስከ ሩብ ኪሎ ድረስ የሚጎልብት ጊዜ አለ፡፡›› በሚል ቅሬታቸውን ያሳያሉ።
ወይዘሪት ሰላማዊት አይቸው፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ የእፎይታ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር በገንዘብ ተቀባይነት ታገለግላለች። ማህበሩ በ2000 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን፣ አሁን አንድ ሺህ 876 አባላትን ይዞ ይንቀሳቀሳል።
ማኅበሩ አንድ ሚሊዮን ካፒታል እንዳለው የምትናገረው ወይዘሪት ሰላማዊት ስኳር፣ ዘይትና ዱቄት የመሳሰሉ የድጎማ ምርቶችን ለነዋሪዎችና ለአባላት እንደሚያከፋፍሉ ነው የምትገልጸው። ጨው፣ ምስር፣ ፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ሩዝና ሳሙና የሚከፋፈለውም በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሆነ ተናግራ፤ የአገልግሎት መስጫ ቦታው ለመንገድ ይፈለጋል ስለተባለ ግን ብዙም መሥራት አለመቻላቸውን ነው ያስረዳችው።
የእፎይታ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዳንኤል ፀጋው፣ ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበሩ ከመጡ ሦስት ዓመት፣ አመራርም ከሆኑ ስድስት ወር እንደሆናቸው ይገልፃሉ። አባላቱ አንድ ዕጣ ብቻ ገዝተው ትርፍ እንደሚከፋፈል ቀደም ሲል የሁለት ዓመት ኦዲት ተሠርቶ ዕጣ ላላቸው አባላት 80 ብር መከፋፈሉን ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው ከተመረጡ በኋላ የአንድ ዓመት ኦዲት ተደርጎ ለእያንዳንዱ አባል 325 ብር መከፋፈሉንም ነው ያብራሩት፡፡
አቶ ዳንኤል፣ በአመራርነትም ነፃ አገልግሎት እንደሚሰጡና የተወሰነ የስልክ ካርድ እንደሚያገኙም ይገልፃሉ። አባላቱ በ4 ኪሎ ልማት ምክንያት ተነስተው ወደ ጀሞና ሰሚት በመሄድ የሚኖሩ እንዳሉ ጠቁመው፤ ‹‹ያለፈውን ዓመት ሂሳብ ኦዲት አስደርገን ለአባላቱ ትርፍ ለማከፋፈል እየተሠራ ሲሆን፣ አንድ ሰው ከአንድ በላይ ዕጣ መውሰድ የሚችልበትን መንገድ ለማመቻቸት አባላቱን ሰብስበን በቅርቡ ለመወያየት አስበናል፡፡›› በማለት ያብራራሉ። የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበሩ ከነዋሪው ውጪ አካባቢው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በብዛት ያሉበት ስለሆነ ለመንግሥት ሠራተኞች የበለጠ አገልግሎት ለመሥጠት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የዚሁ ኅብረት ሥራ ማኅበር አንድ አመራር አቶ ጌትነት… በበኩላቸው እንዳሉት፤ ወደ ሁለት ሺህ የሚደርሱ አባላት አሉ፡፡ አብዛኛው በልማት የተሰናበተ ሲሆን፣ ከጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች አብዛኛው ተከራይ ነው፡፡ በመሆኑም በአባልነት የተያዙት ጥቂት ነዋሪዎች ናቸው። የተለያዩ ሸቀጦችን ለመሸጥ አመቺ የሆኑ ሦስት ሱቆች በአካባቢያቸው በተለያዩ ቦታዎች ከመስተዳድሩ እንደተሰጣቸው እና ዕቃ ማከማቻ ባይሆኑም ምርት በማከፋፈል ሰርዓት ግርግር ስለሚፈጠርና ወረፋ ስለሚበዛ ለማስተንፈስ የሚረዳ ነው።
በየካ ክፍለ ከተማ ሾላ አካባቢ በሚገኘው የቁም ነገር ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ገንዘብ ተቀባይ ወይዘሪት የዋግ ኃይሌ፣ ‹‹ሰው የሚፈልገውን ነገር ይጠይቃል፤ እናመጣለን። እንደ ዘይት፣ ስኳርና ዱቄት የመሳሰሉት የድጎማ ምርቶች ለአባላትና ከወረዳ ሰርተፍኬት አውጥተው የሚጠቀሙ ሰዎች በቋሚነት ይሸምታሉ፡፡ ሌሎች ምርቶችን የፈለገ ሰው መውሰድ ይችላል፡፡›› ስትል ታብራራለች።
ቢያንስ በቀን ከ80 እስከ 100 ሰዎች በመደበኛ ገበያ እንደሚስተናገዱ ትገልፃለች። ‹‹አቅርቦት ስላለ የሽያጭ እጦትም የለም። ሰው ከሌላ ቦታ የዋጋ ልዩነት ስላለው የገበያ መስተንግዶ ተመችቶታል›› በማለትም ነው የተናገረቸው።
የቁምነገር ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ክምችት ሠራተኛ የሆነችው ወይዘሪት ዓይናለም አንፍዬ፣ ለድጎማ ምርቶች ኩፖን እንደሚጠየቅ እና ለበዓል ሲሆን ሽንኩርት፣ ቅቤ፣ዶሮና ዕንቁላል ጭምር እያመጡ እንደሚያከፋፍሉ እንዲሁም በአንድ ቀበሌ አምስት ሱቆች እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ይህም ዕቃዎች ሲመጡ ወረፋ እንዳይበዛ የተቀላጠፈ መስተንግዶ ለማቅረብ እንዳስቻላቸው አመልክተዋል፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የመሳለሚያ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ሥር በሚተዳደረው አማኑኤል ሆስፒታል አቅራቢያ ባለው ሱፐር ማርኬት የሚሠሩት አቶ ከድር ኑርገባ፣ በሽያጭ ሠራተኝነት እንደሚሠሩ እና የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበሩ ሁለት ወፍጮ ቤቶችን ጨምሮ በአማኑኤል፣ በሠፈረ ሰላም እና በ18 ማዞሪያ ሦስት ሱፐር ማርኬት እንዳለው ገልጸዋል። ስድስት ሺህ የሚደርሱ አባላት ያሉት ሲሆን፣ በሥራቸው የሚተዳደረውን መዝናኛ ክበብ ጨምሮ ወደ 200 ሰዎች እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።
የሚዛን ጉድለት ችግር አለ ወይ? ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳስረዱት፤ እንደ ዱቄት የመሳሰሉ ምርቶች ከፋብሪካ ከወጡ በኋላ ኪሎዋቸው ይቀንሳል፤ ከፋብሪካ ሲወጡ በተወሰነ መልኩ እርጥበት አዘል ናቸው፡፡ ሲጫንና ሲወርድ እንዲሁም በሚዛን ሲሰፈር የተወሰነ የሚቀንሱ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ መኮሮኒም ቢሆን ከፋብሪካ ሲወጣ የተወሰነ እርጥበት ይኖረዋል፡፡ እየቆየ ሲሄድ ደግሞ ክብደቱ ይቀንሳል እንጂ ሆን ተብሎ ሚዛን ለማዛባት የሚሠራ ነገር የለም፡፡ የወረዳ ስነ ልኬት ባለሙያዎችም በሦስት ወር እንዲሁም በስድስት ወር እየመጡ የሚዛኖች ፍተሻ ያደርጋሉ። የተመዘነውንም ያያሉ፤ ይለካሉ፡፡ ጉድለት ካለ እንዲስተካከል ያሳስባሉ እንጂ በእነሱ በኩል የሚዛን መዛባት ችግሮች አላጋጠማቸውም፡፡ ቀደም ሲልም በሸማቾች ሱቅ ይሰሩ ስለነበር የጎላ ችግር የለም፡፡
አቶ ሲሳይ አረጋ የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። በመዲናዋ ያሉት 143 መሠረታዊ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት በአሥር ዩኒየኖች የሚመሩ እና ከ325 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በሸማች አባልነት ታቅፈው ይንቀሳቀሳሉ፡፡የገንዘብ አቅማቸውም ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል ከአንድ ሺህ 39 በላይ የአገልግሎት መስጫ ያላቸው እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
ዓላማቸው በመንግሥት የሚደጎሙ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በኃላፊነት ወስደው በትንሽ ትርፍ ድሃውን መደጎምና ማሠራጨት ነው። የምርት አቅርቦቶቹ ለሸማቾች ማኅበር አባላት እንዲሁም ለአካባቢው ነዋሪ የሚዳረሱ ሲሆን፣ የተጠቃሚዎችን ኑሮ ለመደጎም ጥሩ አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ ይገኛሉ።
የሸማቾች ማኅበር አባላት ከምርት አቅርቦት ሽያጩን በተመጣጣኝ ዋጋ ከመግዛት በተጨማሪ በገዙት ዕጣ ልክ ከሚገኘው ትርፍ ተካፋይ ይሆናሉ። ስለዚህ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን ማርገብ የድሀውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሥራቸው ነው። ምርቶች የሚመጡት በቀጥታ ከቦታው ስለሆነ ይቀንሳሉ፡፡ ስለዚህ ህዝቡን ከኑሮ ውድነት ጣጣ ነፃ እንዲወጣ ይረዳዋል።
በደንብ ቁጥር 46/2004 መሠረት አንድ ሺ 39 መዝናኛዎች ከባለ አደራ ቦርድ ወደ ሸማቾች ተላልፈዋል። እነዚህም 15 ሚሊየን የማይንቀሳቀስ ጥሬ ሀብት አላቸው። የመዝናኛ ቤቶቹን ጥራትና ብቃት ለማሻሻል ጥናት ተካሂዷል። ከመፀዳጃ፣ ወንበር፣ ከሠራተኞችና ከምግብ ማብሰያ ጋር በተያያዘ የማሻሻያ ሥራዎች ይሠራሉ። የአሠራር ጉድለትና ችግር፣ የሀብት አጠቃቀም፣ የአገልግሎት አሠጣጥ፣ ለሦስተኛ ወገን ሲያከራዩ የነበሩ የህዝብ መዝናኛ ማዕከሎችም ተገኝተዋል፡፡
ችግሮቹን ለመቅረፍ የንቅናቄ ሰነድ ተዘጋጅቶ የማዘመን ሥራ ለመሥራት ታስቧል። ለዚህም የንቅናቄ ሰነድ መዘጋጀቱን አቶ ሲሳይ አረጋ አስታውቀዋል። በየደረጃው እስከወረዳ ድረስ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በንቅናቄው ሰነድ እንዲወያዩ ደካመ ጎኖች ተነስተው ሊታረሙ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚመቻች ጠቅሰዋል፡፡
‹‹የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ጥንካሬያቸው እንደ አመራሮቻቸው ብቃትና ትጋት እንደሚለያይ ሁሉ ጠንካራዎች አሉ፤ በድጎማ ምርቶች ላይ ብቻ ታጥረው የሚቀሩም አሉ፡፡›› የሚሉት አቶ ሲሳይ፣ የተወሰነ የሚዛን መዛባት ችግር የአገልግሎት ሥርዓት ጉድለት እንደሚታይም ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለማጠናከርና ለነዋሪዎቹና ለአባላቱ የቅርብ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል 1ሺህ 332 የሸማቾች ሱቆችን ለመገንባት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አረጋ እንዳስታወቁት፤ ሱቆቹ የሚገነቡት በ243 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ሲሆን፣ወጪንም የሚሸፍኑት የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ይሆናሉ፡፡
እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ፤ ተጨማሪ የሸማቾች ሱቆች የሚገነቡት ለ1ሺህ 500 አባወራዎች ቢያንስ አንድ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ሱቅ ያስፈልጋል በሚል የከተማው መስተዳድር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ነው፡፡ ሱቆቹ እያንዳንዳቸው 50 ካሬ ሜትር ስፋት እንዲኖራቸው እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ኮንስትራክሽን ቢሮ ያደረገውን ጥናት ዋቢ አርገው የጠቀሱት አቶ ሲሲይ፣ ከነመደርደሪያቸው እስከ 183 ሺህ ብር ድረስ ወጪ አንደሚደረግባቸውም ገልጸዋል።
ከምዝበራም እንዲድኑ ገንዘባቸው በኦዲት ሕግ መሠረት ኦዲት እንደሚደረጉም ተናግረዋል።ዋና ዳይሬክተሩ የኅብረት ሥራን ሚና የኑሮ ቀወስን ማቃለል መሆኑን ጠቅሰው፣ አባል ሲሆን እንደሚጠቅምም ተናግረዋል፡፡ ‹‹የመደመር ፍልስፍናም የሚያሳየው ይህን አንድነት ነው፡፡ ያልተደራጀ ይናጣል፤ ይዋጣልም፡፡›› በማለት ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011
በሀይለማርያም ወንድሙ