በፍሬህይወት አወቀ
ገበያን በማረጋጋት ዓላማ አድርገው የሚሰሩ የህብረት ሥራ ማህበራት ለአርሶ አደሩም ሆነ ለሸማቹ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ይሁን እንጂ ነጋዴውና ደላላው ባለው ፈርጣማ ክንድ ገበያው እንዳይረጋጋ በማድረግ አርተፊሻል የዋጋ መናር እንዲከሰት ያደርጋሉ። ለዚህም በዘንድሮው ዓመት በተለይም በሰብል ምርት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት መከሰቱ ምንም ተጨባጭ ምክንያት የለውም።
በደብረብርሃን ከተማ የወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ዩኒየን ባለሙያ አቶ ለዓለም ቀለመወርቅ ዩኒየናቸው 12 ወረዳዎችና በእያንዳንዱ ወረዳ ውስጥ 132 ዩኒየኖች መኖራቸውን አንስተው በጥቅሉ 150 ሺ ገበሬዎችን ያቀፈ እና 60 ቋሚ ከ30 በላይ ደግሞ በጊዜያዊነት በድምሩ ከ100 ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አጫውተውናል።
የህብረት ሥራ ማህበራት ከማህበረሰቡ ወስደው ለማህበረሰቡ የሚያደርሱ እንደመሆናቸው ገበያን የማረጋጋት ትልቅ አቅም አላቸው ፤ ወደራ ዩኒየን መነሻውን ያደረገው የአርሶ አደሩን ምርት የተሻለ ገበያ አፈላልጎ ለመሸጥ ነው። በተመሳሳይ ደግሞ አርሶ አደሩ የሚፈልጋቸውን የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በዓመት ከሰባት መቶ ሺ በላይ ኩንታል ማዳበሪያ ለአርአደሩ ያቀርባል። እንዲሁም የተለያዩ የአረምና የተባይ ማጥፊያ ኬሚካሎችን በወቅቱ በማቅረብ አርሶ አደሩን የሚደገፍ በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።
አርሶ አደሩ የሚያመርተው ሰብል በነጋዴ እጅ ቢገባ አርሶ አደሩም ሆነ ማህበረሰቡም ተጠቃሚ አይሆንም። ነገር ግን አርሶ አደሩ የማሕበሩን ዓላማ በሚገባ የተረዳ በመሆኑ ተጠቃሚም እየሆነ ይገኛል። ወደራ ዩኒየን የተመሰረተው በሰባት መቶ ሃያ አምስት ሺ ብር ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከዘጠና አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማፍራት ችሏል። ከጥሬ ካፒታሉ በተጨማሪም የራሱ ህንጻ ያለውና የተለያዩ የስራ መኪኖች እንዲሁም ከ39 በላይ መውቂያ ማሽኖችን፤ ሶስት የእንስሳት መኖ ማቀነባባሪያ፣ የዱቄት ፋብሪካና የእርሻ ማዕከልም አቋቁሟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ በአሁን ወቅት ምርትና ምርታማነቱን ከፍ በማድረግ ከምንጊዜውም በበለጠ ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል።
በአካባቢው በዋናነት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ባቄላ፣ ምስርና ሽንብራ የሚመረት ሲሆን፤ በተለያዩ ሸማቾች በኩል የገበያ ትስስር በመፍጠር በየጊዜው ምርቶቻቸውን ለገበያ ያቀርባሉ። በተለይም ከፍተኛ የጤፍ ምርት የሚመረት ሲሆን እሴት በመጨመር አበጥረው ለገበያ የሚቀርቡ መሆኑን አቶ ለዓለም አንስተዋል። በዚህም መሰረት የተበጠረ ነጭ ጤፍ ደረጃ አንድ በኪሎ 46 ብር፣ የተበጠረ ቀይ ጤፍ 38 ብር፣ ባቄላ 32፣ ቀይ ሽንብራ በኪሎ 32 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛሉ።
ደብረብርሃን ከተማ ለአዲስ አበባ ቅርብ በመሆኗ ወደራ ዩኒየን አዲስ አበባ ካሉ ዩኒየኖች ጋርም ትስስር በመፍጠር በየዓመቱ እስከ 10 ሺ ኩንታል የሚደርስ ሰብል ምርቶችን ያቀርባሉ። ከዚህ በተጨማሪም በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከ20 ሺ በላይ ለሚደርሱ ተማሪዎች በየዓመቱ የምግብ አቅርቦት ምስር፣ ጤፍና ባቄላ ያቀርባሉ። ከዚህ ውጭም ጎጃም ከሚገኘው መርከብ ዩኒየን ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር በአካባቢው ታዋቂ፣ ተመራጭና ተፈላጊ ስንዴና ጤፍ እያቀረበ ይገኛል።
ማህበራት አርሶ አደሩን በመደገፍ ምርትና ምርታማነት እያደገ የመጣ ቢሆንም በአሁን ወቅት ግን እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበት መነሻ ምክንያት የሌለው ሰው ሰራሽ ነው የሚለው አቶ ለዓለም፤ ዩኒየኖች የሚወዳደሩት በአካባቢው ከሚገኙ ነጋዴዎች ጋር መሆኑንና እነሱ በየጊዜው በሚያወጡት ዋጋ ላይ መመስረታቸውን አስረድተዋል። ለአርሶ አደሩ ነጋዴው የሚሰጠውን ዋጋ ልክ ካልሰጠነው አርሶ አደሩ ከዩኒየኖቹ ይሸሻል። ምክንያቱም ዓመት ሙሉ ሲለፋበት የነበረው ሰብል የተሻለ ዋጋ እንዲያወጣለት የሚፈልግ በመሆኑ ነው። ስለዚህ ዩኒየኑ ከነጋዴው ዋጋ ጋር የግድ መወዳደር ይጠበቅበታል። በመሆኑም በአሁን ወቅት ከነጋዴው ጋር አንገት ለአንገት ተያይዘው እየሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።
አርሶ አደሩን ከዩኒየኖች የበለጠ የሚያውቃቸው አለመኖሩን ያነሱት አቶ ለዓለም፤ በዘንድሮው ዓመት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ምርትና ምርታማነት የተሻሻለበትና ያደገበት መሆኑን ይናገራሉ። ነገር ግን የሰብል ዋጋ ደግሞ በተቃራኒው ዘንድሮ የተጋነነበት ዓመትም ነው። ይህ ደግሞ እርስ በእርሱ የሚጋጭና ግራ የሚጋባ ነገር ነው። የዚህ ችግር ፈጣሪዎች ነጋዴዎች በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት ጣልቃ ገብተው ሊሰሩ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ምክንያቱም አቅም ያለው ነጋዴ ሳይንሳዊ ያልሆነ ግምት በመስጠት ወደፊት ይወደዳል በሚል ስግብግብነት ምርቱን በራሱ እያከማቸ ዋጋው እንዲንር የሚያደርግበት እና ህብረት ስራዎችንም ከገበያው ለማስወጣት የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ ገበያን የማረጋጋት ትልቅ አቅም ያላቸውን ዩኒየኖች በመደገፍ መሀል ላይ ያለውን ደላላና ነጋዴ መንግስት ሊከላከል ይገባል።
ዩኒየኑ አርሶ አደሩ የሚፈልጋቸውን ግብዓቶች በወቅቱና በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ጀምሮ ከገበሬው ማሳ ላይ ምርቱን ይሰበስባል። በአካባቢው ያሉ ሞረትና ጅሩ፣ ሞጃና ወደራ ሲያደብር የሚባሉ ኩታ ገጠም የሆነ ሰፋፊ መሬት ደጋማ ቦታዎች በመኖራቸው እነዚህ ቦታዎች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም የሚያስችሉ ናቸው። በመሆኑ በትራክተር ማረስና በውቂያ ወቅትም የመውቂያ ማሽን ይቀርብላቸዋል።
በሌሎች አካባቢዎች የተበጣጠሰ መሬት ቢኖርም አሁን ላይ ላለው የዋጋ ንረት መነሻ ምክንያት አይደሉም። ምንም አይነት የአቅርቦት ችግር በሌለበት በዚህ ጊዜ የሚመለከታቸው አካላት ጣልቃ ገብተው ሊያስተካክሉ አልቻሉም። ነገር ግን የዋጋው ጉዳይ ከአምራቾች እጅ የወጣ በመሆኑ ሰዋዊ የሆነውን ችግር መቆጣጠር ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ከተቻለ ችግሩን መፍታት የሚቻል እንደሆነ አቶ ለዓለም ያነሳሉ።
የገበያው ሁኔታ በቀን ሁለት ጊዜና ከዛም በላይ ሊቀያየር እንደሚችል ያነሱት አቶ ለዓለም፤ የህብረት ሥራዎች ሚና የገበያውን ሚዛን ጠብቀው መሄድ ያለባቸው በመሆኑ አምራቹ ብቻ ሳይሆን ሸማቹም ተጠቃሚ እንዲሆን መታሰብ ያለበት ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/ 2013 ዓ.ም
Feel free to post your own predictions or discuss the writer predictions in the comments priligy united states