ከቱሪዝም ዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን መስህቦችን መጠበቅ፣ መዳረሻዎችን እንዲሁም መሠረተ ልማት መገንባት መሥራትን ይጠይቃል። ቅርሶችን ማደስ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ መመዝገብ ያለባቸውን ማስመዝገብ ወዘተ ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው።
ሌሎች የቱረስት ቆይታን የሚያራዝሙ ተግባሮችን ማከናወን ሌሎች የቱሪዝም ዘርፎች ላይ መሥራትም ያስፈልጋል። ከዘርፉ ይበልጥ ለመጠቀም እነዚሀ ሁሉ ላይበቁ ይችላሉ፤ የቱሪዝም ምርት አማራጮችን ማስፋት ያስፈልጋል።
የተለመዱን የቱሪዝም ምርቶች ብቻ ይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተዋዳዳሪ በመሆን ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ መሆን አይቻልም። ይህን የተረዱ ሀገሮች አዳዲስ አማራጮችን በመጠቀም በጥቂት የቱሪዝም ሀብቶቻቸው ከፍተኛ ሀብት ከዘርፉ ማግኘት እየቻሉ ነው።
ከእነዚህ አማራጮች መካከል አንዱ የዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርኮችና ጂኦቱሪዝም ዘርፍ ነው። በእዚህ ዘርፍ ጥብቅ ፓርኮችና መልክአ ምድሮች የየአካባቢያቸውን ማህበረሰቦች በሚገባ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል የሀገሮች ተሞክሮን ዋቢ ያደረጉ ወገኖች ይጠቁማሉ።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በ50 ሀገሮች 229 የዩኔስኮ ጂኦፓርኮች ይገኛሉ። በርካታ ጥብቅ ፓርኮችና መልክአ ምድሮች ያላት አፍሪካ ግን ሁለት ጂኦፓርኮችን ብቻ ነው በዩኔስኮ ያስመዘገበችው።
አትዮጵያ በእዚህ ተጠቃሚ ካልሆኑት ሀገሮች መካከል አንዷ ናት። ሀገሪቱ ይህን ሁኔታ ለመቀየር መሥራት ጀምራለች። በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል ወርክሾፕም በቅርቡ አካሂዳለች። የቱሪዝም ሚኒስቴር ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በእዚህ የዩኔስኮ ጂኦፓርኮችና ጂኦቱሪዝም ወርክሾፕ ላይ እንደተጠቆመውም፤ መንግሥት በጂኦፓርኮች ላይ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፤ ጂኦፓርኮቹንም የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው።
መድረኩ የዘርፉ ባለሙያዎች ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡበት፣ የዩኔስኮጂኦ ፓርኮችንና ጂኦቱሪዝምን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ የተሰጠበት ሲሆን፤ የልምድ ልውውጥ የተደረገበትም ሆኗል፤ ቀጣዩን ጊዜ ኢትዮጵያን ለዩኔስኮ ጂኦፓርኮችና ጂኦቱሪዝም ምቹ ለማድረግ ፈር ቀዳጅ ተብሏል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ ጂኦፓርኮች የምድርን ተፈጥሯዊ ታሪክ የሚነግረን፣ የሰው ልጆችን አኗኗር እና ጥንታዊነት በአጠቃላይ ከጂኦሎጂካል ስሪታቸው ጀምሮ ያለውን ሁኔታ አስተሳስሮ የያዘ የሳይንስ የምርምር ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዩኔስኮ ባለፉት አስርት ዓመታት ከልዩ የተፈጥሮ መስህብ ውስጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት የሚገኝ መሆኑንም አስታውቀዋል። ድርጅቱ የዓለምን ጂኦፓርኮችን የመጠበቅ፣ የመንከባከብና በፓርኮቹ ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ በዓለም አቀፍ ደረጃ 229 የሚሆኑ ጂኦፓርኮች መመዝገባቸውን አስታውቀው፣ አፍሪካን የሚያህል በተፈጥሮ ጸጋ የበለጸገ አህጉር ግን ሁለት ጂኦፓርኮች ብቻ ማስመዝገቡን በቁጭት ገልጸዋል። ይሄንን እውነታ ለመቀየር ማህበረሰቡን በጂኦፓርኮች ዙሪያ ማንቃት፣ የመስህብ ቦታዎችን ማስተዋወቅ፣ ስለሚኖራቸው ጥቅም ማስረዳት እና አስፈላጊነታቸውን ማሳወቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልምድ ያላቸው ግለሰቦች መገኘታቸው እንዲሁም በአፍሪካ ደረጃ በጂኦፓርክ ከተመዘገበችው ታንዛንያ የመጡ እንግዶች ተሳታፊ መሆናቸው፣ በምሥራቅ አፍሪካ ሰባት የሚሆኑ ሀገራት መገኘታቸውን እንደ ሀገር ጥሩ መንገድ እንደሚከፍት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በእዚህ ዘርፍ ውስጥ ትልቅ እና እምቅ አቅም እንዳላት ጠቅሰው፤ጂኦፓርኮቿን የማስመዝገብ፣ በአግባቡ የመያዝ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። የሀገሪቱ የቱሪዝም መስህቦች ተፈጥሮአዊ ይዘታቸው ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆን አመልክተው፤ ለምርምር አገልግሎት እንዲውሉና በአግባቡ እንዲያዙ እና በአካባቢያቸው ያሉ ማህበረሰቦች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከዩኔስኮ ጋር በትብብር እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በእዚህ ሂደት ውስጥ የሀገሪቱን ጂኦፓርኮች የመለየት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ ገልጸው፤ ለእዚህም የመልካ ቁንጥሬን ሳይት በአብነት ጠቅሰዋል። ጂኦፓርኮች እንደ ሌሎቹ ጥብቅ አካባቢዎች ተከልለው እና ተነጥለው የሚቀመጡ አይደሉም ያሉት ሚኒስትሯ፣ ዋና እና መሠረታዊ እሴታቸው ከማህበረሰቡ ጋር ተሳስሮ፣ ራሱ ማህበረሰቡ የሚያስተዳድራቸው፣ የሚጠቀምባቸው፣ የሚኮራባቸው መሆናቸውን አመላክተዋል።
ባለን እና በተሰጠን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ተጠቅመን በቱሪዝሙ ዘርፍ አይነተኛ ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የሁሉም ድርሻ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ መድረኩ ላይ የተነሱት የልምድ እና የተሞክሮ ሃሳቦች መሬት ወርደው ለውጥ ተኮር ሥራ እንዲፈጥሩ መትጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ኅብረትና ኢትዮጵያ የዩኔስኮ ተወካይ ሪትር ሱና(ዶ/ር) እንዳሉት፤ በአፍሪካ በጂኦፓርክ ተጠቃሚ እየሆኑ የሚገኙት ሞሮኮና ታንዛኒያ ብቻ ናቸው። በበለጸገ የተሪዝም ሀብቷ የምትታወቀው ኢትዮጵያም ለእዚህ ምቹ ናት። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ተረድቶ ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑ ሊደነቅ ይገባል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በዩኔስኮ ቅርሶቿን ያስመዘገበች ቀዳሚ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ በእዚህ እና በመሰል ሁኔታዎች በጂኦፓርክ ቀዳሚ የምትሆንበት እድል የሰፋ ነው ብለዋል።
ተወካይዋ እንዳስታወቁት፤ ጂኦፓርክ ለአንድ ሀገር እጅግ ወሳኝ ጥቅም አለው። ዓለም አቀፍ እውቅና ከማግኘት ጀምሮ የአካባቢውን ማህበረሰብ ከመጥቀም፣ በኢኮኖሚው የዳበረ ማህበረሰብ ከመፍጠር እና የራስን ሀብት በራስ ከመጠቀም አኳያ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጂኦሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት አስፋው ወሰን አስራት ከጂኦፓርክ እና ከጂኦሄርቴጅ ጋር በተያያዘ ብዙ መሥራታቸውን አስታውቀው፣ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ በተለይ በሥነህዳር ሀብት ከታወቁት ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት እንደምትጠቀስ አስታውቀዋል። ይህን በጣም ትልቅ ሀብት መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ጂኦፓርክ ከሌላው የጥብቅ አካባቢ ለየት የሚያደርገው የአካባቢው ማህበረሰብ ከመልካም ምድሩ እንዲጠቀም ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ላይ እንደሆነም ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ጂኦፓርክ አቃፊ የሥነምህዳር እሳቤ ነው። ይሄ ጥብቅ ቦታ ነው፣ ይሄ በዓለም አቀፍ የቅርስ መዝገብ ላይ የሰፈረ ነው፣ ሰዎች ከእዚህ ይራቁ በሚሉት አይነት ሥርዓት ስር አይደለም። ከሰዎች ጋር ትስስር ያለው መሆኑ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ቱሪስቶችን ተቀብሎ በማስተናገድ የሚገለጽበት ነው።
ፕሮፌሰሩም ኢትዮጵያ ያልተሠራባቸው እምቅ ሀብቶች እንዳሏት ጠቅሰው፤ ለአብነትም ሶፍ ኡመር ዋሻ፣ ሰሜን ተራሮች እንዲሁም ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች፣ የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች፣ ኤርታሌና ዳሎል፣ ገረአልታ ተራሮች ለጂኦፓርክ ምቹ የመልክአ ምድር መስህቦች መሆናቸውን አብራርተዋል።
በዩኔስኮ ቅርስነት የተመዘገቡትን ጥብቅ ቦታዎች በጂኦፓርክነት ማስመዝገብ ድርብ ድል እንደሆነ ተናግረው“ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ በቅርስነት ያስመዘገብናቸው ቅርሶች እንደየአስፈላጊነቱ ለሌላ የኢኮኖሚ ጥቅም የሚውሉበት አጋጣሚ መፈጠሩ ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ ዕድል መሆኑንም አስታውቀዋል።
ይህ ወርክሾፕ በኢትዮጵያ መካሄዱ የተፈጥሮ ሀብት እንዳለን እንድናውቅ፣ እንድንነቃ፣ ተጠቃሚ እንድንሆን ከሌሎች ሀገራት ጋር ትስስር የሚፈጥርልን ነው ሲሉ ገልጸዋል። የመልክአ ምድር እሳቤ የአንድ ወገን እሳቤ አይደለም ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ሁሉም ተቀናጅቶ እና ተነጋግሮ ለጋራ ጥቅም የሚሠራበት ነው ብለዋል። ቱሪዝም ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላትና ከየአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከሌሎች የሚመለከታቸው የሀገር ውስጥ እና የውጪ ባለሙያዎች ጋር ተናበው የሚሠሩበት ስለመሆኑም ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ቱሪስቶች ሀገሪቱን እንዲመርጡ፣ ለጉብኝት መጥተውም በአንድ እና በሁለት ቀናት ውስጥ እንዳይመለሱ፣ በመስህቦቿ ተማርከው ተመልሰው እንዲመጡ ለማድረግ በትኩረት መሥራት ይገባል።
በቱሪዝሙ ላይ ያልተሠሩ ሥራዎች አሉ፤ በዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ወሳኝ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል። የአካባቢው ማህበረሰብ ይሄን መስህቤን ለዩኔስኮ ላኩልኝ እና ይመዝገብልኝ ብሎ እስኪጠይቅ ድረስ የግንዛቤ ሥራ መሥራት ይገባል።
ትልቅ እና እምቅ የተፈጥሮ መልክአ ምድር ይዞ አፍሪካን በሚያህል ታላቅ አህጉር ውስጥ ሁለት ጂኦፓርኮች ብቻ መመዝገባቸው በዘርፉ እንዳልተሠራ ይጠቁማል። በውጪው ዓለም ማህበረሰቡ ዙሪያውን በመቃኘት ይሄ የኔ መልክአምድር ነው፤ በጂኦፓርክነት ይመዝገብልኝ የሚል ጥያቄ በማቅረብ ይታወቃል።
በአፍሪካ ደረጃ ሲታይ ግን እንደ ማህበረሰብ አይደለም እንደ መንግሥትም እነኚህን ዓይነት ጥያቄዎች ማንሳት አልተለመደም።
በማህበረሰብ ደረጃ ጥያቄን ማቅረብ ባልተለመደበት አህጉር እና ሀገር በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ያስቸግራል ሲሉ ፕሮፌሰር አስፋው ወሰን አስታውቀዋል። ይህን ችግር በመቅረፍ ከታች እስከ ላይ ኃላፊነት የሚሰማው አደረጃጀት ለመፍጠር እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴርን በአብነት ጠቅሰው፣ ሚኒስቴሩ ይሄን ጉዳይ ኃላፊነት ወስዶ በየደረጃው ካለው ማህበረሰብ ጋር ቢነጋገር የሁለቱ ቅንጅት በጂኦፓርኩ ላይ አይነተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
ማህበረሰቡ ራሱን ችሎ ብቻውን የሚናገርበትን ወቅት ለመፍጠር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በአውሮፓ እና በቻይና ያለው የጂኦፓርክ አስተሳሰብ ማህበረሰብ ተኮር መሆኑን ጠቁመው፣ በእዚህም ብዙ ለውጦችን ማስተናገድ መቻሉን ገልጸዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ በሀብት ደረጃ በአፍሪካ ያለው የመልክአ ምድር ጸጋ በሌላው ዓለም የለም። እነዚህን ጸጋዎች ወደ ጂኦፓርክነት ቢቀየሩ ፋይዳቸው ዓለም አቀፋዊ ይሆናል። ቱሪዝም የሀገር ዓርማ እና ከወሳኝ የኢኮኖሚ አውታሮች መካከል የሚመደብ፣ ከተጠቀምንበት ለውጥ ማምጣት የምንችልበት ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
የመድረኩ ታሳታፊ የታላቋ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ እንቁ ሙሉጌታ፤ ሥነምህዳርን በጂኦፓርክነት በመጠቀም ለሀገርና ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል። ጂኦፓርክ ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አኳያ ወደ ሥራ ለመግባት እንደ ሀገር ለምን እንደተዘገየ ተጠይቀው ሲመልሱም ችግሩን ከፖሊሲ ጋር አያይዘው ገልጸውታል።
አሁን እየቀረፍናቸው ካሉት ችግሮች መካከል ዋነኛው የፖሊሲ ችግር መሆኑ ታይቶ በተጠና አግባብ፣ በባለሙያ ውይይት አዋጪ የተባለ የጂኦፓርክ ፖሊሲ መዘጋጀቱን የሚቀረው ማጽደቅ መሆኑን ጠቁመዋል። እስካሁን የተመጣበት መንገድ በፖሊሲ ደረጃ ያልተዋቀረ መሆኑን ተናግረው፣ ከተግዳሮቶቹ በመነሳት አሁን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረስ መቻሉን አመላክተዋል።
ከሀገሮች ልምድ ለመቅሰም በተደረገ ሙከራ እስኪ ፖሊሲያችሁን አምጡ የሚል ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል። በዩኔስኮ በኩልም ሀገራችሁ እውቅና ያልሰጠችውን ሀብት እኛ እውቅና ልንሰጠው አንችልም የሚል ምላሽ እንደተሰጠም አስታውቀዋል።
ምንም እንኳን በተፈጥሮ ሥነምድር የታደልን ብንሆንም በፖሊሲ ደረጃ ግን ሌሎች ሀገራት ይበልጡናል ያሉት አቶ እንቁ፣ ብዙ ሀብት ይዘን መጠቀም ሳንችል የቆየነው ዘርፉ የሚፈልገውን ማሟላት ባለመቻላችን ነው ብለዋል። ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት አንድ ሁለት የተፈጥሮ ሥነ ምህዳሮችን ቢጠቅሱ ነው፤ ወደእኛ ሀገር ስንመጣ ግን ሁሉም ነገር አትኩሮት የሚስብ ሆኖ ታገኘዋለህ ሲሉም አመልክተው፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በጂኦፓርክነት ሊያስመዘግባት በሚችል የተፈጥሮ ውበት የታደለች መሆኗን ገልጸዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በተፈጠረ የፖሊሲ እና የአስተሳሰብ ለውጥ የኢኮ ቱሪዝሙ ዘርፍ እምርታ ማምጣቱን ጠቅሰው፤ በእስካሁኑ ሂደት ወደ ሃያ አምስት የሚጠጉ ጂኦፓርኮች እንደተለዩ ተናግረዋል። ሀብቶቻችንን ከማወቅ፣ ከመቁጠር እና ከመንከባከብ ወደ ተጠቃሚነት መሸጋገር የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል።
ለእዚህም ከፍተኛ ለውጥ እየታየበት ያለውን የሀገር ውስጥ የቱሪዝም ፍሰት በአብነት ጠቅሰዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ዜጎች የራሳቸውን ሀገር፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ተፈጥሮ መጎብኘት ጀምረዋል። እንደ ሀገር ውስጥ ጎብኚ ሁሉ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ለመሳብ እየተሠራ ነው።
ቱሪዝም በባህሪው ሰላም ይፈልጋል፤ ሰላም እና መረጋጋት ለቱሪዝሙ እድገት ወሳኝ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። ለውጪ ቱሪስቶች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ በኢግዚቢሽን፣ በኢንሴንቲቭ፣ እየተካካሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የደህንነት ዋስትናን በመስጠት በኤምባሲ፣ በዲፕሎማቶች በኩል ሀገራችን ያለችበትን የሰላም ደረጃ በመግለጽ ስጋት አልባ የቱሪዝም ምህዳር መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ለእዚህም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን መጠቀም ጥሩ መሆኑን ገልጸው፤ በእዚህ ጉዳይ ላይ ግን እንቅስቃሴ እንደማይታይ ጠቁመዋል። ለአብነትም ታንዛንያን እና ሩዋንዳን ጠቅሰው፤ ሀገሮቹ እንደ ቢቢሲ ያሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን በመጠቀም ራሳቸውን እያስተዋወቁ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
የአስጎብኚ ማህበራት አሁን ላይ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ተናበው እና ተጋግዘው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ይህ ወርክሾፕ ሊካሄድ የቻለው መንግሥት እኛን ማድመጥ በመቻሉ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ዘላለም ተሾመ