
የጋምቤላ ክልል የበርካታ ማዕድናት ሀብቶች ባለቤት ነው። በተለይ በወርቅ ማዕድኑ ይታወቃል። ክልሉ በሀገሪቱ በወርቅ አምራችነት ከሚታወቁ ክልሎች መካከል በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱት አንዱ ነው።
በሌሎች ወርቅ በሚመረትባቸው ክልሎች እንደሆነው ሁሉ በክልሉም የወርቅ ልማት በስፋት ቢካሄድም፣ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ መጠን ግን እየቀነሰ መጥቶ እንደነበር ይታወቃል።
በዚህ የተነሳም በሕገ ወጥ የወርቅ ዝውውርና ግብይት ሳቢያ አምራቹም፣ ክልሉም ሀገሪቱም ከወርቅ ሀብቱ በአግባቡ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቆይተዋል። በሕገ ወጥ ድርጊቱ የውጭ ሀገር ዜጎች ጭምር ተሳትፈውበት እንደነበረም ይታወቃል።
ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት ለመከላከል ከፌዴራልና ከክልል ጸጥታ አካላት የተወጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር በርካታ ሕገ ወጦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ይታወሳል። ይህ ርምጃ ተጠናክሮ በመቀጠሉም አንዳንድ ለውጦች መታየት ጀምረውም የነበረ ቢሆንም፣ ከዚህ ሀብት መገኘት ከሚገባው ጥቅም አኳያ ሲታይ ግን የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት ሳይቻል ቆይቷል።
ይሁን እንጂ በ2017 በጀት ዓመት መጀመሪያ መንግሥት ወደ ሙሉ ትግበራ ባስገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እየጨመረ መጥቷል። ሀገሪቱ በታሪክ ሆኖ በማያውቅ መልኩ በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ብቻ ወደ ውጭ ከተላከ ወርቅ ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ እንዳገኘች መረጃዎች ያመለክታሉ።
በጋምቤላ ክልልም ወደ ብሔራዊ ባንክ በሚገባው የወርቅ መጠን ለውጥ እየታየ ስለመሆኑ ከክልሉ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለእዚህ ለውጥ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተጨማሪ በክልሉ አንድ የወርቅ አምራች ኩባንያ ወደ ሥራ መግባቱ ሌላው ምክንያት መሆን ችሏል።
በክልሉ ወርቅ በብዛት ሲመረት የኖረው በባሕላዊ መንገድ ነው። በቅርቡ ደግሞ ወርቅ በከፍተኛ ደረጃ የሚያመርቱ ኩባንያዎች ብቅ ብቅ እያሉ ናቸው። ወርቅ ለማምረት ወደ ግንባታ ከገቡ የወርቅ አምራች ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ኢትኖ ማይኒንግ ግንባታውን አጠናቅቆ ሥራ መጀመሩ ይታወቃል።
እነዚህ ሁኔታዎች ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ማድረጋቸውን የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት መረጃም ያሳያል።
የጋምቤላ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡጁሉ ጊሎ እንደሚሉት፤ ክልሉ የበርካታ ማዕድናት ባለቤት ነው። በክልሉ ከሚገኙት ማዕድናት መካከል ወርቅ ተጠቃሹ ነው። ግራናይት፣ አሸዋና የኖራ ድንጋይን የመሳሰሉ ለኮንስትራክሽንና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናትም ይገኙበታል። ማዕድናቱን ለማልማት ፍቃድ ወስደው የተሠማሩ አካላትም በርካታ እየሆኑ መጥተዋል።
ክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ወርቅ ላይ ትኩረት አድርጎ ብዙ መሥራቱን ተከትሎ መሻሻሎች መምጣታቸውን የቢሮ ኃላፊው አመላክተዋል። በክልሉ በከፍተኛ የወርቅ ክምችታቸው አራት ወርቅ አምራች ወረዳዎች ተለይተዋል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እነሱም የጋምቤላ፣ አቦቦ፣ መንገሺና ዲማ ወረዳዎች መሆናቸውን አብራርተዋል። በወረዳዎቹ በባሕላዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ በርካታ አምራቾች እንዳሉም ጠቁመው፤ ወርቅ በብዛት እየተመረተ መሆኑንም ይገልጻሉ።
በ2017 በጀት ዓመት ሕገ ወጥነትን በመከላከል ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት በትኩረት መሠራቱን አመልክተው፣ በዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት አንድ ሺ 850 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት አቅዶ፤ አራት ሺ 254 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ባንኩ ማስገባት መቻሉን ይገልጻሉ።
ይህም ከእቅዱ አንጻር ሲታይ አፈጻጸሙ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም አንዱ ምክንያት የበጀት ዓመቱ እቅድ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል። እቅዱ የተዘጋጀው ባለፈው ዓመት በክልሉ የነበረውን የጸጥታና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደነበርም አስታውሰዋል። ባለፈው ዓመት በክልሉ በነበረው የጸጥታ ችግርና አለመረጋጋት የተነሳ ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው ወርቅ መጠን ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በወርቅ የተገኘውን ውጤት በዚህ ደረጃ ከፍተኛ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው መንግሥት ወደ ሙሉ ትግበራ ያስገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ነው። በክልሉ ከሰላምና ጸጥታ አኳያ መረጋገት መታየቱና ከፌዴራል ጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የተቀናጀ ክትትል መደረጉ እንዲሁም የወርቅ አምራቾች በተሻለ አቅም ማምረት መቻላቸው በክልሉ የሚመረተውና ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን ከፍተኛ እንዲሆን አድርገዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በክልሉ ወርቅ በአብዛኛው በባሕላዊ መንገድ በልዩ አነስተኛ ማህበራት እንደሚመረት ይገልጻሉ። ፍቃድ ወስደው በሕጋዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ እንዳሉ ሁሉ ፍቃድ ሳይኖራቸው በተለምዶ በወርቅ ማምረት ሥራ ላይ ገብተው የሚሠሩም አሉ ሲሉ ጠቅሰው፣ እነዚህ አካላት ወደ ሕጋዊ መንገድ እንዲመጡና የሚያመርቱትንም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ ወርቅ ለማምረት ከተቋቋሙት የወርቅ ፋብሪካዎች መካከል ኢትኖ ማይኒንግ ተጠቃሹ መሆኑን የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኩባንያው ባለፈው ኅዳር ወር ተመርቆ ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ 12 ኪሎ ግራም ወርቅ አምርቶ ወደ ብሔራዊ ባንክ ማስገባቱን ለክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ማሳወቁን ጠቅሰዋል።
ኩባንያው ከዚህ ጊዜ በኋላ ምንም ዓይነት ሪፖርት በመላክም ሆነ በሌሎች አማራጮች ተጠቅሞ ያለበትን ሁኔታ ለቢሮው ያሳወቀበት መንገድ እንደሌለ ጠቅሰው፤ ከወረዳውም ሆነ ከክልሉ ማዕድን ሀብት ቢሮ ግንኙነት እያደረገ አለመሆኑን ተናግረዋል። ችግር አጋጥሞት ከሆነም ለማወቅ እንዳልተቻለ አመልክተው፣ ቦታው ድረስ በመሄድ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ለከፍተኛ ደረጃ አምራች ኩባንያዎች ፍቃድ የሚሰጠውም ሆነ በበላይነት የሚከታተላቸው የማዕድን ሚኒስቴር መሆኑን ጠቅሰው፤ ኩባንያዎቹ ወደ ክልሉ ሲመጡ ክልሉ ቦታ እንደሚያቀርብ እንዲሁም የክትትልና ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ እንዳለም ይገልጻሉ። በዚህም የተነሳ ኢትኖ ማይኒንግ ኩባንያም ማምረቻ ቦታ ክልሉ ውስጥ እስከ ሆነ ድረስ ከክልሉ ማዕድን ሀብት ልማትና በተለይም ደግሞ ከወረዳው ጋር በመገናኘት በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል።
በክልሉ እስካሁን ድረስ ወርቅ በአራት ወረዳዎች ላይ እየተመረተ መሆኑ የሚጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በክልል ደረጃ በሌሎች አካባቢዎች ያለውን የወርቅ ክምችት ለማወቅ የሚያስችል ጥናት አለመደረጉን ይገልጻሉ። እስከ አሁንም ቀደም ሲል በማዕድን ሚኒስቴር በተደረጉ ጥናቶች ላይ በመመሥረት እየተሠራ መሆኑን ያመላክታሉ።
እነዚህ ጥናቶችም ቢሆኑ በክልሉ በየትኛው ወረዳ ምን ያህል የወርቅ ክምችት ይኖራል የሚለውን እንደማያመላክቱ ተናግረው፣ እንደዚያም ሆኖ ግን የክልሉ ማዕድናት ሀብት ማመላከቻ እነዚሁ ጥናቶች መሆናቸውንና እነሱን በመረጃነት እየተገለገለ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ማህበረሰቡ በራሱ በባሕላዊ መንገድ ወርቅ አለባቸው የተባሉ ቦታዎችን ለማረጋገጥ ሙከራዎች እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል። ወርቅ ያለበት ቦታ ከተለየ በኋላ በሰፊው ማምረት ወደሚያስችል ሥራ እንደሚገባም ይጠቁማሉ።
‹‹በተለምዶ ለወርቅ ፍለጋ የተቆፈሩ ጉድጓዶች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ወርቅ ይገኝባቸዋል ተብሎ ይታመናል፤ በትክክልም እየሆነ ያለውም ይሄ ነው›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በእንደዚህ ዓይነት መልኩ የወርቅ ማዕድን ያለበት ስፍራ እንደሚለይ ይገልጻሉ። በቀጣይ በክልሉ ያለውን የወርቅ ማዕድን ክምችት አቅም ለመለየት የሚያስችል ጥናት ለማካሄድ መታቀዱን ተናግረዋል።
በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት በማዕድን ዘርፉ በተለያዩ መልኩ ገቢ ለማስገኘት ሲሠራ ቆይቷል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከልዩ ልዩ ማዕድናት ልማትና ግብይት አንድ ሚሊዮን 500ሺ ብር ለማግኘት ታቅዶ፤ ከአንድ ሚሊዮን 870ሺ በላይ ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በወረዳ ደረጃ ከልዩ ልዩ የማዕድን ገቢዎች 43ሚሊዮን 500ሺ ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 81 ሚሊዮን 308ሺ 54 ገቢ ተሰብስቧል። በክልሉ ከማዕድን ዘርፍ 45 ሚሊዮን ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 83 ሚሊዮን 185ሺ 964 በላይ በመሰብሰብ ተችሏል። ይህም አፈጻጸሙ ከእቅድ በላይ እንደሆነ ያሳያል። ለዚህም ምክንያቱ ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት የተጠናከረ የክትትልና የድጋፍ ሥራ መሠራቱ መሆኑን አስገንዘበዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ ለብዙ ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ እድል ከሚፈጥሩ ዘርፎች መካከል የማዕድን ዘርፍ አንዱ ነው። በዘጠኝ ወራት የሥራ እድል በመፍጠር ረገድም የተሻለ አፈጻጻሙ ተመዝግቧል።
በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት የሚውሉ ማዕድናትና በወርቅ ምርትና ግብይት ለአምስት ሺ 760 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ታቅዶ፤ ለስድስት ሺ 050 ዜጎች (ቀጥተኛ ተሳትፎ ላላቸው ለ677 በቋሚነት እና ለ5372 በጊዜያዊነት) የሥራ እድል ተፈጥሯል። ከእነዚህ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ 21 በመቶ ያህል ነው።
በክልሉ የሚገኙ ማዕድናትን በተለይም ወርቅ በማምረት ረገድ ብዙ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙ ጠቅሰው፣ ወርቅ አምራቾች የሚያጋጥማቸው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በዋናነት እንደሚጠቀስ ጠቁመዋል። በጋ ሲሆን የውሃ እጥረት እንደሚያጋጥም አመልክተዋል። በተለይ በበጋ ወንዞች ስለሚቀነሱ ወርቅ ያለበትን አፈር ውሃ ወዳለበት ሩቅ አካባቢ ለማጓጓዝ እንደሚገደዱ ገልጸዋል። ይህም ወርቅ የማምረቱን ሥራ ጫና የበዛበት እንዲሆን እንደሚያደርገው አስታውቀዋል።
በቀጣይም የክልሉን ማዕድናት የማጥናትና የመለየት ሥራ እንደሚሠራ ተናግረው፣ በተለይ ወርቅ በሕገ ወጥ መንገድ እንዳይወጣና ወርቅ አምራቾች በአግባቡ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ እየተደረገ ያለው ክትትልና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል። የድጋፍና ክትትል ሥራው ከተጠናከረ አሁን ከተመዘገበው የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ ያስችላል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በወርቅ አምራቾች ዘንድ ባለው የወርቅ ልማትና ግብይት ላይ ግንዛቤን ለማስፋት ውይይቶች ይደረጋሉ። በዚህም ያመረቱትን ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ የማስገባት ጠቀሜታው ለራሳቸውና ለሀገር መሆኑን በደንብ እንዲረዱ ይደርጋል።
በማዕድን ዘርፉ በሕገ ወጥ መንገድ ወርቅን በተለያዩ መልኩ በሕገ ወጥ መንገድ እንዲወጣ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ሕገ ወጦች ሕጉን ተከትለው እንዲሠሩ ለማድረግ የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚካሄድም ገልጸዋል። እነዚህን ሥራዎች መሠረት በማድረግ መሥራት ከተቻለ በሚቀጥሉት ጊዜያት በማዕድን ዘርፉ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም አስታውቀዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም