በአስናቀ ፀጋዬ
በኢትዮጵያ በርካታ የመአድን ሀብት እንደሚገኙ በተለያዩ ግዜያት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ከከበሩት ጀምሮ ለኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ግብአትነት ልዩ ልዩ ማእድናት እንዳሉም እነዚሁ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ መአድናቱ በበቂ ጥናት ባለመረጋገጣቸው በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል። በጥናት የተረጋገጡትም ጥቂት መአድናት በመሆናቸው ከዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ጥቅም ማግኘት አልተቻለም። ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
በሀገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ክልሎችም በርካታ የመአድን ክምችት ሃብት አለ ብሎ ከማውራት በዘለለ መአድኑ በጥናት ተረጋግጦ ጥቅም ላይ ሲውል አይታይም። ከዚህ ይልቅ በአብዛኛዎቹ ክልሎች የኮንስትራክሽን መአድናት በተሻለ ሁኔታ ጥቅም ላይ ሲውሉ ይታያል። እነዚህን መአድናት በስፋት ጥቅም ላይ እያዋሉ ከሚገኙ የሀገሪቱ የክልል ዞኖች ውስጥ አንዱ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኘው ስልጤ ዞን ነው።
የስልጤ ዞን ውሃ፣ ማእንድና ኢነርጂ መመምሪያ ሃላፊ አቶ እስማኤል ወራቄ እንደሚሉት በዞኑ በአብዛኛው ለኮንስትራክሽን ግብአትነት የሚውሉ ማአድናት ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥም ተመርተው ለገበያ እየቀረቡ ያሉ የአሽዋ፣ ድንጋይና፣ ጠጠር ምርቶች ይጠቀሳሉ። መአድናቱ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ የሚገኙ ቢሆንም በዋናነት በተለይ የድንጋይ ምርት በውልባረግ ወረዳና በወራቤ ከተማ ዙሪያ ይገኛል። በተመሳሳይ የአሸዋ ምርትም በሶስት ወረዳዎች ላይ በዳሎቻ፣ ላንፋሮና ሚቶ ወረዳዎች ላይ በስፋት ይመረታል። ከአዲስ አበባ እስከ ጅማ ድረስም ለገበያ ይቀርባል።
ከዚህ አኳያም በዞኑ የኮንስትራክሽን መአድን ሃብቱ ገቢ እንዲያስገኝና ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንዲችል ታስቦ እየተሰራበት ይገኛል። በዚሁ መሰረትም የመአድን ሀብቱ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው እያመርቱ ለገበያ ያቀርባሉ። ከዚህ ባለፈም በተመጣጠነ ሁኔታ ከማእድን የሚገኘው ገቢ ለወረዳዎች ገቢ እንዲሆን ይደረጋል። በበጀት አመቱ የመጀመሪያው ስድስት ወራት ውስጥም 430 ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ ልማትና ለወጣቶች የሚፈጠሩ የስራ እድሎች ዘላቂ መሆን የሚገባቸው ቢሆኑም መምሪያው በዋናነት በዞኑ የሚገኘውን መአድን በዘላቂነት የማልማት ውስንነት ገጥሞታል። በዞኑ በውጤታማነት ማምረትና የለሙ ቦታዎችን መልሶ ከማልማት ጋር በተያያዘም ችግሮች ይታያሉ። እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም የኮንስትራክሽን ማአድን ማውጫ ስፍራዎች ከለሙ በኋላ ለህብረተሰቡ ምቹ እንዲሆኑ ከተፋሰስ ስራዎች ጋር በማስተሳሰር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢ የሚያደርሰውን ተፅእኖ ለመቀነስ ተመሳሳይ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
ከነዚህ የኮንስትራክሽን ማአድናት ውጪ በዞኑ ሌሎች የከበሩ ማአድናት በተለይ ደግሞ ግራናይትን የመሳሰሉና ለኢንዱስትሪ ግብአትነት የሚውሉ መአድናት ክምችቶችም እንዳሉ የሚታወቅ ቢሆንም ክምችታቸውና የጥራት ደረጃቸው ገና በጥናት አልተረጋገጠም። እስካሁን ድረስም ተጠንተው ወደስራ አልተገባባቸውም። ከዚህ አንፃር ባለሃብቱ በመአድን ማውጣት ስራ ገብቶ እንዲሰራ ይጠበቃል።
በመንግስት ደረጃም በመአድን ማውጣት ስራ ገብቶ ለመስራት የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጅቷል። ይሁንና ባለሃብቱ ዝርዝር ፕሮፖዛል ሰርቶ ገብቶ ከመስራትና መአድኑን ጥቅም ላይ ከማዋል አንፃር ውስንቶች በመኖራቸው ይህን ክፍተት ለመሙላት መምሪያው ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በተለይ ባለሀብቶች ለኢንዱስትሪ ግብአት በሚውሉ የመአድን ዘርፎች ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ማእድናቱ ይገኙባቸዋል ተብለው በሚታሰቡ ቦታዎች ላይ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ተደራሽ የሚያደርጉ መንገዶች ግንባታ ማከናወን ተጀምሯል። ወደዚህ የመአድን ልማት ገብተው ለሚያለሙ ባለሃብቶችም በከተማው የኢንዱስትሪ መንደር ተዘጋጅቷል። ይህንኑ የኢንዱስትሪ መንደር በመሰረተ ልማት የማሟላት ስራዎችም እየተከናወኑ ነው።
ሃላፊው እንደሚሉት ሌሎች መአድናትን በጥናት አውቆ ከማልማት አንፃርም ውስንነቶች ይታያሉ። ይህም ሊሆን የቻለው ከዞኑ አቅም በላይ በመሆኑና ዘርፉ እውቀት፣ ልምድ፣ የቴክኖሎጂ አቅምና የሰለጠነ የሰው ሃይል የሚጠይቅ በመሆኑ ነው። ከዚህ አኳያም ከወራቤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር መስራት የሚቻልበት ፕሮፖዛል እየተዘጋጀ ይገኛል።
ዞኑ ሰፊ የመአድን ሃብት እንዳለው ቢታወቅም አሁንም ድረስ ሀብቱን በስፋት በመጠቀም ረገድ ውስንነቶች ይታያሉ። እንደክልል ያለው ነባራዊ ሁኔታም ይህንኑ ያሳያል። ሆኖም ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በተለይ በበጀት አመቱ ግማሽ አመት በዞኑ ከመአድን ሃብቱ 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 12 ነጥብ 4 ሚሊዮን ያህሉን ማሳካት ተችሏል። መአድኑ በአካባቢው ያሉ ሌሎች ልማቶችን የማገዝ አቅሙ ተሻሽሏል።
ይሁንና የዞኑን መአድን ሃብት አሟጦ ከመጠቀምና ለህብረተሰቡ ጥቅም እንዲሰጥ ከማድረግ አኳያ በርካታ ጥረቶች ይቀራሉ። የዘርፉን መሰረታዊ ችግሮች መቅረፍ የሚቻል ከሆነና በዞኑ ያለው የመአድን ሃብት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መለየት የሚቻል ከሆነ በቀጣይ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። አዲስ ዘመን መጋቢት 27/ 2013 ዓ.ም