ብስለት
ሰው የመሆኔ ልክ ከእንስሶች አልቆ ካላሳየኝ፤ ሰው መሆኔ ዝርያውን ከማይበላው አውሬ በጥቂቱ ከፍ ከላደረገኝ ሰው ከመሆን ሰውሩኝ። መሰወር ያሰኘኝ ሰው በመሆን ውስጥ ሰው ለሰው መተዛዘን ያጣበት፤ ሰውነቱ ተረስቶ እገሌ ከዚህ ብሔር ስለሆነ ሞቱ የውሻ ሞት ያህል የማያስደነግጥበት፤ ሰው ሞቱ የቅጠል መርገፈን ያህል የማያስቆጭበት ዘመን ላይ በመቆሜ ሰው መሆን ሰቆኛል፤ ሰው ከመሆን ደብቁኝ፤ አሰኝቶኛል።
መወደድ መከባበሩ ቢቀርብን በሰበአዊነት መተዛዘኑ ጠፍቶ ሀገራችን ላይ ሊሆን ቀርቶ ሊደመጥ ስለመቻሉ የምንጠራጠረው ጉዳይ የእየለቱ የቀን መጀመሪያ የሞት የእልቂት ዜና በሆነበት በዚህ ወቅት ተፈጠረኩና የምሰወርበት ስርቻ ናፍቆኛል፤ የምደበቅበትን እሻለሁ ሰው ሆኜ ሰው ማዳን ከከበደኝ ሰው ከመሆን ሰውሩኝ ብያለሁ።
ሰዎች ከፍጥረቱ ጀምሮ ተንኮለኛ፥ ሸረኛ፥ ምቀኛ፥ ብሎም ደግ፣ አስተዋይ ሆነው በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ መስተጋብር ፈጥረው መኖር የሰው ፍጥረቱ መገለጫ ቢሆንም፤ ከአንዱ ብሔር ወንጀለኛ ሲገኝ ወንጀለኛው በወንጀሉ ልክ መጠየቅ ሲገባው የክፋት መጠሪያን ላንዱ ብሔር ሰጥቶ ስም መጠለሻሸቱ እርስ በእርስ መጠቋቆሩ በዝቶ ከሰው መሆን ልክ ዝቅ ብሎ ማንነት ትቢያ ውስጥ ስለተጣለ ሰው መሆን ሰቆኛል ሰው አልሁን የቀርበኝ፤ ሰው ከመሆን ቁጥር ከሰው ተራ አስጥሉኝ።
ሰውነቴን ነጥቆ ከብርሃን አክናፍ በአንድ የሚጥል፤ ሰው ከመሆን ነጥሎ ከሰማያ ሰማያት ወስዶ የሚዶል የሆነ ተአምር ነገር እሻለሁ፤ ወይም ከፅልመት ጉያ ወስዶ የሚከተኝ ብረሃን ነኝ እያልኩ ምግባሬ በጨለማ ከሚመላልሰኝ በሰው መሆን ውስጥ መታረድ መሞት መነቃቀፍ መጠላላት ሁሉም አይነት የጨለማ ስራ የክፋት መገለጫ በእኔ ከሚገለጥ በኔ ሰው መሆን ይቅርብኝ ሚናዬን ልለየው ወይ መልአክ ወይ ሰይጣን ልሁንና ያለምንም ገደብ ወይ ደግ ወይ ክፉ ተብዬ እፈረጅ ዘንድ እድል ስጡኝ እባካችሁ ልለምናችሁ ሰው ከመሆን አስጥሉኝ፤ እላለሁ።
ሰው መሆኔን እኔን አስረስቶ ቋንቋዬን አስጠፍቶ በሰውኛ መናገሬ ላይሰማ በአንዱ ሙሾ የሌላው ጭፈራ ገኖ ሲታይ ሰው መለኪያው ጠፍቶ ማንነቱ ምግባሩ ሳይታይ ሳይወድ የተፈጠረበት አከባቢ መለያው ሆኖ በተለጠፈበት መለያ የቤተ መቅደስን ያህል ክቡር ንፁህ የሆነው የሰው አካል እንዳልባሌ ሲፈርስ፤ መፍረሱ ደግሞ ከመጤፍ ሳይቆጠር በየቀኑ የእለት ከእለት ሙዚቃ ያህል ጆሬዬ ተለማምዶት፤ የእንባ ግድቤን ማፍረስ ሲያቅተው፤ ማንባቴም ከደመና በላይ ከፍ አልል ቢለኝ ሰው መሆን ቀርቶብኝ እንደ ብርሃን አለሞቹ ፍጥረታት ከፍ ብዬ እየበረርኩ የምድሩ ጩኸትን ከሰማየ ሰማያት አድርሼ መልስ አመጣላችሁ ዘንድ ሰው ከመሆን ተርታ አውጥታችሁ በሰውነት ልክ መኖር ለምን እንደተሳነን ልጠይቃችሁ ሰው ከመሆን አሰጥሉኝ ሰው መሆኔ ቀረቶ ሌላ በቃ ሌላውን ፍጥረት እንድሆን እድል ሰጡኝ። ወይም ደግሞ ልክ እንደ ንፋስ ባሻኝ ላይ የምገኝ፤ ስፈልግ እዚህ ጋ፤ ደግሞ ሲየሻኝ እዛ፤ ከሰቆቃው ቦታ ወጥቼ ወደ ሰላሙ የምነፍስ፤ የደም ሽታ ሲያሰጠላኝ ውሃው ላይ ሄጄ የማንዣብብ እሆን ዘንድ ሰው ከመሆን ክልል፤ ከሰው መሆን ድንበር እበካችሁን ነጥሉኝ፤ ሰው ከመሆን የሚለያየ አንዳች ነገር እንደላችሁ እማፀናለሁ ሰው መሆን በቀቶኛል።
ከአጥንት ከስጋ ከደምስር ፈትቼ፤ ስጋዬን እዚህ ጥዬ ረትቼ፤ ብቻ ቅልል ብዬ ከንፋሰ ንፋስ ብሎም ከአውሎ ንፋሰ ከትልቁ ንፋስ የተቀላቀልክ እለት ያኔ ሰው መሆኑን ረስቶ ከእንስሳዎች በታች እጅግ በጣም በታች በመሆን ክልል ውስጥ ሰውን እያረደ ፎቶ የሚነሳ፤ ሰው እያፈረሰ መኖሩን የረሳ፤ ሰው ለማለት ያህል ሰሙን አንጠልጥሎ፤ ከስጋ ላይ ስጋ የደራረበ ፈራሽ መሆኑን ሳያውቀው ሰውን ሰው ሲያፈርሰው ራሱ የሆነው የአፈር ላይ ሰሪት የሰው መሆን ዕዳ ሞተን በጀርባው ያዘለ እንደሆነ ረስቶ፤ ያንን ሰው መርጬ በራሱ አለም ውስጥ ለይቼ እንዳኖረው ሰው ከመሆን ድንበር ከሰው መሆን ክልል ባካችሁ አስጥሉኝ።
በማንም ክልከላ ውስጥ ያልወደቀ ፤ አጥር የሌለው ፤ሰው የመሆን ዳርቻ፤ ሰው የመሆኔን ድንበር ስጋዬን የሚያስጥል ልክ እንደንፋስ ከሁሉም የምገኝ፤ ከየስሜት አፍታ ላይ ሁሉንም ተመልካች ሁሉንም ተዛቢ ለመሆን ልታደል። ሰው ከመሆን ክልል ሰው መሆን ቀርቶብኝ በየስሜቱ ጫፍ እስክስታ ምደልቅ ከሀዘን ከደስታ ሚስጥር የምካፈል ብቻ ሰው ያልሆንኩኝ ልሁን፤ የሰው መሆን ህመም ዘለቆ የሚሰማኝ ህመሙንም ሳውቀው መፍትሄ ምሻለት ሰው ለመሆን ሳይሆን ከሰው በላይ ሆኜ ለሰው ምራራለት ለመሆን እሻለሁ ሰው መሆን አንሶኛል ሰው ከመሆን ክልል መለየት እሻለሁ ሰው ከመሆን ደንበር ልሰርዝ ልውጣበት ሰው ከመሆን ልዳን።
ከፅልመት ከብርሃን ከሁለቱም ጎራ ወገን የማልወግን፤ የእገሌ እኮ ነኝ ብዬ የማላወራ፤ ልክ እንደንፋስ የእገሌነት አጥር የእገሌ ድንበር ስም የማልደርብ፤ ከሁሉም የምገኝ ከሁሉ የምነፍስ ንፋስ የመሆን አምሮት አቅሌን አስቶኛል በጉጉት ላብድ ነው በምኞት ሰክሬ ፍጥረቴን ረስቼ እንደመንሳፈፍ እያደረገኝ ነው። ሰው ከመሆን ድውይ ሰው ከመሆን ህመም የምድንበትን መድሃኒት እሻለሁ። አፈሩን ምሳችሁ ቅጠሉን ቆረጣችሁ አቅምሱኝ ሰው መሆን ደጃፍ ላይ ዝር እንዳልል ሰዎች ሰው ከመሆን አብራክ ሰው ከመሆን ማህፀን ሰው ከመሆን ውልደት ሰው ከመሆን ሰውሩኝ።
ከአነተነህና ከአንቺ ነሽ የሚባልበት ሲያሻኝ ከሰሜኑ ሲለኝ ከደቡቡ ከምስራቅ ከምዕራብ ምንም ሳያሰጋኝ እንደልቤ እየነፈሰኩ የሀገሬን ድንቅ ውበት የሀገሬን ክፋት የሀገሬን ሀጥያት ብቻ ከህዝቡ ላይ ከሰማይ በታች ላይ እየተመላለስኩ መመልከት ንፋስ የመሆን አምሮት ሰቅዞ ይዞኛ ከክፋቱ ዘር ውስጥ የማልቆጠርበት ከልዩ የተለየሁ ለመሆን እሻለሁ ከሰው መሆነ ትውልድ እኔን ሰርዛችሁ ከንፋስ ውለዱኝ።
ሰው ማለት ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋለት ሲባል ሰምቻለሁ፤ ሰው ሆኜ ለሰው ከላዘንኩ ሰው ሆኜ ሰው ሲሞት ከእነእገሌ ስለሆነ የማይገደኝ ከሆነ ሰው ከመሆን ሰውሩኝ፤ ከሰው ተራ አውጡኝ። ቸር እንሰንብት!
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/ 2013 ዓ.ም