አዲሱ ገረመው
በ1962 በጅማ ከተማ ነው የተወለደው። እስከ ስምንተኛ ክፍል እዚያው ጅማ ተምሯል:: ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል አዲስ አበባ ሽመልስ ሀብቴ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል:: በመቀጠልም አዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ የኮሌጅ ትምህርቱን ተምሯል:: ቀጥሎ ሎሳንጀለስ ፊልም ትምህርት ቤት የፊልም ሥራን ተማረ:: ባለፉት ዓመታትም በርከት ያሉ ፊልሞችን በመድረስ፤ በማዘጋጀት፤ በመተወን ዝናን ማትረፍ ችሏል። አሁን ባለ ትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነው:: የዛሬው የዝነኞች የእረፍት ውሎ እንግዳችን አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ::
ከልጅነቱ ጀምሮ የህንድ ፊልም አዘውትሮ ይመለከት ነበር:: ይህ ተዋናይ የመሆን ፍላጎቱን አሳድጎለታል:: ጎን ለጎን የፎቶግራፍ ሙያን ይማር ነበር:: ይህም ከኪነ ጥበቡ ዓለም ጎራ እንዲሰለፍ ምክንያት ነበር:: ከኮሌጅ ከተመረቀ በኋላ በአዲስ አበባ በኋላም በጅማ የፎቶግራፍ አንሺ ሆኖ ሰርቷል::
የሴባስቶፖል መዝናኛ ኃ.የተ.የግ.ማ እና የቴዲ ስቱዲዮ” ባለቤት የሆነው ቴዎድሮስ፤ ፕሮዲውሰር፣ ደራሲና ዳይሬክተር ተዋናይ ነው:: የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪን በማነቃቃትም ይታወቃል:: በራሱ ፊልሞች ውስጥ ይመራል፣ ይጽፋል፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱና ብሄራዊ ይዘት ያላቸው ፊልሞችን ያዘጋጃል። ይህም እውቅናን ያተረፈ ነው::
በኢትዮጵያ የፊልም ታሪክ በሲኒማ ቤቶች ረዥም ጊዜ የቆዩና በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኙ “ቀዝቃዛ ወላፈን፣ ፍቅር ሲፈርድ፣ አባይ ወይስ ቬጋስ” እና ሌሎችንም ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የጥበብ ውጤቶችን ያበረከተ አርቲስት ነው:: በሀዋሳ፣ መቀሌ፣ ጅማና አምቦ ከተሞች ውስጥ የፊልምና ቴአትር ሙያን ያስፋፋም ስመጥር ነው:: ስኬታማ በሆነው ፊልሙ ላይ አባይ ወይስቬጋስ በመፃፍ እና በማዘጋጀት ተዋናይ ሆኖ በመስራት ከኢትዮጵያ ባህር ዳር እስከ አሜሪካው ላስ ቬጋስ፣ ኔቫዳ ድረስ ያለውን የፍቅር ትሪያንግል ታሪክ በመንገር የኪነ ጥበብ ቤተሰቡን አጃኢብ አሰኝቷል::
የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪ መነቃቃትን በማስጀመር እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ በፊልም ሥራ ከፍተኛ እድገት እንዲፈጠር ማገዙ በተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች ይነገርለታል:: እምነት ጽናትና ትዕግስት ደግሞ ለዚህ ስኬት አብቅተውታል::
አርቲስት ቴዎድሮስ አሁን 51ዓመቱ ነው:: “እንደገና መነሳት ችያለሁ” የሚለው ይህ ትንታግ አሁን ላይ ከፊልሙ ኢንዱስትሪ ባሻገር ሌሎች የቢዝነስ ተግባራት ላይ ተሰማርቷል:: “ግሮቭ ጋርደን ወክ” የመዝናኛ መናፈሻ የሰራ ሲሆን ወደፊት ትልቅ የፊልም ሲኒማ ለመክፈትም በዝግጅት ላይ ነው:: ምንግዜም እንደማይረፍድና ሁልጊዜም ነገሮችን ከዜሮ መጀመር እንደሚቻ ይመክራል::
የእረፍት ውሎ
አርቲስት ቴዎድሮስ አብዛኛውን ጊዜ በሥራ ስለሚያሳልፍ ብዙ እረፍት ጊዜ የለውም:: የተገኘውን የእረፍት ጊዜ አጋጣሚ ግን ሳያባክን ባለመው ነገር ላይ እንደሚያውል ነው የሚናገረው:: መጽሐፍ ማንበብ፣ ፊልም ማየትና ከልጆቹ ጋር በመዝናናት ያሳልፋል:: በተለይ ዘወትር እሁድ የማይነካውን የእረፍት ጊዜ የሚያሳልፈው ከልጆቹ ጋር ነው:: የውጭ አገር ጉዞ ካላደረገ በቀር ይህን ጊዜ ማንም እንደማይነካበትም ይናገራል::
አርቲስቱን ከልጆቹ ጋር እንደማሳለፍ የሚያስደስተው ነገር የለም:: “ከልጆች የሚገኘው ፍቅር ምንም አይነት ሚዛን የለውም:: ልጆች ሲወዱ የእውነት ነው፤ ሲቆጡም የእውነት ነው፤ ለዚህ ነው የልጆች ፍቅር የደስታ ልኬት የሌለው” ይላል::
መጽሐፍም እንዲሁ በመስጠት ላይ የተመሰረተ ስለሆነና እውቀትን ስለሚመግብ፣ እንዲሁም የአስተሳሰብ አድማስን ስለሚያሰፋ እንደ ጥሩ ፍቅረኛ መታየቱን አርቲስት ቴዎድሮስ ይገልጻል:: በዚህም ምክንያት ነው ያለውን የእረፍት ጊዜ ለማንበብ የተጠቀመበት::
መልዕክት
አርቲስቱ ለትውልዱ የሚያጋራው የህይወት ልምድና ምክር አለ “እንምራ፣ እንከተል ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን መንገዱን እንልቀቅ” ይላል። በመቀጠልም “ሁላችንም የተሰጠን መክሊት አለን:: የተሰጠን ሙያ አለ:: ተሰጥኦ አለ:: በነዚህ ሁሉ አገርን ማገዝ አለብን:: አገርን ማገዝ ማለት ሰልፍ ወጥቶ መበጥበጥ ማለት አይደለም:: አገርን ማገዝ ማለት የግድ ፖለቲከኛ መሆን ማለትም አይደለም:: ሁሉም በተሰማራበት መስክ እገዛ ማድረግ ይኖርበታል” በማለት ትውልዱ መልካሙን እንዲመርጥና እንዲይዝ መልዕክቱን ያስተላልፋል። እንደ እርሱ እምነት ሁሉም እንደ ሙያው ለአገሩ የድርሻውን ማበርከት አለበት “ሹፌሩ አገሩን የሚያግዘው አደጋ እንዳይደርስበት ተጠንቅቆ ህዝቡን በማድረስ ነው:: ፎቶግራፈር አገሩን የሚያግዘው በጥሩ ፎቶ አገሩን በማስተዋወቅ ነው” በማለት በምሳሌ ያስረዳል።
“ድንጋይ ይዞ መውጣት አገርን ማገዝ አይደለም” የሚለው አርቲስቱ፤ “ሁላችንም በምናውቀውና በተሰማራንበት ሙያ የተሰጠንን ኃላፊነት ስንወጣ ነው አገርን የምናግዘው:: እውቀቱ ያላቸው ሰዎች ይምሩ፤ የማይችሉት ይከተሉ፤ ከሁለቱም ያልሆኑት ደግሞ መንገዱን ይልቀቁ:: እኔ ፊልም ሰሪ ነኝ አገሬን የማግዘው ጥሩ አስተማሪና ትውልድን የሚቀርጽ ፊልም በመስራት ብቻ ነው” ሲል ከትውልዱ የሚጠበቀውን ኃላፊነት ያመላክታል::
እንደ አርቲስቱ ማብራሪያ፤ በተለይ ወጣቱ በተሰጠው መክሊትና ባለው እውቀት በተሰማራበት የሙያ መስክ ሥራውን በአግባቡ ሲወጣ ብቻ አገሩን ማገዝ እንደሚችል ይገልፃል “ሁሉም ነገር እውቀት ይጠይቃል በስሜት የምንነዳና በስሜት ተነሳስተን በጥፋት ውስጥ የምንሳተፍ ከሆነ አገር እያገዝን አይደለም” ይላል። አያይዞም “ኢትዮጵያ በብዙ ምክንያቶች እንደ አገር እንዳትቀጥል የሚፈልጉ ብዙ ጠላቶች አሏት:: እነዚህ ጠላቶች በህዝቡ የተለያዩ ስሜቶች ውስጥ እየገቡ በመበጥበጥ ላይ ይገኛሉ:: ይህ የሚሆነው ለምንድነው ብለን መጠየቅ አለብን” በማለት ትውልዱን ይሞግታል::
“የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ይህንን በማቃናት ረገድ ብዙ ድርሻ ነበራቸው ነገር ግን አቅም የላቸውም:: መንግስትም በዚህ ጉዳይ ሊያስበብት ይገባል” የሚለው አርቲስት ቴዎድሮስ፤ በመድረክ ላይ አሊያም በቴሌቪዥን “ፊልም ስሩ” ማለት ብቻውን ጥቅም የለውም ይላል:: እንዴትና የት ማሳየት እንደሚችል አቅም ያስፈልጋል:: ይሄንን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል:: ትውልድ የሚቀርጽ ሥራ ለመስራት ማሳያ አዳራሽና በጀትን ጨምሮ ትልቅ አቅም ይፈልጋል በማለት፤ ኪነ ጥበቡ እንዲመነድግ የባለ ድርሻ አካል ትኩረት እንደሚያስፈልግ በመግለፅ ሃሳቡን ይቋጫል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2013