ኢያሱ መሰለ
ታመነ በቀለ ይባላል። የተወለደው በ1971 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ዞን ጃርሶ ወረዳ፣ ቶርባን በተባለ የገጠር ቀበሌ ነው። ለቤተሰቦቹ ስድስተኛ ልጅ የሆነው የያኔው ብላቴና እድሜው ለትምህርት እስኪደርስ ከሰፈሩ ልጆች ጋር እየተጫወተ ማደጉን ያስታውሳል። ከዚያም ከፍ ሲል ትምህርት ቤት ገብቶ ፌደል መቁጠር ይጀምራል።
ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በጃርሶ አንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በነጆ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን መከታተሉን ይናገራል። ታመነ በ1992 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ወስዶ ውጤት በመጠባበቅ ላይ እንዳለ ያልታሰበ የጤና ችግር ይገጥመዋል።
አንድ ቀን በተለመደው የዘወትር እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳለ ሰውነቱ ይብረከረካል፤ ይደነዝዘዋል፤ ድካምና የጀርባ ትኩሳት ይሰማዋል፤ በተለይም እግሩን ማዘዝ ይሳነዋል። በኋላም መራመድ አቅቶት ተሳስሮ ይቀመጣል። ያ እንደልቡ የሚሯሯጠውና ቤተሰቦቹን በስራ የሚያግዘው ባለተስፋ ወጣት ህመሙ እየተባባሰበት ሄዶ የአልጋ ቁራኛ ይሆናል።
በሁኔታው የተደነጋገጡት ቤተሰቦቹ ያላቸውን ጥሪት እያሟጠጡ ታመነን በነጆ፣ ጊምቢ እና አሶሳ ሆስፒታሎች እያመላለሱ ቢያሳክሙትም የጤና ለውጥ ሳያገኝ ይቀራል። ህመሙ ቲቪ እንደሆነ ተነግሮት የቲቪ መድኃኒት እንዲወስድ ይደረጋል። ታመነ ግን የሰውነቱ በድንገት አለመታዘዝ ምናልባትም ከነርቭ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ጥርጣሬ ይገባዋል።
ኋላም ወደ ሌላ ሆስፒታል ሪፈር እንዲጽፉለት ጠይቆ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ይመጣል። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በተደረገለት ምርመራ ሃብለ ሰረሰሩ ላይ ውሃ የቋጠረ እጢ እንዳለበትና ይህም የነርቭ ችግር እንደፈጠረበት ይነገረዋል።
ወዲያው ኦፕሬሽን ተደርጎ ፈሳሹ ከተወገደለት በኋላ መጠነኛ እፎይታ ያገኛል። አመት ሳይቆይ ህመሙ ያገረሽበታል። ከግብርና ውጭ መተዳደሪያ የሌላቸው ቤተሰቦቹ የማሳከም አቅማቸው መዳከሙን የተረዳው ወጣት በራሱ ጥረት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ያፈላልግና ‹‹በሚሺነሪ ኦፍ ቻሪቲ ማዘር ትሬዛ›› ድርጅት ውስጥ ይታቀፋል።
የምግብ የማረፊያና የህክምና ወጪው ተችሎት ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሲረዳ ከቆየ በኋላ ድርጅቱ የሰጠውን የህክምና እድል እንደጨረሰ ተነግሮት ይወጣል። ድርጅቱ ወደ ቤተሰቦቹ ሊመልሰው እንደተዘጋጀ ይነግረዋል። እርሱ ግን ዳግም ቤተሰቦቹ ጋር ሄዶ ሸክም መሆን ስላልፈለገ እራሱን ችሎ ለመኖር በማሰብ አዲስ አበባ መቀመጥን ይመርጣል።
እርሱ እቤት ተኝቶ ቤተሰቦቹ የግብርና ስራ ሰርተው እየመጡ የሚያደርጉለት እንክብካቤ ያሳቅቀው እንደነበር ታመነ ያስታውሳል። እቤት ተኝቶ የሚበላው ምግብ እንደ ግራዋና እሬት ይመረው እንደበር ይገልጻል። ያም ብቻ ሳይሆን ገጠር ሲኖር በዊልቸር የመንቀሳቀስ እድል እንኳን አያገኝም። በነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ነበር ወደ ቤተሰቦቹ መመለስ ያልፈለገው።
ድርጅቱ ካሰናበተው በኋላ ታመነ ጎዳና ላይ ተኝቶ ሰዎችን እየተማጸነ መኖር ይጀምራል። የጎዳና ህይወት ግን እርሱ እንዳሰበው ቀላል አልነበረም። ህመሙ ይባባስበታል፤ ተኝቶ የሚውልበት ታፋው ይቆስላል። ለጥቂት ወራት ህይወቱን በጎዳና ላይ የመራው ታመነ ሁኔታዎች ሲከብዱት እንደገና ያንኑ ድርጅት ተማጽኖ ወደ ነበረበት ድርጅት ይመለሳል።
ከህመሙ በላይ ፈተና የሆነበት የስነ ልቦና ችግር እንደነበር ያስታውሳል። ሰዎች ለሰዎች መድኃኒት እንደመሆናቸው መጠን አንዳንዶች ግን አካል ጉዳተኞች ራዕይ እንደሌላቸው በማሰብ የሚያደርሱበት የስነ ልቦና ጫና ከባድ እንደነበር ያስታውሳል። ያንን ሁሉ አልፎ ዛሬ ባለበት ደረጃ ላይ መድረሱን ሲያስብ ይገርመዋል።
ታመነ ዳግም ወደ እርዳታ ድርጅቱ ሲመለስ የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን መለማመድ ይጀምራል፤ እንደ እስካርቭ፣ ኮፊያና ፎጣዎችን እየሠራ የተወሰኑትንም ከሽሮ ሜዳ እያስመጣ ለውጭ ዜጎች መሸጥ ይጀምራል። አንዳንዴም የጆሊ ጁስ ፓውደሮችን እየበጠበጠ በድርጅቱ ለሚገኙ ሰዎች በመሸጥ መጠነኛ ገቢ ማግኘት ይጀምራል።
በጥቁር አንበሳና በየካቲት ሆስፒታል ጀርባው ላይ ሶስት ጊዜ፣ ታፋው ላይ ሁለት ጊዜ፣ በድምሩ አምስት ጊዜ ኦፕሬሽን ቢደረግም ሊሻለው አልቻለም። የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከዚህ በኋላ የሀገር ውስጥ ህክምናውን እንደጨረሰና የተሻለ ህክምና ሊያገኝ የሚችለው ውጭ ሀገር ከሄደ ብቻ እንደሆነ በመጥቀስ ያስናብተዋል።
ይህ የህክምና ውጤት ሲነገረው ታመነ ስሜቱ ክፉኛ እንደተጎዳና መኖርን ጠልቶ እንደነበር ያወሳል። በመኖርና ባለመኖር መካከል ከራሱ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባው አካል ጉዳተኛ ወጣት ሠርቶ መኖር እንደሚችል እራሱን አሳምኖ ከህይወት ጋር ትግል ለመጀመር ይዘጋጃል።
ለሁለተኛ ጊዜ ከበጎ አድራጎት ድርጅቱ በ2001 ዓ.ም ሲሰናበት በእጁ የተሰጠው ሶስት መቶ ብር ብቻ ነበር። ነገር ግን እየሠራ ያጠራቀማትን ትንሽ ገንዘብ እና ከአንድ የውጭ ዜጋ የተለገሰውን አምስት ሺህ ብር ይዞ ወደ ሥራ ይገባል። የመጀመሪያ እርምጃው ቤት መከራየት ነበር። በወቅቱ አንዲት ጠባብ ክፍል በአምስት መቶ ብር ይከራያል።
ከዚያም አምስት ኪሎ ብሄራዊ ሙዚየም መግቢያ በር አጠገብ መጠነኛ ሸቀጥ በተንቀሳቃሽ ጋሪ ላይ አድርጎ መነገድ ይጀምራል። የሙዚየሙ ኃላፊዎችና የጥበቃ ሠራተኞቹ ትብብርና ድጋፍ እራሱን ችሎ ለመኖር ያደረገለትን አስተዋጽኦ በልዩ ሁኔታ ያነሳል።
ዊልቸሩ ላይ ቁጭ ብሎ የሚነግደው አካል ጉዳተኛ ቀን ቀን እየሠራ ማታ እቃውን እዚያው በር ላይ ለሚያድሩ የጥበቃ ሠራተኞች እየተወ ወደ ቤቱ ይሄዳል። ዛሬም ድረስ የሙዚየሙ ድጋፍ እንዳልተለየው የሚናገረው ታመነ ኃላፊዎቹና ጥበቃዎቹ የመኖሩ ምስጢር መሆናቸውን በመጥቀስ ምስጋና ያቀርብላቸዋል። የብሉ ቶፕ ሆቴል ያደርግለት የነበረውን የምግብ ድጋፍም አይረሳውም።
ታመነ መኖር ሲጀምር አጋዥ የምትሆነውን ታናሽ እህቱን ከሀገር ቤት አስመጥቶ አጠገቡ ያስቀምጣል። ልብሱን ታጥብለታለች፤ ምግቡን ታበስልለታለች፤ ነግዶ በሚያገኛት ገንዘብ የቤት ወጪውን እየሸፈነ ለመኖር ይጥራል፤ በዚህም ላይ ያስተምራታል።
በሥራው የሚበረታቱትና የሚረዱት እንዳሉ ሁሉ እንቅፋት የሚሆኑበትም መኖራቸውን ታመነ ይናገራል። በተለይም ደንብ አስከባሪዎች ከአንድም ሁለት ጊዜ ህገ ወጥ ነጋዴ ነህ በሚል እቃውን እየወሰዱበት እንዳጉላሉት ያስታውሳል።
ከዚያም ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት እየመጡ እንደሚያስፈራሩት ይገልጻል፤ መንገድ ላይ ቁጭ ብሎ በሚለምን ሰዓት ያልተናገሩት አሁን ራሱን ችሎ ለመኖር ጥረት ሲያደርግ ህገ ወጥ ነህ ብለው ማሳደዳቸው ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራል።
አካል ጉዳተኛ ሠርቶ ሲበላ ሊበረታታ እንጂ ሊወገዝ አይገባውም የሚለው ታመነ እራሳቸውን አሸንፈው ለመኖር የሚጥሩ አካል ጉዳተኞችን ለሌሎች ምሳሌ ናቸው ይላል። ታመነ በወር ወይም በ20 ቀን አንድ ጊዜ ዊልቸሩ ላይ ተቀምጦ መርካቶ በመሄድ የሚፈልጋቸውን እቃዎች እየገዛ ይመጣል። ያን እየሸጠ ህይወቱን ይገፋል። ከሰኞ እስከ አርብ አምስት ኪሎ ብሄራዊ ሙዚየም በር ላይ፤ ቅዳሜና እሁድ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት አጠገብ ይሠራል።
ሳምንቱን በሙሉ ጠዋት እየወጣ ማታ ይገባል። ሠርቶ መኖሩ፤ በልቶ ማደሩና ለብሶ መውጣቱ እንደሚያስደስተው ይገልጻል። አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም የሚለው ታመነ ሁሉም አካል ጉዳተኛ የሥራ ሁኔታ ቢመቻችለት ሠርቶ የመኖር ፍላጎት እንዳለው ይገልጻል። ታመነ ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ዊልቸር ለማግኘት ተቸግሮ እንደነበር ይገልጻል።
ከሰውነቱ ክብደት መጨመር ጋር በተያያዘ በየጊዜው የሚገዛው ዊልቸር ስለሚበላሽበት ከአንድ ዓመት በላይ አገልግሎት አይሰጠውም። በየዓመቱ ያገለገሉ ዊልቸሮችን ከአምስት እስከ ስድስት ሺህ ብር እየገዛ እንደሚጠቀም ይገልጻል።
መንገዶችና ህንጻዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ እያደረጉ ባለመሠራታቸው ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች መጋለጡን ይናገራል። በተለይም ጉዳይ ለማስፈጸም ወደ ቀበሌና ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ሲሄድ ሕንጻውን በዊልቸር መውጣት ስለማይቻል የሚፈልጋቸውን ኃላፊዎች በመግቢያና መውጫ ሰዓት ብቻ በር ላይ እየጠበቀ ለማናገር መገደዱን ይገልጻል።
ታመነ ከሥራው ጎን ለጎን በ2003 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ፈተናን በግል ተፈትኖ ባስመዘገበው ውጤት መሰረት የመሰናዶ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ለሁለት ዓመት ተከታትሏል። ከዚያም በኋላ ማትሪክ አልፎ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይመደባል። ትምህርቱን በመማር ላይ እያለ የህክምና ቀጠሮ ይደርስበትና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለሶስተኛ ጊዜ ቀዶ ጥገና ያደርጋል።
በዚህን ምክንያት ትምህርቱን አቋርጦ ህክምናውን መከታተል ይጀምራል። ከህመሙ ቶሎ ማገገም ባለመቻሉ ዊዝድሯል ሞልቶ ይወጣል። ዛሬም በጤና ችግርና በኑሮው ሁኔታ የሚፈተነው ታመነ ከነገ ዛሬ ህይወቴን ለውጬ ወደ ትምህርቴ እመለሳለሁ ቢልም ምንም ጠብ የሚል ነገር ባለማግኘቱ እስከ አሁን ትምህርቱን እንዳቋረጠ ይገኛል።
ትዳር መያዝ ልጅ ወልዶ መሳም ይመኛል፤ ነገር ግን በደረሰበት የነርቭ ችግር ምክንያት ምኞቱን እውን ማድረግ እንደሚያዳግተው ታመነ ይገልጻል። አሁን ግን የወንድሞቹንና የእህቶቹን ልጆች ተራ በተራ እያስተማረ ለቁም ነገር በማድረስ ላይ ይገኛል።
ከቤተሰብ ሸክም ወጥቶ ለቤተሰቡ መድህን የሆነው አካል ጉዳተኛ እስከ አሁን አራት የሚሆኑ የቤተሰቡን አባላት አስተምሮ ለቁም ነገር እንዳበቃ ይገልጻል። ታመነ ከኪራይ ቤት ወጥቶ የቀበሌ ቤት ቢሰጠውም የተሰጠችው የኮንቴነር ቤት ከእርሱ ጤንነት ጋር የማትሄድ በመሆኑ መቸገሩን ይናገራል። ታመነ የሚኖርባት ቤት እንደሌሎች የቀበሌ ቤቶች ከጭቃ ወይም ከብሎኬት የተሠራች ሳትሆን በአንድ የቀበሌ ቤቶች ግቢ ውስጥ የተቀመጠች ኮንቴነር ነች።
ኮንቴነሯ በበጋ ትሞቃለች፤ በክረምት ትቀዘቅዛለች። ቤቷን የሰጠው የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ሲሆን እንደቤት የተመዘገበ የቤት ቁጥር የላትም። ማብሰያዋም መተኛዋም እዚያው ነው። ለአካል ጉዳተኛ ምቹ የሆነ የመፀዳጃ ቤት በግቢው ውስጥ ባለመኖሩ ታመነ ፖፖ ላይ ነው የሚፀዳዳው በዝችው ኮንቴነር ውስጥ ነው።
አንድ ጊዜ ያጋጠመውን ክስተት ታመነ እንዲህ ይገልጻል። ምሽት ነው፤ ከሰል አያይዘው ምግብ አብስለው ይበሉና ይተኛሉ። ከትንሽ ሰዓት በኋላ ታመነ እንደማፈን ሲለው ቶሎ ብሎ ከተኛበት ይነሳና ሌሎቹንም ይቀሰቅሳል። ሁሉም ከእንቅልፉ ሲነቃ ምግብ እያበሰለች የምትንከባከባቸው የእህቱ ልጅ ሳትነቃ ትቀራለች። በከሰሉ ጭስ በጣም ታፍና ስለነበር በተኛችበት አረፋ ደፍቃ ታንኳራፋለች፤ እንደምንም ዊልቸር ላይ አስቀምጠው ሀኪም ቤት አድርሰዋት በህክምና እርዳታ እንደዳነች ያስታውሳል።
አሁን ታመነ ከጤናው ጋር የሚሄድና ትንሽ ሰፋ ያለ ቤት እንዲሰጠው አመልክቶ በመጠባበቅ ላይ እንዳለ ይናገራል።
ከኮቪድ-19 መከሰት ጋር ተያይዞ ቱሪስቶች በመቅረታቸው የገቢ ምንጩ እንደቀነሰበት ይናገራል። የእቃዎች ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ እንደታየበት የሚገልጸው ታመነ ሰዎች አልባሳትን የመግዛት ፍላጎት እንደሌላቸውና የኑሮ ውድነቱ እየፈተነው መሆኑን ይናገራል። በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም ኑሮውን ለማሸነፍ እየታገለ ይገኛል።
አካል ጉዳተኞችን ማበረታታት ከልመና እንዲወጡና ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ የመንግሥትና የባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ነው ሲል ታመነ ይናገራል። ከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ይገልጻል። በተለይም ኢትዮጵያ አካል ጉዳተኝነትን አስመልክቶ የፈረመችውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ማክበር ይኖርባታል ይላል ታመነ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም