
ኢትዮጵያ አብዛኛውን የግብርና ምርቶች በጥሬው ወደ ውጭ የምትልክ ሀገር በመሆኗ እሴት በመጨመር ማግኘት የሚገባትን ተጨማሪ ጥቅም ለሌሎች አሳልፋ ስትሰጥ ኖራለች። ይህም ሀገሪቱ በዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ ተግዳሮት ሆኗ ዘልቋል።
የግብርና ምርቶች ላይ እሴት እየጨመሩ ከመላክ አንጻር አሁን ምን እንመስላለን? ምን ተግዳሮቶች አሉብን? በምን መልኩ ብንሠራ ውጤታማ መሆን እንችላለን? በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ ተነግሯል አሁንም እየተነገረ ነው ።
በርግጥ እንደሀገር በግብርና ምርቶች ላይ እሴት መጨመር ላይ ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም አሁንም ችግሩ በብዙ መልኩ የሚስተዋል ነው። ብዙዎች ለችግሩ በዋነኛነት ተጠቃሽ የሆነው በዘርፉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በሚገባ አለመጠቀም ወይም በሚፈለገው መጠን አለመኖሩ እንደሆነ ይስማማሉ።
በተለይ ለማቀነባበር፣ ለማሸግ፣ ጥራት ለማስጠበቅ፣ የተቀነባበረውን ለመላክ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ማምጣትና መተግበር ይጠይቃል። አብዛኛውን ጊዜ ከውጭ የምናመጣቸው ማሽኖችና ቴክኖሎጂዎች የእውቀት ሽግግር ላይ የተወሰነ ክፍተቶች አሉባቸው።
የመሠረተ ልማት ተግዳሮትም ሌላው ተጠቃሽ ችግር ነው። የግብርና ምርቶች የሚመረቱባቸው ቦታዎች ፋብሪካዎች ካሉበት ራቅ ያሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ወደ ፋብሪካ ለማምጣት የተሳለጠ የመንገድ መሠረተ ልማት ያስፈልጋል። ቶሎ የሚበላሹ እንደ ወተት፣ ፍራፍሬ ዓይነቶቹ የራሳቸው ማቀዝቀዣ ያላቸው ትራንስፖርት የሚፈልጉ በመሆናቸው በወቅቱ የሚቀርብበት ሁኔታ አለመኖሩ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው።
የኤሌክትሪክ ኃይል ተጨማሪ ችግር እንደሆነም የሚያነሱ አሉ። ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲሠሩ የኤሌክትሪክ ኃይል መኖሩ ወሳኝ ስለሆነ በሚፈለገው ደረጃ እየቀረበ እንዳልሆነ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ከሚያቀርቧቸው የጥናት ሪፖርቶች መረዳት ይቻላል። በተጨማሪም የማከማቻ መጋዘኖች እጥረትም መኖሩ ምርት በሚኖርበት ጊዜ አከማችቶ ዓመቱን ሙሉ አቀነባበሮ ለመሸጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል።
የፋይናንስ እጥረት ከተግዳሮቶቹ መካከል የሚጠቀስ ነው፤ መጠነኛ የሆነ ፋብሪካ ለመገንባት ፋይናንስ የሚያስፈልግ ቢሆንም የብድር አገልግሎትም ሆነ ሌሎች የፋይናንስ ምንጮችም በብዛት ለማግኘት ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። ይህ የፋይናንስ እጥረት ትልልቅ ፋብሪካዎች እንዳይገነቡ፣ ከተገነቡም በኋላ ጥሬ እቃ በሚፈለገው መጠን እንዳይገዙ ይደረጋል። የሠለጠነ የሰው ኃይል ቀጥሮ ለማሠራት ከፍተኛ የሆነ ፋይናንስ እጥረት ስለሚያጋጥም ይህንን የሚሸፈን ፋይናንስና የብድር አገልግሎት በበቂ ሁኔታ አይገኝም።
በሀገሪቱ አብዛኛውን ግብዓት የሚያቀርቡ 95 በመቶ በሚሆኑት አነስተኛ አርሶ አደሮች ወይም ባህላዊ የእርሻ ሥርዓትን በሚጠቀሙ ግለሰቦች ነው። ይህም ምርቱን ከአንድ ቦታ ገዝቶ ወደ ፋብሪካ ለማምጣት አስቸጋሪ ያደርገዋል። አሁን ላይ የተጀመረው በክላስተር ማምረት በተወሰነ መልኩ ችግር እየፈታ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት የወጡ አዋጆችም በኮንትራት መልክ በአንድ አድርጎ አምራቹንና ፋብሪካውን ማስተሳሰር እንደሚያስችልም የታመነበት ነው።
እንደሀገር ለዘመናት ይዘን የመጣነው ልምድ እሴት ጨምሮ መላክ ሳይሆን ጥሬው መላክ ነው፤ በጥሬው መላክ ቀላል ስለሆነ ላኪዎች ቢሆን በተለመደ መንገድ መፍሰስ መፈለጉ በራሱ ችግር ነው። ለረጅም ዘመናት በላኪነት ተሠማርተው የቆዩ ነጋዴዎች ምርቶቻቸውን በተሻለ ዘመናዊ መሣሪያ ፕሮሰስ በማድረግ ለዜጎች የሥራ ዕድል፤ ለነሱም ተጨማሪ ገቢን ከማግኘት ይልቅ በቀላሉ ከገበሬው ገዝተው መላክን ይመርጣሉ። ይሄውም ችግር ለዘመናት በመቆየቱ የራሳችንን የግብርና ምርት እሴት ተጨምሮበት በእጥፍ ዋጋ መልሰን እንድንሸምት እንገደዳለን።
ዘመናዊ የሆኑ የጥራት ማረጋገጫ ስልቶች፣ ላብራቶሪዎች እና በዘርፉ በበቂ ሁኔታ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖሩ ለዘርፉ ተጨማሪ ችግር ነው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛው ታዳጊ ሀገር ጥሬ እቃዎች ወደ ውጭ ይልካሉ። በሀገሪቱ ቡና፣ እንስሳት፣ ሰሊጥ እና የመሳሰሉት የግብርና ውጤቶች ዕሴት ሳይጨመርባቸው ጥሬ እቃው ይልካሉ። ሀገር ውስጥ ያሉ አምራቾች አቅማቸው ዝቅተኛ መሆኑ፤ ከሌሎች ሀገራት ጋር ለመወዳደር የሚያስችል አቅም እንዳልፈጠሩም ግልጽ ነው።
እንደአሜሪካ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬት፣ ቻይናና የመሳሰሉ ሀገራት ቡናን ከኢትዮጵያ ወሰደው ዕሴት ጨምረው ይሸጣሉ። በተለይ ቅመማ ቅመምና ሰሊጥ ምርቶች ከእኛ ገዝተው ዕሴት ጨምረው ይሸጣሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና መገኛ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ቡና ላኪ የሆነችው ሀገራችን እምብዛም ዕሴት የተጨመረበት አስተሻሸጉ ዓለማቀፍ ስታንዳርድን የጠበቀ ቡና ላኪ ስለሌላት በየዓመቱ ብዙ ሚሊዮኖችን ታጣለች።
ቡና ላይ ብቻ ሳይሆን እንደሀገር ዕሴት መጨመር ላይ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት ያለባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ።
የግብርና ኢንቨስትመንት በስፋት ይካሄዳል። ግብርና ላይ የፈሰሰውን መዋለ ንዋይ ደግሞ እንደየምርት ዓይነት ፋብሪካዎች በስፋት መገንባት ላይ ትኩረት መደረግ አለበት። የጥራት ማረጋገጫዎችን ማጠናከርና የጥራት ቁጥጥር የሚመጣበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል።
የትራንስፖርት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። በተጨማሪ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ላይ መሥራት ስለሚያስፈልግ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመጠቀም የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልምድ ልውውጥ ማድረግ ይጠይቃል።
የምርቶች መለያ (ብራንድ) መገንባት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ነው። የኢትዮጵያ ምርቶች በተፈጥሯቸው የራሳቸው የሆነ ጣዕም ስላላቸው ወተትና የወተት ተዋፅዖ፣ እንቁላል፣ ሥጋ እና ቡና፣ ቅመማ ቅመምና የመሳሰሉት ምርቶች ከሌሎች ዓለም የሚለዩባቸው የራሳቸው ጣዕምና ጥራት አላቸው። ይህንን ተጠቅሞ ብራንድ ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የሚያስፈልግ ነው። ምርቶቹ ከዓለም የሚለዩበት የተለየ ሁኔታ እንዳለ ማመላከቱ ላይ ከፍተኛ ሥራን መሥራትም ያስፈልጋል።
ምርትን በክላስተር ማምረትና የኮንትራት እርሻዎች ማጠናከር ለአምራቾችም ሆነ ለባለፋብሪካው ስለሚጠቅም የወጡ ሕጎች ተግባራዊ እንዲደረጉ ክትትል ማድረግ፤ ጠንከር ያሉ ሕጎች ለባንኮችና ለግል ባለሀብቶች ማውጣት በተወሰነ መልኩ ማኑፋክቸሪንግ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መደረግ፤ በተመሳሳይ ባንኮችም እንዲሁ ለማኑፋክቸሪንጉ ዘርፍ የሚያበደሩትን ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል።
ይሄንን ማድረግ የማንችል ከሆነ ግን ዓለም ውድድር በመሆኑ ሌሎች ጥለውን እንዲያልፉ ዕድል እንሰጣለን። እሮጠን መቅደም ቢያቅተን እንኳን ጥሩ ተከታይ ወይም ተፎካካሪ መሆን ይገባናል። ይህንን ካላደረግን የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማት ነውና ነገሩ የራሳችንን ምርት ቅርጽ እና ማሸጊያ ቀይረው በሚያመጡ ብልሆች የምንታለል እንሆናለን። የሰጡትን በእጥፍ የሚመልስ መሬት፤ የዘሩበትን በልግስና የሚያበዛ የአየር ንብረት እና የፀሐይ ብርሃን ይዘን በስንፍናችን የምናጣውን እናበዛለን።
ሀገሬን እወዳለሁ የሚል ነጋዴም ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለወገኑም የሥራ በር ለመክፈት፤ አድካሚ ቢሆንም ውጤታማ ነውና የሚልከውን በጥሬ ከመላክ ዕሴት በመጨመር መውደዱን በተግባር ሊገልጥ ይገባል እላለሁ። አበቃሁ!
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም