የዓባይን ወንዝ ተጠቅሞ የመልማት የዘመናት ህልም የነበራቸው ኢትዮጵያውያን፣ ህልማቸውን እውን ለማድረግ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቆይቷል፡፡ ‹ለሁሉም ጊዜ አለው› እንዲሉ፣ የዓባይ ታሪክ ከተጓዥነት ወደ አዳሪነት ሊቀየር የሚችልበት የህዳሴ ግድቡ ፕሮጀክት የዛሬ 10 ዓመት መጋቢት 23 ቀን 2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት በይፋ ግንባታው ተጀመረ፡፡
ፕሮጀክቱ በአምስት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጀመር ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ እና አንድነትን የፈጠረ ከዛም በላይ የቅርብ ተስፋን ሰንቆ የነበረ ቢሆንም ባጋጠሙት ተግዳሮቶች ዘንድሮ አስር ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡ ይህ እውነታ ለብዙ ኢትዮጵያውያን መራራ እውነት ቢሆንም የግድቡ ግንባታ ዛሬም የነገ ብሩህ ተስፋ ተምሳሌት መሆኑ ግን አልቀረም፡፡
ቀደም ሲል የነበረው የፖለቲካ ሥርዓት ፕሮጀክቱን በተገቢው ጊዜና ጥራት ሠርቶ አገርና ህዝብ ለሚጠቀምበት ዓላማ ከማዋል ይልቅ የግለሰቦችና የቡድኖች መበልፀጊያ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በቢሊዬን የሚቆጠር የፕሮጀክቱ ሀብት ተመዝብሯል፡፡ ምናልባትም አገራዊ ለውጡ እውን ባይሆን እና የለውጥ አመራሩ ችግሮቹን ፈትቶ ወደሥራ ባይገባ ኖሮ ዛሬ የሚታየውን አይነት ገጽታ በግድቡ ላይ ላናይ እንችል እንደነበር መንገር አስፈላጊ አይደለም፡፡
መረጃዎች እንደሚያመከክቱት የግድቡ አንደኛ ዓመት ሲከበር የግንባታ አፈፃፀሙ 13 በመቶ፣ በሁለተኛ ዓመቱ 24 በመቶ፣ ሦስተኛ ዓመቱ ላይ 31 በመቶ፣ አራተኛ ዓመቱ ላይ 42 በመቶ እንዲሁም አምስተኛ ዓመቱ ላይ 50 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡ ይህ ማለት ግድቡ መጠናቀቅ በሚገባው ጊዜ ላይ ግንባታው ገና ግማሽ ላይ ነበር ማለት ነው፡፡ በስድስተኛ ዓመቱ 59 በመቶ፣ በሰባተኛው 64 በመቶን መሻገር አልቻለም ነበር፡፡ በእነዚህ ዓመታት የግድቡ አለመጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን ግድቡ የሙከራ ኃይል ማመንጨት ሥራ ይጀምራል የሚሉ ከንቱ ተስፋዎችም የተነገሩባቸው ነበሩ፡፡
2 010 ዓ.ም ወደ ሥልጣን የመጣው የለውጥ ኃይል ለግድቡ ግንባታ ትንሣኤ ሊባል የሚችል አቅምና ቁርጠኝነት ይዞ መምጣቱ፣ ግንባታው ግልጽ በሆነ መንገድ ያጋጠሙት ችግሮች ተለይተው እና ለህዝብ ግልጽ ሆነው ወደ ሥራ መገባቱ ዛሬ ላይ ግድቡ ላለ በት የግንባታ ምዕራፍ ዋነኛ ምክንያት ነው።
ዛሬ ላይ የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 79 በመቶ መድረስ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በተባለው መሰረት ተከናውኗል። የሁለተኛው ዙር ሙሌትም ቢሆን በተቀመጠለት ጊዜ መከናወን የሚያስችለው ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ ይህን ከማድረግ የሚያግድ ቴክኒካዊ ሆነ ፖለቲካዊ ምክንያት እንደሌለም በአደባባይ በይፋ እየተነገረ ነው። ሁሉም በጊዜው ይሆናል።
በለውጡ ማግስት በተነቃቃ ሕዝባዊ መንፈስና ቁርጠኝነት ትንሣኤውን ያበሰረው የግድቡ ግንባታ የሦስት ዓመት ጉዞው አልጋ በአልጋ አልነበረውም። ግንባታውን ለማስተጓጎል የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ከውስጥ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት አገር እስከ ማፍረስ የሚዘል ሴራዎችን ለመተግበር ሌት ተቀን ተንቀሳቅሰዋል። የታችኛው የተፋስ አገራት በተለይ ግብጽ ሙሉ ትኩረቷን በግድቡ ላይ በማድረግ የድርድር ሂደቱን የማደናቀፍ ሰፊ ሥራዎችን ያለዕረፍት በትጋት እያከናወነች ትገኛለች፡፡
ይሁን እንጂ የለውጥ አመራሩ በአገር ሉዓላዊነት፣ ጥቅምና ክብር ላይ እንደማይደራደር በአደባባይ በግልጽ ቋንቋ በማሳወቅ ተግዳሮቶቹ የቱንም ያህል ፈታኝ ቢሆኑም “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን“ በሚል የቁርጠኝነት መንፈስ የግድቡን ግንባታ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ አድርሶታል።
መላው ህዝባችንም የግድቡን ግንባታ ከዓድዋው ድል ጋር በማስተሳሰር ከፍ ባለ ቁርጠኝነትና ሕዝባዊ ተሳትፎ የግድቡ ግንባታ ስኬት ለመላው ጥቁር ህዝብ የልማት ፋና ወጊ ነው በሚል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የግድቡ ግንባታ ከልማትም ከፍ ያለ ፋይዳ ያለው የሀገራዊ ህዳሴአችን መሰረትና ተምሳሌት፤ ድህነትን አሸንፈን የምንወጣበት አልፋና ኦሜጋ አቅማችን ነው በሚልም ዓይኖቹን ከግንባታው ሳያነሳ የግድቡን ግንባታ በስኬት ለማጠናቀቅ ገንዘቡን፤ አቅሙንና እውቀቱን ሁለንተናውን ሰጥቷል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ አይታለፉም የተባሉ ትናንቶችን በስኬት አልፈን አይተናል፣ ብዙው ታሪካችንም በእንደዚህ አይነት ትርክቶች የተሞሉ ናቸው። ዛሬ ላይ ከብደው ያንገዳገዱን ብዙ ተግዳሮቶችም ነበሩ፣ ተሻግረን አይተናቸዋል፤ ብዙ የጨለሙ ቀናቶች አስጨንቀውን ብርሃን ወጥቶባቸው በብርሃን አልፈናቸዋል፤ ዛሬም አዲስ ነገር የለም እንደ ትናንቱ የማይታለፉ የሚመስሉንና በብዙ ተግዳሮት የተያዙ እነዚህ ቀናት ያልፋሉ። የህዳሴው ብርሃን የተግዳሮቶቻችንን ፈተና ያህል እያበራ ወደ ተስፋችን እንገባለን፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም