ፍሬህይወት አወቀ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚታየውን የመኖርያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችልና የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ጥያቄ በተቻለ መጠን ለመመለስ ያስችላል ብሎ ያሰበውን አዲስ የመኖሪያ ቤት አማራጭ ይዞ መቅረቡን መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።ይሄ የምስራች በተለይ የኢኮኖሚ አቅማቸው የተሻሉ የሆኑና መሬት ተረክበው ቤት ለመስራት አቅም ያላቸውን የከተማውን ነዋሪ ጆሮ ያልሰጠ ነበር።
በ2005 ዓ.ም በ20/80 እና በ40/60 ፕሮግራሞች የተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች አቅም እና ፍላጎት ያላቸው በጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤት የህብረት ሥራ ማህበር ተደራጅተው ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ጊዜያቸውን በማቀናጀት የቤት ችግሮቻቸውን በጋራ ጥረት መፍታት የሚችሉበትን አዲስ አማራጭ ይዞ መቅረቡ ይታወቃል።
በ2005 ዓ.ም በቤት ልማት ፕሮግራሞች ተጠቃሚ ለመሆን የተመዘገቡና ስማቸው በምዝገባ ቋት የሚገኝ ቤት ፈላጊዎች በምዝገባው የሚካተቱ ሲሆን፤ በማኅበር ቤት ለመገንባት ተመዝግበው ዕጣ የሚወጣላቸው ተመዝጋቢዎች የግንባታውን ወጪ 70 በመቶ በመረጠው ባንክ በዝግ ማስቀመጥ የሚኖርበት መሆኑን ጨምሮ ሌሎች ዝርዝር ማብራሪያዎችንም አስቀምጧል።
መንግስት በከተማዋ ተንሰራፍቶ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ባስቀመጠው የሙከራ አማራጭ ምን ያህል ዜጎች በምን አግባብ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ፤ በማህበር የመደራጀት አቅም የሌላቸው ቤት ፈላጊዎች አማራጭ ምን ሊሆን እንደሚችል እና አብዛኛው የመኖሪያ ቤት ችግር ያለበት የማህበረሰብ ክፍል በቤት ልማቱ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው እንዴት ባለ መንገድ ነው በማለት ላነሳነው ጥያቄ በአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር አማራጭ የቤት ልማት አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ ታምራት የሚከተለውን መረጃ ሰጥተውናል።
በአሁን ወቅት ለሙከራ የቀረበው የማህበር ቤት ግንባታ አማራጩ ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ተብሎ የተዘጋጀ ፕሮግራም አለመሆኑን ገልጸው፤ መንግስት ድጎማ እያደረገ የሚገነባቸውን ቤቶች ሀብታሙም ደሃውም፤ አቅም ያለውም የሌለውም እኩል ወረፋ ጠብቆ እየተጠቀመ ነው። ነገር ግን በራሱ መኖሪያ ቤት ገንብቶ መኖር የሚችለው ዜጋ አቅም የሌለውንና መንግስትን ብቻ መጠበቅ ግዴታ የሆነበትን የማህበረሰብ ክፍል ዕድል እየዘጋ በመሆኑ አሁን የተጀመረው የማህበር ቤት ይህን መነሻ በማድረግ የተጀመረ አማራጭ የቤት ልማት ፕሮግራም ነው።
20/80 እና 10/90 የቤት ልማት ፕሮግራሞች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች እንደመሆኑ 40/60 ደግሞ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ያካትታል። ይሁንና በማንኛውም ፕሮግራም የተመዘገቡ አቅምና ፍላጎት ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች አቅም ከሌላቸው ጋር እኩል ከሚጠብቁ የራሳቸውን አማራጭ መጠቀም እንዲችሉ ያለመ ፕሮግራም መሆኑን አቶ ጳውሎስ ያስረዳሉ። ለዚህ ፕሮግራም መነሻ የሆናቸውም በተለይም በ40/60 ፕሮግራም መቶ በመቶ ከፍለው ነገር ግን ቤት ሳይደርሳቸው የቀሩ በርካታ ዜጎች መኖራቸው ነው።
እነዚህ ዜጎች በአንድነት ተሰባስበው ያላቸውን ገንዘብ፣ ዕውቀትና ጊዜ በመጠቀም መንግስት በሚያቀርብላቸው መሬት በሚፈልጉት መጠን ቤት መገንባት ቢችሉ አንደኛ እነሱ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ። ሁለተኛ አቅም የሌላቸውና የግድ የመንግስት ድጎማ ለሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ሰፊ ዕድል መፍጠር ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ፕሮግራሙ አዲስና የሙከራ እንደመሆኑ ከፍተኛ ወጪንና ሰፊ የመሬት ዝግጅት የሚጠይቅ ነው። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ይቻላል አይቻልም በምን አግባብ የሚለውን በተግባር ለመፈተሽና ነገር ግን ህብረተሰቡ 20 በመቶ ብቻ ቆጥቦ ፕሮግራሙ ባይሳካ ህብረተሰቡም መንግስትም ተጎጂ ይሆናል።
ስለዚህ አቅም ያለውን ህብረተሰብ በማሳተፍ የሙከራ ፕሮግራሙን በሚገባ በመተግበር ልምድ በመቅሰም በቀጣይ መመሪያውን በማሻሻል በአዲስ አማራጭ ለመመለስ መታቀዱን ያነሱት ፤ በሚገኘው ልምድ የባንኮችን የማበደር አቅም በማየት በቀጣይ ፕሮግራሞች ማህበረሰቡ 10 እና 20 በመቶ ቆጥቦ ቀሪውን 90 እና 80 በመቶ ባንክ የሚሸፍንበትን አሰራር ለመዘርጋት ታስቦ የተጀመረ የቤት ልማት አማራጭ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የኪራይ ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች አምስት አይነት የቤት ልማት አማራጮች የሚቀርቡ መሆኑን ያነሱት አቶ ጳውሎስ፤ አቅም ያላቸው የማህበር ቤት ለመገንባት ሲወጡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ደግሞ በእነዚህ አማራጮች በፍጥነት ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን መንገድ ለመፍጠር የታሰበ ፕሮግራም እንጂ አግላይ አለመሆኑን አስረድተዋል። ነባር ፕሮግራሞችም ቀጣይነት ያላቸው መሆናቸውን ይናገራሉ ።
የክፍያ መጠኑን በተመለከተም የማህበር ቤት ዕድለኛ የሆነው ሰው 70 በመቶ ክፍያ መፈጸም ያለበት በመሆኑ በ20/80 ይሁን በ40/60 ተመዝግቦ ቁጠባን ያላቋረጠ ከሆነና ፍላጎት ካለው የክፍያ መጠኑን 70 በመቶ ማድረስ ይጠበቅበታል። ነገር ግን አቅም የለኝም የሚል ካለ የመንግስት የቤት ልማትን የሚጠብቅ መሆኑንና ሁሉም ፕሮግራሞች በየጊዜው የሚቀጥል ይሆናል እንጂ አስገዳጅ አለመሆኑን አንስተዋል።
በከተማዋ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እጥረት የከፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቤቶች ልማት ቢሮ ሰፋፊ ዕቅዶችን አቅዶ እየሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ ጳውሎስ፤ የማህበር ቤቶቹም ከተያዙት ዕቅዶች መካካል አንዱ እንደመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሞከረ ነው።ለዚህም ግንባታ የሚሆኑ ቦታዎች በአምስት ክፍለ ከተሞች መሬት ተዘጋጅቷል። አቅምና ፍላጎት ያላቸው አካላት መመሪያውን አሟልተው በተቀመጠው የ15 ቀናት የጊዜ ገደብ ምዝገባውን ማጠናቀቅ ሲቻል ወደ ተግባር የሚገባ ይሆናል።
ፕሮግራሙ ከ100 እስከ 130 ማህበራት ይኖሩታል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን 10 ሺ የሚደርሱ ቤት ፈላጊ አባወራዎችን ያሳትፋል ተብሎ ይጠበቃል። ግንባታው የሚከናወነው በሁለት አይነት መንገድ ሲሆን፤ አንደኛው እስከ ዘጠኝ ፎቆች ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ 13 ፎቆች ይኖሩታል። የግንባታ ሥራው በ18 ወራት የሚጠናቀቅ በመሆኑ አቅምና ፍላጎት ያላቸው ቤት ፈላጊዎች ገንዘባቸውን፣ አቅማቸውንና ጊዜያቸውን ተጠቅመው ባጠረ ጊዜ የቤት ባለቤት መሆን የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራል። የመንግስት የቤት ልማት ፕሮግራምን ለሚጠብቁ ቤት ፈላጊ ዜጎች ተስፋ የሚሰጥ ይሆናል ።
ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ እየተስፋፋ የመጣበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንዲሁም ሰዎች ሥራ ፈተው ለምዝገባ ጊዜያቸውን እንዳያቃጥሉ ምዝገባው በዌብሳይት መሆኑ መልካም ነው። ነገር ግን ምን ያህሉ ሰው ለቴክኖሎጂ ተደራሽ ነው፤ እስካሁን ባለው ሂደትስ ያጋጠሙ ችግሮች አሉ ወይ በማለት ላነሳነው ጥያቄ አቶ ጳውሎስ ሲመልሱ፤
‹‹በአሁን ወቅት አብዛኛው ማህበረሰብ ዘመናዊ ስልክ በእጁ ያለ መሆኑን በመገንዘብና ጊዜና ጉልበቱን በአግባቡ መጠቀም እንዲችል በተለይም የኮሮና ቫይረስ ባለበት መሰባሰብን ለመቀነስ ከሚል የተጀመረው የኦንላይን ምዝገባ በታሰበው ልክ እየሄደ ነው። ነገር ግን በአብዛኛው ሰዎች መረጃውን ለማንበብም እየገቡ የሚመዘገቡ ሰዎች በፍጥነት እንዳይመዘገቡ ኔትዎርኩን ለረጅም ጊዜ የመያዝና የማጨናነቅ ሁኔታ አለ። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ከቴሌኮሚዩኒኬሽን ጋር በመነጋጋር ለመፍታት እየተሞከረ ነው። ያም ሆኖ በአሁን ወቅት በተጠበቀው ቁጥር ልክ ምዝገባው እየተካሄደ ይገኛል።›› ሲሉ ተናግረዋል።
የምዝገባ ጊዜው 15 ቀን መሆኑም አጭር ጊዜ አይደለም የሚሉት አቶ ጳውሎስ ማንም ሰው እጁ ላይ ባለ ዘመናዊ ስልክ ቢበዛ 30 ሰከንድ ተጠቅሞ መመዝገብ ይችላል። ምዝገባውን ሲያከናውንም ቀድሞ ከተመዘገበው የቤት አይነት ውጭ ማለትም ባለ አንድ መኝታ ከሆነ ቀድሞ የተመዘገበው አሁን ባለሁለትና ባለ ሶስት መኝታ ማድረግና የተሻለውንና የፈለገውን የመምረጥና የመቀየር ዕድሉን ተጠቅሞ ተመዝግቦ መውጣት ነው። በመጨረሻዎቹ ሶስት የምዝገባ ቀናትም በተለያዩ ምክንያት ለአብነትም ኢንተርኔት ያስቸገራቸው ሰዎች ካሉ ዝርዝራቸው ተይዞ የሚስተናገዱበት ሁኔታ ተመቻችቷል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት አርብ መጋቢት 24 ቀን አራት ሰዓት ድረስ ምዝገባው በተጀመረ በአራት ቀን ውስጥም 3000 የማህበር ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ማድረጋቸውን አቶ ጳውሎስ ተናግረዋል።
የከተማውን ነዋሪዎች ሰፊ የመኖሪያ ቤት ችግር በቀጣይም ለመፍታት መንግስት የተለያዩ አማራጮችን እንደሚከተል ነው የጠቀሱት። ይሄውም በመንግስትና በግል ሽርክና፤ በመንግስትና በግል አጋርነት፤ በመንግስት የኪራይ ቤቶች ፤ በማህበራት በማደራጀት እንዲሁም ከሪልስቴት ቤት አልሚዎች ጋር በጋራ በመቀናጀት ቤቶች በስፋት የሚሰራበት ሁኔታ እንደሚኖር ነው ያብራሩት። የሪል እስቴት አልሚዎችም እስካሁን ከሚሄዱበት አካሄድ በተሻለ ሰፊውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ የቤት ግንባታ እንዲያካሂዱ ይደረጋል። ይሄንንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አዋጅ ተዘጋጅቶ እስኪጸድቅ ድረስ እየተጠበቀ መሆኑን አስታውቀዋል። የቤት ልማቱን ማሳለጥ ለአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ቢሮ በአዋጅ የተሰጠው ስልጣን በመሆኑ ባለሀብቶችን አሳትፎ የቤት ልማት ፕሮግራሙ እንዲሳለጥና የከተማው ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር እንዲቃለል ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል። በቀጣይም የተለያዩ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት አላቸው።
መንግስት የቤት ልማት ፕሮግራሙን በሞኖፖሊ በመያዙ ምክንያት የኢኮኖሚ አቅም ያለውም የሌለውም ሁሉም ሰው መንግስትን ጠባቂ ሆኗል። መንግስት ደግሞ እየመጣ ካለው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ጋር የመገንባት አቅሙ ሊጣጣም አልቻለም። በመሆኑም ባለፉት 17 ዓመታትም መገንባት የቻለው 400 ሺህ ቤቶችን ብቻ ነው። ይህ አዋጭ አይደለም።
አሁን ያለው ፍላጎት ደግሞ ዕለት ከዕለት እየጨመረ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ጳውሎስ፤ በቅርቡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባጠናው ጥናት መሰረት የተገኘው ውጤት የሚያመለከተው የቤት ፈላጊው ሰው ቁጥር አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ደርሷል። ይህ ሁሉ ቤት ፈላጊ ባለበት ሁኔታ ላይ መንግስትን ብቻ መጠበቅ ተገቢም አዋጭም አይደለም። በመሆኑም የተለያዩ አማራጮች ማየትና መተግበር አስፈላጊ ነው። አሁን ከተጀመረው የማህበራት ቤት ግንባታ በተጨማሪ በሀገር ውስጥና በውጭ ካሉ ባለሀብቶች ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ጳውሎስ እንዳሉት ፤የቤት ልማት ትልቅ የፋይናንስ አቅምን የሚፈልግ በመሆኑ ባለሃብቶች ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዲችሉ መንግስት ከማሳተፍም አልፎ በማስገደድ በጋራ መስራት የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። አንዱ የሪልስቴት አዋጅም በዘርፉ ያለውን ችግር ሊፈታ የሚችል ነው። ለዚህም ደንብና መመሪያ ተዘጋጅቶ እስኪጸድቅ እየተጠበቀ ይገኛል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም