በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
ሰሞኑን በሐገራችን ውስጥ እየሆነ ያለውና እየተነገረ ባለው መካከል ያለው ውዝግብ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ አያጠያይቅም። ድሮ ድሮ እንደምሰማው ዋሺንግተንና ሞስኮ እንዲህ እና እንዲያ ተባባሉ ሲባልና የምስራቅንና እና የምዕራብን ክፍል ወክለው ሲተጋተጉ ነበር። በቀደሙት ሰዎቻችንም መካከል የነበረው ልዩነት የርዕዮት እንደነበረ ከዚያም አነስ ሲል የስትራቴጂና ታክቲክ እንደሆነ ነበር ያነበብነውም የምናውቀውም። አሁን ግን በአንድ ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ ነገር ግን፣ ግንብ ገንብተው ላለመስማማት እንደተስማሙ ያሉ የሰዎች ስብስብ የፈጠረው፣ የአንጃና ግራንጃ ጠርዘኛነት ነው፤ የሚታየው።
ለዚህ ነው፤ በሚባለውና እየሆነ ባለው መካከል ገደል አለ፤ የምለው። ሰሞኑን አጣዬ እና ዋግ ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ስለሞቱ ሰዎች (የዋጉ አልተነሳም መሰለኝ) ሲነሳ፣ የተነሳው አቤቱታ በሸንጎው ውስጥ ሲሰማ፣ ይህን ያህል አማራ ሞተ፣ ተሰደደ እና በሌላ በኩልም ኦሮሞ ተጨፈጨፈ ተገደለ፤ ተፈናቀለ፤ ተብሎ ሲነገርና ሌሎች የተያያዙ አፈላማዎች መነሳታቸው እጅግ አስገርመውኛል፤ አስቆጥተውኝማል፤ ለመሆኑ መቼ ነው፤ ከተሰራብን የቋንቋ ከሎ፣ ከተሰራብን የአንተና የእሱ ክልል ስሪት ወጥተን መነጋገርና መግባባት የምንችለው ብዬ ግራ ተጋባሁ። “ግራ አጋቢ” አይጥፋና! አንደኛው “ሃይሉን በመመካት” ሲል፣ ሌላኛው “እንዳባቶቼ እገዛችኋለሁ”፤ እያሉ ሲሉ መነታረኪያ ማንሳት፣ ውሃ የማያነሳ ዘመንን የኋሊት የሚጎትት፣ ስለ ዜጋ ስብዕናና ሐገር በቅርቡ እንኳን የተከፈለውንና እየተከፈለ ያለውን ዋጋ የሚያወርድ ትርክት መሆኑን ማን እንደሚያስታውስልኝ አልገባህ አለኝ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ተወካዮች ምክር ቤት በተባለው ቤታችን ውስጥ፣ የሚነሱት ሐሳቦች በአመዛኙ፣ አንድ እርምጃ ወደፊት በመሄድ፣ ይህንን በመብራት፣ በውሃ፣ በመንገድ፣ በእህል ረሐብ ጭምር ያለውን ህዝብ ኑሮ እንዴት አድርገን እንለውጥና እንድረስለት፣ በሚያስብሉ ዘዴዎች ላይ ሐሳብ ሊያመነጭ፣ ሊተጋተግና ወደ መፍትሔው ሊገባ የሚገባው ከፍተኛ ተቋም፣ ሙትና ቁስለኛን በዘር ለይቶ ሲያቆጣጥርና እና በደራሽ ግጭት አጥር ውስጥ ታጥሮ ደም ሥርን ገትሮ ሲሟገት ማየት ከማሳፈሩም በላይ አጥሩን ከማጠባበቅ ውጭ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ አጥተውት ነው እንዴ፣ ያሰኛል።
ይህንንም ስል በየትኛውም የሐገሪቱ ክፍል የሚሞተው ዜጋ ሞት ስለማያሳስበኝና ስለማይነዝረኝ አይደለም፤ ይልቅስ ሞትን በዘር ቀሳ የመለየቱ አዚም አናድዶኝ እንጂ። በጥቅምት 24/2013ዓ.ም. የሰሜኑ ህግን የማስከበር ዘመቻ ወቅት አሸናፊ እንደሚሆን ገምቶ የነበረው ኃይል፣ ሲነሳ “የርዕዮት መስመር ተጣሰ”፤ “መርህ ተዘለሰ”፤ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተቀለበሰ” ሳይሆን አስፈሪ አደጋ በትግራይ ህዝብ ላይ ተደቀነ ብለው ነበረ፤ በሐገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት ላይ በአንዴ 200 ነቁጣዎች ላይ ግጭት በመፍጠር፣ በእነርሱ ቋንቋ ለመጠቀም “መብረቃዊ ጥቃት” በመፈፀም ነበር ጦርነቱን የጀመሩት። ለጥቃቱ አፀፋ ጥቃት ሲወሰድበት ደግሞ “የትግራይ ሰው ተጨፈጨፈ– ትግራዋይ ላይ ጄኖሳይድ ተፈፀመ” በማለት የአብዬን እከክ ወደ እምዬ አላከኩት። ገፋፊዎቹና ጠንሳሾቹ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ለምን ፈጸማችሁ፣ ተብለው ቢጠየቁ ደግሞ አማሮችና እንትን ብሄረሰብ ስለተነኮሱን ብለው ድህረ-ጦርነት ልፈፋ መቀጠላቸውን ሁሉም ያስታውሳል።
እኔ የእነዚህ ሁሉ ነገሮች መንስኤ ወገናችን ብለን ስለምንጠራው ቋንቋ ተናጋሪና ስለሌላው ያለን አስተሳሰብ ባለፉት አርባ ዓመታት ትርዕዬ (የአስተሳሰብ ዘዬ) የተሰናከለ በመሆኑ ነው፤ እንዲህ የሆንነው ስል ነው፤ የምረዳው። ሰው ስለተራበ እናበላዋለን፤ ስለታረዘ እናለብሰዋለን እንጂ፣ የተራበው የእኔ ቋንቋ ተናጋሪ ነው ወይስ አይደለም፤ ብለን የምንጠይቅ ያለን አይመስለኝም፤ ልክ በዚህ ትይዩም እርዳታው ከእንትን ብሔረሰብ የመጣ ስለሆነ አንቀበልም የማለት አባዜ ጤነኛ አይመስለኝም። “ሲጣመም አይጥም” ማለትም እንዲህ ነው። አሁን ማን ይሙት፣ አድዋና ማይጨው ላይ ሊወርረን መጥቶ ነበረና የጣሊያን ሸሚዝ አንለብስም፤ የጣሊያን ካናቴራ አናደርግም፤ የጣሊያን ፓስታና ማካሮኒ አንበላም ይባላልን? የአንዳንዶቻችን አካሄድ እስከዚህ ውልግድ ያለና የዘመኑ “አስቂኝ” ዚቅ ሆኗል።
የማይካድራውን ጭካኔ ወደ አንድ ዘር ማውረድ ከቶም አይገባም፤ እዚህ ላይ እንደ ምሳሌ ላነሳው የወደድኩትን የአንድ ወንድማችንን ታሪክ ላንሳ። ከቤንች ማጂ ለንግድ ነው፤ የሄድኩት ያለው፣ ይኸው ወንድማችን ፣ ቀደም ሲል ከማእከላዊ መንግስት ጋር ለምናደርገው ጦርነት መቶ ሺህ ብር፣ “ትህነጎች” አዋጣ ብለውኝ፣ ካዋጣሁ በኋላ በየሱቃችን እና መኖሪያ ቤታችን ላይ ምልክት አደረጉ። ምንድነው ስንላቸው፤ የከፈለና ያልከፈለ ለመለየት ነው፤ ያሉት እንጂ ሌላ አልነበረም፤ ይሁንናም ጭፍጨፋውን ሲጀምሩ አማርኛ ተናጋሪውን ሁሉ እንጂ የመጣንበት ዘር አልተፈተሹም፤ እኔም በጎረቤቴ ያየሁት ጥፋት አስበርግጎኝ ነው፤ በሌሊት ጠፍቼ እንድወጣ ያደረገኝ ሲል መስክሯል። ክፉ ሰው ሊረዳህም አይፈልግም፤ ሊያስረዳህም አይሞክርም። ክፋት ሰበብ እንጂ ቀድሞውኑ በቂ ምክንያት የታለውና?!
የቤንቹ ልጅ ምስክርነት እንደሚያሳየው እኔን ካልመሰልክ “ወዮልህ!” የሚል ጥፋት ፈጻሚነት ነው፤ አጥፊዎቹን ወደ ጥፋት፣ የወሰዳቸው። በእነዚያ ዜጎቻችን ላይ እልቂት የተፈፀመው፣ በታወረ ማንነት በተሰራ ልዩ ባልሆነው ልዩነታቸው ሳቢያ ነው። እንደ እኔ እምነት ጥፋቱ ግፉ በተፈጸመባቸው ወገኖቻችን ላይ ብቻ ሳይሆን አጥፊውንም ራሱን የበደለ፣ አጥፊውንም ያቀለለ ድርጊት እንደሆነ ነው፤ የማምነው።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የህብረቱን ኃይል (Allied Power) የመሩት፣ አሜሪካዊው ጄኔራል እና በኋላ ዋይት ሐውስን በፕሬዝዳንትነት የተቆጣጠሩት አይዘነሐወር፣ ናዚ ጀርመንን ለመቆጣጠር ይገፋ ለነበረው ጦራቸው ያስተላለፉት ድንቅ የሬዲዮ መልእክት ላይ፣ አሁን እየተዋጋ ባለው ሃይልም መካከል ብዙዎቹንም ነጻ ልናወጣ እንደምንጓዝ አትዘንጉ፤ ስለዚህ ሊዋጋችሁ ከቆመው ሃይል በስተቀር በሁሉም ላይ እጃችሁን አታንሱ ነበረ፤ ያሉት። ነገን የሚያይና በነጻይቱ አውሮፓ ውስጥ ነገ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ጀርመናውያን ለጊዜው በተጻራሪነት ቆመው ሊሆን ቢችልም፤ ውጊያውን ከእልህና ከቁጣ ነጻ በሆነ መልክ እንዲያደርጉ ነበረ፤ ያስተላለፉት መመሪያ።
አዎ፤ በተጻራሪ የቆመ ኃይል ሁሉ ሊጠፋ እንደሚገባው ጠብመንጃና ታንክ (ቁሳቁስ) አድርገን ካየነው የጥፋታችን መጠን የትየለሌ ይሆንብናል። ስለዚህ ሊዋጋን ይምጣ እንጂ፣ ነጻ ሊወጣም የሚገባው ተገድዶ የገባ ሃይል እንዳለ ማሰብም መልካም ነው፤ ለእነዚህ ወገኖቻችን ነጻ አውጪ ከግብጽ አይመጣላቸውምና።
ፕሬዝዳንት አይዘነሐወር፣ ይጠነቀቁ የነበሩት ለተዋጊዎቻቸው የህብረቱ ኃይል ፈረንሳውያን፣ አሜሪካውያንና ብሪታኒያውያን ብቻ አልነበረም፤ በተጻራሪ ለቆሙት ጀርመናውያን ጭምር እንጂ። መሪ በዚህ ልዕልና ሲቆም ሕዝብንም ሐገርንም ከከፋ ጥፋት ያድናል። እንደ ጠላቶቻችን አደራረግ እኛም እናድርግ ዘይቤው የሆነ አመራር ከሆነ ግን፣ እኛስ ከእነርሱ በምን ተሻልን? ማለት ይኼኔ ነው።
ስለዚህ ነው፤ በቀዳሚነት ባነሳሁት አንቀጽ ላይ፣ እየተነገረ ያለውን ካላስተዋልነው እየተደረገ ያለው ነገር እንደማይገባን ለመናገር የሞከርኩት። በዚህ ጊዜ፣ እርስ በእርስ መሳሳብና መደጋገፍ፣ እርስ በእርስ መጠራራትና መተቃቀፍ እንጂ የቋንቋ አጥር ፈጥሮ፣ ዜግነትን መሬት ለመሬት አዋራ በሚያስልሱ ትናንሽ በደሎች እየደፈቅን መጓዝ፣ሁላችንንም በደም ያጨቀየን ይሆናል እንጂ ሰላም አያወርድም።
ብዙ ሰዎች አክቲቪስቶች በላቸው፣ ፖለቲከኞች፣ አንቀሳቃሹም ሆነ ተንቀሳቃሹ በየስፍራው የሚያነሳቸው የጃጁ አጀንዳዎች ሐገራችንን የትም ሊያደርሱ እንደማይችሉ ተገንዝበን፣ ሊያሳድጋትና ሊያበለጽጋት በሚያስችሉ ተተግባሪ ሐሳቦች ላይ መነጋገር ያዋጣናል። ሰዉ ውስጡ ከሚነግረው እውነት ይልቅ፣ በውጭው ሐሳብ ከተያዘ፣ ውስጡ ከተረዳው ነገር ይልቅ ለሌሎች አጀንዳ ካደረ እያስፈጸመ ያለው ወይም የሚኖረው ለራሱ አይደለምና ፍጻሜው አሳዛኝም አሳፋሪም ነው።
ትናንት ጎረቤቱ፣ የእድር አባሉ፣ የመስሪያ ቤት ባልደረባው፣ የብርጌድ አባሉ ወረድም ሲል የሰፈሩ ልጅ የነበረውን ሰው ከምድር ተነስቶ፣ በሚናገረው ቋንቋና ባህል ሳቢያ ከማድነቅ ይልቅ “እርሱና እኛ” ብሎ ከሎ ከልሎ፣ የኩርፊያ መድረክ መፍጠር አስቂኝ ነው። እንቶኔ፣ እቁብ በልቶ የከለከለኝ፣ የእንትን ብሔረሰብ አባል ስለሆነ ነው፤ ማለት ነው፤ ወይስ ለቃሉና ለገባው ቃል ኪዳን ያልታመነ ሰው በመሆኑ ነው፤ ብሎ ማሰብ ነው፤ የሚቀለው? ምን ሲደረግ ብሎ ወግድልኝም ሆነ፣ “ጎርነራ” (አትጠጋኝ ማለት ነው በኦሮምኛ) ማለት አይገባም፤ ለእኛ የሚበጀን መተሳሰቡ ነው፤ የእንቧይ ካብ ሊያደርገን ለሚመኝ ወገን እንዳንመች መጠንቀቅ አለብን።
“ሐገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ ፣
ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ።” 1929 ዓ.ም. (ባለቅኔ ዮፍታኼ ንጉሴ)
የዛሬ 66 ዓመት ካይሮ ላይ የተጀመረው ኢትዮጵያን የማዳከም ሴራ ተጠንስሶ የተጠናከረው ለልዩነት የአዕምሮ ማሳችንን ስለሰራነው ነው። በዚህ ሳቢያ ካይሮ ምን ትጠቀማለች? ለሚለኝ የምመልሰው በአንድነት የማትቆም፣ ፍርክርክና ለራሷ የማትፀና ሐገር ወደ ልማትና ቅናት ፊቷን አታዞርም። አሁንም አሁንም የሚነሳ እሳትን የምታጠፋ በዘመቻ እሳት ማጥፋት የተወጠረች፣ “ምናምንቴ” ትሆናለች፤ ያም ዓባይን ቀርቶ የቡልቡላን ወንዝ ለማሳ ጥቅም የማታውል ምስኪን ተመጽዋች ሐገር ያደርጋታልና ነው።
ሐገራችን፣ ባሳለፍናቸው ሰባ አመቶች ውስጥ አንዴ በውጭ፣ ሌላ ጊዜ በውስጥ ተግዳሮቶች የተወጠረች፣ ሐገር ሆና ነው፣ የኖረችው። ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ስትቀላቀል፤ አስመሳይ የይሁንታ ድምጽ ከሰጡት የአፍሪካ ሐገሮች ቀዳሚ የሆነችው ግብጽ የመጀመሪያውን የጀብሐ (E L F) ጽህፈት ቤት የከፈተችው ካይሮ ላይ ነው። በኋላም በራሳችን ድክመትና የአሰራር ስህተት የሆነው ጥፋት ሁሉ ሆኗል። ያኔ የተከፈተው ጽህፈት ቤት በኋላም አንዴ ለኦነግ፣ ሌላ ጊዜ ለኦብነግ፣ እና ለሌሎች ጭምር የተሟሉ ደልቃቃ ጽህፈት ቤቶችን ስትከፍትና ጦርነት ስታስከፍት ነው፤ የኖረችው። ዛሬም ይህንና መሰል ነገሮችን ከማድረግ ጀምሮ ከሱዳን ጋር ተመሳጥራ ጦር እስከመማዘዝ ገፍታለች። ታዲያ በዚህ ጊዜ፣ ታዲያ በዚህ ሰዓት ፣ እርስ በእርስ መገፋፋት አለብንን?
ኢትዮጵያን መሪ ቃልና ኮከብ፣ አድርገን ካላሰብን፣ ኢትዮጵያን ማእከላዊ አጀንዳችን ካላደረግን በስተቀር፣ የምናደርጋቸው መናቆሮች ሁሉ የሚያደርሱን ወደ ጥፋት መንገድ ነው። ሐገሬን የጎዳት እኮ ከውጭ ከሚወረወረው ፍላጻ ይልቅ ከውስጥ የሚነሳው መቆጣቆጥ ነው። ይህን በመገንዘብም ነው፤ በሚሆነውና በምንናገረው ነገር ላይ ብርቱ ጥንቃቄ አድርገን፣ ወንድሜ ሆይ! በየትኛውም የሀገሪቱ ምድር በሚነሳ ግጭት፣ በሰዎች ላይ በደልና ጉዳት ሲደርስ፣ “ሰው ሞተብን እንበል፣ ወገን ወደቀብን እንበል” እንጂ፣ የዚህ ብሔረሰብ፣ የዚያ ጎሳ አረፈብን እያልን አናሳንሰው። ሰው መሞቱ፣ እኮ ራሱ በቂ ጉዳት ነው፤ ወገናችንን አሳጥቶናል፤ ብለን፣ ሐዘናችንን እንጋራ እንጂ ሐዘናችንን በከሎ አንጠረው። ዛሬ በብሔረሰብ ያደረግነውን ጸብና እጦት፣ ነገ ደግሞ በጎሳ፣ ከነገ ወዲያ ደግሞ በጎጥና በቤተሰብ አውርደነው፣ በወሳንሳ እንዳንቀር ያሰጋናል።
ሰው፣ ዛሬ አዕምሮውን መቆጣጠር ካልቻለ ምኞትና ስሜቱን መግዛት ካልቻለ በስተቀር ነገ የስሜትና አእምሮው ተገዢ ይሆናል። በጆሯችን ስሚ ስሚም ሆነ በአካላዊ ድርጊት የምናየው ጥቃት እየፈጠረብን ያለውን የስሜት መነሳሳት ልንቆጣጠረውና ልንገዛው ካልቻልን በስተቀር፣ ነገ የስሜታችን መጫወቻ መሆናችን ሳይታለም የተፈታ ነው፤ ለዚህ ነው፤ ከክፋት እናድብ እንጂ፣ ለክፋት አናድም ማለት የምወድደው።
ሰዓቱ ካለፈ በኋላ የምናስባቸው ነገሮች ላይመለሱ ታጥፈው የሚቀሩ ናቸው። አንድ መቶ ሰላሳና ሃምሳ ዓመት ወደ ኋላ እየሄድን ሙሾ ከምንደረድርና ዛሬንም ለነገ ሙሾ ድርደራ ከምናበቃ፤ ዛሬ እንንቃ! ዛሬ ከነቃን ነገ ቆንጆ ይሆናል።
ከእገሌም አይደለም፤ ከዘሩ ከቁጥሩ፣
ሲሞት ሠው ጎደለ በሉ ላገር ምድሩ።
ለክፉ ፍላጎት ለስልጣን ማመንዘር፣
ሰው አይሙት በከንቱ በማይረባ ምክር፤
ይከበርባት ሰው በፍቅር ይሁንታ፣
በቀጠሮ እንገኝ፤ ጠዋትም ይባል ማታ!!