
በክረምቱ መግቢያ ወር በሰኔ ገበሬው ወገቡን ጠበቅ አድሮ፤ ሞፈርና ቀንበሩን አበጃጅቶና ጥንድ በሬዎቹን አጀግኖ ለሥራ ይነሳል። የሰኔ የመጨረሻዎቹ ቀናት በዚህ ወቅት ዝናብና ደመና ምድርን የሚያለመልሙበት፣ ዘር የሚዘራበት ፣ የተዘራው የሚበቅልበት በፀሐይ ሐሩር የደረቁ ዛፎች ሁሉ የሚያቆጠቁጡበት ወቅት ነው።
ስለዚህም ጀግናው አርሶ አደር ድካምና አንቅልፍን አሸንፎ ከእርሻው መሬት ጋር ይወዳጃል። በውሃ የራሰውን መሬት እየተረተረ ለእርሻ ዝግጁ እንዲሆን ያደርገዋል። በጨቀየው መሬትና ከላይ እንደጉድ በሚወርደው ዶፍ ዝናብ ሳይበገር በሬዎቹን ጠምዶ ያርሳል፤ ቀጥሎም ዘር በማሳው ላይ ይበትናል። የተዘራው ዘርም መሬትን አሸንፎ ሲወጣ ተግቶ በማረም ጥሩ ምርት ለማፈስ ቀን ከሌት ይታትራል።
ይህ ተግባር ክረምት በመጣ ቁጥር በገበሬው ዘንድ ሰርክ የሚፈጸም ሥራ ነው። ብርቱው ገበሬ የክረምትን ጨለማ አሸንፎ፤ ብርድና ውርጩን ተቋቁሞ፤ ጭቃና ዶፉን ተጋፍጦ ከራሱ አልፎ ለሀገር የሚተርፍ ምርት ያገኛል። ከራሱ አልፎም ለሌሎች መድህን ይሆናል።
ወደ ከተሜው ስንመጣ ክረምት የስንፍና እና የእረፍት ጊዜ ተደርጎ የሚወሰድ ነበር። ትምህርት ቤቶች ይዘጋሉ፤አብዛኞቹ ሥራ እንቅስቃሴዎች ይቀዛቀዛሉ፤ ሁሉም ብርድና ዝናቡን ሽሽት በያለበት መሸጎጥን ይመርጣል። ስለዚህም የክረምት ሶስት ወራት ለአርሶ አደሩ የጥንካሬና የተስፋ ወራት ለከተሜው ደግሞ የእንቅልፍ ጊዜያት ሆነው ኖረዋል።
ዛሬ ግን ሁኔታዎች ተቀይረዋል። ከረምት ግም ሲል ለከተሜውም ተስፋ ይዞ መምጣት ጀምሯል። በተለይም ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ክረምት ሲመጣ ምድሪቷን በአረንጓዴ ማልበስ፤ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ሥራዎችን ማከናወንና ነዋሪዎችን ከጎርፍ አደጋ መታደግ የመሳሰሉት ተግባራት የሚከናወኑበት ወቅት ሆኗል።
ክረምት በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያውያን እንደ ባህል ከያዟቸው ተግባራት አንዱ እና ዋነናው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በክረምት ብቻ 40 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ዓለምን ጉድ አሰኝታለች። ዘንድሮም የክረምት መርሃ ግብርም ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል ቁጥሩን ወደ 50 ቢሊዮን ለማስጠጋት እቅድ ይዛለች።
በሌላም በኩል የክረምት ወራት መገለጫ እየሆኑ ከመጡ ተግባራት ውስጥ አንዱ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ናቸው። ኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ በርካታ አኩሪ እሴቶች አሏቸው። ከእነዚህ ውስጥ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶቻችን በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸው። ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲያጋጥሙ መሰናክሎችን በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን ከማዳበራቸውም በላይ ለተበደሉት መሸሸጊያ፤ ለተሰደዱት መጠለያ ሆነው ዘልቀዋል።
ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን የተላበሱ ሕዝቦች ናቸው። በርሃብም ሆነ በድርቅ፤ በግጭትም ሆነ በጦርነት ወቅት በመረዳዳት አስከፊ ጊዜያቶችን አሳልፈዋል።
ኢትዮጵያውያን የእምነት ልዩነት ሳይበግራቸው ደስታንም ሆነ ኀዘንን በጋራ ያሳልፋሉ። የሀገራቸውንም ዳር ድንበር ይጠብቃሉ፤ ወራሪን በጋራ ድል ይመታሉ፤ በልማት ይሳተፋሉ ፤ ሀገራቸው ጥሪ ስታደርግላቸው ያለምንም ማመንታት ከጎኗ ይቆማሉ። ይህ አንድነታቸውን አብሮነታቸውም ከበርካታ የዓለም ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብርና ግርማ ሞገስ አጎናጽፏቸዋል። በአርአያነትም እንዲወሰዱ አድርጓቸዋል።
ይህ የመተሳሰብ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑ ዜጎች ማዕድ ማጋራትና ድሃ ድሃ ቤት እድሳት በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው።
በዝቅተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን ሲገፉ የቆዩ ነዋሪዎችን ቤት በማደስ ዜጎች በተለይም በኋለኛ ዘመናቸው በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ የሚደረጉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ዛሬ የእኛነታችን መገለጫዎች እየሆኑ ነው። በየዓመቱም ክረምት በመጣ ቁጥር የበርካታ አቅመ ደካማ ዜጎች ቤቶች እየታደሱ ዜጎችን ከዝናብና ከብርድ የመታደጉ ተግባር በመንግሥት፤ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በነዋሪው ተሳትፎ እውን እየሆነ ነው።
በየዓመቱም እስከ 10 ሺህ የሚጠጉ ቤቶችን በማደስ አቅመ ደካማ የሆኑ ሰዎች ከዝናብ እና ከብርድ የማዳን ሥራዎች ይከናወናሉ። በዚህም በአቅም ማነስ የተነሳ የተጎሳቆሉ እና ያዘመሙ ቤቶች ዛሬ በበጎ ፈቃደኞች ቀና ብለው ለአቅመ ደካሞች ማረፍያ እና መጠለያ ለመሆን በቅተዋል።
ክረምት በመጣ ቁጥር የሚከናወኑት የበጎ ፈቃድ ሥራዎች በዝቅተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን ሲገፉ የቆዩ ነዋሪዎችን ቤት በማደስ ዜጎች በተለይም በኋለኛ ዘመናቸው በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ የሚደረጉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ዛሬ የእኛነታችን መገለጫዎች እየሆኑ ነው።
መንግሥት በሚከተለው ዜጋ ተኮር ፖሊሲ ምክንያት ዜጎች የተሻለ መጠለያ እንዲያገኙ በተያዘው ዕቅድ በየዓመቱ እስከ 10ሺህ የሚደርሱ የአቅመ ደካማ ቤቶች እየታደሱ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ ዜጎች በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ ከማስቻሉም በላይ የከተማዋን ገጽታ ከስር መሠረቱ እየቀየረው ይገኛል። ይህ ተግባር በ2017 የክረምት ወራትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
አረንጓዴ ዐሻራን ጨምሮ የአረጋውያንና አቅመ ደካማ ዜጎች ቤት እድሳትና ሌሎች የልማት ሥራዎች የዚሁ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል ናቸው። ደም መለገስ፤ የትራፊክ እንቅስቃሴን ማስተባበር፤ ተማሪዎችን በጥናት ማገዝ እና መሰል ሥራዎች በክረምቱ ወራት ደምቀው ይከናወናሉ።
በሌላም በኩል በአቅም ማነስ ምክንያት በቀን አንድ ጊዜ እንኳን እራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በጋራ ማእድ እንዲቆርሱ በማድረግ ረገድ የተጀመሩት በጎ ተግባራት የኢትዮጵያውያንን በጎ እሴቶች ማስቀጠያዎች እየሆኑ ነው። በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ጭምር የሚከናወኑ የማዕድ ማጋራት በጎ ሥራዎችን ለተመለከተ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን መተሳሰብና መረዳዳት የሚያመላክት ነው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያውን ከመረዳዳትና ከመደጋገፍ ውጪ መገለጫም የላቸውም። ኢትዮጵያም ቆማ መቀጠል የቻለችው ዜጎቿ በሚከውኗቸው መልካም ተግባራት ነው። ስለዚህም እነዚህን በጎ እሴቶች በማጠናከር ኢትዮጵያን የማጽናቱ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። እያስገመገመ ያለው ክረምትም በበጎ ሥራዎች የደመቀ እንዲሆን ከወዲሁ ወገባችንን ጠበቅ ማድረግ አለብን።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም