ራስወርቅ ሙሉጌታ
ለአገር ሰላም መከበር ለልማትና ብልጽግና የወጣቶች ተሳትፎ ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዝ ይታወቃል። በኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት የተከናወኑ ለውጦች የወጣቱ እንቅስቃሴ በስፋት የታየባቸው ናቸው። በቅርቡም ለሃያ ሰባት ዓመታት የነበረው ሥርዓት እንዲቆም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተናጠልና በቡድን እንዳስፈላጊነቱ በህቡና በይፋ ለዓመታት ሲታገሉና መስዋዕትነት ሲከፍሉ የነበሩት ወጣቶች ናቸው። ወጣቶች በከፈሉት መስዋዕትነትም እንደ ተራራ ገዝፎ ይታይ የነበረውን መስመር የሳተ ሥርዓት ለማስቆም የተቻለ ቢሆንም ዛሬም ድረስ ሆን ተብለው ሀገር ለማፍረስና ሕዝብን ከሕዝብ ለማራራቅ በተሰሩ ሥራዎች የተለያዩ ችግሮች በመከሰት ላይ ይገኛሉ። ምንም እንኳን ለውጡን ተከትለው እየተፈጠሩ ላሉት ችግሮች ቀዳሚ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸው የራሳቸው አገር የማፍረስ አጀንዳ ያላቸው በአገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ አካላት ቢሆኑም የጥፋት ተልዕኮውን በማሳካት ላይ ያሉት ግን በሀገር ውስጥ ያሉ ወጣቶች ናቸው።
«ምንም አንኳን በየዘመኑ ያሉ ወጣቶች የሚያነሷቸው የየራሳቸው ጥያቄዎች ያሏቸው መሆኑ ቢታወቅም የሚቀርቡት ጥያቄዎች የራሳቸውን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ፣ የአገርና የሕዝብን ሰላምና አንድነት የማያናጉ መሆን አለባቸው። በተጨማሪም ድብቅ አላማ ያላቸው ሰዎች መጠቀሚያ ከመሆን በጸዳ መልኩ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊቀርቡ እንደሚገባ በመግለጽ፤ በኢትዮጵያ ለተከሰተው ለውጥም ወጣቱ ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደከፈለ ሁሉ ለውጡ ፍሬ አፍርቶ አገር ሰላም ሆና ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ወጣቶች ለውጡን የመጠበቅ ኃላፊነትም አለባቸው።» ሲሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ ወጣት ኤርሚያስ ማቲዮስ ተናግሯል።
ወጣት ኤርሚያስ እንደተናገረው ለአገር ሰላም የሁሉም ማህበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ ቢሆንም ከቁጥሩ ብዛት አንጻርና በቀዳሚ ተሳታፊነት ወጣቱ የተለየ ድርሻ አለው። እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ወጣቶች ያሉባቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ በተለያዩ ማህበራትና አደረጃጀቶች ስር በመታቀፍ ከመንግሥት፤ ከግል ተቋማትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሲንቀሳቀሱ የነበረ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ በውጤቱ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቆይተዋል። በዚህም የተነሳ ወጣቱ በአንድ ወገን ራሱ ለሚያነሳቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት በሌላ በኩል የሕዝብንም ብሶት በመረዳትና ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ አንዲሰጥ በተለያየ መንገድ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በዚህ ዓመታትን በወሰደ እልህ አስጨራሽ ትግልም ከጅምሩ አንስቶ ፊት አውራሪ አንቀሳቃሽ በመሆንና አስከ ነፍስ መሰዋዕትነት በመክፈል በሀገሪቱ ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ በቅቷል። የለውጡ መከሰትም ምንም እንኳን ለሁሉም ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ ምላሽ ማስገኘት ያልቻለ ቢሆንም ለወጣቶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም የፖለቲካ ተሳትፎ መዳበር በር የከፈተ መሆን ችሏል።
ነገር ግን ለውጡ ሲመጣ በሂደቱ ወጣቱ በምን በምን ሊሳተፍና አገሩን በመርዳት ራሱንም ሊጠቅም የሚችልበትን መስመር የሚያሳይ በግልጽ የተቀመጠ አቅጣጫ አልነበረም። በዚህም የተነሳ እንደሚነሳው ጥያቄ ሁሉ የጋራ ተጠቃሚነቱ የሚደገፍ የሚበረታታም ቢሆንም በአንዳንድ ቦታዎች በጥቂት ወጣቶች እኔ ብቻዬን ልጠቀም የሚል እንድምታ በያዘ አካሄድ በለውጡ ሰሞን አላግባብ ካለ ሕግ የግለሰብ ንብረት የመንጠቅ የማውደምና የመዝረፍ እንቅስቃሴዎች በወጣቶች ሲፈጸሙ ተስተውለዋል። ይህ ነገር እንዲከሰት መንገድ የጠረገው ደግሞ ወጣቱ ሁኔታዎችን የሚመለከትበትና የሚረዳበት ብሎም ወደ ተግባር የሚገባበት የተሳሳቱ መንገዶች ስለነበሩ ነው። ከነዚህም መካከል የመጀመሪያው ማንነታቸው የማይታወቅ፣ የራሳቸው ድበቅ አጀንዳ ያላቸው ግለሰቦች በማህበራዊ ሚድያ የሚያናፍሱትን የሀሰትና የተጋነነ መረጃ በመስማት ብቻ ሳያረጋግጥና ሳያጣራ የእነዚህ አካላት ድብቅ ፍላጎት ማሟያ በመሆኑ ነው። ሁለተኛው እንደ ሀገር የተፈጠሩ ችግሮች ቢኖሩም ችግሮቹን ቁጭ ብሎ በሰለጠነ መንገድ በውይይትና በድርድር ለእኛም ለአገርና ለሕዝብም ምን ይጠቅማል በማለት ሳይሆን በግብታዊነት ስለነበር ነው። ይህንንም በማድረጋቸው የንጹሀን ሕይወት ያለፈ፤ በሕዝብና በመንግሥት ንብረት ላይም ኪሳራ የደረሰ ሲሆን ራሳቸውንም ለተለያዩ ችግሮች እየዳረጋቸው ይገኛል።
በተጨማሪ በቅርቡ ከሚከናወነው ተስፋም ስጋትም ከተጋረጠበት ምርጫ ጋር በተያያዘም ከወጣቱ ብዙ ነገር ይጠበቃል ያለው ወጣት ኤርሚያስ ወጣቱ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ያለበትን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል። የምርጫው መካሄድ በራሱ ለወጣቱ የሚኖረው የራሱ ትልቅ ፋይዳ አለው። በመሆኑም በአንድ በኩል ወጣቶች እንደ ዜጋ ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በመጠቀም በንቃት ካርድ በማውጣትና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ይበጀናል የሚሉትን በመለየት ለመምረጥ መዘጋጀት ያለባቸው ሲሆን በሌላ በኩል ምርጫው የሕዝብ ድምጽ ሊከበርበት የሚገባ መሆኑን በመገንዘብ ራስን አላስፈላጊ ከሆኑ የጥፋት እንቅስቃሴዎች በማቀብ የሚመጣውን ውጤት ለመቀበል ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል።
በተጨማሪም በሀገሪቱ በሚከሰቱ ችግሮች ወጣቱ ተጎጂም እንደሚሆን በመገንዘብ የአገር አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን መስራት፤ የመቻቻል የመተሳሰብ እሴቶች እንደ አገር እንዲዳብሩ የበኩላቸውን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን የማስተማሪያ ፈቃድ ከምርጫ ቦርድ ያገኘ በመሆኑ በመላው አገሪቱ በስፋት እየሰራበት አንደሆነም አቶ ኤርምያስ ጨምረው ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል እንደ አገር የወጣቶች የልማት ተሳትፎ ፍላጎትና ጥያቄ ተመሳሳይ ቢሆንም በፍትሀዊነት ምላሽ ከማግኘት አንጻር ግን ዛሬም ድረስ ያልተቀረፉ በርካታ ችግሮች አሉ። ከእነዚህም መካከል በየክልሎች ተመጣጣኝ የሥራ ፈጠራም ሆነ የወጣቶች ተጠቃሚነት ዕድል አለመኖር ይጠቀሳል። የሥራ ዕድል የፈጠሩ አንዳንድ ባለሀብቶች በጣም ዝቀተኛ ክፍያ ለወጣቶች በመክፈል ለማህበራዊ ችግር እንዲዳረጉ ሲያደርጉ መቆየታቸውም አንዱ ችግር ነው። ከመንግሥትም በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች ይቀርቡ የነበሩ ለሥራ የተዘጋጁ የሚባሉ ሼዶች መንገድ፤ ውሃና መብራት የመሳሰሉት መሠረታዊ ነገሮች የጎደሏቸው መሆናቸው እንደ አገር ቀዳሚ የጋራ ችግሮች ናቸው።
ይህ ልዩነት ለሥራ ፈጠራ የሚውሉ ሀብቶችን ከመለየትና ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በክልሎች መካከልም በስፋት የተንጸባረቀና ወጣቶችን ያስኮረፈም ነበር። በዚህ ረገድ መንግሥትም የወጣቶችን ተጠቃሚ መሆን አለበን አጀንዳ በመቀበል ሁሉም እኩል ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚገባው እንደ ፖሊሲ ቢያስቀምጥም በአግባቡ ሲተገበር ግን አልነበረም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከለውጡ በፊት የነበሩት ወጣቶችን የሚያሰባስቡት ማህበራትና ሊጎች በመንግሥት ስር በመሆን ከመንግሥት ጋር የሚሰሩና መንግሥት ለሚፈልገው ጉዳይ የሚንቀሳቀሱ ናቸው የሚል እይታ ስለነበር ነፃ ሆነው ለብዙኃኑ ወጣት ተጠቃሚነት እየሰሩ አይደለም የሚል ቅሬታም በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል። በመሆኑም በለውጡ ሂደት እነዚህ ነገሮች ተስተካክለው በአግባቡ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንሆናለን የሚል በርካታ ወጣቶች ተስፋ ሰንቀው እየጠበቁ ይገኛል።
«ብዙ ጊዜ በጥፋት መንገድ እየተሰማሩ የሚገኙ ሥራ አልባ የሆኑ ወጣቶችና በሥራ ውስጥም ቢሆኑ በተለያዩ ምከንያቶች ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉ ናቸው። በሀገሪቱ ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲቀረፉ የፖለቲካ አመለካከቱም እየተስተካከለ መምጣቱ አይቀርም።» ያለው ወጣት ኤርሚያስ ጨምሮ እንዳብራራው ወጣቱን በኢኮኖሚ ተሳታፊ ለማድረግ ከለውጡ በፊትም የተሰሩ ሥራዎች የነበሩ ቢሆንም በተገቢው ደረጃ ውጤታማ ሆነዋል ማለት አይቻልም ነበር። ከእነዚሀም ተግዳሮቶች መካከል አንደኛው መንግሥት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ሲያመቻችና ሲፈጠር የነበረው በአብዛኛው የወጣቶቹን ፍላጎትና ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ባስገባ መልኩ አለመሆኑ ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት የሚያቀርባቸው ሼዶችን ወጣቶች ለአምስት ዓመት ብቻ ተገልግለው ለሌላ ማስተላለፍ የነበረባቸው ቢሆንም በነበረው ያልተስተካከለ አሠራር ለረጅም ጊዜ ይዘውት በመቆየታቸው ከስር የሚመጡት ወጣቶች የድርሻቸውን ያህል ተጠቃሚ ሆነው ሰርተው አንዳይለወጡ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። እነዚህ ክፍተቶች በመንግሥት በኩል የሚታዩ ሲሆን በራሳቸው በወጣቶችምረገድ ደግሞ ዛሬም ድረስ ያልተቀረፉ ተግዳሮቶች አሉ። ከነዚህም መካከል የመጀመሪያው ወጣቱ ሁሉንም ነገር ቁጭ ብሎ ከመንግሥት ከመጠበቅ ይልቅ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የራሱን ተነሳሽም ቀዳሚ ተሳታፊም በማድረግ የሥራ ባለቤት ለመሆን አለመፍቀድ ይጠቀሳል። ሥራ የመምረጥ፤ አንዳንዶችም ብድር ሲያገኙ ሥራ በመፍጠርና ገንዘቡን ለታሰበለት አላማ በማዋል ራስን ማህበረሰብንና ብሎም ሀገርን ለመጥቀም ከመስራትና በልፋት ተገቢውን ዋጋ ከማግኘት ይልቅ በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ መንቀሳቀስ በስፋት ይስተዋላል።
በሥራ ፈጠራ ረገድ የመንግሥት አላማ ወጣቶችን ሲደግፍ ወይንም ሲያበቃ መኖር ሳይሆን እንደ ሀገር ራሳቸውን የሚያበቁ ወጣቶችን ማፍራት ነው። በአሁኑ ወቅትም መንግሥት በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ነገር ግን በየዓመቱ ከመንግሥትና ከግል የትምህርት ተቋማት ብቻ አየተመረቁ የሚወጡትን ተማሪዎች ሥራ እንዲይዙ ለማድረግ የመንግሥት አቅም ብቻውን በቂ አይደለም። የግል ባለሀብቶች ተሳትፎም ቢሆን በበቂ ደረጃ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል አይደለም። በመሆኑም ወጣቱ ራሱ ሀሳብ በማመንጨት እንደየነባራዊው ሁኔታ ራሱ በመቆጠብና ጥሪት በማፍራት የሥራ ፈጠራው ባለቤትም ሠራተኛም ተጠቃሚም በመሆን ራሱንና አገሩን ለመጥቀም መንቀሳቀስ ይኖርበታል። በዚህ ረገድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ቁጥራቸው በሚጠበቀው ደረጃ ብዙ ባይሆንም ለቁም ነገር የሚበደሩ የተበደሩትንም በወቅቱ የሚመልሱ፤ ብሎም ከእነሱ አልፈው ለሌሎች ዜጎችም የሥራ እድል መፍጠር የቻሉና ሊመሰገኑ የሚገባቸው ወጣቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እነዚሀን እየደገፉ ወደ ትልቅ ደረጃ ማድረስ ከመንግሥት የሚጠበቅ ሲሆን ሚዲያዎችም አርአያነታቸውን በማንሳት ልምዳቸውን ለሌሎች በማካፈል በላብ ሰርቶ ማደግን ለማስተማር ለሕዝብ ጆሮና ዓይን ሊያደርሷቸው እንደሚገባ አቶ ኤርሚያስ አሳስበዋል።
መንግሥት የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ሥራ ሊሆን እንደሚገባ በመገንዘብ ከለውጡ በኋላ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ማቋቋሙን ያስታወሰው ወጣት ኤርሚያስ ይህም ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ያለውን መዋቅር በማስተባበር እየሰራ መሆኑንም ተናግሯል። ችግሮችና ኃላፊነቶችን ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ብቻ መምራት ተገቢ አለመሆኑን የተናገረው ወጣት ኤርሚያስ ክልሎችም በሥራቸው ያሉትን ጸጋዎች በመለየት በማውጣትና በማዘጋጀት ወጣቱን የሥራ ባለቤት ማድረግ፤ በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካውና በኢኮኖሚው መስክ ያለውም ተሳትፎ እንዲያድግ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝቧል።
ለውጡ በግለሰብ ደረጃ አልመጣም፣ በግለሰብ ደረጃም የሚቀጥል አይደለም፣ የሁሉንም ዜጎች በተለይ የወጣቱን ተሳትፎ የሚፈልግ ነው። በፖለቲካው በኢኮኖሚውና ማህበራዊ ዘርፍ አዳዲስ ሀሳቦች ያሏቸው በርካታ ወጣቶች እንዳሉ ይታወቃል፤ እነዚህን ወደ ፊት ማምጣት ይጠበቃል። በተጨማሪም እያንዳንዱ ወጣት ለአኔ ምን ተደረገልኝ ከሚል እሳቤ ሳይሆን ራሱን እየጠቀመ፣ እኔ ለአገሬና ለሕዝቤ ምን ሰራሁ ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት። ለእዚህም በተለያዩ ቦታዎች እየተከናወኑ ያሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን በማየት ራሳችንን ልናዘጋጅ ይገባል። በተጨማሪ የተጀመረው ለውጥ መቀጠል በየደረጃው ሁላችንንም ተጠቃሚ እንደሚያደርገን ሁሉ ለውጡ ምን አልባት ቢቀለበስ የሚያስከፍለን መስዋዕትነት ስለሚኖር ለለውጡ ውጤታማነት ሁላችንም በተለይ ወጣቶች የሚጠበቅብንን ልንሰራ ይገባል ሲል ወጣት ኤርሚያስ ተናግሯል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013