አስቴር ኤልያስ
እነሆ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዛሬ አስረኛ ዓመቱን ደፈነ። በኢትዮጵያውያን ብርቱ ጥረትና በመንግሥት ቆራጥ አመራር ዛሬ ላይ ሲደርስ ያስቆጠረው ዓመታትን ብቻ ሳይሆን በተባበረ ክንድ ተገንብቶ ከ78 በመቶ በላይ ተጠናቆም ጭምር ነው። በእስካሁኑም ሂደት ከግንባታው ጎን ለጎን እየተደረጉ ያሉ ድርድሮችን ኢትዮጵያ በብቃትና በተሻለ እይታ እየተወጣች የመምጣቷን ያህል ያረጁና ያፈጁ የግብጽና የአጋሮቿ ስምምነቶች ደግሞ መከበር አለባቸው የሚሉ ማደናገሪያዎች አሰልቺ እንደነበሩም ይታወሳል።
እነዚህ ግብጽ የሙጥኝ ያለቻቸው የ1929ኙ እና የ1959ኙ አሮጌ ስምምነቶችን እና ሌሎች የተፋሰሱ አገራትን የሚመለከቱ ውሎችና መርህን በማስመልከት ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር እንዴት ይታያሉ? የሚለውንና ሌሎች ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሰነዶችን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የዓለም አቀፍ ሕግ መምህር ከአቶ ዘወዱ መንገሻ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡– ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር አንድ አገር በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን አልምታ እንዳትጠቀም የሚከለክል ድንጋጌ አለ?
አቶ ዘውዱ፡– እንደሚታወቀው አገራት በድንበራ ቸው ውስጥ ሉዓላዊ ናቸው፤ ይህም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ላይ ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ውስጥ የሚታዩ ናቸው። አገራት በድንራቸው ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ያለ ከልካይ ማልማት ይችላሉ። እንዲህ ሲባል ምንም ኃላፊነት የለባቸውም ማለት አይደለም፤ አገራት በተለይ የሚጋሯቸው ወንዞች ወይም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ካሉ በአጠቃቀም ዙሪያ ገደቦች አሉ። የውሃ አጠቃቀማቸው በሌሎች የተፋሰሱ አገራት ላይ ተጽዕኖ እንዳይደርስ ወይም የውሃ አጠቃቀማቸው ፍትሃዊነትንን መሠረት ያደረገ እንዲሆን የተቀመጡ መርሆዎች አሉ።
አዲስ ዘመን፡– አንድ አገር በሌለችበት የስም ምነት ማዕቀፍ እንድትገዛ የሚያስገድዳት የሕግ ወይም የሞራል ግዴታ ይኖር ይሆን?
አቶ ዘውዱ፡– ይህን ለመመለስ ዓለም አቀፍ ሕግ ምንድን ነው የሚለውን ነገር በመጀመሪያ ማየቱ አስፈላጊ ነው። ዓለም አቀፍ ሕግ ስንል በአገራት ስምምነት፣ ዓለም አቀፍ የልማት ሕጎች እና እንዲሁም አጠቃላይ መርሆች አሉት። እነዚህን የሚያጠቃልል ነው፤ ከዚህ አንጻር ስናየው በመርህ ረገድ አገራት ባልፈረሙት ወይም ደግሞ ስምምነታቸውን ባልሰጡበት ሕግ ሊገደዱ አይችሉም።
ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በዚያ ስምምነት ሊገደዱ የሚችሉበት ሁኔታ አለ፤ በተለይ ደግሞ በስምምነቱ ውስጥ የሰፈሩት እሳቤዎች ዓለም አቀፍ የልማት ሕግ ሆኖ ከተገኘ ለምሳሌ አንድ አገር የባርነት ንግድ መፈጸም አትችልም፤ ለምን ቢባል ምንም እንኳ ስምምነት ባይኖርም ይህን ነገር መፈጸም ዓለም አቀፍ የባህል ወይም የልማድ ሕግ ስለሚገድብ እንደ ማለት ነው።
ልክ እንደዚህ ሁሉ አንዳንድ ጉዳዮች ምንም እንኳ አገራት አባል ባይሆኑም ሊገደዱ የሚችሉበት ሁኔታ አለ። ከዚህ ውጪ ግን በአብዛኛው አገራት ስምምነት ባልሰጡበት ጉዳይ በምንም ዓይነት አግባብ ተጠያቂ አይሆኑም። ምክንያቱም የዓለም አቀፍ ሕግ ዋናው መርህ የአገራት ሉዓላዊነት ነው። ሉዓላዊነት ላይ ደግሞ በምንም ዓይነት መንገድ ሌላ ተጽዕኖ ሊፈጠርበት አይችልም። ይሁንና አገራት ይህንን ወይም ደግሞ ያንን አደርጋለሁ ብለው ስምምነታቸውን ከሰጡ ብቻ ነው ሊገደዱ የሚችሉት። እሱ ካልሆነ ግን አይገደዱም።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በ1929 እና በ1959 በግብጽ እና በሱዳን መካከል ለተደረሰው ስምምነት ተገዥ የምትሆ ንበት አግባብ ይኖራል?
አቶ ዘውዱ፡– ያነሳሻቸው ስምምነቶች የ1929 እና የ1959 ሁለት ስምምነቶች በተደጋጋሚ በታችኛው ተፋሰስ አገራት ሲነሱ ይስተዋላል። የ1929 ስምምነት የሚባለው የተደረገው በግብጽና በታላቋ ብርታኒያ መካከል ነው፤ ይህ ስምምነት ሲደረግ ግብጽ ራሷን ወክላ ሲሆን፣ ታላቋ ብሪታኒያ ደግሞ በቅኝ ግዛት ስር የምታስተዳድራቸውን አገራት ወክላ ያደረገችው ስምምነት ነው። ይህ ስምምነት የሚያሳየን ነገር ግብጽ በአንድ በኩል ሆና ታላቋ ብሪታኒያ ደግሞ በላይኛው ተፋሰስ በቅኝ ግዛት የምታስዳድራቸው አገራት መካከል የተደረገ ስምምነት ነው።
ሌላው ያነሳሽው የ1959 ስምምነት ደግሞ ልክ ሱዳን ከቅኝ ግዛት ነፃ ስትወጣ በግብጽ እና በአዲሱ ሱዳንን ሲያተዳድር የነበረው ቡድን ጋር የተደረገ ስምምነት ነው። የ1959 ስምምነት ለመመስረቱ ዋናው ገፊ ምክንያት የነበረው ሱዳን ልክ ከቅኝ ግዛት በምትወጣበት ወቅት በ1929 የተደረገው ስምምነት የሱዳንን ጥቅም በአግባቡ የሚያስጠበቅ ባለመሆኑ ከግብጽ ጋር ስምምነት ለማድረግ በሱዳን ውስጥ ያለው እንቅስቃሴን በማየት ግብጾች ይህን ስምምነት የግድ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን በመረዳት የተደረገ ስምምነት ነው።
በነገራችን ላይ ይህ የ1959 ስምምነት ሂደት ላይ እያለ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይሥላሴ ስምምነቱን መቃወማቸው ይታወቃል። ምክንያቱም በስምምነቱ ውስጥ ሌሎች የተፋሰሱ አገራት በተለይ ኢትዮጵያ መሳተፍ እንዳለባት በተደጋጋሚ ባሏቸው የዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ሲያሳውቁ እንደነበር ይታወቃል።
ይህ ስምምነት ብዙ ጊዜ የሚነሳ ሲሆን፣ በዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ ትገዛለች ወይ የሚለውን ጥያቄ ስናነሳ በዚህ ስምምነት ኢትዮጵያን የሚመለከት ምንም ነገር የለም። በተለይ ስምምነቶች እንዴት ይደረጋሉ፤ የስምምነቶቹ አመራር እንዴት ይመራል የሚል አንድ የቬና ስምምነት የሚባለው ሕግ አለ፤ ይህ የቬና ስምምነት ሁለት አገራት ያደረጉትን ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል ብቻ የሚቆም እንጂ ሌላ ሦስተኛ አገር ላይ መብትም ሆነ ግዴታ መፍጠር አይችሉም የሚል ነው።
ስለዚህ እኤአ በ1929ኙ ስምምት ሆነ በ1959ኙ ስምምነት ኢትዮጵያን በምንም ዓይነት አግባብ የሚመለከት ጉዳይ የለውም። ምክንያቱም ስምምነቱ ያለው በግብጽ እና በሱዳን፣ እንዲሁም በግብጽ እና በወቅቱ በቅኝ ግዛት ስታስተዳድራቸው በነበሩ የእንግሊዝ ግዛቶች መካከል የተደረገ ስምምነት ነው። በመሆኑም ከኢትዮጵያ ጋር የሚያያይዘው ጉዳይ የለም፤ ነገር ግን እነርሱ ለምሳሌ እኤአ በ1959 ብዙ ጊዜ እንደሚነሳው 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለግብጽ ሲሰጥ፤ 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ደግሞ ለሱዳን ይሰጣል።
ሱዳን እስካሁን ድረስም ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ ይህን 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንኳ መጠቀም አልቻለችም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በተደጋጋሚ የሚወርደው ጎርፍ ስላለ ያንን ገድበው ማቆየት አቅምም የላቸውም፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ የሚነሳው የሮሰሪስ ግድብ ቢሆንም የመያዝ አቅሙ ወደ አራት ነጥብ ዘጠኝ ወይም ወደ አምስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ነው። ስለዚህ ይህ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ለምሳሌ ማንሳት ካስፈለገ ሙሉ በሙሉ በሚያስችል ረገድ መጠቀም የሚችሉት ከ 12 እስከ 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ብቻ ነው፤ አሁን ላይ ሱዳኖች እየተጠቀሙበት ያለው ውሃ ይህን ያህል ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሱዳን እና በግብጽ የሚነሱ ጥያቄዎች ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር እንዴት ይታያል?
አቶ ዘውዱ፡– እንዳልሽው በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የተለያዩ ሐሳቦች ይነሳሉ። በተለይ አንደኛው የግብጽ ጥያቄ ቀድሞ ያለን የመጠቀም መብት በአግባቡ መከበር አለበት የሚል ጥያቄ ነው። ወይም ደግሞ ያንን የመጠቀም መብት እኤአ በ1929ኙ ስምምነት ያገኘነው ነው ብለው ነው የሚሉት። ታሪካዊ መብት ብለው የሚጠሩት ነው፤ ያንን ስምምነት ደግሞ ኢትዮጵያ ልትቀበል ይገባል የሚል ጥያቄ አላቸው።
በሱዳን በኩል ደግሞ የሚነሱ የተለያዩ ማደናገሪያዎች አሉ፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከግድቡ ደህንነት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጉዳይ አለ። እንደምናየው ከሆነ በአሁን ዘመን የሚገነቡ ግድቦች በተለያየ ቴክኖሎጂዎች አኳያ ሲታይ የተሻሉ ናቸው፤ የአስዋን ግድብ ሲገነባ የነበረው ቴክኖሎጂ እና አሁን ላይ የተደረሰበት ቴክኖሎጂ የተለያየ ከመሆኑም በላይ አሁን ላይ ያለው ለግድቦች ደህንነት ይበልጥ የተሻለ ነው ተብሎ ይታመናል።
የአስዋን ግድብ ከተገነባ የቆየ ሲሆን፣ እስከዛሬ ድረስ ያለምንም ችግር እያገለገለ የሚገኝ ግድብ ነው። የግድብ ይዘቱንም ስናይ ከእኛ ግድብ በብዙ እጥፍ ይበልጣል። ለምሳሌ ምንም እንኳ የማመንጨቱ አቅሙ ከፍ ያለ ባይሆንም 162 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም ነው ያለው፤ የእኛ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምንለው ግን 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ነው የሚይዘው፣ ከአስዋን ጋር ሲነጻጸር አስዋን ከእጥፍ በላይ ውሃ ይይዛል ማለት ነው። እንግዲህ በ1950ዎቹ የተገነባው የአስዋን ግድብ አሁንም ድረስ ምንም ችግር ሳይኖርበት እያገለገለ ነው፤ አሁን ደግሞ የግንባታው ቴክኖሎጂ አድጓል።
ስለዚህ ቀደም ሲል እንደገለጽኩልሽ በእነርሱ በኩል እየቀረቡ ያሉት የማደናገሪያ ሐሳቦች ናቸው። የእነዚህ የማደናገሪያ ሐሳቦች ዋናው ግብ ምንድን ነው ሲባል፤ ቀድሞ የነበረን የውሃ አጠቃቀም ሂደትን አስከብሮ ማለፍን ታሳቢ ያደረገ ወይም ደግሞ የመጨረሻ ኢላማው ይህ ቀድሞ ያለውን የአጠቃቀም ሥርዓት አስጠብቆ መሄድን እሳቤ ያደረገ ነው ብሎ መናገር ይቻላል።
በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የሚነሳው ነገር ምንድን ከተባለ በተደጋጋሚ እንደሚነገረው አብዛኛው ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሌለው፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦቱ እጅግ በጣም ዝቅተኛ የሆነ፣ ከዚያም ባለፈ አብዛኛው ማህበረሰብ በችግር ውስጥ እንዳለ የሚታሰብ ነው። እናም ይህን የግድብ ግንባታ እና ከግድቡ ጋር የሚገኙትን ጥቅሞች ማግኘት አለብን ተብሎ የሚታሰበው ውሃ ወይም በድንበር ተሻጋሪ ወንዙ ያለንን በእኩልነት እና በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት ለማረጋገጥ የቀረበ ጥያቄ ነው። ሌላ ምንም ነገር የለም።
ይህን ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር ስናየው ምንም የሚነሳበት ጥያቄ የለም። በተደጋጋሚ እነሱ የሚያነሱት አገራት ሲጠቀሙ በሌላኛዎቹ ተፋሰስ አገራት ላይ ጉልህ የሆነ ጉዳት ማድረስ የለባቸውም፤ ይህ ልክ ነው፤ ነገር ግን ፍትሃዊና ምክንያታዊ የሆነ የአጠቃቀም ሥርዓት ባልተዘረጋበት ሁኔታ አንዳንድ ጊዜም ቢሆን ጉዳቶች ሊደርሱ ይችላሉ።
ምክንያቱም ቀድሞም የነበረ በተፋሰሱ ውስጥ ያለው የውሃ አጠቃቀም ምክንያታዊና ፍትሃዊ ካልሆነ ሌላኛው መጠቀም ሲጀምር ራሱ ብዙ ጉዳት ሊደርስ ይችላል። እናም በዚህ ላይ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ጉዳይ ጉዳት አለማድረስ የሚለው እሳቤ ራሱ በምክንያታዊነት እና ፍትሃዊነት አጠቃቀም ውስጥ መታየት ያለበት ነው።
አዲስ ዘመን፡– በ1929 እና በ1959 በሱዳን እና በግብጽ መካከል ተፈረመ የሚባለው ስምምነት ቅኝ ገዢዎች በስምምነት የፈረሟቸው፤ የአገራቱን ሕዝብ ጥቅም ታሳቢ ያላደረጉ እንደሆነ በስፋት ይነገራል፤ ይህን ስምምነት በዚህ ዘመን አንስቶ ለተፈጻሚነቱ መንቀሳቀስ የቅኝ ገዢዎችን ሴራ ማስፈጸም ነው የሚሉ አሉ፤ ይህን እንዴት ያዩታል?
አቶ ዘውዱ፡– አገራት ጥቅሞቻቸውን ሊያስከብሩላ ቸው የሚችሉ ማናቸውንም ነገሮች ሊያደርጉ ይችላሉ። ለምሳሌ የ1929ኙ ስምምነት በተለይ በግብጽ እና በእንግሊዝ መካከል የተደረጉ ውሎች ናቸው። ይህንን ውል በተለይ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ አገራት በተደጋጋሚ ይቃወሙታል።
በተለይ የቀድሞ የታንጋኒካ መሪ (በኋላ ላይ ስሟ ወደታንዛኒያ የተቀየረች አገር) የነበሩት ጁሊየስ ኔሬሬ ልክ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲወጡ በቅኝ ገዢዎች የተደረጉ ውሎችን የመውረስ ግዴታ የለብንም የሚል እይታ ነበራቸው። ይህ ‹‹የጁሊየስ ኔሬሬ›› ዶክትሪን በመባል የሚታወቅ ነው። እርሳቸው አገራት እንደ አዲስ ነው መፈጠርና መወለድ ያለባቸው የሚል አመለካከት አላቸው፤ ሳይፈልጉ በቅኝ ግዛት የተገዙ እንዲሁም ሳይፈልጉ በቅኝ ገዢዎች በተደረገ ውል ሊገዙ ወይም እሱን ሊያከብሩ አይገባም የሚል አስተሳሰብም አለ።
በእርግጥ የአፍሪካ አገራትም ይህንን ሐሳብ ይቀበሉታል። ነገር ግን የድንበር ማካለል ውል ከሆነ የቅኝ ገዢዎችን ውል ልንቀበል ይገባል ብለው በካይሮ ዲክላሬሽን በኋላም በአፍሪካ ህብረት መመስረቻ ጽሑፍ ውስጥ አካተውታል። ስለዚህ ከድንበር ማካለል ውጪ ያሉ ጉዳዮችን፤ የተደረጉ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲወጡ እያዩ የሚጥቅሟቸውን ሊቀበሉ ይገባል፤ የማይጠቅሟቸውን ደግሞ ሊቀበሉ አይገባም የሚለው ተቀባይነት ያለው መርህ ነው።
ከዚህ አንጻር ግብጽም የ1929ን ስምምነት የምታነሳው ለምንድን ነው ቢባል፤ በተሻለ መጠን የግብጽን ጥቅም ስለሚያስከብር ነው። በተደጋጋሚም የ1959ን ውል በተለያየ መልኩ በማደናገሪያነት የምታነሳው ስምምነቱ ለግብጽ የተሻለ የውሃ መጠን የሚሰጥ እና ሌሎቹን የተፋሰሱ አገራት ከጉዳዩ የሚያስወጣ በመሆኑ ነው። ስለዚህ ቀደም ብዬ እንዳልኩት የተለያየ የማደናገሪያ ሐሳቦችን፣ መንገዶችን እና አማራጮችን በማምጣት አገራት የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚሄዱበት መንገድ ስለሆነ ግልጽ ነው።
አዲስ ዘመን፡– እ.ኤ. አ በ2010 የናይል የትብ ብር ማዕቀፍ ስምምነትን (ሲ.ኤፍ.ኤ) ኢትዮጵያ ማስፈረም መቻሏ ከሕግ አኳያ ያበረከተው ጥቅም የት ድረስ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ዘውዱ፡– የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ስንል ከረጅም ጊዜ በኋላ ረቂቅ ሕግ ሆኖ ለፊርማ ክፍት የሆነ ነው። በወቅቱ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ በሚባለው ተቋም /በዓለም ባንክ ድጋፍ ሲደረግለት የነበረ ነው/ በኩል ረጅም ጊዜ ክርክር ሲደረግበት ቆይቷል ። በዚህ ሂደት እውነት ለመናገር በኢትዮጵያ በኩል በጣም ከፍ ያለ ትግል ተደርጓል ማለት እንችላለን። በተለይ የተፋሰሱ አገራትን በማስተባበር ይህ የማቀዕፍ ስምምነት እንዲሆን የተደረገው ጥረት ከፍ ያለ ነው።
ከዚህ በፊት በተለይ ውሃውን በእኩልነትና በፍትሃዊነት ለመጠቀም በሚያስችል መርህ እና አግባብ ሁሉንም የተፋሰሱን አገራት ያካተተ ድርድር እና ውይይት አልተደረገም ማለት ይቻላል። ስለዚህ እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ሚና ለዚህ ስምምነት ትልቅ እንደመሆኑ ሻምፒዮን ነበረች ማለት ይቻላል። ምክንያቱም በጣም ረዘም ያለ ጊዜ ተወስዶበት የመጣ ነው። በእርግጥ ከዚያ በፊት የነበሩ ሙከራዎች አሉ። ነገር ግን የነበሩ ሙከራዎች በአብዛኛው በግብጽ የበላይነት የሚደረጉ ሲሆኑ፣ ትርጉም ያለው የትብብር ማዕቀፍ ሳይሆን ያለውን የውሃ አጠቃቀም ለማስቀጠል የታሰቡ ሂደቶች ነበሩ። የወንድማማችነት እንዲሁም የባህል ልውውጥ ላይ ያተኮረ ነው። በተግባር ግን ውሃውን በፍትሃዊነት እና በእኩልነት ለመጠቀም በሚያስችል መርህ ላይ የታሰበ አልነበረም።
በተደጋጋሚ እንደሚነገረው እዚህ ላይ አንደኛው የልዩነት መንስኤ የነበረው የውሃ ደህንነት የሚለው ሐሳብ ነው፤ በተለይ በአንቀጽ 14 ላይ የሰፈረው ማለት ነው። በዚህ አንቀጽ ላይ ግብጽ እና ሱዳን የውሃ ደህንነት ማለት አሁን ያለውን የውሃ አጠቃቀም በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት የሚል ትርጓሜ ሲሰጡት፤ ሌሎቹ የተፋሰስ አገራት ደግሞ አሁን እና ወደፊት ያለውን የውሃ አጠቃቀምን በአግባቡ ያከበረ ሊሆን ይገባል የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፣ በዚህ ምክንያት በላይኞቹ እና በታችኞቹ ተፋሰስ አገራት መካከል ልዩነት ተፈጠረ ማለት ነው።
ስለዚህ ይህ የሚያሳየው አሁን ያለውን የአጠቃቀም ሂደት ካየን የላይኞቹ ተፋሰስ አገራት ውሃውን በአግባቡ አልተጠቀሙም፤ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት በተለይ ግብጽ ውሃውን ወይም ደግሞ ከተፋሰሱ ውጪ አውጥተው ወደ ፒስ ካናልና ቶሺካ ዲፕሬሽን ወስደው ተጠቅመውበታል፤ ስለዚህ ያንን እውቅና መስጠት በጣም ከባድ ነው። በተፋሰሱ ውስጥ ገና ያልለማ ብዙ እያለ ከተፋሰሱ ውጪ አውጥተው ወደተለያየ ቦታ እየተጠቀሙ ባሉበት ሁኔታ ለግብጽ ጥያቄ እውቅና መስጠት አግባብ ስላልሆነ የልዩነት መንስዔ ይሆናል።
ይህ በግልጽ የሚያሳየን ነገር ግብጾች በተደጋጋሚ በድርድር ሂደት ውስጥ የሲ.ኤፍ.ኤ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ውስጥ ቀድመው የተደረጉ የ1929ኙ እና የ1959ኙ የውሃ ክፍፍሎችን እውቅና እንዲሰጥ ሲጠይቁ እንደነበር ነው። ይህ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የተፋሰስ አገራት ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።
እንደሚታወቀው የትብብር ማዕቀፉን ስድስት አገራት ፈርመው ካጸደቁት ወደተግባራዊነት ይለወጣል ተብሎ ነበር፤ ነገር ግን አሁን ላይ ስምምነቱን በመፈረም እና በማጽደቁ በኩል የመቀዛቀዝ ሁኔታ ይስተዋላል። ምናልባት አንደኛው ምክንያት በወቅቱ በነበረው ደረጃ በኢትዮጵያ በኩል የነበረው እንቅስቃሴ ቀንሷል። አሁን ላይ አራት አገራት የትብብር ማዕቀፉን አጽድቀውታል፤ በተጨማሪ ሁለት አገራት ማጽደቅ ከቻሉ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እዚህ ላይ እንቅስቃሴ ማድረግ ተገቢ ነው። በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ያንን ማድረግ ከተቻለ ወደተግባራዊነት ሊቀየር ይችላል ማለት ነው።
አሁን ላይ ያለው ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ያለው ድርድር ሁለት አገራት በአንድ በኩልና ኢትዮጵያ ብቻዋን መሆኗን የሚያሳይ ነው። ኢትዮጵያ ግን ድርድሩ የትብብር ማዕቀፉ ላይ ከሆነና እሱ ደግሞ ወደ ተግባራዊነቱ ከገባ ሁሉም የተፋሰሱ አገራት በስምምነቱ ላይ ፍላጎት አላቸው ማለት ነው። ስለዚህ ይህ ከሆነ የድርድር ማዕቀፉ ሌሎችም የተፋሰሱ አገራት ፍላጎት ስላላቸው በተለይ ያልፈረሙ አገራትን በማስፈረሙ በኩል ኢትዮጵያ ግፊት ልታደርግ ይገባል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ዑጋንዳ ናቸው በአገራቸው ፓርላማ ያጸደቁት። ኬንያ እና ቡሩንዲ ስምምነቱን ፈርመዋል፤ ነገር ግን በየፓርላማቸው አላጸደቁትም። እነዚህ አገራት እንዲያጸድቁት ግፊት ማሳደር ከተቻለ የስምምነት ማዕቀፉ አንድ ነገር በተፋሰሱ ውስጥ ላሉ አገራት ይጨምራል ማለት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ በዚህ ነገር የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባታል።
አዲስ ዘመን፡– ስምምነቱ ተፈርሞ ቢጠናቀቅ በ1929 እና በ1959 የተደረጉት ስምምነቶች ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ይችላል ተብሎ ይታሰባል?
አቶ ዘውዱ፡– አዎ! ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የ1959ኙ ስምምነት በተደጋጋሚ ግብጽ እና ሱዳን ሌሎች በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ እነ ኬንያን እና ታንዛንያን ዓይነት አገራትን ያስገድዳል የሚል ሐሳብ አላቸው። ስለዚህ ይህንን ከመሰረቱ አልቀበልም የሚል ስምምነት ነው። ይህ ስምምነት ሲታይ አብዛኛዎቹ ሐሳቦች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ1997 ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ከመጓጓዣ ውጪ ለመጠቀም የተደረገው ስምምነት ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ሐሳቦች ናቸው የተካተቱት፤ ስለዚህ በአብዛኛው ጥቅል የሆነው መርሆ ውሃውን በእኩልነትና በፍትሃዊነት የመጠቀም ነው። ስለዚህ እሱ ከሆነ ቀድሞ የነበረውን የቅኝ ግዛት ስምምነት መሠረት በግብጽና በሱዳን የሚጠየቀውን ጥያቄ በአንድ በኩል ወደጎን ትቶ አዲስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ለማምጣት ያስችላል።
በነገራችን ላይ የአረብ ርዕዮት የሚባለው የመንግሥት ግልበጣዎች እንቅስቃሴ በነበረበት ወቅት የግብጽ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በነበረበት ጊዜ ግብጾች ወደዚህ ስምምነት ማዕቀፍ የመግባትም ሐሳብ እንዳላቸው የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ቡድን አባላት ሲናገሩ እንደነበርም ይታወሳል። በወቅቱ እንዲያውም በተወሰነ መልኩ ሱዳን የስምምነቱን ማዕቀፍ አይተን እና አጥንተን ልንቀላቀል እንችላለን የሚል ዓይነት እሳቤ ያላቸው ንግግሮች በባለሥልጣናቱ በኩል ሲወጡ ነበር። ስለዚህ እዚህ ጉዳይ ላይ መግፋት ከተቻለ ቀድሞ የነበረውና ለታችኛዎቹ ተፋሰስ አገራት መሠረት ያደረገውን የውሃ አጠቃቀም ሂደት ለመቀየር የሚቻልበት ዕድል ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡– እ.ኤ.አ በ2015 በሦስቱ አገሮች መካከል በግድቡ ዙሪያ «የመርህ መግለጫ» የሚል ባለ አስር አንቀጽ ውል ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወቃል፤ ይህ ውል በአገራቱ መካከል የሰፈነውን ውጥረት ከማርገቡ ሌላ ሰነዱ ለኢትዮጵያ ያስገኘው ውጤት ምንድን ነው?
አቶ ዘውዱ፡– እንዳልሽው ስምምነቱ በመጋቢት ወር 2015 ላይ መደረጉ ይታወቃል። ስምምነቱ በወቅቱ የነበረውን ውጥረት እንዳልሽው ቀንሷል። ግድቡ ለአገራቱ እድገት እንጂ የግጭት መንስኤ እንዳይሆን ታሳቢ ያደረገ ስምምነት መሆኑን ነው መግቢያው ላይ ያስቀመጠው።
በስምምነቱ ውስጥ የተቀመጡ መርሆች በአንድም ሆነ በሌላም መልኩ በዓለም አቀፍ ሕግ እውቅና ያላቸው ናቸው ማለት ይቻላል። ነገር ግን አንዳንዴ ደግሞ የተወሰኑ ነገሮችም አሉት። የግድቡን ጥቅም የኃይል ማመንጫ ብቻ አድርጎ ለመውሰድ መሞከሩ፤ በተለይ ትኩረት የተሰጠው ጉልህ ጉዳት ያለመድረስ የሚል መርህ የሚመስል ነገር አለው። ምክንያቱም አንዳንዴ የየራሱ አንቀጽ በሕግ ሲረቀቅ ቅድሚያ ምን ተሰጥቶታል የሚለው ነገር የራሱ የሆነ ዋጋ ሊኖረው ይችላል።
ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ለምሳሌ ሦስቱ አገራት ናይል ላይ በተለይ ብሉ ናይል በሚሉት ላይ ጉልህ ጉዳት ላለማድረስ ስምምነት እንዳደረጉ አንቀጽ ሦስት ላይ ተቀምጧል። አንዳንዴ እንዲህ ሲታይ ይበልጥ ግዴታውን ወደላይኛው ተፋሰስ አገር ኢትዮጵያ የማድረግ ዓይነት ስሜት ያለው ይመስላል። ምክንያቱም አሁን ግድብ እየገነባን ነው፤ ግድብ እየገነባን ባለበት ሁኔታ ጉልህ ጉዳት አናደርስም የሚል ዓይነት እሳቤ አለው።
ነገር ግን መሆን ያለበት መጀመሪያ በተፋሰሱ ውስጥ የእኩልነትና ምክንያታዊ የሆነ የአጠቃቀም ሥራ መዘርጋት መቅደም አለበት። ይህ እኩል እና ፍትሃዊ የሆነ የውሃ አጠቃቀም ሥርዓት ባልተዘረጋበት ሁኔታ አንዱ አገር ቀድሞ ብዙ ፕሮጀክቶች እና ብዙ ሥራ በሰራበት ሁኔታ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስን ቀድሞ እንደመርህ ማስቀመጥ ተገቢ አይሆንም። ስለዚህም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባዋል ብዬ የማስበው ያንን ነው።
ይህ እንዳለ ሆኖ ይህ ስምምነት መደረጉ በአገራቱ መካከል ያለውን ውጥረት ቀንሷል፤ ከዚያም ባለፈ ከ2015 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ላሉት የድርድርና ውይይት ዋና መነሻ ሆኖ አገልግሏል። በርካታ ነገሮችም ላይ ስምምነት መደረስ ተችሏል። በተለይ በአገራቱ መካከል በተወሰነ መልኩ ግን በፕሮጀክቶቹ የሆነ ዓይነት በራስ የመተማመን ነገር እንዲኖር አድርጓል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– የግድቡ የውሃ ሙሌት ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ ነው ብለው ያምናሉ? የግድቡን የውሃ ሙሌትስ የሚከለክል ዓለም አቀፍ ሕግስ አለ?
አቶ ዘውዱ፡– ዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ስንመጣ ያሉ ስምምነቶች አሉ፤ ከእነዚህ ስምምነቶች ውጪ ደግሞ ዓለም አቀፍ ያልሆኑ የልማድ ሕጎች ወይም ደግሞ መርሆች ናቸው። በስምምነት ረገድ ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረግ ግድብ መሙላት አትችልም የሚል ምንም ዓይነት ስምምነት ከታችኛዎቹ የተፋሰሱ አገራት ጋር አልገባችም። ኢትዮጵያ በእኩልነትና በፍትሃዊነት መርህ መሠረት ግድቡን የመሙላት መብት አላት። ይህን የሚከለክል ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ሕግ የለም። በጥቅሉ የህዳሴ ግድቡን ለመሙላት የሚከለክል ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ሕግ የለም ማለት ይቻላል።
ነገር ግን ይህን ስታደርግ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ዓይነት መርሆችን የመከተል ግዴታ ይጥልባታል። እስካሁን ያለን አጠቃቀም በፍትሃዊነት እና በእኩልነት ነው ወይ የሚለው ነገር ዋናው ቀድሞ መምጣት ያለበት ጉዳይ ነው።
ምክንያቱም በተፋሰሱ ውስጥ ያለው የአጠቃቀም ሂደት በአማካይ ሲታይ ልዩነት ቢኖርም የናይል ወንዝ ፍሰት አለ፤ ለምሳሌ ብሉ ናይል ወደ 49 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ነው የሚባለው። ጠቅላላ የናይል ወንዝ ፍሰት ደግሞ ወደ 84 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ነው። እዚህ ውስጥ ሁለቱ አገራት 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በሁለቱ አገራት መካከል ተከፋፍሎ ተቀምጧልና ይህ ራሱ በቀላሉ የሚያሳየን ነገር እነሱ እንዲከበር ብለው የሚጠይቁት የቀድሞ ስምምነቶች ሙሉ ፍትሃዊነትና ምክንያታዊነት የጎደለው ነው ማለት እንችላለን።
ስለዚህ በኢትዮጵያ በኩል ይህን ለመሙላት የሚደረገው ሂደት ሊገድብ የሚችል ስምምነት የለም። የመርህ ስምምነቱም ቢሆን ይህን አይገድብም። ያሉትም ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ዓለም አቀፍ መርሆች ወይም የልማድ ሕጎችም ይህንን አይገድቡም። ዝርዝርነት የሌላቸው ሕጎች ናቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣውን አሊያም የሚጥለው ዝርዝር ግዴታ የለም።
አዲስ ዘመን፡– በውሃ ጉዳይ የሚነሱ አለመግ ባባቶች በምን መልኩ መፈታት አለባቸው ብለው ያምናሉ? ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችስ ምን ይመስ ላሉ?
አቶ ዘውዱ፡– ዓለም አቀፍ ወንዞችን በተመለከተ የሚገቡ አለመግባባቶች መፈታት ያለባቸው በአገራት ስምምነት ነው። በተለይ እነዚህ ወንዞች በተገቢው አግባብ በትብብር ማዕቀፍ አንዱ ለአንዱ ታሳቢ ባደረገ መልኩ መፈታት መቻል አለበት። ብዙ ጊዜ የሚስተዋለው በተለይ በግብጽ በኩል የሚነሱ ነገሮች አሉ።
ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው የተለያዩ አገራት አሉ። በተለይ ወንዙ ሁሉንም አገራት ባማከለ መልኩ የሚጠቀሙበት አሉ። ለምሳሌ ያህል ኢስያ ውስጥ ካሉ አገሮች አንደኛው አገር ለኃይል ማመንጫ ግድብ የሚያስፈልግ ድጋፍ ሲያደርግ ሌላኛው አገር ደግሞ የሚመነጨውን ኃይል ለመስጠት ስምምነት ያደረገ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል። በአህጉራችን አፍሪካ ውስጥ ራሱ እኤአ በ1980ዎቹ በሌሴቶ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል የተደረገውን ስምምነት ሲታይ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ገንዘብ ደግፋለች፤ ሌሴቶ ደግሞ ለመጠጥና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሆነውን ውሃ ያቀረበችበት ሁኔታ አለ። እነፓኪስታን እና ካዛኪስታን ጋርም እንዲሁ ዓይነት ነገሮች አሉ።
ውሃውን በአግባቡ እርስ በእርስ የሁለቱንም ወይም በተፋሰሱ ውስጥ ያሉ አገራትን ጥቅም ባማከለ መልኩ የሁሉንም ፍላጎት በመተማመን መንፈስ መጠቀም ይቻላል። ዋናው የዚህ መፍትሄ የሚሆነው በንግግር እና በድርድር ነው። ሌሎቹ መፍትሄዎች የቱንም ያህል ሊያራምዱን አይችሉም። የውሃው ጥቅም ከውሃው መከፋፈል ይልቅ ውሃው ሊያስገኘው የሚችለውን ጥቅም በአግባቡ መከፋፈል የሚችልበትን ሥርዓት መዘርጋት ነው። የአውሮፓ አገራትም ልምድ ብናይ የሚያሳየው ይህንን ነው።
እነዚያን ተሞክሮ አምጥቶ በአግባቡ መጠቀም ያለውን ችግር ለመፍታት ያስችላል። ነገር ግን በታችኛዎቹ ተፋሰሶች በተለይም በግብጽ የሚራመድ ሀሳብ ቀድሞ ያሉትን እንደ ቀኝ ግዛት ስምምነት ዓይነት ወይም ከቅኝ ግዛት ማግስት የተደረጉ ስምምነት ላይ የተቀመጡ መብቶችን ሙሉ ለሙሉ ማክበር አለባችሁ የሚለው ሀሳብ በመሰረቱ ችግር ያለበት ነው። ማንም ወደዚህ ዓይነት ድርድር ውስጥ አይገባም። ስለዚህም የሁሉንም የተፋሰሱ አገራት ችግር ታሳቢ ያደረገ አዲስ ስምምነት ውስጥ መግባት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– በግድቡ ግንባታም ሆነ በፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግሥት የያዘውን አቋም እንዴት ያዩታል?
አቶ ዘውዱ፡– ይህ ግድብ ከመጀመሩ በፊት ቅድም ባልኩት የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ በሚባለው ተቋም ውስጥ ለረጅም ጊዜ ድርድር በማድረግ፣ የናይል ወንዝ ትብብር ማዕቀፍ እንዲመጣ በማድረግ በኩል ኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራት። ከዚያም ባሻገር ይህ ግድብ ከተጀመረ አንስቶ በተለያየ አግባብ ፕሮጀክቱን በተመለከተ በግብጽ በኩል የሚነሱ ቅሬታዎችንም ይሁን ጥያቄዎችን የተለያዩ መዋቅሮችን በመፍጠር አቀናጅቶ በዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲሁም በሦስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴ፣ ገለልተኛ በሆነ ብሔራዊ የሳይንስ ምርምር ቡድን በሚባሉ ተቋማት ውስጥ ኢትዮጵያ የግብጽን ባለሙያዎች በማሳተፍ ጭምር ስለ ፕሮጀክቱ እውነታውን እንዲገነዘቡ በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጋለች።
እዚህ ላይ የሚታየኝ ነገር በኢትዮጵያ በኩል በፍጹም ቅንነት በተመሰረተ መርህ የግብጽ ወንድሞቻችን ወይም የታችኛው ተፋሰስ አገራት በሂደቱ ውስጥ ያለውን ነገር እንዲረዱ የማድረግ ሥራ ተሞክሯል።
ለዓለምአቀፍ ሕጉ ቅን ልቦና የሚባለው ዋና መርህ ነው፤ ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ተግባቦቱም ጭምር። ነገር ግን በታችኛው ተፋሰስ አገራት በኩል የነበረው እሳቤ ታሪካዊ ባለመብትነት፣ አዲስ የሚመጡ አጠቃቀሞች ቀድመው ያሉ የግብጽን የመጠቀም ሂደቶች ሊያከብሩ ይገባል የሚል ነው። አሁንም እርሱን ነው በተለያየ ዓይነት በተደጋጋሚ መንገድ እየተናገሩ ያሉት።
ለምሳሌ ከግድቡ የውሃ ፍሰት፣ ከታችኞቹ ተፋሰስ ላይ የተሰሩ ግድቦችን ለመያያዝ የሚደረገው ጥረት ሁሉ እሳቤያቸው ቀድሞ ያለውን የውሃ አጠቃቀም ለማስጠበቅ ነው። ይህ ደግሞ በተለይ ለናይል ተፋሰስ ውስጥ ላሉ አገራት በተለይ ፍትሀዊና ምክንያታዊ የሆነ የአጠቃቀም ሥርዓት ያልተመሰረተበት ስለሆነ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም እነርሱ ያንኑ ለማስጠበቅ ነው የሚፈልጉት። እኛ ደግሞ እንጠቀም ባይ ነን። ስለዚህም እነዚህን ማስታረቅ የሚገባው በተለይ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ለላይኞቹ የተፋሰስ አገራት ጥያቄ የቅን ልቦና መልስ መስጠት ከቻሉ ነው። እሱ ካልሆነ አስቸጋሪ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ማራሪያ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ዘውዱ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013