በአፍሪካ ሕብረት ዓርማ ላይ አሻራውን ያሳረፈ ወጣት

አርቲስት ያዴሳ ዘውገ ቦጂአ ይባላል። በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ አስጎሪ ከተማ የተወለደ ሲሆን፤ ለቤቱ ከስምንት ወንድ እና ከዘጠኝ ሴት ልጆች በኋላ የተወለደ ለእናት እና አባቱ አስራስምንተኛ ልጅ ነው። አባቱ በመጫና ቱለማ ትግል ውስጥ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው። አቶ ዘውገ ከእነ ጓደኛቸው ሲገደሉ፤ ያዴስ ከእነ ቤተሰቡ ተሰዶ በለጋነት ዕድሜው አዲስ አበባ ገባ።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የካቲት 23 ትምህርት ቤት የተከታተለ ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ጎበዝ በመሆኑና በስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገቡ አዲስ ከተማ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመማር ችሏል።

ያዴሳ መማር እንጂ መወዳደር ተገቢ አይደለም ብሎ ቢያምንም፤ በውድድር የልጅነት ሕይወቱን አሳልፏል። በኋላም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ገብቶ፤ በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ አሜሪካን የገባው ያዴሳ፤ አሜሪካን ሲገባ ግን አካውንቲንጉን ትቶ ሲያትል ዩኒቨርሲቲ ዲዛይን ተማረ።

የአፍሪካ ሕብረት ዓርማን ዲዛይን በማድረግ ኢትዮጵያን ያስጠራው ያዴሳ ዘውገ ቦጂአ፤ የዛሬው የዘመን እንግዳችን ነው። ከእርሱ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-

አዲስ ዘመን፡- የልጅነት ሕይወትህ ምን ይመስላል ?

አርቲስት ያዴሳ፡- ቤተሰቤ በጣም ጥሩ የሃብት ደረጃ ላይ የነበሩ ቢሆንም፤ ያደግኩት በችግር ነው። አባታችን ስለተገደለብን እና ቤታችን ስለተወረሰብን በተጨማሪ ንብረትም ስለተወሰደብን በድጎማ ለመኖር ተገደን ነበር። ስለዚህ እንደማንኛውም የመሳለሚያ ልጅ በችግር ውስጥ በማደጌ ሰዎችን የማየው በሰውነታቸው እንጂ በሃብታቸው አይደለም። በችግር ውስጥ በማደጌ ትልቅነት በሃብት እንደማይለካ አውቄያለሁ።

ለቤቴ አስራ ስምንተኛ ልጅ ነኝ። ጋሽ ወርቁ የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ ብቻ የተወለደው ከሌላ ነው። ሌሎቻችን አስራ ስምንታችንም የተወለድነው ከአንድ እናት እና ከአንድ አባት ነው።

አዲስ ዘመን፡- የጥበብ ፍቅር ውስጥ እንዳለ ያወከው እና ወደ ተግባር መለወጥ የጀመርከው መቼ ነው?

አርቲስት ያዴሳ፡- አርት ድሮም ጀምሮ እወድ ነበር። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የአርት ትምህርት ለመማር አልቻልኩም። 12ኛ ክፍል እንዳጠናቀቅኩ የከተማ ፕላን ኮሌጅ ላይ ተመድቤ ነበር። ነገር ግን በሒሳብ ትምህርት ውጤትህ ‹‹ቢ›› በመሆኑ አይቻልም አሉኝ። ስለዚህ ተገፍቼ አካውንቲንግ መማር ጀመርኩኝ። አሜሪካን እንደገባሁኝ ግን ፋይን አርት ተማርኩኝ።

ፋይን አርት ከራስ ሃሳብ በማመንጨት የሚሠራ ሲሆን፤ ኮሜርሻል አርት ደግሞ የራስን ስሜት ሳይሆን የገዢውን ፍላጎት በማሟላት ዲዛይን ማድረግ እና መሳል ነው። እነዚህን ሁለቱን በደንብ በመማር በሁለቱም መንገድ መሥራት ችያለሁ። አሁን የምሠራው ከሥራዬ ጋር ያተያያዘ ብቻ ሳይሆን፤ ሌሎችም ሞያዎች ላይ እሰራለሁ። አፍሪካ ዩኒየንም የሰራሁት በዚሁ መልኩ ነው።

ኢትዮጵያም እያለሁ በልጅነቴ እሞካክር ነበር። ጫንጮ ላይ ለሆቴል ማስዋቢያ ስያለሁ። ለሌሎችም ለሆቴሎች እስል ነበር። ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለሁ፤ ‹‹ እኔም እንደአባባ›› የሚል ስዕል ስዬ ነበር። ስዕሉ የጦርነት ጊዜ በመሆኑ አባትየው የወታደር ልብስ ለብሶ ልጁ ከጎኑ ቆሞ ነው። ስለዚህ እሞክር ነበር። ሰዎችም ይህንን ስለሚያውቁ ቤቴ ድረስ መጥተው ፈልገው ያስሉኝ ነበር። ሰዎችም በሚያምር ዲዛይን ስም ፃፍልኝ ይሉኝ ነበር። ነገር ግን ተማሪ ስለነበርኩ እንደዋና ሥራ አልወስደውም ነበር።

አዲስ ዘመን፡- ልጅነትህ ከጥበብ ጋር የተሳሰረ ነው ማለት እንችላለን?

አርቲስት ያዴሳ፡- ድሮ ልጅ እያለሁ በኦሮምኛ አንድ ዘፈን ዘፍኜ ነበር። በዛ ሰዓት ሰዎች በኦሮምኛ አይዘፍኑም ነበር። እኔ የከፍተኛ ስድስት ኪነት ሆኜ በሕፃንነቴ በኦሮምኛ ጋንጌን ኦሮሞ የሚል ዘፈን ስዘፍን ብዙም የተለመደ አልነበረም። ዘፈኑን የፃፈው ወንድሜ ነበር። የኦሮሞ ሕዝብ ወደ ፊት የሚገጥመው ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ አዘል ዘፈን ነበር። በእርግጥ ዘፈኑን የዘፈንኩት ሃሳቡ ገብቶኝ አልነበረም።

አንድ ትልቅ ሰው ግን ይሔ ልጅ ትምህርቱ ላይ ጎበዝ ነው። እንዲህ ዓይነት ዘፈን መዝፈን ከጀመረ ሕይወቱ ይበላሻል ብለውኝ ከኪነት ቡድኑ ወጣሁ። ውስጤ ሙዚቃ ነበር። ባልዘፍንም ራሴ ሙዚቃ እፅፍ ነበር። አሜሪካን ስሔድ ግን የሆኑ የውጪ ባንዶች ነበሩ። እናም ለአምስት እና ስድስት ዓመታት አሜሪካን ዘፈንኩኝ። አልበምም አወጣሁኝ። ዘፈኖቹ እንግሊዘኛ ሲሆኑ፤ አንድ ብቻ አማርኛ ዘፈን አለኝ።

የዘፈኖቹ ይዘት በአብዛኛው ስለአገሬ የተዘፈኑ ናቸው። የራሴን ታሪክ አካትቼ ከአገሬ ተገፍቼ ተባርሬ ብወጣም፤ አገሬን አልረሳም የሚል ዘፈን ዘፍኛለሁ። በምንም ቋንቋ ብፅፈው በአማርኛም ሆነ በሌላ ቋንቋ ስፅፈው ኦሮሞነቴንም አከብርበታለሁ። አንዳችን የሌላችን ጠላት መሆን አንችልም። ሰው ደግሞ ቋንቋ ስለተናገረ አይደለም። ለምሳሌ ኦሮምኛ ስለተናገረ ሳይሆን አማራ ሆኖ ኦሮምኛ ሊናገር ይችላል። ቅርበት የሚባል ነገር አለ። ሁሉንም ያጋጠሙኝን ነገሮች የምቆጥራቸው እንደመባረክ ነው። ማወቄ እና መማሬ ያስደስተኛል።

አዲስ ዘመን፡- አሜሪካን ከገባህ በኋላ ከጥበብ ጋር በተያያዘ ምን ሰራህ?

አርቲስት ያዴሳ፡- አዎ! የብዙ ሆቴሎችን ሎጎዎች ሰርቻለሁ። የድርጅቶችን መለያዎች እንዲሁም ዌብሳይቶችን እሰራለሁ። ኮሜርሻል አርት ላይ በጣም ለብዙ ሰዎች የሠራሁ ሲሆን፤ ፋይን አርት ላይም ብዙ ጋለሪዎችን አሳይቻለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ያዴሳ ሲነሳ የአፍሪካ ሕብረት ዓርማ ይጠቀሳል። ዓርማውን ወደ መቅረፅ የገባኸው በምን አጋጣሚ ነው?

አርቲስት ያዴሳ፡- ድሮም ትልቅ የዲዛይን ጥያቄ ሲነሳ ሰዎች አይተው እንድወዳደር ይልኩልኝ ነበር። እኔም እሳተፋለሁ። ነገር ግን ይሔን ሳየው በጣም የምፈልገው እና የማስበው ስለነበር በደንብ ጊዜ ወስጄ በቅድሚያ ኦርጋናይዜሽን ኦፍ አፍሪካን ዩኒቲ (ኦ ኤ ዩ) ን አጠናሁ። እነሱ ያደረጉት እንደአገራት ነበር። አፍሪካ ሕብረት (ኤ ዩ) ሲሆን ግን መለየት ነበረበት። ያንን በደንብ አጠናሁኝ። ስንወዳደርም እነርሱ ያሰቡት እንደአገር እንዲሆን ነው።፡

ነገር ግን ከነበረው ቀኝ ተገዢነት ወጥተን ያለፈውን እያሰብን እየተበሳጨን ጊዜያችንን ከማሳለፍ ይልቅ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንሻገር የሚል ሃሳብ አቀረብኩኝ። ያንኑ ፅፌ ጨረሩን አካትቼ ላኩላቸሁ። ከ130 አካባቢ ተወዳዳሪዎች መካከል የእኔ አሸነፈ። መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ ሲባል ደስ የሚል ሆኖ ተገኘ።

አዲስ ዘመን፡-ማሸነፍሕ ምን ፈጠረብህ?

አርቲስት ያዴሳ፡- የይቻላል መንፈስን ፈጥሮልኛል። አንድ ልጅ ከችግር ውስጥ ወጥቶ፤ አዲስ አበባ መሳለሚያ አድጎ ዓለም ላይ ሊታይ የሚችል ሥራ መሥራት ከቻለ ሁሉም ሰው መሥራት ይችላል። ይህ መንፈስ ሁሉም ሰው ላይ የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ከእኔ አልፈው ሰዎች ይማሩበታል፤ ይከበሩበታል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- የአገርን ባህል ከአርት ጋር አስተሳስረህ ለማስተዋወቅ ምን እየሠራህ ነው?

አርቲስት ያዴሳ፡- የተለያዩ ከኢሬቻ ጋር የተሳሰሩ ሥዕሎች አሉኝ። በጣም ታዋቂ ሥዕል አለኝ። ሌላው ከአምቦ ስለመጣች አንዲት ሴት የሠራሁት አዋርድ ያሸነፈኩበት ዘፈን አለኝ። ዘፈኑ አሜሪካን ውስጥ የታወቀ ነው።

እሁድ የኢሬቻ ዕለት

ብርሃን መስላ በረከት

ቢሾፍቱ ትሄዳለች

ሰላም አውለኝ እያለች …ይላል። ይህ አንዲት ወጣት ኢሬቻ ለማክበር ከአምቦ ወደ ቢሾፍቱ እንዴት እና ለምን እንደሔደች እንዴት እንደሞተች ያሳያል። ኢሬቻን ማክበር የኦሮሞ መሠረታዊ መብት መሆኑን አምናለሁ። ባህልን ማክበር ለአገርም ይጠቅማል። ለቀጣዮቹ ትውልዶችም አርዓያ ይሆናል። ስለዚህ ባህልን በአርት ከማስተዋወቅ አንፃር ከሠራሁት መካከል ይህንን መጥቀስ እችላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- የምትኖረው ውጪ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ኢሬቻ ላይ ተሳትፈህ ታውቃለህ?

አርቲስት ያዴሳ፡- አሜሪካን አገርም ኢሬቻን እናከብራለን።

አዲስ ዘመን፡- ከስዕሉ ባሻገር በዘፋኝነትም እንጠብቅህ?

አርቲስት ያዴሳ፡- ታዲያስ! አርቲስትነት ሃሳብ ማፍለቅ ነው። ሃሳብ ደግሞ በስዕልም ሆነ በዘፈን በሌሎችም የስነጥበብ እና የኪነጥበብ ሥራዎች ይገለፃል። ሃሳባችንን በተለየ መልኩ መግለፃችን ሃሳባችን የበለጠ ተደማጭነት እንዲያገኝ ያስችላል።

አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ዘፈኖችን ዘፍነሃል?

አርቲስት ያዴሳ፡- አልበሙ አስራ ሁለት ዘፈኖችን የያዘ ነው። አራት ነጠላ ዘፈኖችም አሉኝ። አሁን ደግሞ አዲስ ያወጣሁት የእንግሊዘኛ ዘፈን አለ። ገና ቅርብ ጊዜው ነው። በደንብ አላስተዋወቁትም። በኦሮምኛ ሶስት ዘፈኖች አሉኝ።

አዲስ ዘመን፡- ወደፊት በጥበቡ ዙሪያ ምን ለመስራት አስበሃል?

አርቲስት ያዴሳ፡- ለራሴ ብዙ ነገር አግኝቻለሁ። አሁን ግን የማስበው ስለሕዝብ ነው። ስለዚህ ከኦሮሚያ መንግስት ጋር በመተባበር ልጆችን ለማስተማር ጥረት እያደረግኩ ነው። ወደፊት ቦታ ወስጄ ልጆች የሚማሩበት ጋለሪ ከፍቼ እኔ እዚህ አገር ስኖር ያላገኘሁትን ሌሎች እንዲያገኙት ለማስቻል እሞክራለሁ። ሌላ ትምህርት ቤት ለመክፈት ብዙ ሃብት እና ንብረት ያስፈልጋል። እንደዛ ዓይነት እርዳታዎችን ባገኝ ለአገር እና ለሕዝብ እጠቅማለሁ የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- አሜሪካን የቆየኸው ለስንት ዓመት ነው?

አርቲስት ያዴሳ፡- ለሃያ ዘጠኝ ዓመታት የቆየሁ ሲሆን፤እ.አ.አ በ2005 ዓ.ም ለሠርግ መጥቼ ነበር።

 

በ2010 የአፍሪካ ሕብረት ሥራን ለመስራት ለአንድ ወር መጣሁ። በ2019 ደግሞ የቀዳማይ ሃይለስላሴ ሃውልት ምርቃት ነበር። በዛ ጊዜም ተጠርቼ መጥቼ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ በኦሮምያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክንያት ለኢሬቻ መጣሁ።

አዲስ ዘመን፡- አገር ውስጥ ሆኖ ስለሀገር ማሰብ፤ እና ከአገር ውጪ ሆኖ ስለሀገር ማሰብ ልዩነቱ ምን ያህል ነው?

አርቲስት ያዴሳ፡- በጣም ይለያያል። ምክንያቱም ውጪ ሀገር ሆኖ ሀገርን በምናብ ማየት ልክ በአካል እንደማየት አይደለም። በሌላ በኩል የበዓል ድባብ ከተባለ ግን ውጪም ሆኖ ሲከበር የሚሰጠው ስሜት ተመሳሳይነት አለው። ነገር ግን በአካል ከመገኘት አንፃር ሲታይ ለምሳሌ በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብ የሚታደምበት የአደባባይ ክብረ በዓል ላይ መገኘት በጣም የተለየ ስሜት ይፈጥራል። ይሔንን እዚያ ማግኘት አይቻልም።

አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባን እንዴት አየኻት?

አርቲስት ያዴሳ፡- በጣም ከተማዋ ተቀይራለች። ብዙውን ነገር ለማስታወስ እስከሚከብደኝ ድረስ ተቀይራለች።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለውን ሀገራዊ ልማት ዲያስፖራው በምን መልኩ መደገፍ አለበት ትላለህ?

አርቲስት ያዴሳ፡- ዳያስፖራ የሚናገረው ያየውን ነው። ለምሳሌ አንዳንዱ በጣም ያጋንናል። ሌሎቹ ደግሞ ገልብጠው የሚያዩ አሉ። አሁን ይሔ ከተማ ያገኘሁት በጣም ተውቦ ነው ። ነገር ግን በየትኛውም ዓለም ላይ የታወቀ ነገር አለ። ነጮች ሆምሌት ለመሥራት እንቁላሏ መሠበር አለባት ይላሉ። ስለዚህ አንዳንድ ለውጦች ሲመጡ፤ የሚጎዱ እና የሚገፉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ማየት ያለብን አስፈላጊውን እና ትልቁን ነገር ነው።

ከተማዋ በአዲስ መልክ ስትገነባ የሚፈርሱ መኖሪያ ቤቶች እና ሱቆች ሊኖሩ ይችላሉ። በፊት የቆረቆዙ እና ተስፋ የማይሰጡ የነበሩ አካባቢዎች አሁን በጣም ተቀይረዋል። ከዛ አካባቢ የሚነሱትም ሰዎች ተከብረው ቤት ተሰጥቷቸው እያየን ነው። ነገር ግን በተቃራኒው ሁሉም ደስተኛ ይሆናል ማለት አይቻልም። በበኩሌ ማለት የምችለው እያየሁ ያለሁት በጣም የተዋበች እና ያማረች ከተማን ነው።

አሁን ያለውን ሁኔታ ስመለከት ‹‹ እስከ ዛሬ ድረስ ሳንችል ቀርተን ሳይሆን ፈርተን እንጂ መሥራት ይቻል ነበር።›› እላለሁ። ስለዚህ አሁን በድፍረት የሠሩትን በጣም አመሰግናለሁ። ወደ ፊት ደግሞ እየመጣን በየጊዜው የምናያት ብቻ ሳትሆን የምንኮራባት ሁሉም ሰው ሲያያት የሚደሰትባት ከተማ ልትሆን እንደምትችል አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ውጪ የሚኖሩ አንዳንድ ግለሰቦች በየማህበራዊ ሚዲያው ስለ ሚያስተላልፏቸው አፀያፊ ስድቦች እና የሌሎችን ሰዎች ሞራል የሚነኩ ቃላቶች ምን ትላለህ?

አርቲስት ያዴሳ፡- ቃላቶች ከጥይት በላይ ከባዶች እና ሰዎችን የሚጎዱ ናቸው። ማሕበራዊ ሚዲያን እጠቀማለሁ ማንም ሊያውቀው እንደሚችለው ፍትሃዊ ሃሳቦችን እሰነዝራለሁ። አሁን የማየውን ፍትሃዊ የሆነ ነገርን እፅፋለሁ። የማንም ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ አይደለሁም። ወደ ፊትም ያየሁትን በፍትሃዊ መልኩ ከመፃፍ ወደ ኋላ አልልም። ሰዎች ቢሳደቡም ግድ የለኝም።

ነገር ግን ሰዎች በቀናነት ነገሮችን ማየት አለባቸው። የምንሳደብ እና የምንኮንን ከሆነ የምንወቅሰው የራሳችንን አካል መሆኑን ማወቅ አለብን። ስድብ እና የፖለቲካ ፍጆታ ሁልጊዜ በአንድ ፓርቲ ላይ የተመሠረተ ነው። አገር ግን ሀገር ፓርቲ አይደለችም፤ ዘላቂ ናት። ሰዎች ውጪ ቢኖሩም አገር ውስጥ ቤተሰብ አላቸው። ስለዚህ አገራቸውን እና የአገራቸውን ሕዝብ መኮነን እና መስደብ የለባቸውም።

ማወቅ ያለብን ሁላችንም የምንኖረው በመስታወት በተሠራ ቤት ውስጥ ነው። አንድ ቀን መስታወቱ ከተሰበረ ከባድ ነው። በቃኝ መረረኝ እያልን በግዴለሽነት መጥፎ ቃላትን ከመወራወር መጠንቀቅ አለብን። የምንወደውን ሰው ልናጣ እንችላለን። አንዱ ሞቶ ሌላው ሊኖር አይችልም። ስለዚህ የሚጠበቅብን በጥንካሬ እና በመተማመን በአንድነት ላይ መመስረት አለብን። ዳያስፖራ የሚለው ቃል እራሱ እኛን ማራቅ ይመስለኛል። ቤተሰቦቻችን የሚኖሩት እዚሁ ነው። በቀናነት ከቀጠልን ረዥም ዕድሜ እና ትልቅ ተስፋ ይኖረናል።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር እየተሠሩ ስላሉ ሥራዎች ምን አስተያየት አለህ?

አርቲስት ያዴሳ፡- አሁን እየተረዳሁ ያለሁት በጣም ብዙ ነገር እየተሠራ ነው። ነገር ግን ማስተዋወቅ ላይ ክፍተት አለ። ለምሳሌ ሰዎች አገሪቷ አማረች ቢባሉም ብዙም ላይታያቸው ይችላል። ከዛ ይልቅ የአንድ ከተማ አንድ ሺ ሰው ከእዚህ በፊት የኤሌክትሪክ ኃይል አገኘ ቢባል ሰዎች ይገባቸዋል። ይሔ ፖለቲካ ሳይሆን ምን ተሠራ? ከየት ወደ የት እየሄድን ነው? የሚለውን በግልፅ ማሳየት ነው።

ማሳየት ከተቻለ የመተባበር ስሜቱ እየጨመረ ይመጣል። በእኔ በኩል ይህንን መረጃ ለሕዝብ ለማቀበል እና ለማስተላለፍ እሠራለሁ። አንዳንድ ሰዎች ይሠራሉ እንጂ የሠሩትን ማሳወቅን በተመለከተ ዞር ብለው አያዩም። ነገር ግን ሁለቱም ጎን ለጎን መሔድ አለባቸው። እስከ አሁን እንዳየሁት፤ ለእዚህም ሁሉም እንደሚተባበረኝ እርግጠኛ ነኝ። እኔ ከማንም ምንም አልፈልግም።

የመጣሁት ለመቀበል ሳይሆን ለመሥጠት ነው። የምፈልገው ድንጋይ እየተሸከሙ አስፓልት ከሚሠሩ ሰዎች ጋር ለመቆም ነው። ምክንያቱም ሌላው ምንም ጥቅም የለውም። የሚጠቅመው ሥራውን በአግባቡ የሚሠራው ብቻ ነው። ሥራን ጠንክረን መሥራት አለብን። ያለበለዚያ ነገሮች ይበላሻሉ።

አዲስ ዘመን፡- በአንተ እይታ የኢትዮጵያ ጥበብ ምን ደረጃ ላይ ነው?

አርቲስት ያዴሳ፡- የእኛ አርት በጣም አግላይ ነው። ለምሳሌ በብዙ የሚታዩት አርቶች ሁሉም የሚሳተፍባቸው አይደሉም። በሙዚቃውም ሆነ በአልባሳቱ ኦሮሚያ እና የደቡብ ሕዝቦች ሌሎችም ራሳቸውን ማየት የጀመሩት አሁን ነው። ይሔ ጊዜ ይፈጃል። በአንድ ቀን መለወጥ አይችልም። እንለውጣለን ሳይሆን የራሳችንን እናሳያለን እያልን ነው። ለመለወጥ ዘር ማጥፋት የለብንም። አግላዮች ጋር ሔደንም በቂ ምላሽ አናገኝም።

የሌሎች መልስ የተወሰነ ማነቃቂያ እንጂ ሙሉ አይሆንም። ስለዚህ የሚያስፈልገው የራሳችንን ሥራ መሥራት ነው። ያልታዩ ቦታዎች እየታዩ፤ ያልተዳሰሱ ቦታዎች እየተዳሰሱ ናቸው። ለምሳሌ እነ ወንጪን መጥቀስ ይቻላል። ድሮ የት ነበሩ? እንዴት ታለፉ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ግራ ያጋባሉ። የሆነ ሰው ይሄ መሠራት አለበት ብሎ አስቧል ማለት ነው። ስለዚህ ዋናው ጉዳይ አካታች መሆን እና ሁሉንም አሳታፊ ለመሆን መለመን ሳይሆን የሚያዋጣን መሥራት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነህ፤ ልጆችህ ኢትዮጵያን በተመለከተ ያላቸው እሳቤ ምን ይመስላል? ለልጆችህ ስለአገራቸው ታሳውቃቸዋለህ?

አርቲስት ያዴሳ፡- በእርግጥ ተወልደው ያደጉት አሜሪካን ነው። ነገር ግን ስለማንነታቸው በደንብ እነግራቸዋለሁ። ባለቤቴ የትግራይ ተወላጅ ናት። ስለእርሷም ሆነ ስለእኔ በደንብ ያውቃሉ። ሁለታችንም እኛ የተከለከልነውን ነገር እነርሱ እንዲያውቁ እንፈልጋለን። እኛ ራስን ማክበርም ሆነ ሌሎችን ማክበር ተከልክለን አድገናል። ስለዚህ ቤታችን ውስጥ ያገኘነውን እናስተምራቸዋለን። ምንም ዓይነት ሽኩቻ የለም።

አንዱ የአንዱ የበላይ ነው ብለን ካስተማርናቸው እኛ የጠላነውን ስሜት ይዘው ያድጋሉ። ስለዚህ ባሕላችንን በትክክል አስተምረናቸዋል። አማርኛውንም ትግሬኛውንም ሆነ ኦሮምኛውን ሁሉንም ይሰማሉ። አሜሪካን ውስጥ ያሉ የኢትዮጵያውያን ልጆች በጣም ይከባበራሉ። አንዳንድ ጊዜ በሽታዎች ቢያጋጥሙም ይመካከራሉ። ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ አለ። እዛ የባሕል ቀን ይከበራል። እዛ ላይ የተለያዩ የኢትዮጵያውያን ባሕሎች ይቀርባሉ፤ እነርሱ ደግሞ ይጠይቃሉ።

አዲስ ዘመን፡- ወደፊት መሻሻል አለበት የምትለው እና የምታስተላልፈው መልዕክት ካለህ?

አርቲስት ያዴሳ፡- የምናምረው ስንጠነክር፤ ስንዋደድ እና ስንተባበር ነው። የምናንሰው ስንናናቅ እና ስንጠላላ ነው። ትልቁ ስህተት ዘረኝነት ማለት ዘርን መውደድ እንደሆነ መታሰቡ ነው። ዘረኝነት ማለት ሌሎችን በብሔራቸው መጥላት ማለት ነው። ሌላ ምንም ቀመር የለውም። አንድ ሰው የአንድ ብሔርን የባሕል ልብስ ሲለብስ ዘረኛ ይባላል። ይህ መቅረት አለበት።

ሰዎች እዚህ ላይ ትልቅ ስህተት ውስጥ ሲገቡ ይታያሉ። አንድሰው ማንነቴን እና ባሕሌን ሳያከብርልኝ የእርሱን ላከብርለት አልችልም። ባሕሌን ሳከብር ደግሞ እንደዘረኛ መታየት የለብኝም። የሌላውን ብሔር ባሕል እያከበርኩ የራሴን ብሔር ባሕል እንዳላከብር ከተደረገ ተገቢ አይደለም።

በተጨማሪ በእኔ እምነት ማንነት እና ዜግነት ሊለይ ይገባል። ለምሳሌ እኔ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ነበረኝ። አሁን አይደለሁም። አሁን አሜሪካዊ ብሆንም የሕግ ማንነቴ እንጂ ዋናው ማንነቴ አሜሪካዊነት አይደለም። ኦሮሞ ከነበርኩኝ፤ ዛሬ ጉራጌ መሆን አልችልም። ያ ማንነቴ ነው። ይህ አይለወጥም።

ኦሮሞ መሆን ከኢትዮጵያዊነት ጋር የሚጋጭ አይደለም። ባሕሉን ማክበር ይችላል። ይህ ግጭት የሚመጣው ሰዎች ዜግነት እና ማንነትን መለየት ሲያቅተን ነው። ማናችንም በአገር ውስጥ እኩል መታየት አለብን። ሁላችንም እኩል መብት አለን። ያንን መረዳት ያስፈልጋል። ከንባታውም በከንባታነቱ፣ ኢትዮጵያዊ መሆን ይችላል። ጉራጌውም በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያዊ መሆን ይችላል። ብሔር እና ዜግነት ምርጫ መሆን የለባቸውም።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ እናመሰግናለን።

አርቲስት ያዴሳ፡- እኔም አመሠግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

 

Recommended For You