አዲስ አበባ፡- እንደ አገር የመጣው ለውጥ በግለሰቦች ፍላጎት የተካሄደ ሳይሆን ኢህአዴግ በውስጡ የመራውና በህዝብ ተጠንስሶ የተወለደ፤ ሕገ መንግሥታዊ መሆኑን ኢህአዴግ ገለጸ፡፡
የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአጋር ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ማስተባበሪያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ ለውጡ በህዝብ ተጀምሮ ለውጤት የበቃ ቢሆንም፤ ኢህአዴግ በውስጡ በጀመረው የለውጥ እርምጃ መርቶታል፡፡ ሂደቱም ሕገ-መንግሥታዊና የህግ መሰረትን ጠብቆ የተከናወነ ነው፡፡
‹‹ለውጡን በመቀስቀስ ረገድ ህዝቡ ከፍተኛ ሚና ነበረው፡፡ አርቲስቱ፣ አትሌቱ፣ አክቲቪስቱ፣ ሚዲያው ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡ ወጣቱም ደረቱን እስከመስጠት ሄዷል፡፡ በየቤቱ ያለው ሁሉም ኢትዮጵያዊ የለውጡ ባለቤት ነው፡፡ የለውጡ ጠባቂም ህዝቡ ነው፡፡›› ያሉት አቶ ፍቃዱ፣ ኢህአዴግም እንደ መሪ ድርጅት ወይ ሪፎርሙን መርቶ ለዚህ ደረጃ ማድረስ፤ አለበለዚያ መጥፋት ነበረበት ብለዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ትክክለኛውን አማራጭ በመያዝ አሁን ለተደረሰበት ደረጃ ማድረስ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
«ለውጡ ከኢህአዴግ መርህ የወጣና በግለሰቦች ፍላጎት እየሄደ እንደሆነ አድርገው በማውራት የግለሰቦች አድርገው የሚያዩም አሉ፤» ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ ሂደቱን በመምራትና ትክክለኛውን መስመር በማስያዝ ግለሰቦች ሚና የላቸውም ባይባልም ለውጡን ኢህአዴግ የመራው እንደመሆኑ መጠን ለውጡ ኢህአዴጋዊ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም ለውጡን ከኢህአዴግ መርህ የወጣና በግለሰቦች ፍላጎት የሚጓዝ አድርጎ የማሰቡ ሂደትመታረም እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
የለውጡ ሕገ መንግሥታዊነትም ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም በለውጥ ሂደቱ ኢህአዴግ ሊቀመንበሩን ሲመርጥም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሾሙ የፓርቲውንም ሆነ የፓርላማውን አሠራር በመከተል መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ ከለውጡ በኋላም ከሕገ መንግሥቱ ውጪ የተደረገ ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ፣ ሕገ መንግሥቱ ሰው ያላግባብ እሰሩ፣ አሰቃዩ አይልም፡፡ እናም እስረኞች መፈታታቸው ህገ መንግሥታዊ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሃሳብ ነፃነትን፣ በነፃነት መንቀሳቀስን ይፈቅዳል፤ እናም ይሄን የሚገድቡ አዋጆች መነሳትና መሻሻላቸውም ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ለውጡ ኢህአዴጋዊ፣ ሕገ-መንግሥታዊና ህዝባዊ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011 በወንድወሰን ሽመልስ