ግርማ መንግሥቴ
በአንድ አገር የፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፤ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ሕይወት፣ ሂደትና እድገት ውስጥ የፍትህ ሥርዓትን ተገቢነትና አስፈላጊነት የሚወዳደረው ያለ እስከማይመስል ድረስ የሁሉንም ልዩ ትኩረት ሲስብ የኖረ ዘርፍ ነው። በመሆኑም ዘርፉን በርዕሰ ጉዳይነት ወስዶ መነጋገር የተለመደ ብቻ ሳይሆን የግድም ነው። በተለይም፤ ሌላው እንኳን ቢቀር፣ «የሰው ልጅ» ሰው በመሆኑ ብቻ በተፈጥሮ ከተሰጡት ሰብአዊ መብቶች አንዱንም ሊያጣ አይገባምና ከዚህ ሁሉ አኳያ ሲታይ ዘርፉ «ወሳኝ» በሚለው ስር መካተቱ፤ ባላቋረጠ መልኩ የውይይት ርዕሰ ጉዳይ መሆኑ ከተገቢው በላይ ተገቢ ነው።
«የፍትህ ሥርዓት» ስንል በተለይም ከግለሰብ ጀምሮ የሁሉንም ሰው ሰብአዊ መብቶች (በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት «መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች» በሚል ርዕስ በአንቀጽ 17 እና ሌሎቹም ስር እንደሰፈረው ማለት ነው) የሚነካና ከሁሉም ጉዳዮች ጋር የተሳሰረ ማለታችን ሲሆን፤ በዘርፉ ያለው ተግዳሮትም እንዲሁ ከሁሉም ሰው ጋር ጥብቅ ትስስር አለው ማለታችን ነው። በመሆኑም ቀጥለን በዚሁ ዘርፍ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ እንነጋገራለን። ለዚህም የተሰሩ ጥናቶችንና በቀጥታ ከጉዳዩ ጋር ቀረቤታ ያላቸውን ሰዎች ምስክርነት መሠረት እናደርጋለን። በተለይም ከአገራችን ተጨባጭ እውነታና ሁኔታ አንፃር ከሰዎች የ«መታሰር» እና የ«አለመታሰር» መብቶች ጋር በተያያዘ ያለውን እውነት እናስቀድማለን፤ ቀጥለንም አጠቃላይ የአገራችን የፍትህ ሥርዓት ምን እንደሚመስል እናያለን።
እርግጥ ነው በጉዳዩ ላይ ብዙዎች ብዙ ብለዋል። የሰማም ሆነ የሚሰማ ቢታጣም ተንታኞችም ሆኑ ሌሎች የየዘርፉ (የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሕገ መንግሥት አውጪና ተርጓሚዎች፣ የሕግ ሊቃውንት ወዘተ) «ያላሉት የለም» እስከሚባል ድረስ ተችተዋል፤ ይበጃል ያሏቸውን አስተያየቶችም ሰንዝረዋል። የሚከተሉት ጥናቶችም የእነዚሁ አካል ናቸው።
«የነፃነት መብት አጠቃላይ መርህ» እና «የነፃነት መብት የሚገደብባቸው ልዩ ሁኔታዎች»ን መሠረት ባደረገ መልኩ ያለመያዝ እና ያለመታሰር መብት ከሕግ አንጻር የሚተረጎምበት አግባብ በተለይም ደግሞ በወንጀል ተግባር ተጠርጥረው በሕግ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎችን ስለሚያዙበትና የሚታሰሩበት ሕጋዊ ምክንያቶችን እና ሥነሥርዓታዊ አካሄዶችን ከዓለምአቀፍ ሕጎችና ልምዶች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሕጎች አንጻር በመቃኘት የሪፖርተሩ የሕግ አምድ አምደኛ ገብረእግዚአብሔር ወልደገብርኤል አጭር ዳሰሳ አድርገዋል። «ማንኛውም የሰው ልጅ ፍጡር በየትኛውም ጊዜ፣ ቦታ እና አካል ሊገሰስ ሆነ ሊገፈፍ ወይም ሊደፈር የማይችል በተፈጥሮ የታደለውን የነፃነትና የአካል ደህንነት መብት አለው። ሁሉም ሰብአዊ መብቶች እርስ በእርሳቸው ፍጹም የማይበላለጡና የማይነጣጠሉ፣ እኩል እና የሚደጋገፉ መሆናቸውን እንደተጠበቀ ሆኖ የነፃነትና የደህንነት መብቶችን ግን በሕይወት ከመኖር መብት ቀጥለው ቁልፍና መሠረታዊ የግለሰቦች መብት ናቸው።» ያሉት አምደኛው ምክንያቱን ሲያስቀምጡም «የነፃነት እና የደህንነት መብቶች ሳይከበሩ ሌሎች መሠረታዊ የሰው ልጅ መብቶች ይከበራሉ ማለት ዘበት» እንደሆነ ይናገራሉ።
ፀሐፊው እንዳለው መብቶች የሚነጣጠሉ ሳይሆን፤ ይልቁንም የተቆራኙና አንዱ ያለ አንዱ የማይቆሙ፤ የአንዱ መነካት የሌላው መነካት መሆኑን በሚያስተምር መልኩ «በመርህ ደረጃ ሁሉም ሰብአዊ መብቶች እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ፣ የሚደጋገፉ እና ፍፁም ሊነጣጠሉ የማይችሉ በመሆናቸው የአንድ ሰብአዊ መብት ጥሰት የሌሎች ሰብአዊ መብቶችን መከበር አደጋ ላይ የሚጥል እና በውጤት ደረጃ ሁሉንም ሰብአዊ መብቶችን የሚበክል፤ እንደ ወረርሽኝ በሽታ በቀላሉ የሚሰራጭ ነው።
አጥኝው የሚሉት «የጤና መብት ያልተከበረለት፣ የምግብ ዋስትና ያልተረጋገጠለት፣ የመኖሪያ/መጠለያ መብት ያልተመቻቸለት ግለሰብ በሕይወት የመኖር መብቱንም እንደሚነካ የሚያከራክር ጉዳይ አይሆንም ብለዋል። በተጨማሪም የደህንነት መብቱ ያልተረጋገጠለት ወይም ሙሉ ዋስትና ያልተሰጠው ግለሰብ በሕይወት የመኖር መብቱም አደጋ ላይ መውደቁ የማይቀር ነው።» ይላሉ። «አደጋ» የሚሉትንም እንዲህ ሲሉ ይገልፁታል።
«በተመሳሳይ መልኩ ከሕግ ውጭ ነፃነቱን የታፈነ ግለሰብ አያሌ መሠረታዊ መብቶቹን ሊነጠቅ ይችላል። ለምሳሌ በተገቢው ጊዜ ፍርድ ቤት ያለመቅረብ በደል፣ የሕግ አማካሪ የማግኘት መብትን መንፈግ፣ በቅርብ ቤተሰቡ እና ጓደኞቹ እንዳይጎበኝ ማድረግ እንዲሁም ሌሎች ግፎች፣ ድብደባዎች፣ ግርፋቶች፣ ኢ-ሰብአዊ እና ክብሩን የሚያዋርዱ አያያዞች ሊደርስበት ይችላል። ምክንያቱም ከጅምሩ ከሕግ ውጪ የተያዘ እና የታሰረ ሰው ከዚህ ቀጥለው ለሚደርሱበት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሕግ በመሀል ጣልቃ ገብቶ ያስቆማል ወይም ዋስትና ይሰጣል ብሎ ለመከራከር እምብዛም የሚያስተማምን አይሆንም። በሌላ አገላለጽ ከመጀመሪያ ጀምሮ ከሕግ ውጪ የተከናወነ የመያዝ እና የማሰር ተግባር ሆኖ እያለ ቀጥሎ የሚከናወነው ሂደት እና ውጤት ሕጋዊ ሊሆን ይችላል ብሎ መናገር ምኞት ነው» በማለት ይገልፁታል።
እንደ አጥኝው አስተያየት «በተለይ ደግሞ መንግሥት መሠረታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች ራሱ መሪ ተዋናይ በሚሆንባቸው ጉዳዮች ላይ ጉዳቱ ከፍተኛና አደገኛ ነው።» ፀሐፊው አክለውም «ለመሆኑ ከሕግ ውጪ መያዝ እና ማሰር ምንድን ነው? የሕጋዊነት መርህስ ምን ማለት ነው?» በማለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ጠይቀዋል፤ ከጉዳዩ ጋር በቀጥታ የተያያዙ በርካታ ነጥቦችንም በማስረጃነት አንስተው አብራርተዋል።
በተጨማሪም ሀገራት ነፃነትን በመገደብ ሰውን መያዝ እና ማሰር የሚችሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካገኙ የሰብኣዊ መብቶች ሕግጋት እና እነዚህ መሠረታዊ እና ሥነሥርዓታዊ ሕግጋት ጋር በሚጣጣም መልኩ በብሔራዊ ሕጎቻቸው ላይ በተደነገጉት ግልጽ ሕጎች እና ሥነሥርዓታዊ አካሄዶች መሠረት በማድረግ መሆን ስላለበት ሕግን በማክበር እና ሥርዓትን በጥብቅ በመከተል ብቻ መሆን ይኖርበታል። ከዚህ ውጪ የሚከናወን የመያዝ እና የማሰር ሂደት ብሔራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተጠያቂነትን ያስከትላል። ምክንያቱም ሰዎችን የመያዝ እና የማሰር ሥልጣን ምንም ዓይነት ምክንያት ሳይኖር በዘፈቀደ የሚከናወን ገደብ አልባ ተግባር አይደለም ብለዋል።
«በመጀመሪያ ደረጃ በግልጽ የተጣሰ የሕግ ድንጋጌ እና የተፈጸመ የወንጀል ተግባር መኖር አለበት። በመቀጠል ከፖለቲካዊ ሴራ እና ጥቃት የፀዳ፣ ምንም ዓይነት አድልዎ የሌለበት፣ ምክንያታዊነቱ እና አስፈላጊነቱ ከአጠቃላይ የሕዝብ ጥቅም አንጻር ተለክቶ ሕግ እና ሕግን ብቻ የተከተለ መሆን አለበት።» በሌላ አገላለጽ «አንድን ግለሰብ ለመያዝ ወይም ለማሰር የሕጋዊነት መርህን መከተል እንደተጠበቀ ሆኖ ሕጎች እና የሕጎች ተፈጻሚነትም ፍትሃዊ እና ከምንም ዓይነት አድሏዊ አሠራር ነፃ ለማድረግ ተገቢነት ያላቸው እና ከኢ-ምክንያታዊት የፀዱ፣ ተገማችነት እና ተመጣጣኝነትን (Foreseeable and Proportionality) እንዲሁም ሕግን የተከተለ አሠራር (Due Process of Law) መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።» በማለት በአገራችን በከፋ ደረጃ የነበረውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊያርም በሚችል መልኩ በ«ያለመያዝ እና ያለመታሰር መብት» በሚል ርዕስ ስር አስፍረዋል።
ይህ እንግዲህ በቅድመ-አብይ አስተዳደር በአገራችን በግልፅ ሲታይ፤ እስከ «ጥፍር መንቀል» ድረስ ሲከናወንና ዜጎችን ላልተፈለገ ስቃይና መከራ ሲዳርግ የነበረ ሲሆን በአብይ አስተዳደር ያለውን ደግሞ የመስኩ ተመራማሪዎችና የሥራ ኃላፊዎች እንደሚከተለው ይገልፁታል።
በተደጋጋሚ ሲገለፅም ሆነ ሲብራራ እንደሚሰ ማው፤ ይህ ፀሐፊም ከዚህ በፊት በአንድ ፅሑፉ ላይ የሚመለከታቸውን አነጋግሮ እንዳሰፈረው «የፍትህ ሥርዓታችን በርካታ ክፍተቶች ያሉበት ነው። ነፃነት፣ ግልፅነት እና ተጠያቂነት የጎደለው፤ የዜጎች ሰብአዊ መብት ጥሰት የሚታይበት፤ የዳኝነት ነፃነትን ያላከበረ፣ የፀጥታ ኃይሉ ተግባር መብታቸውን የሚጠይቁ ዜጎችን እየተከታተሉ ከማፈን ያላለፈበት፤ በወንጀል ጉዳይ የተጠረጠሩ ሰዎች ቶሎ ፍ/ቤት የማይቀርቡበት፤ የወንጀል ምርመራ ሥርዓቱም በሕግ የማይገዛ/ሕግን የማይከተልበት፣ ታራሚዎች የሚጉላሉበትና መብታቸው የማይከበርበት፣ የግለሰብ መብትና ነፃነት ፍፁም የተዘነጋበት፤ «ፍ/ቤት ለሁሉም እኩል ነው» የሚለውን መሠረታዊ የሕግና ፍትሕ ፍልስፍና የጣሰ አሠራር የሰፈነበት ነው።»
ይህ ብቻም አይደለም በቅድመ-አብይ አስተዳደር «የነበረው አጠቃላይ ሁኔታ ሰው በቶርች የሚሰቃይበት፣ በፀረ ሽብር አዋጁ አማካይነት ያለ ሥራቸው የሚታገቱበትና የሚሰደዱበት፤ የፖሊስ ማስረጃ ፍለጋ ኋላቀር በመሆኑ የፍትህ ጥያቄ ምላሽ እማያገኝበት ነበር። በአጠቃላይ የሕግ የበላይነት መርህ (“Principle of Supremacy of Law” የሚባለው) የሚጣስበት እና ሕግን ያማከለ አስተዳደር ወይም የሕግ ማእከላዊነት» የሌለበትና አገሪቱ የምድር ሲኦል የነበረችበት ወቅት ነበር።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ ሦስተኛ ዓመታዊ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለው እምነት እየጨመረ መጥቷል። ይህ እየጨመረ የመጣውን ሕዝቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን እምነት በመመለስ በሁሉም ዘንድ ተአማኒነት ያለው የፍትህ አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋቱ ነው። በቅድመ አብይ አስተዳደር ዘመን ስለዳኝነት ነፃነት እና ገለልተኛነት በመንግሥት ኃላፊዎችም ሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ ያለመያዝና ዳኞች ተጠያቂ የሚሆኑበት ግልጽ መመዘኛ ያለመኖሩ ትልቁ ችግር ሆኖ ነበር የቆየው።
በአጠቃላይ መረዳት የሚቻለው ከለውጡ በፊት ከፍተኛ የፍትህ ሥርዓት ክፍተት የነበረ ሲሆን፤ ከለውጡ በኋላ ያለው አስተዳደር የቀጠለው በፊት የነበሩትን የፍትህ፣ ርትእና ሰብአዊ መብቶች ጉድፎች እየጠረገ መሄዱንም ጭምር ነው።
በአጠቃላይ «ቅድመ» እና «ድህረ» ለውጥ በሚል ጉዳዮችን በጊዜ፤ ሁነት፣ ኩነት እና የአስተዳደር ዘይቤ ከፍሎ ማየት አዲስ አይደለም። በመሆኑም የአገራችንን የፍትህ ሥርዓት በ«ቅድመ» እና «ድህረ» ለውጥ አስተዳደር ከፍለን ብንፈትሽ ስህተት አይሆንም። ስህተት የማይሆንበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ካለፈው የተሻለ፤ ያለፈውን የሚያርምና የሚያቃና ፍትህና ርትእ የነገሰባት፤ የሰው ልጆች በተለይም የመጪው ትውልድ ሁለንተናዊ መብቶች የሚከበሩባት፤ የግለሰብ ወይም የቡድን የበላይነት ሳይሆን የሕግ የበላይነት የነገሰባት ኢትዮጵያን ከመፍጠር አንፃር ሊከናወኑ የሚገባቸውን ተግባራት ታሳቢ ያደረገ መልዕክት ለማስገንዘብ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013