አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ፊት ለፊት ከሚያካሄደው ጦርነት ጎን ለጎን የኢኮኖሚ ጦርነት በመክፈት በአገሪቱ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እንዲፈጠርና ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲማረር የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል። በዚህም የሽብር ቡድኑ ስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት በዘረጋቸው ኔትዎርኮችና ቅጥረኞች አማካኝነት መሰረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎችን፣ የግንባታ ቁሳቁሶችን ወ.ዘ.ተ በህገወጥ መንገድ በማከማቸት አሁን ላይ በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ንረት ላይ ቤንዚል እያርከፈከፉበት ይገኛሉ።
ከዚህ አኳያ በዛሬው የዘመን ችሎት አምዳችን ከንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንጻር፤ ምርት በህገወጥ መንገድ ተከማችቷል የሚባለው መቼ ነው? ምርትን በህገወጥ መንገድ አከማችቶ መያዝ የሚያስከትለው የህግ ተጠያቂነት ምን ይመስላል? ስንል በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የአቤቱታ ምርመራና ክስ አቀራረብ ዳይሬክተር አቶ ጌትነት አሸናፊን አነጋገረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ የንግድ እቃው ወይም ምርቱ እንደሚከማችበት የሃሳብ ሁኔታ ህገወጥ የምርት ክምችትን በሶስት ከፍለን ማየት ይቻላል። በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 24 ላይ በሰፈረው ድንጋጌ መሰረት፤ በገበያ ላይ እጥረት ያለባቸው መሆኑ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በወጣው የህዝብ ማስታወቂያ የታወቁና መንግስት በተለያየ መንገድ ድጎማ የሚያደርግባቸው እንደ ስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ የስንዴ ዱቄት እንደዚሁም ነዳጅ የመሳሰሉት መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ወይም ምርቶችን ማከማቸት በህግ ያስቀጣል።
ስለዚህ አንድ ነጋዴ ከመደበኛው የግብይት አሰራር ውጭ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን አከማችቷል የሚባለው ግምቱ ከነጋዴው ካፒታል 25 በመቶ የማያንስ ምርት አከማችቶ ወይም ከዝኖ ሲገኝ ነው። ከውጭ አገር የገባ የንግድ እቃ ሲሆን፤ ደግሞ አስመጪው ለራሱ ለቀጣይ የምርት ሂደት በጥሬ እቃነት ወይም በግብዓትነት የሚጠቀምበት ካልሆነ በስተቀር የጉምሩክ ፎርማሊቲ ካጠናቀቀ በኋላ በሶስት ወራት ውስጥ ለሽያጭ ካልቀረበ ምርት በህገወጥ መንገድ አከማችቷል እንደሚባል ይናገራሉ።
ስለዚህ በአፍቅሮተ ንዋይ ያልተገባ ጥቅምን ለማግኘት መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በህገወጥ መንገድ አከማችቶ ወይም ሲያጓጉዝ የተገኝ ነጋዴ የንግድ እቃ ከመወረሱ ባሻገር የነጋዴውን ዓመታዊ ገቢውን ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደሚያስቀጣ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል አንድ ነጋዴ ለትርፍ የተለያዩ የአገር ውስጥ የግብርና ምርቶችን (እህል፣ ጥራጥሬና ፍራፍሬ ወ.ዘ.ተ) ከገበሬው ከገዛው ጊዜ ጀምሮ በሁለት ወር ውስጥ ለሽያጭ ካላቀረበ ምርት በህገወጥ መንገድ አከማችቷል እንደሚባል ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ በጅምላ ለማከፋፈል ወይም በችርቻሮ ለመሸጥ የተገዛ የንግድ እቃ ሲሆን፤ ደግሞ ጅምላ አከፋፋዩ ወይም ችርቻሮ ሻጩ እቃውን ከገዛበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ ለሽያጭ ካላቀረበ ህገወጥ ምርት አከማችቷል እንደሚባል ያስረዳሉ።
በመሆኑም በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን አዋጁ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 5 ንዑስ 1 ላይ እንደሰፈረው ከመሰረታዊ የፍጆታ እቃ ባለፈ ማንኛውንም ምርት በበላይነት የያዘ ነጋዴ “ሌሎች ተወዳዳሪዎች የሉም፤ ስለዚህ ይሄንን ከዝኜ ይዤ፣ በፈለግሁት ጊዜ ለፈለግሁት አካል እሸጣለሁ” ብሎ ያልተገባ ትርፍ ለማግበስበስ በህገወጥ መንገድ አከማችቶ ወይም ሲያጓጉዝ የተገኘ ነጋዴ የተያዘውን እቃ በወቅቱ የገበያ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ እንደተጠበቀ ሆኖ የነጋዴውን ዓመታዊ ገቢ እስከ 10 በመቶ የሚደርስ ቅጣት እንደሚጣልበት ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ ህገወጥ ምርት ተከማችቷል ለማለት ከላይ የተጠቀሱትን ሶስት መስፈርቶች ማሟላት ያለበት ቢሆንም ቅሉ ከመደበኛ ግብይት መስመር ውጭ በህገወጥ መንገድ መሰረታዊ የንግድ እቃዎች ወይም ሌሎች ምርቶች ሲዘዋወር ከተገኘ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ምርቶቹ ተወርሰው መጠየቅ ያለበት አካል በህግ እንዲጠየቅ ይደረጋል ብለዋል።
ነገር ግን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 523 በሰፈረው ድንጋጌ መሰረት በአንድ አገር ውስጥ ረሃብ ወይም ችግር እንዲደርስ ማንም ሰው አስቦ ወይም ሆን ብሎ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ በተለይም ምርትን ያለአግባብ በመደበቅና በማከማቸት ለሰውና ለሌሎች እንስሳትን ጨምሮ አስፈላጊ የሆኑ የምግብ ፍጆታ እቃ፣ መድሃኒት፣ የግንባታ እቃ እና አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ምርቶችን ገበያ ላይ እንዲጠፋ በማድረግ በአገር ውስጥ ከባድ መከራ፣ ጦስ፣ ረሃብ ወይም ችግር እንዲደርስ ያደረገ እንደሆነ የንግድ እቃው ከመወረሱ ባሻገር በወንጀል ህጉ ከ15 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ አሁን ላይ በአገሪቱ የሚታየው የግንባታ ብረታ ብረቶችን አከማችቶ ብረቱ ዝጎ ከጥቅም ውጭ እስኪሆን ድረስ ማከማቸት የለየለት የኢኮኖሚ አሻጥር ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ምርትን በህገወጥ መንገድ ማከማቸት በህብረተሰቡ ላይ ረሃብና ቸነፈር እንዲደርስ ያነጣጠረ ጥቃት ሲሆን፤ ህብረተሰቡ በኑሮው ተማሮ ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ እና አገሪቷ ምስቅልቅሏ እንዲወጣ ታቅዶበትና ሆን ተብሎ የሚደረግ የኢኮኖሚ አሻጥር ወይም በአፍቅሮተ ንዋይ ያልተገባ ጥቅም ለማካበት የሚደረግ እኩይ ተግባር ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ አሁን ላይ ህግ አስከባሪው አካል ከኢኮኖሚ አሻጥሩ ጋር በተያያዘ በህገወጦች ላይ ተጨባጭ እርምጃዎች እየወሰደ የሚገኘው ከህብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማ መሰረት ነው። ምክንያቱም ህብረተሰቡ በየትኛውም ቦታ ስለሚገኝ ከህብረተሰቡ አይንና ጆሮ የሚሰወር ወንጀል የለም። ስለዚህ ይህንን ህገወጥ ተግባር ለመቆጣጠር ህግ አስከባሪው አካል ተደራሽ የሚሆንበት ቦታ ውስን መሆኑን አውቆ፤ በጦር ግንባር ከሚካሄደው ውጊያ ባልተናነሰ በህብረተሰቡ ላይ የኢኮኖሚ አሻጥር ጦርነት እንደተከፈተበት ተገንዝቦ ለህግ አስከባሪ አካላት አይንና ጆሮ በመሆን መረጃዎችን በመስጠት መተባበር አለበት።
ስለዚህ ህገወጥ የምርት ክምችትና ዝውውር ሲኖር ህብረተሰቡ በስልክ ቁጥር 0114701755 በመደወል ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቢያሳውቅ፤ ተቋሙ ጥቆማውን ተቀብሎ ከሌሎች ህግ አስከባሪ አካላት ጋር በመቀናጀትም ሆነ በተናጠል ፈጣን ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2013