የዓለም ሀገራት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ግንኙነት ይፈጥራሉ። በተለይ በአሁኑ ወቅት የዓለም ሀገራት የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር በጋራ የሚሰሩበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የሀገራት ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ በፖለቲካ ወይም በፀጥታ ዘርፍ በትብብር መስራት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል።
በሀገራት መካከል የሚደረግ ማናቸውም ግንኙነት የሚገዛው በዓለምአቀፍ ህግ መሰረት ነው። ዓለምአቀፍ ህግ ደግሞ የራሱ የሆኑ መርሆዎች፣ መብቶችና የሀገራት ግዴታዎች ያሉት ሰፊ ማእቀፍ ነው። ዓለምአቀፍ ህግ በተለያዩ የዓለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፎች ገዢ የሆኑ ድንጋጌዎችና ደንቦች አሉት። የዓለም አቀፍ ህግ ምንጭ በዋናነት የሀገራት የፅሁፍ ስምምነት (ሁለትዮሽም ሆነ ባለብዙ)፣ የዳበረና የታወቀ ልማድ፣ ጠቅላላ መርሆዎች እና እነዚህን የሚያረጋግጡ ዓለምአቀፍ ፍርዶችና የታወቁ የምሁራን ፅሁፎች ናቸው።
ከዚህ አኳያ የሀገራት ግንኙነት መርሆችን ስንመለከት እያንዳንዱ ሀገር ትልቅም ሆነ ትንሽ፣ ደሀም ሆነ ባለፀጋ እኩል መብትና ግዴታ አለው። በተጨማሪም የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትና የሚያስተዳድረው ግዛት አንድነት የማይደፈር፣ በሀገሩ ያሉ ሰዎችና ንብረት ላይ ሙሉ ስልጣን ያለው ነው።
ከዚህ አንፃር የታወቁና የተጠበቁ የዓለምአቀፍ ህግ ግንኙነት መርሆዎች መካከል፤ ሁሉም ሀገራት እኩል መሆናቸው፣ ሀገራት ሉዓላዊ ስልጣን ያላቸው መሆናቸው፣ ዓለምአቀፍ ግንኙነቶችን በቅን ልቦና ማድረግ፣ በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ማንም ጣልቃ መግባት አለመቻሉ፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ራስን በመከላከል ካልሆነ በቀር ኃይልን አለመጠቀም፣ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚሉት ይገኙበታል።
ሀገራት ግንኙነታቸውን እና በተለያዩ ጉዳዮች ያሉ ትብብራቸውን ለማሳለጥ በሁለትዮሽ ግንኙነትም ይሁን በባለብዙ ዘርፍ ግንኙነት በጋራ እየሆኑ ዓለምአቀፍ እና አህጉራዊ ድርጅቶችን መስርተው በጋራ ለመስራት ጥረት ያደርጋሉ። የማናቸውም ሀገራት ግንኙነት ከላይ በተመለከቱት አጠቃላይ የዓለምአቀፍ ህጎች እና መርሆች የሚገዙ ናቸው። ማናቸውም ሀገር የሌላው ሀገር ሉአላዊነት፣ የግዛት አንድነት፣ የፖለቲካ ነፃነት፣ እኩልነት ማክበር እና በውስጥ ጉዳይ ከመግባት መቆጠብ አለባቸው።
አንድ ሀገር ከሌላ ሀገር ጋር ግንኙነቱ የሻከረ እንደሆነ ወይም አለመግባባት የተፈጠረ እንደሆነ ይህን ለማስተካከል ሰላማዊ በሆነ መንገድ በቀጥታ ወይም ሶስተኛ ወገንን ጨምሮ መነጋገርና ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ከመጣር በዘለለ በሌላ ሀገር ጉዳይ ጣልቃ መግባት አይችሉም።
በሌላ አገላለፅ በአንድ ሀገር ውስጥ አንድን ወገን መደገፍ ሌላውን መቃወም ወይም አንድ መንግሥት ይህን አድርግ ይህን አታድርግ በማለት ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ጫና ወይም ማእቀብ በመንግሥት ላይ ማድረግ በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ በቀጥታ ጣልቃ መግባት ማለት ነው።
አንድ ሀገር በሌላ ሀገር ውስጥ ጉዳይ ላይ በራሱም ሆነ ሌሎች ሀገራት ጫና እንዲያደርጉበት፣ እንዲያገሉት ወይም ግንኙነት እንዳያደርጉ ማድረግ ግልፅ የሆነ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት እርምጃ እና የዓለም አቀፍ ህግ ጥሰት ነው። ነገር ግን ሀገራት ከእነዚህ መርሆዎች ውጭ የተለያዩ ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ በሌላ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሲገቡ እና የተለያዩ ጫናዎችን ሲፈጥሩ ይስተዋላል። ለአብነት አሜሪካና ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ወቅታዊ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት “ይሄን አድርጉ፣ ይሄን አታድርጎ” በሚል ሉዓላዊ በሆነች አገር ላይ ጣልቃ በመግባት ሲፈተፍቱ ይስተዋላል።
በተለይም ግብዣ ሳይቀርብና ፈቃድ ሳይሰጥ በአንድ ሀገር የውስጥ አስተዳደር ጉዳይ በመግባት እንዲህ አድርጉ ወይም እንደዚህ አታድርጉ በማለት በውስጥ ጉዳይ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ ተግባር ነው።
በሌላ በኩል ሀገራት በፈቃዳቸው ያቋቋሙት እና አባል የሆኑበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋነኛ አላማዎች ወይም ተግባራት መካከል ዓለም አቀፍ ሰላምና ፀጥታ ማስጠበቅ፣ የሀገራትን ወዳጅነት በሉዓላዊ እኩልነት ላይ ተመስርቶ ማራመድ፣ የኢኮኖሚ ማህበራዊና ባህላዊ ችግሮችን ለመፍታትና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር በትብብር መስራት ይገኙበታል።
ከዚህ አንፃር በአንድ ሀገር ያሉ ሁነቶች ዓለምአቀፍ ሰላምና ጸጥታን የሚመለከቱ ከሆኑ ወይም በሁለት ሀገራት መካከል ያለ ግንኙነት ዓለምአቀፍ ሰላምና ፀጥታን የሚያደፈርስ ከሆነ ጉዳዩን በመመልከት ህጋዊ የሆነ መፍትሄ የመስጠት ኃላፊነት ይኖረዋል። አባል ሀገራትም በዚህ ማእቀፍ ውስጥ መስራት ይችላሉ።
የሀገራት ግንኙነት ሊመራ የሚገባው በዚህ ማዕቀፍ ቢሆንም በአንድ ሀገር ውስጥ ሊከሰት የሚችለው ችግር ዓለምአቀፍ ሰላምና ፀጥታን የሚመለከቱ ጉዳዮች ባልሆነ ጊዜ የሀገራትን ግንኙነት መርሆዎችን ተከትሎ መንቀሳቀስ ላይ የወጥነት ችግር እና መርህን መሰረት አለማድረግ እንደ ችግር ይታያል።
ዓለምአቀፍ ሰላምና ፀጥታን የሚመለከት ችግር ባጋጠመ ጊዜ የግጭቶች አካሄድ ዓለምአቀፍ ህግን ያከበረ እንዲሆን እና ወደ ጎረቤት ሀገሮች ግጭቶች እና ችግሮች ተስፋፍተው አካባቢያዊ ሰላምና ፀጥታን የሚያደፈርስ እንዳይሆን የመከታተልና የመደገፍ ሥራ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሉ ተቋማት ሊሰሩ ይችላሉ።
ከዚህ አንፃር ቢሆን የተባበሩት መንግሥታት በጉዳዩ የሚመለከተው በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ሳይሆን ሀገራት የገቡትን ዓለምአቀፍ ግዴታ ከማክበራቸው አንፃር እና የሀገራት እርምጃ ከዓለም አቀፍ ሰላምና ፀጥታ መጠበቅ ላይ ከሚኖረው ተፅእኖ አንፃር ብቻ ሊሆን ይገባል።
በሌላ በኩል የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚያጋጥሙ ቢሆን የአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ እና ዓለምአቀፍ ግዴታን የመወጣት ጉዳይ ነው። የሰብአዊ መብት ጥሰት ከፍ ያለ እና ስርአታዊ (systemic) መልክ ያለው ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት ችግሩን ለመቅረፍ ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ የሚጋብዝ ከሚሆን ውጪ ዓለምአቀፍ ሰላምና ፀጥታን የሚያናጋ እስካልሆነ ድረስ በስልጣኑ ስር የሚወድቅ ጉዳይ አይሆንም።
በተመሳሳይ የሰብአዊ እርዳታ በምግብም ሆነ መጠለያ በስፋት ማስፈለጉ የአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ቢሆንም ዓለምአቀፍ ህብረተሰቡ ድጋፍ የማድረግ ሰብአዊ ግዴታ አለበት። ከዚህ አንፃርም የተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ አንድን ሀገር ይህን አድርግ ይህን አታድርግ ለማስባል የሚበቃ አይደለም። ወደእዚህ ደረጃ ከፍ ሊል የሚችለው ችግሩ ዓለምአቀፍ የሰላምና ፀጥታ ችግር ወደ መሆን ደርሷል ወይም ሊደርስ ይችላል የሚባል ሲሆን ብቻ ነው።
በመሆኑም ሀገራት በዓለምአቀፍ ግንኙነታቸው አንዱ የሌላውን እኩልነት እና ሉአላዊነት ማክበር፣ በቅን ልቦና ግንኙነቶችን ማድረግ፣ በሌሎች ሀገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባትና ጫና አለማድረግ ያስፈልጋል። የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ የስልጣንና ኃላፊነት ወሰኑን በሚገባ በመጠበቅ ዓለምአቀፍ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እና የአባል ሀገራትን እኩልነት እና ሉአላዊነት ማክበርና ማስከበር ይጠበቅበታል። በተጨማሪም ሀገራት ዓለምአቀፍ ግዴታቸውን ለመወጣት የሚያደርጉትን ጥረት የመደገፍ እና ሰብአዊ ድጋፍ የማድረግ ዓለምአቀፍ ግዴታውን በተቻለ መጠን ለመወጣት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ. ም
ሶሎሞን በየነ