ሕግ ማለት የህብረተሰቡን ሰላም፣ ደህንነትና ጸጥታ ለመጠብቅ ከአንድ መንግሥት የወጣ መተዳደሪያ ደንብ ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ በተለምዶ የምናደርጋቸው ነገር ግን በህግ አውጭዎች ደግሞ እንደ ህግ የወጡ፣ በህግ ተርጓሚዎች የሚተረጎሙ እና በህግ አስፈጻሚዎች ደግሞ የሚተገበሩ ህጎችን ህብረተሰቡ ጠንቅቆ የማወቅ ክፍተት በሃገራችን በጉልህ የሚታይ ችግር ነው ፡፡ ለአብነት በተለምዶ በሻጭ እና ገዥ በኩል የሚደረግ የቀበድ ስምምነት እና ህጋዊነቱ አንዱ ነው ፡፡
በኢትዮጵያ ከቤት ኪራይ ጀምሮ ቀላል እና ከባድ እቃዎችን ስንገዛ እና ስንሸጥ ሻጩ ሙሉ ክፍያ እስከሚከፈለው ድረስ ሌላ ገዥ ቢመጣ እንዳይሸጥ፤ ገዥውም ሌላ አማራጭ ቢያገኝ ወደ አዲሱ አማራጭ ሂዶ ሻጩን ባጣ ቆየኝ እንዳያደርገው በሚል ሻጭ እና ገዥ ቀብድ የመስጠት እና የመቀበል ልምድ አለ፡፡
ይሁን እና አንዳንዴ ቀብድ ከከፈሉ በኋላ ሌላ ማራጭ ስላገኘሁ ወይም መግዛቱን ስለተውኩት የከፈልኩትን ቀብድ መልሱልኝ ወይም ደግሞ ሻጭ መሸጡን ስለተውኩት ወይም አንተ/አንች ከከፈልከኝ/ሽኝ ገንዘብ በላይ የሚከፍለኝ ሰው ስላገኘሁበት ገንዘብህን/ሽን ውሰድ/ጂ በሚል እሰጣ ገባ በመግባት ወደ አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ እየተገባ አያሌ ችግር ሲፈጠሩ ይስተዋላል ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በዛሬው የዘመን ችሎት አምዳችን ስለቀብድ ምንነት እና ህጋዊ ውጤቱ እንደሚከተለው የሚዳስስ ይሆናል፡፡
ስለቀብድ ምንነት እና ህጋዊ ውጤቱ እንዲያስረዱን በማንኛውም ፍርድ ቤት ጠበቃና የሕግ አማካሪ የሆኑትን አቶ ዘመድኩን ካሱን አናጋግረን በሰጡን ማብራሪያ፤ አብዛኛው ማህበረሰብ ማለት ይቻላል የተለያዩ እቃዎችን ለመግዛት ወይም ለመሸጥ ውል በመፈጸም ቅድሚያ ቀብድ ሲከፍል ወይም ሲቀበል ይስተዋላል። ነገር ግን ቀብድ ተቀባዩም ሆነ ቀብድ ሰጪው አካል ስለ ቀብድ ምንነትና ውጤት ያለው ግንዛቤ አናሳ ነው። ስለሆነም ስለቀበድ ህጋዊነት መገንዘብ የሚገባን ነገሮች ላይ መነጋገር አንደሚያስፈልግ የህግ ባለሙያው ያምናሉ፡፡
በኢትዮጵያ ፍታብሄር ህግ ከቁጥር 1883- 1885 ድረስ ባሉት ሶስት አንቀፆች ውስጥ ቀብድን የሚመለከቱ ሀሳቦች የተቀመጡ ቢሆንም “ቀብድ” ለሚለው ቃል ግን የሚሰጡት ትርጉም የለም የሚሉት አቶ ዘመድኩን፤ እነዚህ ድንጋጌዎችም ቀብድን ከውል ምስረታ ማስረጃነት ገፅታው እና በተዋዋይ ወገኖች መካከል እንደ አግባብነቱ ቅጣት በመወሰን ቀብድ ያለበት ውል በማናቸውም ጊዜ ቀሪ ሊሆን መቻሉን በመደንገግ ላይ የተወሰኑ መሆናቸውን አመላክተዋል።
እንደ አቶ ዘመድኩን ገለጻ ፤ በኢትዮጵያ የፍታብሄር ህግ ላይ ቀብድ (earnest) የሚለው ቃል በግልፅ ትርጓሜ የተሰጠው ባይሆንም በእንግሊዘኛው አነጋገር በblacks law dictionary ውስጥ በተሰጠው ትርጉም መሰረት “ቀብድ ማለት ተዋዋይ ወገኖች ከግዴታቸው እንዳያፈነግጡ ለማድረግ ተብሎ የሚሰጥ የተሸጠ ዕቃ ከፊል ዋጋ ነው። እንዲሁም ዕቃው መሸጡን ለማሳየትና ለማፅደቅ ተብሎ አንዱ ተዋዋይ ለሌላው የሚሰጠው የመተማመኛ ገንዘብ ነው” በሚል ያስቀምጣል ብለዋል።
ቀብድ አብዛኛውን ጊዜ የሚሰጠው ውሉ የሽያጭ ውል ሲሆን ነው የሚሉት አቶ ዘመድኩን ፤ ገዥው በሽያጭ ውሉ ለመገደድ ያለውን ሀሳብ ለማሳየት እና ሻጩ ደግሞ እሸጣለሁ ብሎ የሰጠውን ቃል እንዳያጥፍ ውሉ መፈፀሙ እርግጠኛ በሆነበት ሰዓት አንዱ ወገን ለሌላው ወገን ውሉ ሲደረግ ለማሰር የሚሰጠው ክፍያ መሆኑን ገልጸዋል።
የቀብድ ህጋዊ ውጤት
ቀብድ ሻጭና ገዥ በተነጋገሩበት ጉዳይ ላይ ውል መፈፀማቸውን እርግጠኛ ሲሆኑ የሚቀባበሉት ገንዘብ በመሆኑ ይህን ማድረጋቸው ገንዘቡን ለመቀባበላቸው ብቻ ሳይሆን ውሉን ለመዋዋላቸውም ማስተባበያ የማይቀርብበት ማስረጃ መሆኑን የፍታብሄር ህግ ቁጥር 1883 ይደነግጋል የሚሉት አቶ ዘመድኩን ፤ ገዥና ሻጭ አንድን ቤት ሲሻሻጡ በፍታብሄር ህግ ቁጥር 1723(1) ስር የተመለከተውን ፎርም ባያሟሉም ሻጭ ለዚሁ የሽያጭ ውል ማስፈፀሚያ ቀብድ መቀበሉ ከተረጋገጠ በማያከራክር ሁኔታ ውሉ መደረጉን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጻዋል።
አንድ ውል የህጉን ፎርም ካላሟላ በህግ ፊት የማይፀና ይሆናል፡፡ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ የቀብድ ገንዘብ ክፍያ ካለ ውሉ የህጉን ፎርም ያላሟላ ቢሆንም የቤት ሽያጭ ውል ስለመኖሩ የማያከራክር ማረጋገጫ ስለሆነ ውሉ የፀና እንደሚሆን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰነድ መዝገብ ቁጥር 56794 ቅፅ 12 በግልፅ ተመላክቷል የሚሉት አቶ ዘመድኩን፤ የተከፈለው ክፍያ ግን ቀብድ መሆኑ በውሉ ላይ ካልተገለፀ በቀር ቀብድ ነው ተብሎ ሻጭ አጠፌታውን እንዲከፍል የማያስገድድ ከመሆኑ በላይ ውሉ መኖሩንም ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ዘመድኩን ገለጻ ፤ የቀብድ ክፍያ መኖሩ የውሉን መኖር የሚያረጋግጥ ብቁ ማስረጃ ቢሆንም ተዋዋይ ወገኖች ውሉን ለማፍረስ ተቃራኒ ስምምነት ካላደረጉ በቀር ቀብድ ተቀባዩ የተቀበለውን ገንዘብ እጥፍ አድርጎ በመመለስ፣ ቀብድ ሰጪው ደግሞ ይህንኑ የሰጠውን ገንዘብ ለተቀባዩ በመልቀቅ ያለሌላ ተጨማሪ ሁኔታ ውሉን የማፍረስና በመካከላቸው የተመሰረተውን ግዴታ ለማስቀረት መብት አላቸው።
ይህም አሰራር በቀብድ የታሰረ ውል ከሌሎች ውሎች የሚለይበት ልዩ ባህሪ በኢትዮጵያ የፍታብሄር ህግ ቁጥር 1885 ተመላክቷል፡፡ ፍርድ ቤቶችም በተዋዋይ ወገኖች መካከል ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በቀር ሻጩ የቀብዱን አጠፌታ ከፍሎ ውሉን በማፍረስ የሸጠው ቤት እንዲመለስለት ከጠየቀ መወሰን የሚገባቸውና ተገዶ እንዲፈፅም ማድረግ የሌለባቸው መሆኑ ግልፅ ነው።
ነገር ግን የተደረገው ውል ሊፈፀም የማይችል (impossible)፣ ወደ ገዥ ሊተላለፍ የማይችል እና ህገ ወጥ (unlawful) ከሆነ ግን ውሉ ፈርሶ ተዋዋይ ወገኖች አይነታቸዉን (የየራሳቸውን) ከመመላለስ በስተቀር ሻጭም እጥፉን እንዲመልስና ገዢም የከፈለውን እንዲለቅ የሚጣልባቸው ግዴታ የለም።
ውሉ በአግባቡ ከተፈፀመ እና ለቀብዱ ገንዘብ ዕጣ ፋንታ በተዋዋዬቹ መሀል የተደረገ ሌላ ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ የቀብድ ሂሳቡ ከጠቅላላው የሽያጭ ዋጋ ላይ የሚታሰብ ወይም እንዲመለስ እንደሚደረግ በኢትዮጵያ የፍታብሄር ህግ ቁጥር 1884 መደንገጉንም አቶ ዘመድኩን አመላክተዋል፡፡
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2013