በጦርነት ጊዜ ሊከበሩ የሚገባቸው የተለያዩ ተግባራትን የሚከለክሉ፣ ተፈጽመው ሲገኙ በዓለም አቀፍ ወንጀልነት የሚያስጠይቁ ተግባራት አሉ። እነዚህ በትጥቅ ትግል ወቅት የተከለከሉ ተግባራት አጀማመራቸው ብዙ ክፍለ ዘመንን ቢያስቆጥርም የጦር ወንጀል ጽንሰ ሃሳብ መቀንቀን የጀመረው በ19ኛው ክፈለ ዘመን መጨረሻ እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ አካባቢ የዓለም አቀፍ ሰብአዊነት (በትጥቅ የታገዘ ግጭት) ህግ መረቀቅን ተከትሎ ነው።
በእነዚህ ወቅቶች የተረቀቁት የጦር ወንጀልን የሚደነግጉ ስምምነቶች በጦርነት ወቅት የተከለከሉ ተግባራትን በተለይም የተከለከሉ መሳሪያዎችና በጦርነት ውስጥ ያልተሳተፉ እና በፊት የተሳተፉ ቢሆንም ከጦርነቱ የወጡ ሰዎች እንዲሁም በግጭቱ ጊዜ ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባን የተለያዩ ሰዎች እና ንብረቶች በተመለከተ ሊደረግ የሚገባ ጥበቃን በስፋት የሚደነግጉ ናቸው።
በዚህ ህግ ክልከላ ወይም ግዳጅ የተጣለባቸው ሁለት ወገኖች ሲሆኑ፤ እነዚህም ግራ እና ቀኝ ይዘው በትጥቅ በመታገዝ ግጭትን (በተለምዶ ጦርነት) እያደረጉ ያሉ ወገኖች ናቸው። ሁለቱም የጄኔቫ እና የሄግ ስምምነቶች እንደመነሻ ያስቀመጧቸው እና በክልከላ የደነገጓቸውን እሴቶች እና ደምቦችን መጣስ እ.ኤ.አ በ1998 የዓለምአቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ስምምነት ከአንቀጽ 5 እስከ 8 በተደነገገው መሰረት በጦር ወንጀልነት የሚያስከስሱ ናቸው።
ከዚህ አኳያ በአራቱ የጄኔቫ ስምምነት እና ሁለቱ ተጨማሪ ፕሮቶኮሎች መሰረት በትጥቅ በታገዘ ግጭት ውስጥ የገባ ማንኛውም ወገን የሚከተሉትን የህግ ግዴታዎች ማክበር አለበት። እነዚህን ግዴታዎች ተላልፎ መገኘት በጦር ወንጀል ያስከስሳል።
ስለዚህ በግጭቱ ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸው እና ተሳትፎ ቢኖራቸውም የፍልሚያ አቅማቸው ያበቃ ወይም የደከሙ ወታደሮች አካላዊና ሞራላዊ ደህንነታቸው መጠበቅ አለበት፤ በሰብአዊነት በተሞላው መልኩ መያዝ አለባቸው። ከጠላት ወገን የተማረኩ ተዋጊዎችን መግደል እና ማሰቃየት የተከለከለ ነው። በጦርነቱ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው እና የታመሙ ተዋጊዎች በተቆጣጠራቸው ሃይል ተሰብስበው እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል።
እንዲሁም የተማረኩ ተዋጊዎች እና ሲቪል ሰዎች ሰብአዊ ክብራቸው፣ በህይወት የመኖር እና ከበቀል እርምጃ የመጠበቅ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል። እርዳታ የማግኘት እና ከቤተሰቦቻቸው የመገናኘት መብት መጠበቅ አለበት። የዳኘነት ሥርዓት ዋስትና ማግኘት አለባቸው። ያለመሰቃየት እና አዋራጅ ከሆነ አያያዝ የመጠበቅ መብትም አላቸው። ማንም ሰው በመደበኛ ህግ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት በዳኝነት ሥርዓት ውስጥ ሳያልፍ ሊገደል እና ሌሎች መብቶቹ ሊገደቡበት አይገባም።
በሌላ በኩል የጥበቃ፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የትራንስፖርት ባለሙያዎች፣ የሚጠቀሙባቸው መሳሪያ ዎች፣ የቀይ መስቀል እና የቀይ ጨረቃ አርማዎች ላይ ጥቃት መድረስ የለበትም። ይልቁኑ ጥበቃ ሊደረግ ይገባል። ተሳታፊ ተዋጊዎች የተገደበ የጦርነት አካሄድ መጠቀም አለባቸው። አላስፈላጊ ጉዳት የሚያስከትሉ መሳሪዎችን መጠቀም የለባቸውም። በጦርነቱ ተሳትፎ የሌላቸው (ሲቪል ሰዎች) ንብረታቸው ሊከበር ይገባል። ጥቃቶች ወታደራዊ ኢላማዎችን ብቻ ታርጌት አድርገው መፈጸም አለባቸው።
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ ክልከላዎች እና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተላልፎ ጉዳት ያደረሰ ቡድን ወይም ግለሰብ እንደየተሳትፎው እና የጉዳቱ መጠን በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ስምምነት መሰረት በጦር ወንጀል ተከሶ እስከ እድሜ ልክ ከፍ ሲልም በሞት ቅጣት የሚያስቀጣ ይሆናል። ከዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ክስ ቢያመልጥም በአገራቱ ፍርድ ቤት ወንጀል ህግ መሰረት ተከሶ ይቀጣል።
እነዚህ ወንጀሎች ጉዳታቸው ከባድ በመሆኑ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችም እንደመሆናቸው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ህገመንግስት አንቀጽ 28 መሰረት ክስ የማቅረቢያ የይርጋ ጊዜ የሌላቸው በመሆኑ፤ በየትኛውም ጊዜ ክስ ሊቀርብባቸው የሚገባ ወንጀሎች ናቸው። በተጨማሪም በጦር ወንጀል የተፈረደባቸው ወንጀለኞች ፍርድና ቅጣት በምንም ምክንያት በየትኛውም የመንግስት አካል በይቅርታም ሆነ በምህረት ሊታለፉ የማይችሉ ወንጀሎች መሆናቸውን ከህገመንግስቱ መረዳት የቻላል።
ከዚህ አኳያ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ የተደነገጉ የጦር ወንጀሎች ዓለምአቀፍ ህጎችን በመጣስ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሚል ርእስ ከአንቀጽ 270 እስከ 283 ስር ተዘርዝረው የሚገኙ ሲሆን፤ በይዘታቸው ከላይ ካነሳነው በዓለም አቀፍ ህግጋት ስር የተዘረዘሩትን የወንጀል ማቋቋሚያ የተደነገጉ ክልከላዎች እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ጋር በአብዛኛው ተመሳሳይ ናቸው።
በወንጀል ህጉም በጦርነት ወቅት ሰዎችን በማንነታቸው ለይቶ በከፊልም ይሁን በሙሉ ዘራቸውን ለማጥፋት የሚፈጸም ማናቸውም ድርጊት የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲሆን፤ ከ5 እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት እና ጉዳዩ ከባድ ሲሆን እስከ ሞት ቅጣት ድረስ የሚያስቀጣ ከባድ ወንጀል እንደሆነ ይደነግጋል።
በጦርነት ተሳትፎ የሌላቸውን ሰላማዊ ሰዎች መግደል፣ ከመኖሪያቸው በሃይል ማፈናቀል፣ እንዲበተኑ ማድረግ፣ በተደራጀ እቅድ ከሀገር ማስወጣት፣ ሥነ ህይወታዊ ሙከራ ማድረግ፣ ማሰቃየት እና ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶችን መፈጸም፣ የኢኮኖሚ አሻጥር መፈጸም፣ የገንዘብን ዋጋ ዝቅ ማድረግ፣ ሀሰተኛ ገንዘብ ማተም፣ በተደራጀ ሴራ ህዝብን ለከፍተኛ ረሀብ እና ችግር መዳረግ በህግ ያስቀጣል።
እንዲሁም ሰላማዊ ሰውን በሃይል አስገድዶ በጠላት የስለላ ወይም ወታደራዊ መዋቅር ውስጥ መልምሎ ማሰራት፣ በግዴታ ዜግነቱን ወይም ሃይማኖቱን ማስቀየር፣ በማስገደድ የዝሙት ድርጊት (የግብረስጋ በደል መፈጸም)፣ ንብረትን ማውደም እና ተገቢ ያልሆነ የተጋነነ ግብር እና ቀረጥ መጣል፣ የእርሻ ቦታዎችን፣ ሰብልን ፣ የእርሻ መሳሪያን እንዲሁም ከብቶችን ማውደምና መግደል፣ መውረስ፣ ማጥፋት፣ የራስ ማድረግ፣ ታሪካዊ ስፍራዎች እና የእምነት ቦታዎችን ማፍረስ፣ በተቆጣጠራቸው ስፍራዎች ለሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ምግብና የህክምና ፍጆታ አለማቅረብ እና እንዲቀርብላቸው አለማድረግ፣ ስደተኞችን (አገር አልባ ሰዎችን) ማጥቃትና መበደል በጦር ወንጀል ህግ የሚያስጠይቅ ነው።
በተጨማሪ በከባቢ ንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ መሳሪዎችን መጠቀም፣ ግድቦችን እና የኤሌክትሪክ ማመንጫ ኒውክለሮችን ማጥቃት፣ ያለ ፍርድ ቤት ዳኝነት እና ውሳኔ በራሱ ቅጣትን መጣል እና ማስፈጸም (ለአብነት መግደል)፣ በውጊያ በቆሰሉ ወይም በታመሙ ተዋጊዎች ላይ የማሰቃየት፣ የጤና አገልግሎት መከልከል እና ሌሎች ዝቅተኛ ሰብአዊ አያያዝን ማጉደል፤ የእርዳታ መስጫ፣ የህክምና ባለሙዎችን እና የህክምና ቁሳቁሶችን ያለ አግባብ ከወታደራዊ አስፈላጊነት ውጪ እንዲበላሹ እና ከአገልግሎት ውጭ ማድረግም እንዲሁ በህጉ ያስቀጣል።
ከዚህ ባሻገር የጤና ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት ሰዎች እና ጋዜጠኞችን አስገድዶ ከሙያ ስነምግባራቸው ውጪ እንዲሰሩ ማድረግ እና በአግባቡ ስራቸውን እንዳያከናውኑ ማድረግ፣ በታሰሩ የጦር ምርኮኞች እና በቁጥጥር ስር የዋሉ ንጹሃን ዜጎችን የመግደል፣ ማሰቃየት እና ማጉላላት ወይም አስገድዶ የጠላት የስላላ ወይም ወታደራዊ ስራ እንዲሰሩ ማድረግ፤ በጦርነት ጊዜ ለወታደራዊ አስፈላጊነት በሚል ሰበብ ዘረፋን፣ ገፋፊነትን፣ ህገወጥ የንብረት ማፍረስ እና የመውሰድ ተግባርን ማዘዝና መፈጸም በጥቅሉ ከላይ የተዘረዘሩ ወንጀሎችን የፈጸመ ማንኛውም ሰው ከ5 ዓመት ጽኑ እስራት እስከ እድሜ ልክ እስራት እና ከፍ ሲል የሞት ቅጣት የሚያስቀጡ ናቸው።
ከላይ የተጠቀሱትን ወንጀሎች እንዲፈጸሙ በንግግር፣ በጽሁፍ ወይም በስእል በአደባባይ ማደፋፈር ወይም መገፋፋት ከ5 አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን፤ እነዚህን ወንጀሎች የሚፈጽም የወንበዴ ቡድን እንዲቋቋም መስራት፤ ህገወጥ በሆኑ የጦር መሳሪያዎች መገልገል ከ3 ወር እስከ እድሜ ልክ እና ከፍ ሲልም በሞት የሚያስቀጣ ይሆናል።
እንዲሁም በቁስለኞች፣ በሽተኞች እና በእስረኞች መጨከን፤ ሰላማዊ ሰውን፣ ቁስለኛን ወይም እስረኛን በፍትህ ሥርዓት የተዘረጋ መብትን በተለይም ራሱን የመከላከል መብቱን መንፈግ ከ3 እስከ 5 ዓመት ሊደርስ የሚችል እስራት እንደሚያስቀጣ በወንጀል ህጉ ተደንግጓል።
ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድርጅቶች አርማ እና ምልክቶችን ያለአግባብ መገልገል እንዲሁም በሰራተኞቻቸው እና በእነርሱ ጥበቃ ስር በሚገኙ ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረስ፣ የድርጅቶቹን ግዙፍ ንብረቶች ወይም ማከማቻቸው ላይ ጥቃት ማድረስ እና ማፍረስ ከቀላል እስራት እስከ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ያስቀጣል። ከጠላት ወገን ለእርቅ ለድርድር ተልዕኮ ይዞ የመጣን ሰው እና ከሱ ጋር ያሉ ሌሎች ሰዎችን በማንኛውም መንገድ ማጉላላት፣ ማስፈራራት፣ ማዋረድ፣ መዛት በቀላል እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው።
ከዚህ አኳያ ከላይ የተዘረዘሩ ከቀላል እስከ ከባድ በዓለም ብሎም በአገር አቀፍ የጦር ወንጀል የሚያስጠይቁ የጦር ወንጀሎችን አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሰሜኑ የአገሪቱ ጦርነት እየፈጸመ እንደሚገኝ “ፀሃይ የሞቀው አገር ያወቀው” ተግባር ነው።
ምንጭ:- የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2014