ታምራት ተስፋዬ
ኮንትሮባንድ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተከለከሉ ነገሮችን ይዞ መገኘት ወይም መግዛት ለማመላከት እኤአ ከ1529 ጀምሮ ጥቅም ላይ መዋሉ ይነገራል። ዓለም አቀፉ የጉምሩክ ድርጅት ፣ኮንትሮባንድ ማለት ማንኛውም በህግ የተከለከለ አሰራር ሲሆን እሱም ከማምረት፣ ከማጓጓዝ፣ ከመቀበል፣ ባለቤት ከመሆን፣ ከማከፋፈል፣ ከመግዛትና መሸጥ እንዲሁም ማንኛውም ለዚህ አሰራር ሁኔታዎችን ማመቻቸትን ያካትታል በማለት ተርጉሞታል።
በኢትዮጵያ የኮንትሮባንድ ንግድ መቼና እንዴት እንደተጀመረ የሚገልጽ የተሟላ ማስረጃ ባይኖርም እንቅስቃሴው ከተጀመረ ግን በርካታ ዓመታትን ማስቆጠሩ ይታመናል። ሀገሪቱም በየጊዜው እየጎለበተ የመጣውን ኮንትሮባንድ ለመግታት የተለያዩ ህጎችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ አድርጋለች።
ኮንትሮባንድ ወንጀልና ቅጣትም በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 በግልጽ ተቀምጧል። ይህ አዋጅም ማንኛውም ሰው እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው የጉምሩክ ህጎችን፣ ደንቦችን ወይም መመሪያዎችን በመተላለፍ የተከለከሉ፣ ገደብ የተደረገባቸውን፣ የንግድ መጠን ያላቸውንና የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈጸመባቸውን ዕቃዎች ከህጋዊ መተላለፊያ መስመሩ ውጪ በድብቅ ወደ ሀገር ካስገባ፣ ካስወጣ ወይም ከሞከረ ወይም በህጋዊ መንገድ የወጡ እቃዎችን በህገ-ወጥ መንገድ መልሶ ካስገባ ከአምስት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል። እንዲሁም ከብር 50ሺ በማያንስና ከብር 200 ሺ በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ ያስቀምጣል።
በህገ-ወጥ መንገድ የተገኙ እቃዎችን ያጓጓዘ፣ ያከማቸ፣ የያዘ፣ ለሽያጭ ያቀረበ ወይም የገዛ ሰው ከሦስት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 50ሺ እስከ 100 ሺ እንደሚቀጣ ያስቀምጣል። ወንጀሉ የተፈፀመው ኃይል በመጠቀም ወይም በቡድን በመደራጀት ከሆነ ደግሞ የእስራት ቅጣቱ እስከ 15 ዓመት ከፍ ይላል።
ምንም እንኳን አገሪቱ ተግባሩን ለመቆጣጠር መሰል ህጎችን ተግባራዊ ብታደርግም በኮንትሮባንድ እቃዎችን በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የማስወጣትና ማስገባት እንቅስቃሴን በሚፈለገው ልክ መግታት አልተቻላትም። ይሄ ድክመትም በኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት ላይ ከባድ ተፅእኖ እንደሚፈጥር የተለያዩ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ መምህር እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ፍሬዘር ጥላሁንም፣ የኢትዮጵያ እና የኮንትሮባንድ ጋብቻ ከለውጡ በፊት እና በኋላ በሚል በሁለት ከፍለው ይመለከቱታል። ከለውጡ በፊት የነበረው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴም በገቢውም ሆነ በወጭ ምርት እጅግ ከፍተኛ እና የመንግስት ባለስልጣናትን ሳይቀር ዋነኛ ተዋናይ የነበሩበት መሆኑን ያስታውሳሉ።
እንደ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ገለፃ፣ በኮንትሮባንድ እቃዎችን በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የማስወጣትና የማስገባት እንቅስቃሴ በአንድ አገር ላይ ከሚያደርሰው ኪሳራ ባሻገር ጉዳቱም የእያንዳንዱን ጓዳ የሚያንኳኳ ነው። የኮንትሮባንድ ንግድ ተገቢው ግብር የማይከፈልበት በመሆኑ አገር በቀረጥም ሆነ በታክስ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ያሳጣል። በርካታ ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸውን እንደ መንገድ፣ የትምህርትና የጤና ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች የልማት ስራዎችን ለመስራት የሚስችላትን ገቢ ይነጥቃል።
የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ተወዳዳሪነት ይቀንሳል። ከወጪና ገቢ ንግድ የሚገኝን ግብር እና ቀረጥ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬን ያሳጣል። በዜጎች መካከል ሰፊ የገቢ ልዩነትን ያስከትላል። ፍትሃዊ የንግድ ሥርዓቱን ያመሰቃቅላል። በሀቀኛ ግብር ከፋዮች ላይ የግብር ጫናን ከፍ ያደርጋል።
ጥቁር ገበያን በማስፋፋት የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመፍጠር፣ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ያዳክማል። ባለሀብቶች በሀገር ውስጥ ያመረቱትን ምርት ገበያ ይሻማል። የሸቀጦችን ዋጋ በማናር የዋጋ ግሽበትን ስለሚፈጥር በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ ያከብዳል።
ወንጀሉ በአጠቃላይ ልማት በሚፈለገው ፍጥነትና መጠን እንዳይስፋፋ በማድረግ ድህነት በመቀነስ ፋንታ እንዲባባስ የሚያደርግ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያትም አገሪቱ በወንጀሉና በወንጀለኞቹ ተተብትባ ለከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ መዳረጓን ያስታውሳሉ።
‹‹በአሁኑ ወቅት የወንጀሉ ተቆጣጣሪ ነኝ እያለ በጎን ዋነኛ ተዋናይ ብሎ ነጋዴ የሆነው ሥርዓት በመወገዱ እንቅስቃሴው እንደቀድሞው አይደለም›› የሚሉት አቶ ፍሬዘር፣ የለውጡ መንግስት ሌብነትን ለማስወገድ በያዘው ቁርጠኛ አቋም የኮንትሮባንድ ወንጀሉ በእጅጉ ተዳክሟል። ይህ ማለት ግን ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። ዛሬም በርካታ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዝ መቻላቸው አሁንም ኮንትሮባንድ አለ ለማለት በቂ ምስክር ነው።
ከፍተኛ መሻሻሎች ቢስተዋሉም ወንጀሉ ዛሬም ቢሆን ፍቱን መድሃኒት ለማጣቱ በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ሀገሪቱ ኮንትሮባንድን ለመግታት የተለያዩ ህጎችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ ብታደርግ ያስቀመጠችው ቅጣት ግን ዝቅተኛ መሆኑም ተዋናዮቹ የልብ ልብ እንዲሰማቸው ማድረጉ ይነሳል።
አቶ ፍሬዘርም፣ ለወንጀሉ መፍትሄ ለመስጠት የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴን ለመግታት የወጡ የህግ ቅጣቶች አቅም መጨመር የግድ መሆኑን ይገልጻሉ። የኮንትሮባንድ ተዋንያኖች ተያዙ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ የት ደረሰ የሚለውን ተከታትለው ህጋዊ እርምጃዎችን ለማስተማሪያነት መጠቀም፣ ለህዝብ ማድረስ እንደሚገባቸው ነው አፅእኖት የሰጡት።
በተለይ የአገር አለመረጋጋት ለተግባሩ መጎልበት ጉልህ ድርሻ ስላለው ለዚህ ቀውስ ተገቢውን አፋጣኝ መልስ መስጠት ቀዳሚ ያደርጉታል። ከዚህ በሻገር አደጋውን የሚመጥን ቅንጅት የቁጥጥር ሥርዓቱን ጥብቅ ማድረግና አመለካከት ላይ በቋሚነትና በስፋት መስራት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
የህግ ባለሙያው አቶ ኪያ ፀጋዬም፣ ከለውጡ በፊት በነበረው የመንግስት ሥርዓት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ብሎም በአገር ላይ የደረሰው ኪሳራ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ይስማሙበታል።
ህውሓት እጅግ ከፍተኛ በሆነ የኮንትሮባንድ ወንጀል የተዘፈቀ ሥርዓት እንደነበር የሚጠቁሙት የህግ ባለሙያው፣ በወቅቱ ኮንትሮባንድ እንደ ፖለቲካ ስትራቴጂ የተወሰደ፣ ተዋናዮች ከውጭ ሆነው በሚሳተፉት ብቻ ሳይሆን ቁልፍ በሆነ የመንግስት ተቋማት፣ የደህንነት እና የመከላከያ መዋቅር የተቆጣጣሪ አካላት በግልፅ የሚሳተፉበት ነበር ይላሉ። የወንጀሉ ከፍታም አጠቃላይ ሥርዓተ መንግስቱን የመቆጣጠር ደረጃ የደረሰ እንደነበር ያስታውሳሉ። ለዚህ አስተያየታቸውም የሶማሌ ክልል በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።
የክልሉ የቀድሞ ፕሬዚዳንት በነበሩት አብዲ ኢሊ አስተዳደር በወቅቱ የምስራቅ እዝ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመቀናጀት እጅግ በጣም ከፍተኛ በሆነ መልኩ የኮንትሮባንድ ስራ ይሰሩ ነበር›› የሚሉት አቶ ኪያ፣ይህ አይነት ህገ ወጥ ድርጊትም በሌሎችም የአገሪቱ ንግድ መውጪያ እና መግቢያ አቅጣጫዎች ሲከወን እንደነበር ይገልፃሉ። ወንጀሉም በአገር ላይ ከባድ ኪሳራን ማስከተሉን ይናገራሉ።
በዶክተር አብይ የሚመራው ለውጥ በአገሪቱ ሲመጣም ከባድ የአገር የኢኮኖሚ ፈተና የነበረው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ መሆኑን የሚጠቁሙት የህግ ባለሙያው፣ በወንጀሉ ተሳታፊ እና የጥቅሙ ተጋሪ የነበሩ ግለሰቦች እንጀራቸው እንደሚቋረጥ በመረዳት ብሄርን ሽፋን በማድረግ ግጭቶችን ሲያስነሱ እንደነበር ያስታውሳሉ።
‹‹እኔ ከለውጡ በኋላ ትልቁ ስራ ተሰራ የምለው የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን መስሪያ ቤትን ለሁለት መነጠል ነው›› የሚሉት አቶ ኪያ፣ ይህ መሆኑም አገሪቱ በኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የሚደርስበትን ዘርፈ ብዙ ኪሳራ መከላከል እንዲቻል ከፍተኛ አቅም መፍጠሩን ነው ያመላከቱት።
ኮንትሮባንድ እጅግ በጣም በቀላሉ የሚከበርበት በመሆኑ በቀላሉ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል የሚል እምነት እንደሌላቸው የሚያስገነዝቡት አቶ ኪያ፣ ቀደም ሲል በነበረው ሥርዓት መንግስታዊ ከለላ በሚሰጠው፣ ደህንነት እና መከላከያን ሳይቀር የሚያሳትፍ ባይሆንም አሁንም ቢሆን ህገ ወጥ እንቅስቃሴው ቆሟል ማለት እንደማያስደፍር ነው ያስረዱት።
በገቢዎች ሚኒስቴር በኩል በተለያዩ ጊዜያት ይህን ያህል መጠን ያላቸው ኮንትሮባንድ ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስራ ዋለ የሚል ዜና የሚሰማውም ለዚሁ መሆኑን በዋቢነት የሚያቀርቡት የህግ ባለሙያው፣ ይሁን እና በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ሳይደነቁ የሚያልፉ እንዳልሆነ ነው አፅእኖት የሠጡት።
ወንጀሉን ከስር መሰረቱ ለማድረቅ መደረግ ስለሚኖርባቸው አበይት ተግባራት ሲያስረዱም፣ ወንጀለኞቹ ተያዙ፣ንብረታቸውም ተወረሰ፣ ከማለትም በላይ ለህግ ቀርበው የተቀጡትን ቅጣት ተከታትሎ ለህብረተሰቡ መግለጽ እንደሚያስፈልግም ነው የሚናገሩት።
‹‹አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ቢውልም ባለቤቱ አልተገኘም›› ከማለት ይልቅ አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ የወንጀሉን ዋና መሰረት እና መሪ ባለቤቱን አድኖ ለህግ ማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ማድረግ እንዳለባቸው አፅእኖት ሰጥተውታል።
የህገ ወጥ ንግዱ ተዋናዮች ላይ የተቀመጠውም የህግ ቅጣት ደረጃ ብሎም በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የሚወሰንባቸው የህግ ቅጣቱ ዝቅተኛ ነው በሚለው እሳቤ የማይስማሙት አቶ ኪያ፣ በአግባቡ ከተተገበረና ክፍተቶቹን በሂደት ማስተካከል ከተቻለ የተቀመጠው የቅጣት ወሰን በቂ ነው የሚል እምነት አላቸው።
መንግስት ወንጀሉን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የያዘውን የፀና አቋም በስኬት ለማጀብ ብሎም የተዋናዮቹ ጡንቻ እየፈረጠመ ከሆነ ለመንግስትም ሆነ ለአገር የሚያሰጋ በመሆኑ ፣ የቅጣት ህጉን በአግባቡ ተፈፃሚ ከማድረግ በተጓዳኝ፣ በተቆጣጣሪ ተቋማት ብሎም ክልሎች መካከል የቅንጅት ስራ መስራት የግድ ስለመሆኑም ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመልክቱት በተለይ ከለውጡ በኋላ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋነኛ ነቀርሳ የሆነውን ኮንትሮባንድ በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ ስኬታማ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። የጉምሩክ ኮሚሽን የተለያዩ የሀገሪቷን መግቢያና መውጫን በመጠቀም የሚገቡ እና የሚወጡ እቃዎች ህጋዊውን መንገድ ብቻ በመከተል እንዲንቀሳቀሱ በሙሉ አቅሙ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በ2013 በጀት ዓመት በተሠራው ጠንካራ የኮንትሮባድ ቁጥጥር ስራ ባለፉት 8 ወራት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባድ ቁሳቁሶች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። የገቢና የወጭ ኮንትሮባንድ መከላከል ረገድ ዕቅድ 1 ቢሊዮን 786 ሚሊዮን 77ሺ ብር ሲሆን ክንውን በአንፃሩ 2 ቢሊዮን 250 ሚሊዮን 496ሺ 217 ብር ነው። ይህም አፈፃፀሙም 126 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።
ከ2012 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ስምንት ወራት አፈጻፀም ጋር ሲነጻፀር በብር 720 ሚሊዮን 298 ሺ 971 ብር ወይንም በ47 በመቶ ጨምሯል። ይህን ስኬታማ አፈፃፀም ማስመዝገብ የቻሉት እንደሌሎች ሥራዎች ጊዜ፣ ዕውቀት፣ ጉልበት ብቻ መስዋዕት በማድረግ ሳይሆን መተኪያ የሌለውን ህይወት በመሰዋትና አካልን በመገበር ጭምር ነው ብሏል።
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎቹ የሚጋሩበት የጋራ ሃሳብም የኮንትሮባንድ ንግድን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራን በዋናነት ለመንግስት እና ለኮሚሽኑ ከመስጠት ይልቅ ከችግሩ ስፋትና ውስብስብነት አንጻር ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት የግድ ይለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013