ኢትዮጵያ እስከ አለፈው ዓመት ድረስ ከወጪ ንግድ በዓመት ታገኝ የነበረው ከፍተኛ ገቢ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር ብዙም ያልዘለለ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ የወጪ ንግድ ገቢ በ2017 በጀት ዓመት ከፍተኛ ለውጥ ማሳየት ጀምሯል። በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ ወደ አምስት ነጥብ ሶስት አምስት ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳይ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንደተናገሩት፤ በ2016 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ግብይት የተገኘው ሦስት ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ነው። በ2017 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ ወደ አምስት ነጥብ ሶስት አምስት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። ይህ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የሁለት ነጥብ ሰባት ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ብልጫ አለው።
ሥራ አሥፈጻሚው እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በከፍተኛ መጠን መጨመር በዘርፍ ደረጃ ሲታይ፤ የግብርና ምርቶች ዕቅድ አፈፃፀም 115 በመቶ ነው። የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች የወጪ ንግድ አፈፃፀም ደግሞ ከዕቅድ አንፃር 57 በመቶ ቢሆንም፤ የማዕድን ዘርፉ ግን ከዕቅድ አንፃር አፈፃፀሙ 370 በመቶ ደርሷል። በተጨማሪ የኤሌክትሪክ እና ሌሎች ወጪ ምርቶች አፈፃፀም 127 ከመቶ ነው።
አፈጻጸሙ እስካሁን ድረስ ከነበረው አፈፃፀም ከፍተኛ መሻሻል የታየበት መሆኑን በማመላከት፤ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ በቀጣይ ማደግ እንደሚችል አመላካች ውጤት ነው ሲሉም ጠቁመዋል። ለዚህ ውጤት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ምክንያቶችን ሲያብራሩም መንግሥት ወደ ሙሉ ትግበራ ያስገባውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ላኪዎች የውጪ ምንዛሪ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት መቻሉን በማስታወስ፤ የውጪ ምንዛሪ ላይ ጫና ፈጥሮ የነበረውን ጥቁር ገበያ የሚያስተካክል ወጥ እና የተሳለጠ የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት መፈጠሩ ለውጤቱ መመዝገብ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።
ሌላኛው በተለያዩ አማራጮች ላኪ ባለሃብቶችን ማበረታታት እና ብዙ አማራጮችን በመስጠት በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ደረጃ ጠንካራ የወጪ ንግድ ማስፋፊያ እና የማስተዋወቅ ሥራዎች መሠራታቸውም ከምክንያቶቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው ሲሉም ይናገራሉ። ለእዚህም ሲያስረዱ፤ የአገሪቷ ላኪዎች በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች፣ ኤግዚቢሽኖች እና የተለያዩ ባዛሮች ላይ እንዲሳተፉ መደረጋቸውን በማሳያነት መጠቀስ እንደሚችልም ይጠቁማሉ።
ከወጪ ንግዱ ለተገኘው ስኬት በዋናነት በዚህ ዓመት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ከወርቅ ግብይት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ መሆኑን ሥራ አሥፈጻሚው ጠቅሰው፣ በዘጠኝ ወራቱ ወደ ሁለት ነጥብ 66 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ ከዚሁ ከወርቅ ምርት መገኘቱን ጠቅሰዋል። ለዚህ ትልቁን አስተዋፅኦ ያበረከተው፤ ከባሕላዊ ወርቅ አምራቾች በቀጥታ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በጣም በመጨመሩ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ወንድሙ ገለፃ፤ በሁለተኛነት የተቀመጠው ከቡና ንግድ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ነው። በዚህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ለውጥ ታይቷል። የኢትዮጵያ የቡና ምርት በዓለም ያለው ፍላጎት በጣም ማደጉ እና የሚገዙ ሀገራት ቁጥርም መጨመሩ የራሱን ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ዓመት የተገኘውን የወጪ ንግድ አፈፃፀም ለማስቀጠል ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ብዙ መሠራት እንዳለበት አያጠያይቅም ሲሉም ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል። በተለይ ባለሃብቶችን ማበረታታት፤ ሕገወጥ ኬላዎችን ማስቀረት እና የጥራት ፍተሻ አቅምን በመጨመር የምርት ጥራትን ማስጠበቅ ከተቻለ ነባር ገበያዎችን ማቆየት እና አዳዲስ ገበያዎችን በየጊዜው ለማሳደግ የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉ ያላቸውን እምነት አስታውቀዋል።
‹‹የክህሎት ሥልጠና ማሻሻያዎች እየተደረጉ በመሆናቸው፤ ሀገራዊ አቅም እያደገ ነው›› ያሉት አቶ ወንድሙ፤የንግዱ ማኅበረሰብም ሆነ አምራቹ አርሶ አደር በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚሳተፉ አካላት በእውቀት እና በክህሎት መሥራት አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል።
ጊዜው የመረጃ ዘመን መሆኑን አስታውቀው፣ ድርድሮች እና ውይይቶች የሚካሄዱት በዲጂታል ነው። ስለዚህ ተወዳዳሪ ለመሆን ዘመኑ በሚጠይቀው ደረጃ ቴክኖሎጂውን ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል። በግልም ሆነ በተናጠል እንደ ሀገር በሚሰጡ ሥልጠናዎች ላይ የንግድ እና የቢዝነስ አቅምን ማሳደግ የግድ መሆኑን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቅርጫት ብዙ ምርቶችን መሳብ አለበት የሚሉት አቶ ወንድሙ፤ ይህን ለማድረግ በጥራት፣ በብዛት እና በዓይነት ለማምረት አቅምን ማሳደግ ያስፈልጋል። ለዚህም የኢትዮጵያ የብሔራዊ የጥራት መንደር ትልቅ ሚና ይኖረዋል።
እንደ አቶ ወንድሙ ገለፃ፤ በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር በኩል አምራቾች እና ላኪዎች እንዲሁም የሀገር ውስጥ ነጋዴዎች የኢንዱስትሪ ዘርፍ ተዋንያን በአጠቃላይ በየዘርፋቸው የየበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ናቸው። የወጪ ንግድ የሚያድግበት ሁኔታ ላይ ብቻ ሳይሆን ተኪ ምርቶች የሚመረቱበትን ሁኔታንም በተመለከተ አቅም እንዲገነባ መሥራት እንደሚያስፈልግ አያጠያይቅም።
ወጪን ማብዛት ብቻ ሳይሆን ገቢን መተካት ለዜጎች የሥራ ዕድልን እንደሚጨምር ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ምርት ኢትዮጵያውያን መኩራት መጀመር እንዳለባቸውም መክረዋል።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚክ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የወጪ ንግድ ገንዘብ ሲቆጠር ካለፈው ያደገ ነው፤ ከዚሁ ጎን ለጎንም የሕዝብ ቁጥር መጨመሩ መዘንጋት የለበትም። የገበያ ሁኔታ በየጊዜው መስፋቱ የማይቀር ነው። የመረጃ ዘመን በመሆኑ የቴክኖሎጂ ጉዳይም የራሱ ተፅዕኖ ይኖረዋል። በቀጣይም ቁጥሩ መጨመሩ አይቀርም፤ ገቢ እየጨመረ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ወደ ውጪ እየተላከ ነው ማለት ግን አይቻልም ብለዋል።
በተገኘው ገቢ መዘናጋት እንደማይገባ አመልክተው፣ በገቢ ለመኩራራት አስቀድሞ መሠራት ያለበትን በሰፊው መሥራት ይገባል ሲሉ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ በወጪ ንግድ ላይ የተሠማሩ የሀገራችን ባለሃብቶችም ሆኑ አምራቾች ከሌሎች ሀገሮች አቻዎቻቸው ጋር ሲነፃፀሩ አቅማቸው በጣም ደካማ ነው። ከዓለም ጋር ተወዳድሮ ለመሸጥ ባለድርሻ አካላት በደንብ ስትራቴጂክ ፕላን ነድፈው መሥራት ይኖርባቸዋል። ባለሃብቱ ምን ያድርግ? መንግሥት ምን ያድርግ? ሌላውስ ምን ያድርግ? በሚሉት ላይ ከግንዛቤ ፈጠራ ጀምሮ መሠራት አለበት ብለዋል።
‹‹አሁንም ገና ብዙ ወደኋላ የቀረን ነን ›› የሚሉት ከፍተኛ ተመራማሪ ሞላ (ዶ/ር)፤ ገቢ እንዲሻሻል ብዙ መሠራት አለበት። ሀገሪቷ ብዙ አቅም አላት። በተለይ ግብርና እና ግብርና ነክ ከሆኑ ነገሮች ጋር ተያይዞ፤ እርሻን ማዘመን እና ዘመናዊነቱን ተደራሽ በማድረግ፤ በቡና እና በተወሰኑ ምርቶች ላይ የተንጠለጠለውን የወጪ ንግድ ማስፋት በዋናነት ጥራትን እና እሴትን በመጨመር የተሻለ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ከብዙዎች የተሻለ አቅም እንዳላት ተናግረው፣ የወጪ ንግድ የሚጠበቀውን ያህል ሳይሆን ለቆየበት ምክንያት በወጪ ንግድ ላይ እስካሁን የተሠራው ሥራ አመርቂ ባለመሆኑ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ።
በዚህ ምክንያት አሁንም ከወጪ ንግዱ የተገኘው ገቢ እና ለገቢ ንግድ የሚያስፈልገው ገንዘብ ልዩነት እየጨመረ ነው ሲሉ ገልጸዋል። አሁን ግን ገቢ ምርት ወደ አራት እጥፍ እየደረሰ መሆኑን እና ጭራሽ የገቢው መጠን የመጨመር ፍጥነት ከወጪው በጣም እየጨመረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ይህም ለኢትዮጵያ ስጋት መሆኑን አስገንዝበዋል።
አንዲት ሀገር የተሻለ ኢኮኖሚ አላት የሚባለው ልዩነቱ የወጪ ንግዱ ከገቢ ንግዱ ሲበልጥ ነው። ይህ ሲሆን የንግድ ሚዛኑ ጤናማ ነው ተብሎ ይታሰባል። የሚሉት ሞላ (ዶ/ር)፤ ይህን ለማመጣጠን ወይም በተወሰነ መልኩ ለማቀራረብ አልተቻለም ብለዋል። ይህ የሆነው የወጪ ንግድ ላይ ኋላቀርነት በመኖሩ እና ተወዳዳሪነት ስለሌለ ነው ሲሉ ጠቁመዋል። ከዘመኑ አንፃር ሲታይ ደግሞ የወጪ ንግድ ላይ አምራቾች በቴክኖሎጂም በሥራም በዓለም ደረጃ ለመወዳደር በጣም ወደ ኋላ የቀሩ መሆናቸው ዋነኛው ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ ከፍተኛ ተመራማሪው ገለፃ፤ ከወጪ ንግድ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እና በደንብ ዕቅድ ተይዞ ሊሠራበት ይገባል። የወጪ ንግድ ላይ የተሠማሩ አምራች ኩባንያዎች በቴክኖሎጂ እንዲሻሻሉ እና አቅማቸው እንዲገነባ መንግሥት መርዳት አለበት። በገንዘብ አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ፣ በዕውቀት ሽግግር ድጋፍ በማድረግ የበለጠ እንዲያገኙ መሥራት ያስፈልጋል።
በሀገር ውስጥ ገበያ ላይ ሕዝቡ የውጪ ምርት ላይ ያዘነብላል ያሉት ሞላ (ዶ/ር)፤ የውጪ ምርትን መጠቀም እንደ መዘመን ወይም እንደሃብት መገለጫ እየታየ ነው ይላሉ። ከዚህ ጀምሮ የሀገር ውስጥ ምርት በመጠቀም ላይ በስፋት መሠራት አለበት። በተለይ አምራቾች ምን ይጎድላቸዋል? ከማን ምን ድጋፍ ማግኘት አለባቸው? የሚሉትን በደንብ አይቶ በጥናት አስደግፎ መሥራት ካልተቻለ በጥቂቱ ብቻ የሚመጣ ለውጥ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ሊለውጥ አይችልም ብለዋል፡፡
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬዘር ጥላሁን በበኩላቸው፤ ባለፈው ዓመት የተላከው እና አሁን የተላከው በመጠንም ሆነ በጥራት ሳይጨምር ዋጋው በእጥፍ ማደጉ እና ልዩነት ማምጣቱ ከዋጋ ንረት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ሊያኩራራ አይገባም ይላሉ፡፡
የወጪ ንግድ ገቢ መጠን መጨመር የሚያኩራራ አይደለም ያስባላቸውን ምክንያት ሲገልፁ፤ በቅድሚያ ወደ ውጪ ምን የተለየ ነገር ተላከ? የሚለው ላይ በደንብ ማሰብ ያስፈልጋል። በዓለም የምርቶች ዋጋ ጨምሮ የወጪ ንግድ ገቢ መጨመሩ እንደ ዕድገት ማሳያ መወሰድ የለበትም›› በማለት አስረድተዋል።
‹‹የቡና ዋጋ ባለፉት 48 ዓመታት ያልታየ ጭማሪ ማምጣቱ እየተነገረ ነው›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬዘር፤ በከፍተኛ መጠን የቡና ዋጋ የጨመረበት ምክንያት ደግሞ እነ ብራዚል እና ኮሎምቢያ በዝናብ ማነስ ተጎድተው የኢትዮጵያ ቡና በተለይ በአሜሪካ ገበያ ላይ ምርጥ ዕድል ተፈጥሮለት በከፍተኛ ዋጋ በመሸጡ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው አመላክተዋል። የብራዚል ቡና በኢትዮጵያ ቡና መተካቱ መልካም ዕድል እና አዲስ ደንበኛ የተገኘበትን ሁኔታ ዘላቂ ለማድረግ መሠራት አለበት ሲሉ አመላክተዋል።
አክለውም ‹‹አሁንም ወደ ውጪ ተልኮ የተገኘው ገቢ እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ለማስገባት በወጣው ወጪ መካከል ያለው ልዩነት በጣም ከፍተኛ ነው። ወደ ውጪ የሚላከው ውስን ሆኖ የሚገባው ሁሉም ነገር ሆኗል። የተጫማነው ጫማም ሆነ ልብስ ጨምሮ ፤ በከፍተኛ ዋጋ ወደ ሀገር የሚገቡ ማሽነሪዎች አሉ›› የሚሉት ረ/ፕ/ር ፍሬዘር፤ ይህ ሁሉ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የምትልከው ቡና እና ሰሊጥ ነው። በእነዚህ ምርቶች አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳርፉ ችግሮች ቢከሰቱ ኢትዮጵያ ምን ትሆናለች? ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። የምርት ዓይነት የተለያየ አለመሆን ችግር ያስከትላል። ኤሌክትሪክ ወደ ውጪ መላክ አንድ የተለየ አማራጭ ነው። እርሱ የምርት ዓይነት ተጨማሪነትን ይፈጥራል። ዝናብ ቢጠፋ የኃይል አቅርቦት ሽያጭ አይቋረጥም። ስለዚህ ጎን ለጎን ወደ ውጪ የሚላኩ ዓይነቶችን ቁጥር መጨመር ያስፈልጋል። ገቢው ከፍ ዝቅ እያለ እንዳይዋልል፤ የሚያደርጉ ነገሮችን ለመላክ መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬዘር፤ ሌላው በሀገር ውስጥ መመረት እየቻሉ ከውጪ የሚገቡ ምርቶች በጣም ብዙ ናቸው። ለአብነትም በግብርና ላይ ኢኮኖሚዋን መሠረት ያደረገች ሀገር ጁስ እና ወተት ከውጪ የምታስገባበት ምክንያት ሊኖር አይገባም።
አንድ ሀገር ከዓለም ተገልሎ መኖር አይችልም። ነገር ግን መግባት ያለበት ሀገር ውስጥ ቢመረት ውድ፤ ከውጪ ቢገባ ርካሽ የሆነ ምርትን ብቻ መሆን አለበት። በሀገር ውስጥ በቀላሉ የሚመረቱትን ከውጪ በዶላር ማስገባት አያስፈልግም ብለዋል።
መኪና ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመረት ጃፓን ቢመረት የተሻለ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም እነርሱ በመኪና ምርት ላይ ነጥረው ወጥተዋል። ያላቸው ጥሬ ዕቃም ርካሽ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬዘር፤ የኢትዮጵያ ሃብት መሬት እና የሰው ኃይል በመሆኑ፤ ሰፊ የሰው ጉልበት እና መሬት የሚፈልጉ ምርቶችን ኢትዮጵያ በራሷ አምርታ ከውጪ የምታስገባውን ማስቀረት እና ወደ ውጪ መላክ ያለባትን መላክ አለባት የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ዙሪያ ክልከላ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ገቢ ምርት ሲቀንስ እና ወጪ ምርት ሲጨምር ኢኮኖሚው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አስታውቀዋል። ወደ ውጪ የሚላከውን የምርት ዓይነት፣ ጥራት እና መጠን ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ምሕረት ሞገስ