
የኢትዮጵያ ቤልጂየም እና ሉክሰምበርግ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፎረም ከሰሞኑ በአዲስ አበባ እየተካሔደ ይገኛል:: ፎረሙ ከፍተኛ ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነቱን ለማጠናከር እና በኢትዮጵያ እና በቤኔሉክስ ሀገራት መካከል አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችን ለመክፈት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ተነግሮለታል::
ለመነሻነት በቤልጂየም እና ሉክሰንበርግ ያሉ 13 ካምፓኒዎች የተሳተፉበት ሲሆን፤ በፕሮግራሙ ከኢትዮጵያ ከ80 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል:: በቀጣዩቹ ዓመታት በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የተነገረለት ይኸው ፎረም፤ ውይይቱ በዋናነት ንግድ ላይ ያተኮረ ቢሆንም፤ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ያላቸው አቅም ላይ አጽንኦት በመስጠት ሲካሔድ ሰንብቷል።
ከፎረሙ አመቻቾች መካከል የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አንደኛው ነው:: በምክር ቤቱ ተጠባባቂ ዋና ፀሃፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ እንደሚናገሩት፤ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ዕድል መኖሩን የማሳወቅ እና የማሳደግ ሥራ የአንድ ሰሞን ጉዳይ አይደለም:: ሁል ጊዜ እያደገ የሚሔድ ሲሆን፤ ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ወይም ግንኙነቶችን ለማሳደግ ሲፈለግ ፎረሞችን በማዘጋጀት ያለውን ዕድል የማስተዋወቅ እና የማሳመን ሥራዎች ይቀጥላሉ::
በሀገራቱ መካከል እ.ኤ.አ በ2023 ግንኙነቱ 350 ሚሊዮን ዶላር ነበር:: አሁን ወደ 718 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል:: ከዚህ በላይ ማደግ እንዳለበት አያጠያይቅም ሲሉ የተናገሩት አቶ ዘካሪያስ፤ በኢትዮጵያ እና በቤኔሉክስ ሀገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት አቻ እንዳልሆነ አብራርተዋል::
አቶ ዘካሪያስ እንዳስረዱት፤ ኢትዮጵያ ለሀገራቱ ከምትሸጠው በላይ የምትገዛው ብዙ ነው:: የምትልከው የግብርና ምርት ቡናና ጥራጥሬ ነው:: እነርሱም እንዲሁ በዓይነትም ሆነ በመጠን በዛ ያሉ ነገሮችን ለኢትዮጵያ ይሸጣሉ:: ይሁንና ሁል ጊዜ ግንኙነቶች የሚፈጠሩት የንግድ ሚዛንን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት አያጠያይቅም:: ስለዚህ ኢትዮጵያ አሁን ካለው በላይ መሔድ አለባት::
በሌሎችም የአውሮፓ ሀገሮች ገበያ ላይ ኢትዮጵያ ከምትልከው በላይ ከአውሮፓ የሚመጣው የበዛ ነው:: ስለዚህ የንግድ ምክር ቤት ሁል ጊዜ ይህንን በመግለፅ፤ በተመረጡ ዘርፎች ላይ ብዙ ገበያዎች መኖራቸውን በማስታወስ፤ አምራቾች እና ነጋዴዎች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተለያዩ መድረኮች እያዘጋጁ እንደሚገኙ ጠቁመዋል::
ከአውሮፓዎችም ሆነ ከሌሎች ከፍተኛ የዓለም ንግድ ተሳታፊዎች ጋር ተመጣጣኝ ግብይት ለመፈፀም፤ የኢትዮጵያን ባለሃብቶች እና ላኪዎች ብቃት ማሳደግ ያስፈልጋል ሲሉ የተናገሩት አቶ ዘካሪያስ፤ ገበያው ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን የእነርሱን የገበያ መለኪያዎች ማሟላት የግድ መሆኑን ሁሉም ሊረዳ እንደሚገባ አስታውሰዋል::
አቶ ዘካሪያስ እንዳመለከቱት፤ ገበያውን ተመጣጣኝ ለማድረግ የአምራቾችን አቅማቸውን ማሳደግ ይፈልጋል:: ‹‹የእኛ ምርት አውሮፓ ገበያ ሔዶ እንዴት ተወዳዳሪ ይሆናል? ›› የሚለውን ለይቶ ምርቶችን የማብዛት አቅም የማሳደግ፤ አሠራሮች እንዲዘምኑ ማስቻል፤ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ከቴክኖሎጂ ጋር አያይዞ የመሔድ እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ብቻ ሳይሆን ብቃት የማሳደግ ሥራዎች መሠራት አለባቸው:: ይህ ሲሆን ያለው ክፍተት እየሞላ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻልበት ዕድል ይፈጠራል::
ኢትዮጵያ ከፎረሙ፣ ከንግድ ትርኢቶች፣ ከኤግዚቢሽኖች በተጨማሪ የንግድ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ በሌሎች መስኮችም በዛ ያሉ የሁለትዮሽ (የቢዝነስ ቱ ቢዝነስ) ጉባኤዎችን አካሂዳለች:: በምክር ቤቱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ምክር ቤቶች እና ማሕበራት እየተሠሩ ያሉ ብዙ ሥራዎች አሉ የሚሉት አቶ ዘካሪያስ፤ የንግድ እና ኢንቨስትመንት የማሳደጊያ ሁነቶች በበዙ ቁጥር የኢትዮጵያ ባለሃብቶች እየተበረታቱ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሚሆኑበት ዕድል ይጨምራል:: ግንኙነቶች ካልተፈጠሩ ደግሞ ወጪ ንግዶችን ማሳደግ አዳጋች ይሆናል ብለዋል::
በተመሳሳይ 17 አባላት የያዘ የልዑካን ቡድን ከቻይናዋ ሻንጋይ በመምጣት ከኢትዮጵያ የንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ፎረም ተካሂዶ እንደነበር አስታውሰው፤ ከኬንያ ጋርም በተመሳሳይ መልኩ ተደርጓል:: የትኛው ገበያ ሊያዋጣ ይችላል? ወይም ስፋት ያለው ገበያ ያለው የት ነው? በሚል ሥራው ቀጣይነት ባለው መልኩ፤ ሰፋ ብሎ እንቅስቃሴ ሊደረግ ይችላል ብለዋል::
አውሮፓ በኢትዮጵያ ገበያ ትሳተፋለች:: በሌላ በኩል ቻይና ደግሞ ብዙውን ድርሻ ትወስዳለች:: እንደገበያው አካባቢ የንግድ ግንኙነት ሁነቶች በዛ ሊሉ ይችላሉ:: አዲስ ምንም መጥተው የማያውቁ ደግሞ ንግድ ሊጀምሩ ይችላሉ ሲሉም ተናግረዋል::
የፎረሙን ውጤት በተመለከተም አቶ ዘካሪያስ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ምን ያህል ለንግድ አመቺ ናት? በሚለው ዙሪያ በጋራ ይሠራል:: ግንኙነቱ ሲቀጥል የንግድ እንቅስቃሴው እየሰፋ ሲሔድ፤ ለንግድ ምቹ ያልሆኑ ምን ከባባዊ ነገሮች አሉ? የሚለውን ሁለቱም አካላት ያነሳሉ፤ በተጨማሪ ጥናቶች ይደረጋሉ:: ግኝቶቻቸው ለሚመለከቷቸው የመንግሥት አካል ይቀርቡና ይሻሻላሉ::
በተጨማሪ የቤልጂየም ንግድ ምክር ቤት እና የአዲስ አበባው ንግድ ምክር ቤት የትብብር ስምምነት እንደሚፈራረሙ የጠቆሙት አቶ ዘካሪያስ፤ ‹‹የመፈራረሙ ጥቅም ከዚህ ወደ እዛ እና ከዛ ወደዚህ እንቅስቃሴ ሲደረግ፤ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማስተዋወቅ እና ለማሳደግ የኢትዮጵያን ምርቶች በአውሮፓ ገበያ እንዲያድጉ ለማድረግ፤ እዛ አካባቢ የሚፈጠሩ ፈታኝ ነገሮች ለመፍታት እንዲቻል የተለያዩ አካላትን እንዲገኙ ለማድረግ ያስችላል::›› ብለዋል::
ከተለያዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ፤ እንዲጎበኙ እና ነጋዴዎችን እንዲያገኙ፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዳረሻ ትልቅ ከተማ እና የንግድ ቦታ እንደሆነች እንዲያውቁ እንዲሁም ምን ምን የልማት ሥራዎች አሉ? ለኢንቨስትመንት እና ለንግድ ምን ያህል ምቹ ናቸው? የሚለውን በገለፃ፣ በቪዲዮ እና በአካል በማስጎብኘት የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል ሲሉ ገልፀዋል::
ቤልጂየም ሉክሰንበርግ የንግድ ልዑካን ቡድን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመገናኘት እና በመነጋገር፤ ከኢትዮጵያ የንግዱ ማሕበረሰብ ጋር ሰፊ ውይይት ለማካሔድ እንዲሁም ሌሎች የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማየት ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል::
በቀጣይም በሀገሪቷ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተገደበ ካልሆነ በስተቀር፤ ኢትዮጵያ ‹‹ንግድ ልሠራ እችላለሁ›› ብሎ ከሚመጣ ከማንኛውም ሀገር ጋር ለመሥራት ሁልጊዜ ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል:: ኤምባሲዎች ንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲያድግ መሥራት አንደኛው ኃላፊነታቸው መሆኑን አስታውሰው፤ ፎረሙም በኢትዮጵያ የቤልጂየም ኤምባሲ ይህንን ግንኙነት መፈለጉን እና ፕሮግራሙን ከአዲስ አበባ ምክርቤት ጋር ተስማምተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል::
በፎረሙ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ፤ በኢትዮጵያ እና በቤልጂየም እንዲሁም በሉክሰምበርግ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብርን ኢትዮጵያ የምትፈልገው መሆኑን አመላክተዋል። ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማካሄዷን አስታውሰው፤ ለንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አላት ያሉት ሚኒስትሩ፤ በቀጠናው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች እንደምትገኝ ገልፀዋል:: ይህን ተከትሎ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴን ለማድረግም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ የሚመጡ የዓለም ሃብታም ኢንቨስተሮችን ኢትዮጵያ ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን አመላክተዋል::
ለውጭ ንግድም ሆነ ኢንቨስትመንት ያሉትን ዘርፈ ብዙ መንገዶች ያብራሩት አቶ አህመድ፤ ‹‹በግብርና፣ በማእድን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች እንድትሳተፉ እንጋብዛለን›› ሲሉ ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን ከቤልጂየም እና ሉክሰንበርግ ጋር እንደምትፈልግ ገልፀዋል:: ሀገሪቱ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማስፋት እና የወጪ ንግዷን ለማሳደግ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በንቃት በማዘመን ላይ እንደምትገኝ ጠቁመዋል።
እንደ ማኑፋክቸሪንግ፣ የኬሚካል ምርት እና የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ባሉ ወሳኝ መስኮች ሰፊ እውቀት ካላቸው የቤልጂየም እና የሉክሰምበርግ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር የመሥራት ፍላጎት መኖሩንም አመላክተዋል። በሕክምናው ዘርፍ ፋርማሲቲካል፣ ሌሎችም ሊመረቱ፣ ገበያ ላይ ሊውሉ የሚችሉ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን መሸጥ ይቻላል ብለዋል::
በተጨማሪ ቱሪዝም ላይ ባሕልን ከመፈለግ እና ከመተሳሰር ጋር ተያይዞ መሥራት እንደሚቻል ጠቁመው፤ አገልግሎት ተኮር የሆኑ ሥራዎችን በመሥራት ገበያው ላይ መቅረብ ይቻላል ሲሉ ገልፀዋል::
‹‹ዓላማችን የኢንዱስትሪ አቅማችንን ለማሳደግ እና የሀገሪቷን ምርት በመጨመር ዓለም ላይ ያለውን የንግድ ተሳትፎ ልምዳችሁን መጠቀም ነው›› ሲሉ ለቤልጂየም እና ሉክሰምበርግ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተም አስረድተዋል:: የውጪ ምንዛሪ እና ሌሎችም የተወሰዱ ማሻሻያዎች መኖራቸውን በመጠቆም፤ ኢትዮጵያ ወደ ማምረት እና ምርቶችን ገበያ የማድረስ ተግባር ላይ በሰፊው መሰማራት እንደምትፈልግ ገልፀዋል:: የሀገራቱ የንግድም ሆነ የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲሁም የባለሃብቶች ተሳትፎ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላቂነት እንዲኖረው በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩን አመላክተዋል::
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ሥራ ለመመስረት ለሚፈልጉ የቤልጂየም እና ሉክሰምበርግ ባለሃብቶች ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መሔዱን እና ትልቅ ቁጥር እንዳለው በማስታወስ፤ የሀገር ውስጥ የግብይት ፍላጎትም ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል::
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉዞ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው ሲሉ የተናገሩት ኮሚሽነር ዘለቀ (ዶ/ር)፤ ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ መግቢያ ናት›› ኢትዮጵያን በመጠቀም የአፍሪካን ገበያ መጠቀም አዋጭ መሆኑን አስረድተዋል:: እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ግልፅ፣ ቀላል፣ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችሉ መንገዶችን አመቻችታለች::
በኢትዮጵያ በንግድም ሆነ በኢንቨስትመንት የሚሠሩ ሥራዎች በተለያዩ መንገዶች ሊከወኑ እንደሚችሉ አስታውሰው፤ በብቸኛ ባለቤትነት ወይም የአጋርነት አካሄድን በመከተል መሥራት ይቻላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር አኔሊስ ቬርስቲቼል በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እና በቤልጂየም መካከል ከ120 ዓመታት በላይ የቆየው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታሪካዊ ፋይዳ እንዳለው አስታውሰዋል:: ፎረሙ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርን በማሳደግ የሀገራቱን ግንኙነቶች እንደሚያጠናክር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ዝግጅቱ የተካሄደው በብራስልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በአዲስ አበባ የቤልጂየም ኤምባሲ እንዲሁም የቤልጂየም፣ ሉክሰምበርግ፣ የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ግብርና ምክር ቤት እና ሌሎችም ተሳትፈውበታል፡፡
በምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም